ባለፈው ጥናታችን ያጠናነው የእግዚአብሔርን መጠሪያ ስሞች ሲሆን በመቀጠል የምናጠናው የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት ስለሚገልጠው ሥላሴ ይሆናል፡፡ በቄስ ማንሰል ስለ ሥላሴ እንዲህ ይላሉ ‹‹በአንዱ እግዚዘብሔር ዘንድ ሦስትነት አለ፤ በመካከላቸው ‹‹እኔ … አንተ… እርሱ›› የሚል አጠራር አለ፡፡ እግዚአብሔር የአስተርእዮን (መገለጥን) ተግባር ወደ ፍጻሜ ሲያደርሰው፣ ልጁንና መንፈሱን ወደ ዓለም በመላክ ሦስትነቱን ገለጠ፤ በአንድ እግዚአብሔር ሦስት መንፈሳውያን አካላት እንዳሉም አሳየ፡፡ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በአዲስ ኪዳን የተገለጠ የእግዚአብሔር ‹‹ስም›› ነው ማለት እንችላለን ማቴ.28፡19›› (ትምህርተ እግዚአብሔር በቄስ ማንሰል ገጽ 23)፡፡

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናገኛቸው መሠረታዊ ትምህርቶች መካከል ለመረዳትና ለሌሎች ለማስረዳትና ለማስተማር፤ በጣም ከባዱ ትምህርት የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ሥላሴ ብለን የምንጠራውን ትምህርት አሁን እንማራለን፡፡ ከዚህ በላይ እንዳየነው የእግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ወይም የሥላሴ ትምህርት ቀስ በቀስ እየተገለጠ የመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ስንመለከት፣ እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች በገለጠ ጊዜ፣ እንደ ተናገራቸው እንዳስተማራቸውና ብዙ እውነቶችን እንደ ገለጸላቸው ከቃሉ ማየት እንችላለን፡፡ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከምናገኛቸው ዕድገታዊ መገለጦች (Progressive Revelation) አንዱ ነው፤ ዕድገታዊ/ሂደታዊ መገለጥ ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ ተገቢ ጥያቄ ይሆናል፡፡ ዕድገታዊ መገለጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተሳሰቦች እያደጉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልፅ ሆነው የሚወጡበት፣ በአዲስ ኪዳን ብርሃን ወደ ብሉይ ኪዳን በማየት ቁልጭ ብለው የሚታዩ ሥነ መለኮታዊ የመገለጥ እውነቶች ናቸው፡፡

እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ጊዜ በነጠላ ኤሎሄ (ዘዳ.6፡4) እና በብዙ ቁጥር (ኤሎሄም ዘፍ.1፡1) እየተባለ ቢጠራም፣ በአዲስ ኪዳን መነፅር ካላየነው በስተቀር በትክክል በቁጥር ስንት እንደሆነ መወሰን አይቻልም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በዘዳግም 6፡4 ላይ ነጠላውንም ብዙውንም ተጠቅሞ እናገኛለን፤ ‹‹… አምላካችን (ያህዌ) እግዚአብሔር (ኤሎሄም) አንድ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነው››፡፡ ያህዌ ሲል ነጠላ አንድ መሆኑን፣ ኤሎሄም ሲል ደግሞ ብዙ ቁጥር እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ በብሉይ ኪዳን በነጠላና በብዙ ቁጥር የተገለጠው እግዚአብሔር ወደ አዲስ ኪዳን ስንመጣ በሦስትነት በግልጽ ተገልጦ እናገኘዋለን፡፡ እግዚአብሔር አብ (አባት)፣ እግዚአብሔር ወልድ (ልጅ)፣ እና እግዚአብሔር መንፈስ (መንፈስ ቅዱስ) ብለን እንጠራቸዋለን፡፡

በብሉይ ኪዳን በነጠላና በብዙ ቁጥር ተገልጦ የምናገኘው እግዚአብሔር፣ በአዲስ ኪዳን ግልጽ በሆነ መንገድ ራሱን በሦስት አካላት ገልጦ እናገኘዋለን፡፡ ለዚህም ብዙ ማስረጃዎች ማግኘት ስለምንችል ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን ብቻ እንመለከታለን፡፡ ማቴዎስ በወንጌሉ ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ታላቁ ተልዕኮ በተናገራቸው ጊዜ ያለውን ሲጽፍ 28፡19 ላይ ‹‹እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ  በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› የሚለው አገላለጽ አንድነቱንና ሦስትነቱን በግልጽ ያሳያል፡፡ ሦስት ስሞች ተጠቅሰው እያለ ‹‹ስሞች›› ሳይሆን ‹‹ስም›› ብሎ ነው የተጠቀመው፤ ስለዚህ አንድ አምላክ በሦስት እኩል ህላዌ (አካል) ተገልጠው እናገኛለን፡፡ ሦስቱም በመለኮት፣ በክብርና በባሕርይ አንድ ናቸው፡፡ ይህን እውነት ቃላት ሊገልጹት ባይችሉም፣ ለሰው አእምሮ በጣም የሚከብድ ቢሆንም፣  በዕድገታዊ መገለጥ የመጣው የሥላሴ እውነት ይህን ይመስላል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ደብዳቤ ጽፎ ጽሑፉን ሲዘጋ ‹‹የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር (አብ) የመንፈስ ቅዱስም ኀብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን›› (2ቆሮ.13፡14) በማለት ይዘጋል፡፡ ማቴዎስም በወንጌሉ እንደ ዘገበው ‹‹ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱም ላይም ሲመጣ አየ እነሆም ድምፅ ከሰማያት መጥቶ፡- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ›› (ማቴ.3፡16-17) በማለት ሦስቱን አካላት ጠቅሶአቸው እናገኛለን፡፡ እነዚህ ጥቅሶች የሚናገሩትን እውነት በእምነት ከመቀበል ውጭ ምን አማራጭ ይኖረናል? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ነው ብለን ከተቀበልን፣ ስለ ሦስቱ አካላት የሚለንን እውነት ነው ብለን ብንቀበል ራስ ከማዞር እንድናለን፡፡

5.1 የሥላሴ ትርጉም፡- ሥላሴ የሚለውን ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኘውም፡፡ ነገር ግን ቃሉ ባይገኝም መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት ያስተማረውን ትምህርት ሀሳቡን ይዞ እናገኛለን፡፡ ይህ ትምህርት ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች በሥጋዊ አእምሮአቸው ተመራምረው ስላልደረሱበት ምስጢረ ሥላሴ ብለው እንደ ጠሩት እናውቃለን፡፡ ትምህርቱ ከባድ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ የሥላሴን አካላት፣ አንድነትና ሦስትነት በግልጽ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ብሎ አስቀምጦት እናገኛለን፡፡

ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለው በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሰሜን አፍሪካው ተርቱሊያን በተባለው የሥነ መለኮትና የቤተ ክርስቲያን አባት ነበር፡፡ በመቀጠልም ቤተ ክርስቲያን ትምህርቱን በመቀበሏ ቀጣይነትን አግኝቶ ዘመናችን ድረስ ደርሷል፡፡ ተርቱሊያን በላቲን ቋንቋ ‹‹ትርንታስ››  ብሎ ሲጠቀምበት፣ የአንጾኪያው ጳጳስ ቴዎፍሎስ ደግሞ በግሪክ ቋንቋ ‹‹ትሪአስ›› በማለት የሥላሴን ትምህርት ሙሉ በሙሉ ገላጭ ባይሆንም አስተምረውበታል፡፡ ቄስ ማንሰልም በመጽሐፋቸው፣ ‹‹ሥላሴ የሚለው ቃልና ትምህርቱ እንደ መነጥር ሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ያለው ትምህርት ጒልህ ሆኖ እንዲታየን ያደርጋሉ እንጂ በእግዚአብሔር ቃል ላይ አዲስ ትምህርት አይጨምሩም›› ይላሉ ገጽ 209፡፡

በእንግሊዝኛም (Trinity) ሆነ በአማርኛው ‹‹ሥላሴ›› የሚለው ቃል ሦስትነቱን እንጂ አንድነቱንና ሦስትነቱን ሁለቱንም ሐሳብ በሚገባ አይገልጹም፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ በእንግሊዝኛ (Tri-Unity) በአማርኛችን አሐዱ-ሥሉስ (ከግዕዝ የመጣ ቃል) የሚለው ቃል በዘመናችን ጥሩ አማራጭ በመሆኑ ተቀባይነትን አግኝቶ ቤተ ክርስቲያን እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡

የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት የያዘ ስለሆነ በጥንቃቄ ልንመለከተው የሚገባ ታላቅ ምስጢር ያዘለ ትምህርት ነው፡፡ ሥላሴ የሚለው ቃል ምንም እንኳን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም በተግባር የተገለጸ እውነት ሲሆን፣ በመለኮት አንድ የሆኑ ሦስት ፍጹማን አካላት እንዳሉ የሚያስረዳ እውነት የሆነ ትምህርት ነው፡፡ በአርባ አምስት ዓመት የማገልገልና የማስተማር ሕይወቴ፣ እንደ ሥላሴ ትምህርት ለመረዳትም ሆነ ለማስተማር በጣም የሚከብደኝ ርዕስ ቢሆንም፤ ከጌታ ከተሰጠኝ ኃላፊነት የተነሳ፣ ከመጻፉ ማስተማሩ የበለጠ የሚቀለኝ ቢሆንም፤ ጽሑፉንም የተረዳሁትን ያህል በጌታ ዕርዳታ ለማቅረብ እየሞከርኩ እገኛለሁ፡፡ በመቀጠልም የሥላሴን የግል ተግባራት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኛቸውን እውነቶች ዘርዘር አድርገን እንመለከታለን፡፡   

5.2 አብ፡- ‹‹እግዚአብሔር አብ›› እግዚአብሔር አንድ ሆኖ ሳለ ራሱን በሦስት አካላት ወይም መንገድ እንደ ገለጠና ትምህርቱ ምስጢረ ሥላሴ ተብሎ እንደተጠራ ቀደም ብለን ለማየት ሞክረናል፡፡ በመጀመሪያ ከሥላሴ ውስጥ እግዚአብሔር አብ የሚለውን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብ የሚያስተምረውን እውነታዎች እንመለከታለን፡፡

             ሀ) ይፈጥራል፡ ስለ እግዚአብሔር አንድነቱ ስናጠና በዘፍጥረት መጽሐፍ ፈጣሪ መሆኑን ተመልክተናል፤ (ዘፍ. 1፡1) ነቢዩ ኢሳይያስም ‹‹አላወቀህምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድርም ዳርቻ ፈጣሪ  ነው፣ አይደክምም፣ አይታክትም፣ ማስተዋሉም አይመረመርም›› በማለት ስለ ፈጣሪነቱ ይናገራል (ኢሳ.40፡28)፡፡ የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊም በምዕራፍ 1፡2 ላይ ‹‹…ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን›› ሲል በዚህ ሥፍራ እግዚአብሔር አብ ዓለማትን ሲፈጥር ብቻውን ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ወልድ ጋር እንደሆነ ቃሉ በሚገባ በግልጽ በማስቀመጡ፤ የአብንም የወልድንም የፈጣሪነት ድርሻ በግልጽ ያሳየናል፡፡

             ለ) ያቅዳል፡- እግዚአብሔርን በዘፍጥረት መጽሐፍ ስንመለከተው የዕቅድ አምላክ እንደ ሆነና ሁሉን በቃሉ ሲፈጥር በዕቅድ እንዳደረገው መረዳት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ከፍጥረት ጊዜ ጀምሮ ሁሉም ነገር ሥርዓቱን ጠብቆ እንዳለ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ፈጣሪነትና አቃጅነት አይነጣጠሉም፤ ስለ አብ ፈጣሪነት ስንመለከት ስለ አቃጅነቱም አያይዘን ማየት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ያለ ዕቅድ የሚሠራ ነገር ውጤትና ቋሚነት የለውም፤ ዕቅድ ከሌለ ምን እንደሚሠራም አይታወቅም፡፡ ፍጥረትንም ሆነ ድነታችንን ሲያዘጋጅ በዕቅድ እንደሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ምዕራፍ 1፡3-6 ላይ ዓለም ሳይፈጠር እንደ መረጠንና ልጆቹ እንድንሆን እንደ ወሰነን ይናገራል፡፡ ጴጥሮስም በ1ኛ.ጴጥሮስ 1፡1 ላይም ‹‹… አስቀድሞ እንዳወቃቸው …›› የሚለውን ሀሳብ ስንመለከት በቅርብም በሩቅም ማቀድ መቻሉን ያመለክተናል፡፡ 

            ሐ) አባትነት፡ እግዚአብሔር አብ ይፈጥራል፣ ያቅዳል፣ አባትም ነው፤ እግዚአብሔር ለብዙዎች ፈጣሪ እንጂ አባት አይደለም፤ ምክንያቱም ሰዎች አባትነቱን አልተቀበሉትም፡፡ ለተቀበሉት ግን እግዚአብሔር አብ ፈጣሪ፣ ዕቅድ አውጭ፣ የሚወስን፣ የሚመርጥ፣ ትዕዛዝ የሚሰጥ፣ የሚፈርድና የሚሾም ህላዌ (አካል) ያለው ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር አብ በፈጣሪነቱ የሰዎች ሁሉ አባት እንደሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ  በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17፡24-29 ላይ የእግዚአብሔር ዘመዶች ነን ለሚሉት ለአቴና ሰዎች ሐሳባቸውን ተጠቅሞበት ገልጾታል፡፡ ሙሴም በመጽሐፉ በዘጸዓት ምዕራፍ 4፡22 ላይ ‹‹እስራኤል የበኵር ልጄ ነው›› በማለቱ እግዚአብሔር (አብ) የእስራኤል ሁሉ አባት ብሎ መጥራቱን ያመለክተናል፡፡ ጌታም በሚጠመቅበት ጊዜ አብ አባቱ በድምጽ እንደ መሠከረለትና ጌታም ራሱ አባቴ ብሎ የተናገረውን ከቃሉ ማንበብ እንችላለን፡፡ ‹‹…የምወደው ልጄ ይህ ነው›› (ማቴ.3፡17)፣ ‹‹… የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል›› (ዮሐ.14፡21) እንዲሁም ስለ አማኞች ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ ‹‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን፣ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው፤›› በማለት እኛም ዛሬ በክርስቶስ በማመናችን ምክንያት ሁላችንም የእግዚአብሔር አብ ልጆች የመሆን ሥልጣን ማግኘታችንን ያሳየናል(ዮሐ.1፡12)፡፡ ጳውሎስም በቆሮንቶስ መልእክቱ ‹‹ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን›› (1ቆሮ.8፡6) ሲል  በገላትያ ደግሞ ‹‹በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና›› (ገላ.3፡26) በማለት እግዚአብሔር ዛሬም ለእኛ ፈጣሪያችን ብቻ ሳይሆን አባታችንም እንደሆነ በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በሚቀጥለው ጥናታችን በሥላሴ ሥር ስለ ወልድ እንመለከታለን፡፡


2 Comments

Sami · January 22, 2022 at 7:17 am

ስለ ትምህርቱ እግዚአብሔር ይባርካቹ። ነገር ግን ጥያቄ አለኝ። ብዙ ጊዜ ወንጌል ስርጭት ላይ ሙስሊም ወንድሞች ሥላሴን አስመልክቶ
1 ኢየሱስ እንዴት ለአብ ልጅ ሆነ ወይም እንዴት ተወለደ ? መቼ ተወለደ?
2 ኢየሱስ ለምን መስቀል ላይ ኤሎሔ ላማሰባክታኒ( አባት ሆይ ለምን ተውከኝ አለ?

    Amberber Gebru · February 6, 2022 at 6:49 pm

    ወንድም ሳሚ የጌታ ጸጋና ሰላም ይብዛልህ! በመጀመሪያ ትምህርቱ እንደ ጠቀመህ ስለ ሰጠኸ አስተያየት አመሰግናለሁ፡፡ የጠየቅኸኝ ጥያቄ በጽሑፌ እንደ ገለጥኩት ለእኔም ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመቀበልና ለማስተማር ከሚከብዱኝ ትምህርቶች አንዱ ነው፡፡ ቢሆንም ይህን እውነትን ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደ ተጻፈ ማወቁ መልካም ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከሰማይ ዝም ብሎ የወረደ መጽሐፍ አይደለም፡፡

    እግዚአብሔር ራሱን የገለጠላችው ሰዎች እንዲጽፉ በተሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት የሰሙትን፣ ያዩትን፣ ቃል በቃል የጻፉ ሲኖሩ፤ እንደ ወንጌላዊ ሉቃስ በወንጌሉ እንደ ጻፈው ‹‹… ከመጀመሪያው በዓይን ያዩትና የቃሉ አገልጋዮች የሆኑት እንዳስተላለፉልን በኛ ዘንድ ስለ ተፈጸመው ነገር ብዙዎች ታሪክን በየተራው ለማዘጋጀት ስለ ሞከሩ እኔ ደግሞ ስለ ተማርኸው ቃል እርግጡን እንድታውቅ በጥንቃቄ ሁሉን ከመጀመሪያው ተከትዬ በየተራው ልጽፍልህ መልካም ሆኖ ታየኝ›› (ሉቃስ 1፡1-4) ጥናት አድርጎ (RESARCH) እንደ ተጻፈው የጻፉ አሉ፤ እንዲሁም ሐዋርያው ጳወሎስ የቆሮንቶስ መልእክቱን ሲጽፍ ‹‹… ወንድሞቼ ሆይ፣ በመካከላችሁ ክርክር እንዳለ ስለ እናንተ የቀሎዔ ቤተ ሰዎች አስታውቀውኛልና›› (1ቆሮ. 1፡9)፣ ‹‹ስለ ጻፋችሁልኝስ..›› 1ቆሮ 7፡1 ብሎ የሚናገራቸው አሳቦች ከሰዎች የደረሰውን ሪፖርትና ሰዎች ለጠየቁት ጥያቄ መለስ ለመስጠት በጌታ ፊት በሚሆንበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንዲጽፍ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት፤ ሌሎችም በዚሁ መንገድ የጻፉት ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ቃል ሆኖ በመጽሐፍ ቅዱስ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡

    ሁለተኛው ልናውቀው የሚገባን ነገር ቢኖር የተጻፈው ቃሉ/መልእክቱ የእግዚአብሔር ሲሆን፣ ቃሉ የተጻፈበት ቋንቋውና የአጻጻፍ ስልቱ (STYLE) ሰዋዊ ነው፤ ብሉይ ኪዳን በአይሁድ ቋንቋ በዕብራይስጥ፣ አዲስ ኪዳን በግሪኮች ቋንቋ በግሪክኛ ነው የተጻፈው፡፡ ቋንቋውና የአጻጻፍ ስልቱ ብቻ ሳይሆን የተጻፈበት ባሕሉም ሰዋዊ ነው፤ ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ከእግዚአብሔር ቃሉን (መልእክቱን) ተቀብለው የጻፉልን በሚገባን ሰዋዊ በሆነ ቋንቋና ባሕል መሠረት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ ኒቆዲሞስን ሲያስተምር ሳለ፣ ‹‹ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? (ዮሐ. 3፡12) ብሎ በተናገረው መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የጻፉልን በሚገባን በሰዋዊ ቋንቋ፣ ባሕልና የአጻጻፍ ስልት ነው፡፡

    በዚህ መሠረት ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ማለት ወይም እግዚአብሔር አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ብሎ ቃሉ በሚገልጽልን ጊዜ፣ እግዚአብሔር ማርያምን አግብቶ ኢየሱስን ወለደ ማለት በፍጹም አይደለም፡፡ የሰው ልጆች እንዲገባን ወልድ እንደ ልጅ ሆኖ ቀርቦአል፡፡ ኢየሱስ በሥጋ ከመወለዱ ከአምስት መቶ ዓመት በፊት በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 7፡13 ላይ ‹‹እነሆ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ…›› ይላል፡፡ ይህ በእምነት ካልተቀበልነው በስተቀር ለሥጋዊ አእምሮአችን የማይገባን፤ በቃሉ ላይ ሠፍሮ የምናገኘው ኢየሱስ በመለኮት የእግዚአብሔር ልጅ፣ በሥጋ የሰው ልጅ ተብሎ ተጠርቶአል፡፡ ኢየሱስ በማርያም ማህጸን መጥቶ በመንፈስ ቅዱስ አደረ እንጂ ሥጋዊነትን ከማንም አልወሰደም፡፡ ቃሉ ስለ አማኞችም ሲናገር ‹‹እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም›› (ዮሐ. 1፡13) በማለት ኢየሱስ ብቻ ሳይሆን እኛም ብናምንበት የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን የመጠራት ዕድል ተሰጥቶናል፡፡ ክርስቶስን ያመንን ሁሉ ከእርሱ የተነሳ የእግዚአብሔር ልጆች ነን፡፡

    ስለዚህ ይህ መለኮታዊ የልጅነት አጠራር እንዲገባን በምድራዊ አጠራር ቃሉን ጸሐፊዎች የተጠቀሙበት እንጂ እኛ እንደምናስበው ኢየሱስ በባልና ሚስት ሁኔታ የመጣ አይደለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ ውስጥ ብዙ ጊዜ ራሱን ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ›› (ዮሐ. 5፡25፣ 6፡69) ‹‹አባቴ›› (8፡14፣28፣35፣49፣54፣ 6፡40፣ 10፡18) የሰው ልጅ (8፡28፣ 6፡53፣62)፣ እያለ ተጠቅሞ እናገኘዋለን፡፡ ቀደም ብለን ባየነው መሠረት አንዱ እግዚአብሔር ራሱን በሦስት መንገድ ገልጾ እናገኛለን፤ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የታላቁን ትእዛዝ ሲሰጥ ‹‹ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቁ›› አላቸው (ማቴ.28፡19)፣ ኢየሱስ በአካል ሲጠመቅ፣ የአባቱ ድምጽ ከሰማይ መጣ፣ መንፈስ ቅዱስ እንደ ርግብ ወረደበት፣ (ማቴ.3፡16-17) ይበል እንጂ ስሞች ሳይሆን ስም ብሎ መጠቀሙ እግዚአብሔር አንድ መሆኑንና በሦስት መገለጡ ያሳየናል፡፡

    ወንድም ሳሚ ኢየሱስ ለአብ ልጅ የሆነበት መንገድ እኛ በምናስበው በምድራዊ አሠራር ከባልና ሚስት የተገኘ ነው ማለት ሳይሆን፣ ራሱን በሚገባን በምድራዊ አሠራር መግለጹ ነው፡፡ ሰው ኃጢአት በሠራ ጊዜ የተፈረደበት ሞት ነበር፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ለማዳን የሚሞት ሥጋ ይዞ መጣ፤ ያ የተገለጠበት የሚሞተው ሥጋ የእግዚአብሔር ልጅ፣ የሰው ልጅ ተብሎ ዓለም ሳይፈጠር የተወሰነ መሆኑንና መጠራቱን፤ በአንድ ጊዜ ኢየሱስ መለኮታዊም ሰብዓዊም እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ ኢየሱስ ለሰው ልጆች ኃጢአት በመስቀል ላይ በሚሞትበት ጊዜ፤ እግዚአብሔር (አባቱ) ኢየሱስ የእኛን ኃጢአት ወስዶ ራሱ ኃጢአት በሆነ ጊዜ፣ አባቱ ከኃጢአት ጋር ስለማይተባበር፣ በኃጢአት ላይ እየፈረደ ስለሆነ ፊቱን አዞረበት (2ቆሮ. 5፡21)፡፡ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ የአባቱን ኅብረት፣ አንድነት፣ እርዳታ በማጣቱ፣ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ›› ትርጉሙም ‹‹አምላኬ አምላኬ ስለ ምን ተውኸኝ›› ማለት ነው (ማቴ. 27፡46፣ ማር. 15፡34)፡፡ ሉቃስ ደግሞ (23፡46) ላይ ‹‹አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ›› በማለት አቅርቦታል፡፡ ጌታም ጸሐፊዎቹም ሰማያዊውን አሠራር ለመግለጽ በምድራዊ በሚገባን መንገድ መግለጣቸው እንደሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡

    ሰው ያለውን ከሰጠ ቢስ አይባልም እንደሚባለው ያለኝን የቃሉን መረዳት ለማካፈል ሙከራ አድረጌአለሁ፤ ቀሪውን መንፈስ ቅዱስ የበለጠ እንደሚያስተምርህ አምናለሁ፡፡ በአንተ ጥያቄም ሌሎቹም ይማሩበታል፤ ጌታ ካንተ ጋር ይሁን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *