1፡2 የሰው ውድቀት
ሰው በኃጢአት ከመውደቁ በፊት፣ በእግዚአብሔር ሲፈጠር በራሱ ነፃ ፈቃድ፣ ምርጫ ማድረግ የሚችል ተደርጎ የተፈጠረ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው አንድ ቦታ እንደ ድንጋይ ወይም የቤት ዕቃ ተጎልቶ የሚቀመጥ፣ የማይንቀሳቀስ ሳይሆን፣ በራሱ ሐሳብና ዕቅድ መሠረት የሚንቀሳቀስ፣ የሚሠራ፣ የሚበላ፣ የሚጠጣና የሚተኛ … አስደናቂ ፈቃድና ምርጫ ማድረግ እንዲችል የተሰጠው ፍጡር ነበር፡፡ ይህን ነፃነቱንና ፈቃዱን ተጠቅሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ሕብረት በኃጢአት ምክንያት አበላሸው፡፡
አለመታዘዝ፡-እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ በፊት፣ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቶለት በዔደን ገነት እንዳስቀመጠው ቀደም ብለን አይተናል፡፡ እግዚአብሔርየሰው ልጅ መታዘዙንና አለመታዘዙን ለማወቅበዔደን ገነት ውስጥ ዛፏን ሲያስቀምጥ እንዲህ ብሎ አስጠንቅቆት ነበር፤ ‹‹መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ›› (ዘፍ.2፡9፣17)ብሎ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶት ነበረ፡፡ዛፉ ለመታዘዙ ምልክት እንጂ፣ ከዚያ ውጭ ሰውን የመጉዳት መርዛማነት አልነበረውም፡፡ የዘፍጥረትንመጽሐፍ ምዕራፍ ሦስትን በሙሉ ስናነብ፤ የምናገኘው ታሪክ በእባብ ተመስሎ ወደ እርሱ በቀረበው ሰይጣን ተታሎ ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተላለፈ፡፡
እግዚአብሔር የመጀመሪያዎቹን ሰዎች አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ካስቀመጣቸው ጊዜ ጀምሮ በየቀኑ ከእርሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ ሰይጣንም በብልጡ እባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ‹‹በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዟልን? ብሎ ሲጠይቃት እርሷም ያልተባለችውን ቃል ጨምራ አትብሉ ብቻ ሳይሆን ‹‹አትንኩት›› እንደተባሉ ጨምራ ነገረችው፡፡ በዚህ ጊዜ ሰይጣንም ባሳየችው ጥርጥር ደስ በመሰኘት ‹‹ሞትን አትሞቱም ከእርሷ በበላችሁ ቀን ዐይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ›› አላት፡፡ ስለዚህ የሰው የውድቀቱ መንስኤ የራሱን ክብር መፈለግ ወይም እንደ እግዚአብሔር ለመሆን መሻቱ እንደነበረ እናያለን፡፡ በዚህ በዘፍጥረት መጽሐፍ ምዕራፍ 3፡1-8 ባለው ውስጥ ስንመለከት አዳም በአምላካዊነት የምኞት ፈረስ እየጋለበ የተሰጠውን ትእዛዝ ረስቶና ጥሶ፣ የባለቤቱን የሔዋንን ቃል ሰምቶ፣ (የሰይጣንን ሐሳብ) ሔዋንም የሰይጣንን ቃል በመስማት፣ የተሰጣቸውን የአምላካቸውን ትእዛዝ ጥሰው አትብሉ የተባሉትን በሉ፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር ካዘጋጀለት መልካም ሥፍራ ከኤደን ገነት ሊባረር ችሎአል፡፡
ያለመታዘዝውጤቱ፡- አዳምና ሔዋን እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ጥሰው፤ በእባቢቱ የተሰጣቸውን ምክር ሰምተውከዛፉ በበሉ ቀን፣ ራቁታቸውን ሆነው አገኙት (ዘፍ.3፡7)፡፡ ይህ ራቁት መሆን የመጀመሪያው ያለመታዘዛቸው (የውድቀታቸው) ውጤት ሲሆን፣ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ህብረትም በሚያሳዝን ሁኔታ ተቋረጠ፡፡ በመልካሙ ጊዜ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሲሰሙ ደስ የሚላቸው፣ አሁን አስፈሪ ሆነባቸው፤ ‹‹… በመሸ ጊዜ የእግዚአብሔርን የአምላክን ድምፅ ከገነት ውስጥ ሲመላለስ ሰሙ፤ አዳምና ሚስቱም ከእግዚአብሔር ከአምላክ ፊት በገነት ዛፎች መካከል ተሸሸጉ›› (ዘፍ.3፡8)፡፡
በዚህ ጊዜ እግዚአብሔርም በጫካ ውስጥ እንደ ተደበቁ አውቆ፤ ወደ ተደበቁበት ሥፍራ ድረስ ሄዶ፣ ምን ነክቷቸው እንደ ተደበቁ ሲጠይቃቸው፣ አዳም በሔዋን፣ ሔዋን ደግሞ በእባብ አመካኝተው ከጥፋታቸው ለማምለጥ ሙከራ ቢያደርጉም፤ምክንያታቸው በቂ ስላልነበረ እግዚአብሔር አልተቀበለውም፡፡ በመቀጠልም እግዚአብሔር እባብን ረገመ(3፡14-15)፤ ለሔዋንም በምትወልድበት ጊዜ በጭንቅ እንደምትወልድ ተነገራት (3፡16)፤ ለአዳምም በሕይወት በሚኖርበት ዘመን ሁሉበፊቱ ወዝ እንጀራ እንደሚበላ ተነገረው (3፡19)፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ሰው በተፈተነበት ኃጢአት ስለ ወደቀ በራሱና በአካባቢው ላይ እንዲሁም በሚቀጥሉት ትውልዶች ላይ ብዙ ውድቀት አስከተለ፡፡
አዳም የሚስቱን ቃል ሰምቶ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመስማቱ ምክንያት፣ በሁለቱና በእባብ ላይ የደረሰውን ርግማን ስንመለከት በዚህ አላበቃም፤‹‹… የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን… እሾህንናአሜኬላን ታበቅልብሃለች (3፡17-18)፤ በማለት መሬትም ባልሠራችው ጥፋት፣ ስለ ሰው ልጅ ጥፋት ሲባል አብራው ተረገመች፡፡በዚሁ መጽሐፍና ምዕራፍ ቁጥር 19 ላይ በሥጋው እንዲሞት ተወሰነበት፤ ሐዋርያው ጳውሎስበሮሜ መልእክቱ ‹‹ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንዲሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ›› በማለት ርግማን ወደ ሰው ሁሉ መድረሱን በማረጋገጥ ያስረዳል (ሮሜ 5፡12)፡፡ አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር የሰጣቸውን ትእዛዝ ከጣሱ በኋላ የኃጢአት ኃይል በሕይወታቸው ነገሠ፣ ከፈጣሪያቸውም ከእግዚአብሔር ለያቸው፡፡ ይህም ኃጢአት በሰዎች ልጆች ሁሉ ላይ በመሰልጠን ሞትን አመጣባቸው፡፡ይህ አሳብ ወደፊት የምንመጣበት ቢሆንም፣ በሮሜ 3፡23 ላይ ‹‹ሁሉኃጠአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል›› በማለት ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ በመሆኑና የርግማኑ ተካፋይ በመሆኑ የፈጣሪው ክብር እንደ ተለየው ያመለክታል፡፡
በመጨረሻ እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋን ከሕይወት ዛፍበልተው ለዘላለም ከነኃጢአቱ ሕያው ሆኖ እንዳይኖር፤ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በማስቀመጥ፤ ሁለቱንም ከዔደን ገነት አስወጣቸው፡፡አዳምና ሔዋን የፈጸሙት አለመታዘዝ ኃጢአት ሆነባቸው፤ በሁለቱም መካከል መለያየትን አስከተለ፡፡ ከአምላካቸውም ለያቸው፤ በሰውና በፍጥረት መካከል ያለው ግንኙነት ተበላሸ፡፡ ሰው የበላይ ሆኖ እሰሳትን ማስተዳደርና መቆጣጠር ባለመቻሉ፣ ምድርም በመረገምዋ ምክንያት እሾህንና አሜኬላን በማብቀል የሰው ጠላት ሆነች፡፡
ከዚህ በላይ ያየናቸው ውጤቶች በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሱ ሲሆኑ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ ቦታዎችምበተለይም ሐዋርያው ጳውሎስ በመልእክቶቹ የሚያነሣቸውንና የሚጠቅሳቸውን ውጤቶች እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው የሰው ልጅ በኃጢአት በመውደቁ ምክንያት፣ ‹‹በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፣ ፈቃድ አለኝና፣ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም›› ብሎ ‹በፈቃዱ ደካማ› እንደ ሆነ፣ ቀጥሎ ሲናገር ‹‹የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም›› ይላል (ሮሜ 7፡18-19)፡፡
በኤፌሶን መልእክቱ ደግሞ የተለያዩ ውጤቶች ዘርዝሮ እናገኛለን፤በኃጢአታችን ሙታን ነበርን (ኤፌ.2፡1)፣
የቁጣ ልጆች ነበር (ኤፌ. 2፡3)፣በአእምሮአችን ከንቱ ነበርን (ኤፌ.4፡17)፣ ልባችን ደንዳና፣ እና ልቡናችን ጨለማ ነበር (ኤፌ 4፡18)፣ በቲቶ መልእክቱ በአእምሮም በሕሊናም ረክሰን ነበር (ቲቶ 1፡15)፣ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ሕይወት ርቀን ነበር በማለት በሠፊው ዘርዝሮ አስቀምጦአል፡፡
ከአዳምና ሔዋን የመጣን የሰው ልጆች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኞች በመሆናችን ከፍርድ በታች ሆነን እንገኛለን፡፡ የዲያቢሎስ ልጆችም ተብለን ተጠራን፡፡ የግብረ ገብ አቋማችን ሲወድቅ በመንፈሳዊና በሥጋዊ ሕይወታችን በኃጢአት ተበከልን፡፡ ይህም ሥጋዊና መንፈሳዊ ሞት አስከተለብን፡፡ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ግንኙነት ተበላሸ፡፡ አዳም ከእግዚአብሔር እንደ ኮበለለ እኛም ጴጥሮስ እንደሚናገረው እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፍተን ነበር (1ጴጥ.1፡25)፡፡ ስለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር መጥቶ የሰውን ያለመታዘዝ ለማስወገድ፣ ራሱ በመታዘዝ መንገድ አልፎ ለኃጠአታችን በመስቀል ላይ መሞት ያስፈለገው፡፡
የዕብራውያን ጸሐፊ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መታዘዝ ሲገልጽ፣ ‹‹እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፣ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤… ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው›› (ዕብ 5፡7-10) በማለት በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረታችን ተቋርጦ የነበረው፣ እንደገና በክርስቶስ በኩል ተመልሶ እንደ ተመሠረተያመለክተናል፡፡
ኃጢአት፡– ኃጢአት የሚባል ነገር የለም የሚሉና ኃጢአት አለ ብለው የሚምኑ በየዘመናቱ ነበሩ፤ ዛሬም ይኖራሉ፡፡ በተለይም ሰው ራሱን ከኃጢአት ለማዳን የተለያዩ ጭብሎችን (Mask) በማጥለቅ ሙከራ አድርጎአል፡፡ ጭብሎቹም በሥልጣኔ ወደፊት መግፋት፣ ሀብት መሰብሰብ፣ ሥልጣን መያዝ፣ ኃይልን መጠቀም፣ ኃይማኖታዊ መሆን፣ በቴክኖሎጂ ማደግ፣ ወደ ተለያዩ ሥፍራዎች ሄዶ መዝናናት፣ ዓመፅን በማድረግ የሰውን ሕይወት ማጥፋት የመሳሰሉትን ጭብሎች ቢለብስም ራሱን በራሱ ከኃጢአት መርዝ ማዳን አልቻለም፡፡ ወደ ክርስቶስ ከመምጣት ይልቅ ራሴን ያድኑኛል ያላቸው ጭብሎች ይበልጥ ሊያጠፉት ደርሰዋል፡፡ ሰው ከመጥፋቱ በፊት ወደ ክርስቶስ ወደ ምሕረቱና ጸጋው በእምነት ቢመለስ ይሻለዋል፣ መዳን ይሆንለታል፣ ይቅርታም ዕርቅም ያገኛል፡፡
የኃጢአት ትርጉም፡-ሰዎች ለኃጢአት የተለያየ ትርጉም ሰጥተውታል፡፡ ከእግዚአብሔር ቁጥጥር ውጭ መሆን፣ ራስ ወዳድነት፣ ሕግ መተላለፍና ማመፅ ማለት ነው ይላሉ፡፡ አዳምና ሔዋን አትብሉ የተባሉትን የተሰጣቸውን ትእዛዝ በመጣስ፣ እንደ እግዚአብሔር ለመሆን ስለ ፈለጉ፣ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ጥሰው ፍሬውን በሉ፡፡ ባለመታዘዝ ዓመፅን እንደፈጸሙ በግልጽ የታወቀነው፤በአዲስ ኪዳን ቃሉን ስንመለከት በክርስቶስ ሞት የተገኘውን ድነት አልቀበልም ማለት ኃጢአት እንደሆነ ያመለክተናል፡፡ ስለዚህ የኃጢአት ትርጉምሊሆን የሚችለው ‹እንቢ› ‹አልቀበልም› ‹አልፈልግም›› ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በጌታ ፊት ስንቀርብ ጥያቄው ሕግ ጠብቀሃል አልጠበቅህም ሳይሆን ነገሩ የሞተልህን ኢየሱስን ተቀብለሃል ወይስ እንቢ ብለሃል ነው፡፡ ምክንያቱም ቃሉ ‹‹መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና›› (የሐዋ.4፡12) ስለሚል በዚህ በተሰጠው ስም ማመናችን የድነታችን መሠረት ነው፡፡ አንተስ እምቢ ከማለት ኃጢአት ወጥተህ ሕይወትህን ለጌታ ሰጥተህ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀህ ነው ያለኸው?
የግል ኃጢአት፡-የእግዚአብሔር ቃል ስለ ኃጢአት በብሉይና በአዲስ ኪዳንምበስፋት ይናገራል፤ ይህንም በሁለት ከፍለን የግል እና የውርስ (የወል) ኃጢአት ብለን ማየትና ማጥናት እንችላለን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስና በገላትያ መልእክቶቹ የግል ኃጢአቶችን ሰብሰብ አድርጎ በአንድ ላይ አስቀምጧቸው እናገኛለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ኃጢአቶች አዳማዊ ሥጋ በመልበሳችን ምክንያት ፈቅደን፣ መርጠንና ወስነን የምንፈጽማቸው ናቸው፡፡ ለመሥራትም ላለመሥራትም ፈቃዱ አለን፡፡ በብሉይ ኪዳን የተሰጡትን አድርግና አታድርግ የተባሉትን ትእዛዛት አለመጠበቅና በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ በግልም በማኅበርም የሚሠራ ኃጢአት ሊሆን ይችላል፡፡ የግል የሚያሰኘው በምርጫና በራስ ውሳኔ የሚደረግ በመሆኑ ነው፡፡ በአንድ ግለሰብ፣ ወይም በቡድን ከሁለት በላይ ሆኖ፣ ወይም በማህበር፣ ወይም በአገር ደረጃም ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህን ኃጢአቶች ስንሠራ የግል ኃጢአቶች ይባላሉ፡፡ (1ቆሮ.6፡9-10፣ ገላ.5፡19-21)
የውርስ ኃጢአት፡-የውርስ ኃጢአት እንደ ግል ኃጢአት በምርጫና በውሳኔ የሚሠራ ሳይሆን፣ የመጀመሪዎቹ ሰዎች አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩበት ጊዜ፣ ከእነርሱ የተነሣ የሰው ልጆች ሁሉ ኃጢአተኞች በመሆናቸው ነው፡፡ ቀደም ብለን ባየነው የሰው ያለመታዘዝ ውጤት መሠረት ሰው በአእምሮው፣ በሕሊናው፣ በፈቃዱ፣በልቦናውና በሁለንተናው ሁሉ ተበላሽቷል፡፡ ስለዚህ ሰው በምርጫውና በፈቃዱ ኃጢአትን ባይሠራም የአዳም ዘር በመሆኑ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአተኛ ነው፡፡
ይህን ትምህርት በስፋት ግልጽ ሊያደርግልን የሚችለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሮሜ ምዕራፍ አምስት ስለሆነ በስፋት እንመልከተው፡፡ ‹‹ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ››(5፡12)፣ ‹‹በአዳም መተላለፍ… ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ… ሞት ነገሠ›› (ቁ.14)፡፡ ‹‹በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና›› (ቁ.15)፣ ‹‹እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኩነኔ ወደ ሰው ሁሉ… መጣ›› (5፡18)፣‹‹በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች…ሆኑ›› (ሮሜ 5፡19)፣በማለት በአንድ ሰው ምክንያት ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኛ እንደሆኑ በማስረዳት የውርስ ኃጢአት እንዳለባቸው (እንዳለብን) ያስረዳል፡፡
አሁንም እንደገና ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ የግሉንና የውርሱንም ኃጢአት እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡፡ ስለ ግሉ ኃጠአት ሲናገር ‹‹… የሥጋችንንና የልቦናችንን ፈቃድ እያደረግን በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን…›› (ኤፌ.2፡3)፣ ስለ ውርሱ ኃጢአት ደግሞ ሲናገር ‹‹…እንደ ሌሎቹም (አይሁድ) ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን›› (2፡3)፡፡ እንደ አይሁዶችም እኛም ማለቱ ነው፡፡ ኃጢአት ከትወልድ ወደ ትውልድ እንደሚተላለፍ ያመለክታል፡፡ የሰው ምንጩ እግዚአብሔር እንደሆነና እርሱን እያመለከ እንዲኖር አድርጎ እንደፈጠረው አየን፡፡ ሰው በኃጢአት ቢወድቅም እግዚአብሔር ወድቆ እንዲቀር ስላልፈለገ እንደገና ከራሱ ጋር የሚታረቅበትን መንገድ አዘጋጅቶለታል፡፡ በመጨረሻም ከሥጋ ሞት በኋላ የሰው መጨረሻው ክርስቶስን ተቀብሎ አዲስ ሕይወት ካገኘ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም መኖር፤ በልጁ ከእግዚአብሔር ጋር ሳይታረቅ ከኖረ ደግሞ ከእግዚአብሔር ተለይቶ ለዘላለም መኖር ዕጣ ፈንታው ይሆናል፡፡ የትኛውን ትመርጣለህ? ወይስ አስቀድመህ መርጠሃል?
2 Comments
Abel · December 15, 2021 at 7:08 pm
ጋሽ አምቤ በጣም ነው የማመሰግነው ብዙ ነገር እንዳውቅበት ስለረዱኝ ቀጣይ ክፍሎችን እንዳይ አጓግቶኛል።
Amberber Gebru · December 29, 2021 at 9:39 pm
Keep it up!