2.2 የእግዚአብሔር መገለጥ

2.1 የመገለጥ ትርጉም፡- ባለፈው ጥናታችን ስለ እግዚአብሔር መኖር ተመልክተን ነበር፤ አሁን ደግሞ ስለ መገለጡ ቀጥለን እናጠናለን፡፡ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ስናጠና መገለጥ ማለት ምን ማለት ነው ብለን በመጠየቅ ስለ መገለጥ በትንሹ ለማየት ሞክረን ነበር፤ አሁን ግን ትንሽ ሰፋ አድርገን ለማየት እንጀምራለን፡፡ መገለጥ የሚለው ቃል  ከግሪኩ አፖካሉፕሲስ (Apokalupsis) ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹የተገለጠ›› ማለት ነው፡፡ የእንግሊዝኛው ቃል (Revelation) የሚለው ይህንኑ ነው የሚያመለክተው፡፡ ተሸፍኖ ተደብቆ፣ ተሰውሮ የነበረ ነገር ሲገለጥና ሲታወቅ መገለጥ ይባላል፡፡ ሰው ኃጢአተኛ በመሆኑና እግዚአብሔርም ከሰው በላይ የላቀና  ወሰን የሌለው በመሆኑ ሰው በምንም ዓይነት መንገድ ሊያገኝና ሊያውቅ የማይችለውን እውነት እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች  የገለጠበት መንገድ መገለጥ ይባላል፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ለመግለጥ የመጀመሪያውን እርምጃ ወስዶአል፡፡ በዚህም መሠረት ሰው እግዚአብሔርን ሊያውቅ የሚችልባቸውን መንገዶች ተራ በተራ እንመልከት፡፡

 እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች በሰው መልክ፣ በመልአክ፣ በድምፅ፣ ቃላት በፊደል በመጻፍና በሕልም  የተገለጠባቸው ብዙ ጊዜያቶች ነበሩ፡፡ ራሱን የገለጠባቸው መንገዶች ሰፊና ብዙ ቢሆኑም ቀጥለን የምንመለከታቸው ጥቂቶቹን ብቻ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ራሱን የገለጸባቸውን ሁለት መንገዶች ብቻ እናነሳለን፡፡ እነርሱም አጠቃላይና ልዩ መገለጥ ተብለው የሚጠሩት ናቸው፡፡

3.2 አጠቃላይ መገለጥ፡- አጠቃላይ መገለጥ የተባለበት ምክንያት ማንኛውም ሰው በአንድ ጊዜ በተለያየ ቦታ ሆነው መገለጡን በፍጥረቱ አማካኝነት ማንነቱን ሊደርሱበት ይችላሉ፡፡ እንደ ልዩ መገለጥ ዝርዝር ነገሮችን ባይዝም ስለ እግዚአብሔር መኖር የተወሰነ እውነት ግንዛቤን እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡ ‹‹አጠቃላይ አስተርእዮ (መገለጥ)፣ ሰው ከእግዚአብሔር መገኘቱን፣ በመግቦተ እግዚአብሔር መኖሩንና ወደ እግዚአብሔር የሚመለስ መሆኑን ስለሚያሳየው፣ የደህንነት ትምህርት ለሚገኝበት ለልዩ አስተርእዮ ያዘጋጀዋል›› (ቄስ ማንሰል ትምህርተ እግዚአብሔር ገጽ 29)፡፡ ይህ መገለጥ ለሰዎች ሁሉ ስለሆነ፣ ሰው ሁሉ በዚህ መገለጥ ለመጠቀም ይችላል፡፡ በአጠቃላይ መገለጥ ሥር እግዚአብሔር የተጠቀመባቸውን ሁለት መንገዶች እንመለከታለን፡፡

ሀ) ተፈጥሮ ይመሰክራል፡- እግዚአብሔር በተፈጥሮ ራሱን ለሰው ልጆች ገልጦአል፤ ሰውም በተፈጥሮ በተገለጠለት መሠረት፣ ሰው ስለ እግዚአብሔር ምስክርነት በመስጠቱና በማስተማሩ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ‹‹እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፣ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና›› በማለት እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች መግለጡን ይናገራል (ሮሜ 1፡18-23)፡፡ ጸሐፊው ሉቃስም በልስጥራን ሕዝቡ ጳውሎስን እንደ አምላክ አድርጎ በተመለከቱት ጊዜ፣ ለሕዝቡ መልስ ሲሰጥ ‹‹ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፣ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም›› በማለት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሚያስልጋቸውን እንደ ጸሐይ፣ ጨረቃ፣ ዝናብና የሚበሉትን ነገሮች በመስጠት፣ ራሱን እንደ ገለጠ ተናገረ (የሐዋ.14፡17)፡፡

 ሰው በፍጥረት መኖር ብዙ ሊማር ይችላል፤ ሥርዓታቸውን በመጠበቃቸው፣ በውበታቸውና ለሰው ልጆች ጠቃሚ መሆናቸውን ሲመለከት ፈጣሪ እንዳላቸው ማስተዋልና መረዳት ይችላል፡፡ ዳዊት በመዝሙሩ 19፡1-6 ላይ ‹‹ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል፡፡ ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፣ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች፡፡ ነገርም የለም መናገርም የለም፣  ድምጻቸውም አይሰማም፡፡ ድምጻቸውም ወደ ምድር ሁሉ፣ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ›› በማለት ፍጥረት የእግዚአብሔርን መኖር እንደሚመሰክሩ ይናገራል፡፡ በኢዮብ መጽሐፍም ስንመለከት፤ ከምዕራፍ 38 እስከ 41 ባለው ክፍል ውስጥ፣ እግዚአብሔር ከኢዮብ ጋር ተከራክሮ ያሸነፈው፤ በሚመለከታቸው በዙሪያው ባሉ በተፈጥሮዎች ነው፡፡ በዓይን የሚታዩ፣ የማይታዩና በአጉሊ  መነጽር የሚታዩት ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩን የገለጠባቸው ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት በየዘመናቱ የሚኖሩ የሰው ልጆች ሁሉ፣ እኛንም ጨምሮ ከዚህ ምስክርነት ማምለጥ አንችልም፡፡ ፍጥረትም መመስከሩን አያቋርጥም፣ መቀበል አለመቀብል ግን የእኛ ድርሻ ነው፤ መቀበሉ ግን እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው፡፡

 ) ህሊና፡- እግዚአብሔር በተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን በሰው ህሊና አማካይነትም ራሱን ገልጾአል፡፡ ሐዋርያው ጳወሎስ በሮሜ መልእክቱ ‹‹… ህሊናቸው ሲመሰክርላቸው፣ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ›› (ሮሜ 2፡15) በማለት እግዚአብሔር በውስጣቸው ባስቀመጠው በህሊናቸው አማካኝነት እንደሚታወቅ ይናገራል፡፡ መዝሙረኛው እንዳለውም  የሰውን ልጅ እግዚአብሔር በሚፈጥርበት ጊዜ ግሩምና ድንቅ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ ይህም የሰውን አካል ስንመለከት ብዙ አስደናቂ ከሆነበት ነገር አንዱ ህሊናው ነው፡፡ ይህም ህሊና ከሌሎች እንሰሳት የበለጠ አሳቢ፣ አቃጅ፣ ጥበበኛ፣ አዋቂና ነገሮችን በማገናዘብ እንዲያደርግ አድርጎታል፡፡ ሰው በተሰጠው ህሊና በተቻለው መጠን በመጠቀሙና ተፈጥሮን መረዳት በመቻሉ ከእንሰሳት ልዩ እንዲሆን ረድቶታል፡፡ ተፈጥሮን ብቻ ሳይሆን የፈጠረውንም አምላክ እንዲያውቅበትና ክፉና ደጉንም እንዲለይበት፣ አምላኩንም እንዲያመሰግንና እንዲያመልክ ህሊና ተሰጥቶታል፡፡ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረው ሰው ሁሉ የአምላኩን መኖር እንዲያውቅ ምስክርነት የሚሰጠው በውስጡ የህሊና ሕግ አለው፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ፣ ሰው የተሰጠውን ህሊና እግዚአብሔርን ለማወቅ ሳይሆን ለክፋት፣ ለዓመፀኝነት፣ ኃጢአት ለመሥራትና እግዚአብሔርን ለመካድ እንደ ተጠቀመበት ይገልጻል፡፡ ‹‹የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ፡፡ ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ የማይጠፋውንም የእግዚአብሔርን ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸው በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ›› (ሮሜ 1፡21-23) በማለት እግዚአብሔርን እንዲያውቅበት የተሰጠውን ህሊና ለክፋት እንዳዋለው ይናገራል፡፡ አሁንም በሮሜ 2፡14-15 ላይ ይህ ለሰው የተሰጠው ህሊና በተፈጥሮ ውስጥ ያለው ሕግ፣ የእግዚአብሔርን የላቀ ሕግ ሰጪ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እግዚአብሔር ሕጉን በሰው ውስጥ ማስቀመጡን ብቻ ሳይሆን፣ ሰው ለዚህ ሕግ ተጠያቂ እንደሆነም ጭምር ያስገነዝባል፡፡ ሰው በውጭ የእግዚአብሔርን መገለጥ ይካድ እንጂ ይህን በውስጡ በህሊናው የተገለጠለትን እውነት መካድ በፍጹም አይችልም፡፡ እግዚአብሔር በተፈጥሮና በህሊና መኖሩን ያስታወቀበትን መንገድ ምን ያህል ለመቀበል ፈቃደኞች ነን፡፡ እነዚህን አጠቃላይ መገለጦች መቀበል ከቻልን፣ ወደሚቀጥለው ደረጃ ወደ ልዩ መገለጥ መምጣት አይከብደንም፡፡

3.3 ልዩ መገለጥ፡- ሰው እግዚአብሔርን እንዲያውቅና ከእርሱም ጋር ኅብረት እንዲያደርግ ልዩ መገለጥ አስፈላጊ ነው፡፡ በአጠቃላይ መገለጥ የእግዚአብሔርን መኖር የተረዳንና ያወቅን ሁሉ፣ ልዩ መገለጥን መቀበል ይቀለናል፡፡ ሰው በኃጢአት በወደቀ ጊዜ የሰው ህሊና ስለ ደነዘዘ ሰው በራሱ መንገድ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔርን መፈለግና ማወቅ አይችልም፤ ምክንያቱም የነበረው ሕብረት በመቋረጡ፡፡ ስለዚህ ይህ ሕብረት እንዲታደስና ሰውም በሙላት አምላኩን እንዲያውቅ ልዩ መገለጥ በማስፈለጉ እግዚአብሔር ራሱ መገለጦችን አዘጋጀለት፡፡ የመጀመሪያው ልዩ መገለጥ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን፣ ከጥንት ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ትንቢተ ሚልክያስ ድረስ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ ሲያመለክት ቆይቶአል፡፡ በአዲስ ኪዳንም ስንመለከት ይህ ልዩ መገለጥ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መገለጥ ጨምሮ እንደመጣ እንመለከታለን፡፡ በዚህ መሠረት ልዩ መገለጥም በሁለት ይከፈላል፡፡

 ሀ) በቃሉ፡- በአስተምህሮተ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተመለከትነው፣ ቃሉ የእግዚአብሔር ልዩ መገለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰዎች ልጆች በተለያዩ  ጊዜያትና ወራት በህልም፣ በራዕይ፣ በድምጽ፣ በመልአክና በሰው መልክ ቢገለጥም፣ በየዘመናቱ ለሚኖሩ ትውልዶች ሁሉ በጽሑፍ ካልተቀመጠ መልእክቱ ሊደርስ አይችልም፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በየዘመናቱ ራሱን ለተለያዩ የሰው ልጆች ከገለጠላቸው በኋላ፣ በጽሑፍ እንዲያሰፍሩት በማዘዙ፣ በጽሑፍ አስፍረው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ አደረጉት፡፡ በዘጸዓት መጽሐፍ እንደምናገኘው እግዚአብሔር ሙሴን ‹‹…ይህን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው›› በማለት እንዳዘዘው እንመለከታለን (ዘጸ.17፡14)፡፡ ስለዚህ እንደ ሙሴ፣ ኤርምያስ፣ ኢሳይያስም ሆኑ ሌሎች ጸሐፊዎች በተሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት የተገለጠላቸውን እውነት በጽሑፍ አስፍረው፣ እስከ ዘመናችን ድረስ ደርሷል፡፡ ‹‹…የነገርሁህን ቃል ሁሉ በመጽሐፍ ጻፍ›› (ኤር.30፡2)፣ ‹‹አሁንም ሂድ፣ ለሚመጣውም ዘመን ለዘላለም እንዲሆን በሰሌዳ ላይ በመጽሐፍም ውስጥ ጻፍላቸው›› (ኢሳ.30፡8) የሚሉት የእግዚአብሔር ሰዎች ጻፉ ተብለው በተሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት እንደ ጻፉት ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በመጨረሻም በእስትንፋሰ-እግዚአብሔር የተጻፈው ቃል ሁሉ፣ ብሉይና አዲስ ኪዳን በአንድ ላይ በመጠቅለል አንድ መጽሐፍ ሆኖ እንደ ቀረበልን ቀደም ባሉት ጥናታችን አይተናል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ልናውቀው የሚገባንን ነገር ሁሉ የሚነግረን መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን፣ ያለ ኢየሱስ ደግሞ እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ማወቅ አንችልም፡፡ ሙሉ በሙሉ ሲባል ስለ እግዚአብሔር ሁሉን ማወቅ እንችላለን ማለት ሳይሆን፤ በልጁና በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የተገለጠውንና ልናውቅ የምንችለውን ብቻ ማለት ነው (ሉቃ.24፡44-45፣ ዮሐ.14፡8-11)፡፡

ልዩ መገለጥ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በምንመለከትበት ጊዜ እግዚአብሔር ሰዎችን የተናገረበት የተለያዩ መንገዶች እንደነበሩ ተመልክተናል፡፡ አንዳንዶችን በህልም፣ በራዕይና በድምጽ … በመሳሰሉት መንገዶች ተጠቅሞ ወደ እርሱ የጠራቸው ሰዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ ዮሴፍን በህልም፣ ሐዋርያው ጳውሎስን በድምጽና  ለዮሐንስ በራዕይ … ራሱን ገልጦላቸዋል፡፡ በየዘመናቱም፣ በዚህም ዘመን እግዚአብሔር ለተለያዩ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ራሱን በመግለጥ ይናገራል፡፡ በእነዚህ መንገዶች ሰዎች ወደ ስሕተት እንዳንገባ ሁሉንም የምንመዝነው ግን በቃሉ መሠረት መሆን አለበት፡፡ ከቃሉ ጋር የሚጋጭ ከሆነ ቆም ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባናል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ብለህና ቃል ኪዳን ገብተህ ያገባሃትን ሚስትህን፣ በመገለጥ ፍታ ብትባል ከቃሉ ጋር ስለሚጋጭ ቃሉ ስለዚህ ነገር ምን ይላል ብለህ ቆም በማለት ራስህን መጠየቅ ይገባሃል (ሚል. 2፡15-16)፡፡

 ለ) በክርስቶስ፡- የዕብራውያን ጸሐፊ እንደሚናገረው፣ ‹‹ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፣ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን›› (ዕብ.1፡1-2) በማለት እግዚአብሔር ራሱን ለሰው ልጆች በተለያየ መንገድ እንደ ገለጠ ይናገራል፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው በህልም፣ በራዕይ፣ በድምጽ፣ በነቢያትና በመላእክት ተናግሮ  በመጨረሻ ልዩ መገለጥ በሆነው ልጁ እንደ ተናገረን ያመለክታል፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስም በወንጌሉ በምዕራፍ 1፡18 ላይ ‹‹መቼም ቢሆን  እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› በማለት እግዚአብሔርን ያየው ሰው አለመኖሩን፤ ነገር ግን ልዩ መገለጥ በሆነው በልጁ በኩል ብቻ እንደ ተገለጠ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ጥቅስ እንደምንረዳው እግዚአብሔር በየዘመናቱ ራሱን ለሰው ልጆች በመግለጥ ሕብረት ማድረግ እንደሚፈልግ ሲሆን፣ በመጨረሻም በልጁ በኩል ሕብረት ማድረግ እንደ ወደደና እርምጃ እንደ ወሰደ እንመለከታለን፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ነው በ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱ ‹‹ወደ ልጁ ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት  የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው›› (1ኛ ቆሮ.1፡9) በማለት እግዚአብሔር የመሠረተው ሕብረት የማይለወጥ አስተማማኝ መሆኑን ያበስራል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሟላ ልዩ መገለጥ ሆኖ ወደ ምድር በመምጣት እግዚአብሔርን፣ ፈቃዱን፣ ባሕርይውንና ጠባዩን ገለጠልን፡፡ ለዚህ ነው ጌታም በወንጌሉ በፊልጶስ ለተጠየቀው ጥያቄ ሲመልስ፣ ‹‹አንተ ፊልጶስ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል እንዴትስ አንተ፡- አብን አሳየን ትላለህ? እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን?›› (ዮሐ.14፡9-10) ያለው፡፡ በመጨረሻም ጳውሎስ ‹‹በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና›› (ቆላ.2፡9) በማለት የማይታየው እግዚአብሔር በሚታይ አካል (ሥጋ) ራሱን ለሰው ልጆች በመግለጡ፤ ይህ የመጨረሻው ልዩ መገለጥ መሆኑን ያመለክታል፡፡

የእግዚአብሔርን መኖር በአጠቃላይና በልዩ መገለጥ ተቀብለን ከሆነ መልካም ነው፤ እነዚህን መገለጦች ካልተቀበልን ግን እግዚአብሔርን ለማወቅና ከእርሱ ጋር ሕብረት ለማድረግ ከዚህ ውጭ ምን ተስፋ አለን?


1 Comment

Assefa Desalegn · July 7, 2023 at 10:48 pm

God is so good

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *