3.2 የወደቁ መላእክት
2፡1 ሰይጣን፡- በባለፈው ጥናታችን መላእክት ያልወደቁ የወደቁት ብለን ተመልክተናል፤ አሁን በመቀጠል በወደቁ መላእክት ላይ ትኩረታችንን እናደርጋለን፡፡ መላእክት አስቀድሞ እግዚአብሔርን የሚያገለግሉ የከበሩ መላእክት ነበሩ፡፡ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛቸው ምክንያት የማገልገላቸውን መብትና ክብር አጡ፡፡ ስለ ወደቁ መላእክት ስንመለከት ያልታሰሩና የታሰሩ መላእክት ብለንበሁለት ከፍለን እንመለከታቸዋለን፡፡ ስለ ውድቀታቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረውን ሁሉ በተቻለ መጠን በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን፡፡
ከወደቁትና ካልታሰሩት መላእክት መካከል ሰይጣን አንዱ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰይጣንና አጋንንቱ መውደቅ በግልጽ የሚናገርበት ሥፍራ የለውም፡፡ ቢሆንም ግን ለንጉሦች ከተነገረው ትንቢት በስተጀርባስለ ሰይጣን መውደቅ በሁለት ሥፍራ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ከዚህ በተረፈ ስለሥራቸው ጥቂት ሐሳብ ከሚሰጠው በስተቀር በስፋትየሚናገረው ነገር የለውም፡፡
‹‹ሰይጣን›› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹‹ባላጋራ›› ወይም ‹‹ተቃዋሚ›› ማለት ሲሆን፣ በሌላ ስሙ በግሪክኛ ‹‹ዲያቢሎስ›› ማለት ‹‹ከሳሽ›› ማለት ነው፡፡ ስለ ሰይጣን በኢሳይያስና በሕዝቅኤል በሁለቱም ቦታ ተጽፎ ያለውን ስንመለከት፤ ሁለቱም የሚናገሩት ስለ ምድራዊ ነገሥታቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው ኢሳይያስ የሚናገረው በዘመኑ ገናና ለነበረውና አሕዛብን ሁሉ ስለ አስጨነቀው የባቢሎን ንጉሥ ሲናገር ሳለ፣ ከበስተጀርባው ስላለው ሰይጣንም ተናገረ፤እንዲህ በማለት፣ ‹‹አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፣ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አህዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፣እንዴት እስከ ምድር ድረስ ተቆረጥህ!አንተም በልብህ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፣ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፤በሰሜን ዳርቻበመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፤ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፤በልዑልም እመሰላለሁ አልህ፡፡ነገር ግን ወደ ሲኦልወደ ጉድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ …››(ኢሳ.14፡12-23)፡፡
በሁለተኛ ስለ ሰይጣን የሚነግረን ነቢዩ ሕዝቅኤል ሲሆን፣ እርሱም ለጢሮስ ንጉሥ በመጣው መልእክት ላይ ሲናገር ሳለ፣ ከንጉሡ በስተ ጀርባ ስለ አለው ሰይጣን እንዲህ ይላል፣ ‹‹ጥበብን የተሞላህ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ፡፡ በእግዚአብሔር ገነት በዔደን ነበርህ፡፡ የከበረ ዕንቁስ ሁሉ… ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር፡፡ አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ፣ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ፡፡ ከተፈጠርክበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ፡፡ በንግድህ ብዛት ግፍ በውስጥህ ተሞላ ኃጢአትንም ሠራህ ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ፣ ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ፡፡ በውበትህ ምክንያት ልብህ ኮርቶአል ከክብርህ የተነሳ ጥበብህን አረከስህ… ››(ሕዝ.28፡12-19)፡፡
ሁለቱም ጸሐፊዎች በተለያየ ሥፍራ ሆነው፣ ኢሳይያስ በአገሩ በኢየሩሳሌም፣ ሕዝቅኤል ደግሞ በባቢሎን በምርኮ በነበረ ጊዜ፣ በተለያየ ጊዜና ነገሥታቶች ሲጽፉ ሳለ ከንጉሦቹ በስተ ጀርባ የሰይጣንን አወዳደቅ እንደ ሥዕል እያዩ መልእክታቸውን ለነገሥታቶቹ አስተላልፈዋል፡፡ ከእነዚህ ውጭ ሰፋ ያለ ሐሳብ የሚሰጠን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የለም፡፡ ጌታም በምድር በነበረበት ጊዜ ቢሆንም ‹‹ሰይጣን ከሰማይ እንደ መብረቅ ሲወድቅ አየሁ›› ከሚለው ሐሳብ ውጭ ሰፋ ያለ ትምህርት የሰጠበት ጊዜ አልነበርም፡፡ ዛሬም ቢሆን ቃሉ የሚናገረውን ከማስተማር ውጭ ስለ ሰይጣን አፈጣጠር፣ ውድቀትና ተግባር ዝርዝር ትምህርት መስጠት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ሰይጣንን ኃይለኛ ነው፣ ቀንዳም ነው፣ እያልን በትምህርታችን አጉልተን ከማሳየት የጌታን ታላቅነት አስበልጠን በማሳየት የበለጠ ብናስተምር፣ ምዕመናንን ከፍርሃት መታደግና መጠበቅ እንችላለን፡፡
ሰይጣን የተጠራባቸው ስሞችና ተግባሩ፡-መጽሐፍ ቅዱስን በምናነብበትና በምናጠናበት ጊዜ፣ ሰይጣን በተለያየ ስሞች ተጠርቶ እናገኛለን፡፡በመጀመሪያ ማቴዎስ በወንጌሉ መዝግቦ የምናገኘው ስም ጌታን በፈተነበት ጊዜ የተጠቀመበት ሲሆን፣ ቃላቱም ዲያቢሎስና ፈታኝ የሚሉት ሲሆኑ፣ ቃሉ በግሪክኛ ‹‹ዲያቦሊስ›› ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ከሳሽ›› ማለት ነው (ማቴ.4፡1፣ ራዕ.12፡9፣ 20፡2፣ 1ተሰ.3፡5)፡፡ በሉቃስ ወንጌልም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድረጎ በላካቸው ጊዜ አጋንንት ስለ ተገዙላቸው ደስ ብሏቸው በመጡ ጊዜ እንዲህ አላቸው፣ ‹‹ሰይጣን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ›› እንደገናም ሉቃስ በሌላ ሥፍራ ኢየሱስ ይህን ስም እንደጠራው ሲናገር፣ ‹‹ ስምዖን ስምዖን ሆይ፣ እነሆ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤›› ብሎ ስሙን ሰይጣን ብሎ በመጥራት እንደተጠቀመ እንመለከታለን(ሉቃ. 10፡18፣ 22፡31)፡፡
ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕዩ ዲያቢሎስ፣ ሰይጣን፣ ዘንዶ፣ እባብና ከሳሽ የሚባሉትን ስሞችን ተጠቅሞአል፤(ራዕ.12፡9፣ 20፡2፣ ዘካ.3፡1) ካሉት ስሞች ቢያንስ አምስቱን ተጠቅሞ እናገኛለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ጋኔን ያደሩበትንሰው በፈወሰው ጊዜ በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል(ማቴ 12፡24)ነው የሚያወጣው ብለው ጌታን ለማንቋሸሽ ሲሉ የሰይጣን ስም የሆነውን ቃል ተጠቀሙ፡፡ በመጨረሻም ሰይጣን ብዙ ስሞች ቢኖሩትም፣ ጳውሎስ የጠራበት አንድ ስም አይተን ትምህርታችንን ወደ መጨረሱ እንመጣለን፡፡ በሁለተኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 6፡15 ላይ የሚያምኑ ከማያምኑ ጋር ምንም ግንኙነት እንደ ሌላቸው ሲናገር ሳለ፣ ‹‹ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው›› በማለት ይህን አዲስ ስም ተጠቅሞእናገኛለን፤ እናንተ ምን ያህል ስሞቹን ታውቁ ነበር?
እንግዲህ ከዚህ በላይ እንዳየነው ሰይጣን የእግዚአብሔርን ክብር ሊጋርድ የተቀባ መላእክ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጥቁር፣ ቀንድ ያለው አስቀያሚ አድርገን እንደምንስለው ሳይሆን፣ ቃሉ እንደሚናገረውየላቀ ጥበብ፣ ፍጹም ውበትና ያማረ መልክ ነበረው፡፡ ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ከክብሩ ወደቀ፤ ሰይጣን የክፋት ሁሉ ሥር፣ የውሸት አባትም ሆነ፤ ሰይጣን መንፈሳዊ አካል ያለው ፍጡር ሆኖ፣ ኪሩቤል ከተባሉት መላእክት ወገንና ከተፈጠሩት መላእክት ሁሉ ከፍተኛው ነበር፡፡ ዕውቀት፣ ስሜትና ፈቃድ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች፣ ሔዋን በእባብ እንዴት እንደ ተታለለች ሲጽፍ፣ ‹‹ እባብ በተንኰሉ ሔዋንን እንዳሳታት አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ›› በዚህ ጥቅስ ውሰጥ የምናየው ዋና ነገር ሰይጣን ባለው ዕውቀት እባብን ተጠቅሞ እንዴት ሔዋንን እንዳታለላት ነው (2ቆሮ.11፡3)፡፡ በራዕይ መጽሐፍ ምዕራፍ 12፡17 ላይ ዘንዶው በሴቲቱ ላይ እንደ ተቆጣ የሚናገረው ክፍል ስሜት እንዳለው ያመለክተናል፡፡ ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ፣ ሰይጣንፈቃድ እንዳለው ሲጽፍለት፣ ‹‹… ፈቃዱን ለማድረግ በዲያብሎስ ሕያዋን ሆነው ከተያዙበት ወጥመድ ወጥተው ወደ አእምሮ ይመለሳሉ ብሎ የሚቃወሙትን በየዋህነት ይቅጣ›› በማለት ሰይጣን ለራሱ ፈቃድ መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ ፈቀዱን ሰዎች እንዲፈጽሙ እንደሚያደርግ ያሳስበውና፣ ጢሞቴዎስም በእርሱ ፈቃድ ውስጥ እንዳይገባ ያስጠነቅቀዋል(2ጢሞ.2፡26)፡፡
ሰይጣን ቀደም ብለን ባየነው የትንቢት መጽሐፍ እንደምንመለከተው ሕዝቅኤል ‹‹ አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብነበርህ›› በማለት በተግባሩ እግዚአብሔርን ሊጋርድ የተቀባ፣ ከኪሩቤሌመካከል አንዱ እንደ ነበረ ያሳየናል (ሕዝ.28፡14)፡፡ ኃጢአት በመሥራቱ ከክብሩ ወርዶ ተገኝቶአል፡፡ በሰማይ የነበረውን ክብሩን ቢያጣም፣ በምድር ሌላ ሥልጣን እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ ጳውሎስ በሁለተኛ ቆሮንቶስ ሰዎች ወደ ክርስቶስ የማይመጡበትን ምክንያት ሲናገር እንዲህ ይላል፣ ‹‹ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ (ሰይጣን) የማያምኑትን አሳብ አሳወረ›› (2ቆሮ.4፡4) በማለት በምድር ላሉት ሰዎች አምላክ እንደ ሆነ ይናገራል፡፡ ሰይጣን ምንም እንኳን በምድር መኖር ባይችልም በአየር ላይ ሆኖ በአጋንንት አማካኝነት ዓለምን እንደሚገዛ በኤፌሶን መልእክቱ ላይ ‹‹በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ በፊት ተመላለሳችሁባቸው›› ብሎ ገልጾ እናገኛለን (ኤፌ.2፡2)፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ፣ አባቱ እንደሚያከብረው ምስክርነት በድምጽ በመጣለት ጊዜ፣ በአጠገቡ ለነበሩት ሰዎች ‹‹ አሁን የዚህ ዓለም ፍርድ ደርሷል አሁን የዚህ ዓለም ገዥ (ሰይጣን) ወደ ውጭ ይጣላል›› በማለት ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዥ እንደ ሆነ በራሱ አንደበት አረጋግጦአል (ዮሐ.12፡31፣ 16፡11)፡፡ ምንም እንኳን የዚህ ዓለም አምላክና ገዥ ቢሆንም፣ ሰው በፈቃዱ ካልተገዛለት በስተቀር በኃይል አምላክና ገዢ ሊሆን አይችልም፡፡
አንድ እናት ክርስቶስ ተመስክሮላቸው ጌታን ወደ ሕይወታቸው አስገብተው አማኝ አልነበሩም፤ ነገር ግን በነበሩበት ሃይማኖት በቤተሰባቸው በወረሱት ልምምድ ክርስቶስን ያውቁት ነበር፡፡ በአጋንንት ታመው ዘመዶቻቸውና ቤተ ሰብ ወደ ተለያየ አዋቂ ቤት፣ በመጨረሻም ወደ የአሩሲዋ እመቤት ወደሚባሉት ሳይፈቅዱ ወስደዋቸው ነበር፡፡ እርሳቸው ግን አጋንንትን ለማምለክ ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ ከዚያ ከተመለሱ በኋላ ቀድሞ እንደሚያደርጉት፣ ሌሊት እየተነሱ በአንድ እግራቸው ቆመው እግዚአብሔር እንዲምራቸው ሲጸልዩ ሳለ፣ ከዕለታት አንድ ቀን አጋንንቱ ለፍልፎ ለቋቸው ሄደ፡፡ ይህ በሴትየዋ የተፈጸመው ታሪክ የሚያሳየን ሰይጣን በፈቃዳችን ካልተገዛንለት በስተቀር፣ በእኛ ላይ ምንም ሥልጣን እንደሌለው ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ሰይጣን ነፍሰ ገዳይና ሐሰተኛ ነው (ዮሐ.8፡44)፤ዮሐንስ በአንደኛ መልእክቱ ሲናገር ‹‹ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን›› በማለት ዓለም በሙሉ በዲያብሎስ መያዙን ያረጋግጣል (1ኛ ዮሐ.5፡19)፡፡ የሰይጣን ዋና ዓላማ በየትኛውም ቦታና በማንኛውም መንገድየእግዚአብሔርን ዕቅድ ማጣመም ወይም ማደናቀፍ ነው፡፡ ይህን ለማከናወንም አለቃ በሆነበት ዓለም የራሱን ሥርዓት መሥርቶ የእግዚአብሔርን ገዥነት ለመቃወምና ለመቀናቀን ይጥራል፡፡ ይህን የሚያደርገው ግልጽና ተቃራኒ የሆነ መንግሥት በማቋቋም ሳይሆን የእግዚአብሔርን ዕቅድ በማስመሰል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ በጥላቻ፣ በውሸት፣ በቂም፣ በዘርና በሥልጣን እንዲገዳደሉና ደም እንዲፋሰሱ ያደርጋል፡፡
ሰይጣን ኢየሱስ ክርስቶስን በምድር በነበረበት ጊዜ ፈትኖታል፤ (ማቴ. 4፡1-1) ቢሆንም ዓላማውንና ተንኮሉን ስላወቀበት ጌታ በፈተናው ሊያሸንፈው ችሎአል፡፡ በመፈተን ስላልሆነለት በጴጥሮስ በኩል በኃዘኔታ መልክ በመቅረብ ወደ መስቀል ሄዶ የሰው ልጆችን እንዳያድን ለማድረግም ሞክሮ ነበር፤ ግን አልተሳካለትም፡፡ በመጨረሻም የዕብራውያን ጸሐፊ ምዕራፍ 2፡14 ላይ ‹‹በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው›› በማለት ኢየሱስ በሞቱ እንዳሸነፈው ይናገራል፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 22፡31 ላይ ሰይጣን ጴጥሮስንና ደቀ መዛሙርቱን ሊያበጥራቸው እንደ ለመነና ወደ ፈተና እንዳስገባቸው ቃሉ ይናገራል፡፡ ስለዚህ ዛሬም አማኞችን በኃይልና በማታለል ለመፈተን ጥረት ያደርጋል፤ እኛም ድል ያደረገው ጌታ ከእኛ ጋር ሆኖ እንደሚረዳን፣ በአሸናፊው ጌታ በመታመንና በእምነት በመደገፍ አሸናፊዎች መሆን ይገባናል፡፡
ሰይጣን ከክብሩ የወደቀና በመስቀሉ የተሸነፈ ጠላት ቢሆንም፣ አሁን ወደ ገሃነመ እሳት ብቻውን ላለመሄድ ብዙ ሰዎችን አስከትሎ መሄድ ስለሚፈልግ፣ ሰዎችን በማታለል ተከታዮቹ ለማድረግ ይፈልጋል፡፡ ‹‹ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልእክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና››፡፡ (2ቆሮ.11፡14) ራሱን በመለወጡ ሳንታለል ሁልጊዜ ወደ መስቀሉ ሥር በጸሎት በመውደቅና በመቅረብ የጌታን አሸናፊነት ልናውጅ ይገባናል፡፡
ቀደም ብለን እንዳየነው ሰይጣን ኃጢአት በሠራ ጊዜ እግዚአብሔር ካለበት የክብር ሥፍራ እንዲለቅ ተደረገ፡፡ ‹‹ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ…›› (ሕዝ.28፡16) ‹‹… እስከ ምድር ድረስ ተቆረጥህ›› (ኢሳ.14፡12) የክብር ሥፍራ መልቀቅ ብቻ ሳይሆን ገደብ እንደ ተደረገበት ማየት እንችላለን፡፡ (2ጴጥ.2፡4፣ ይሁዳ ቁ.9 ላይ ተመልከቱ፡፡ በራዕይ ምዕራፍ 9፡14 ላይ ‹‹… በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው አለው›› የሚለው ሐሳብ ወደፊትተፈተው የሚያደርሱትንና የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ይሆናል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ ሰይጣን የተጣለበት ጊዜ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳየናል፡፡ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ በላካቸው ጊዜና ደስ ባላቸው ጊዜ ጌታ እንዲህ አላቸው ‹‹ሰይጣንን እንደ መብረቅ ከሰማይ ሲወድቅ አየሁ››፡፡ (ሉቃ.10፡18) ይህ ማለት ሰይጣን የመጀመሪያውን ኃጢአት ሲሠራ ከመጀመሪያው ሰማይ ወደ ሁለተኛው ሰማይ ወደቀ፣ ጌታ ያየው ደግሞ ከሁለተኛው ሰማይ ወደ ሦስተኛው ሰማይ መውደቁን ሲሆን ጌታ ወደዚህ ምድር ሲመጣ፤ በራዕይ እንደምናገኘው ከሦስተኛው ሰማይ ወደ ምድር የሚጣልበትን ጊዜ ይሆናል፡፡ ሰይጣን ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ምድር ስለሚጣልበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያቢሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፣ ወደ ምድርም ተጣለ… ስለዚህ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ ደስ ይበላችሁ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው ዲያቢሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና›› (ራዕ.12፡7-12) በምድር ላይ ለተወሰነ ጊዜ (ለሰባት ዓመት) በዓለም ላይ ጥፋት ካመጣ በኋላ ለአንድ ሺህ ዓመት ይታሰራል፤ እንደገና ለጥቂት ጊዜ ይፈታና በመጨረሻም አውሬውና ሐሰተኛው ነብይ ወዳሉበት ገሃነመ እሳት በመጣል ፍጻሜው ይሆናል (ራዕ.20፡1-10)፡፡
2 Comments
Col.Admassu Berhanu · November 1, 2021 at 8:16 am
I am very happy just to learn from you. This is my first time to follow your teaching, I think I have missed so much. From this moment on I will continuously will attend your teaching. Let GOD Bless You and your family and wish you long age.
Amberber Gebru · November 1, 2021 at 10:18 am
Amen