ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን (online) አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት አራት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እና የሶሻል ሚዲያ ቴሌግራምና ፌስ ቡክ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስናጋራ ቆይተናል፡፡ በዚህ በልደት ሰሞን  ‹‹መልካም ልደት›› በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍ ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እናጋራችኋለን፡፡ አሁን በዚህ ሳምንት ልደትን ልናከብር እየተዘጋጀን ባለንበት ጊዜ ከቅዱስ ቃሉ የጌታን ሰው የመሆኑን ታሪክ አብረን እንድንካፈል ወደድን፡፡

የምንካፈለው ጽሑፍ ርዕሱ ‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ›› የሚል ሲሆን፣ ታሪኩ የተመሠረተው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 1፡14 ላይ ‹‹ስለ ኢየሱስ ሰው›› መሆን እንመለከታለን፡፡ ዮሐንስ በዚህ በወንጌሉ ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ›› በማለት ጽሑፉን ይጀምርና ወደ ቁጥር 14 ላይ ሲደርስ ‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ፣ አንድ ልጅም በአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን››፡፡

ከዚህ በላይ ዮሐንስ የተናገራቸውን እውነቶች በአጭሩ እንመልከት፤ ‹‹በመጀመሪያ›› የሚለውን ቃል ስንመለከት መጀመሪያው አይታወቅም፤ ማለት መቼ እንደጀመረ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ‹‹ቃል›› የሚለው በአማርኛችንም ሆነ በእንግሊዝኛው ‹‹WORD›› የሚሉት ቃላቶች በትርጉማቸው ቀላል ሐሳብን ያመለክታሉ፡፡ ዕለት በዕለት፣ በየቀኑ ሐሳባችንን የምንለዋወጠው በቃል ነው፤ እግዚአብሔር በቃሉም፣ በጽሑፍም የተናገረው ቃል በጽሑፍ ሠፍሮ ሲቀመጥና ስንጠቀምበት (መጽሐፍ ቅዱስ፣ Bible) ይባላል፡፡ እኔና እናንተ የምንግባባው በሚወጣ (በንግግር) ድምፅ ነው፡፡ ድምፅ ሳናወጣ በውስጣችን መናገር እንችላለን፤ ነገር ግን ማንም አይሰማንም፡፡ ይህን ቃል የሚለውን መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት በመሠረታዊው ቃል ብንመለከተው ‹‹ሎጎስ›› ይለዋል ይህም ዕውቀት፣ ጥበብ ማለት ነው፡፡

ሐዋርያው ዮሐንስ ሎጎስ የሚለውን ቃል የተጠቀመው ለኢየሱስ ነው፤ ስለዚህ አማርኛችን ሎጎስ የሚለውን ባያሳየንም፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ‹‹ቃል›› ብለው በመተርጎማቸው አንድ የሚያሳዩን እውነት አለ፤ ይህም ቃል የምንግባባበትና ሐሳብ ለሐሳብ የምንለዋወጥበት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቃል እግዚአብሔርን ገላጭ ነው፤ እኛና እግዚአብሔር እንድንግባባም ሐሳብም እንድንለዋወጥ የሚያደርገን ነው፡፡ ዮሐንስ በመቀጠል ‹‹ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ›› ይለናል፤ ይህም ቃል የራሱ አቋም፣ ህልውና (personality) አለው እንጂ፣ የማንም ጥገኛ አይደለም ማለቱ ነው፡፡ ቀጥሎም ዮሐንስ ‹‹ቃልም እግዚአብሔር ነበረ››  በማለት ጽሑፉን ያስቀምጣል፡፡

በመቀጠልም‹‹ቃልም ሥጋ ሆነ ጸጋንና እውነትንም ተሞልቶ በእኛ አደረ፣ አንድ ልጅም በአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነውን ክብሩን አየን›› በማለት ለመልእክት ተቀባዮቹ ያስረዳቸዋል፡፡ ዮሐንስ ቃልም ሥጋ ሆነ በሚልበት ጊዜ ከላይ ባየነው መሠረት ‹‹እግዚአብሔር (ኢየሱስ) ሰው ሆነ ማለቱ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለምን ሰው ሆነ? ብለን ልንጠይቀው የሚገባ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ካልጠየቅን አሁን መጠየቅ ይገባናል፡፡ አምላካችን ለምን ሰው ሆነ? የሚለው ሐሳብ ለማንኛውም የሃይማኖት ከፍል የሚገባ ሐሳብ (ትምህርት) አይደለም፡፡ በክርስትና ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረን በቀላሉ ቶሎ ባይገባንም የምንቀበለው እውነት ነው፡፡

Christmas Manger scene with figures including Jesus, Mary, Joseph, sheep and magi.

እግዚአብሔር ለምን ሰው ሆነ ወይም ኢየሱስ አምላክ ሆኖ ሳለ ለምን ሰው ሆነ? ለሚለው ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መልሶች ቢኖሩትም ዋና ዋና ናቸው የምላቸውን ሦስት እውነቶች ከቃሉ አቀርባለሁ፡፡ እነርሱም አንደኛ ለመሞት እንዲችል፤ ሁለተኛ የችግራችን ተካፋይና ሦስተኛ ምሳሌ ሊሆነን የሚሉ ናቸው፡፡

  1. ለመሞት እንዲችል፡- የመጀመሪያው እግዚአብሔር (ኢየሱስ) ሰው የሆነበት ምክንያት በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ እንደምናገኘው፣ እግዚአብሔር ፈጠረው ሰው በኃጢአት በወደቀበት ጊዜ፣ የፈረደው ፍርድ ሞት ነበረ (ዘፍ.2፡17)፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በጥፋቱ ሞት ቢፈርድበትም፣ የእጁ ሥራ በመሆኑና ስለሚወደው በጥፋቱ ሊተወው አልፈለገም፡፡ ለእግዚአብሔር መሞት በፍጹም የማይታሰብና የማይቻል ጉዳይ ቢሆንም፤  በሥላሴ በሁለተኛው አካል/ ወልድ የሚሞት ሰው ሆኖ መምጣት ነበረበት፡፡ እግዚአብሔር/ኢየሱስ መሞት ለምን አስፈለገው? ብለን ስንጠይቅ፣ የእግዚአብሔር ቃል በሕዝቅኤል ላይ ‹‹ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች›› (ሕዝ.18፡4)፣ በሮሜ ላይም ‹‹የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና…››(ሮሜ.6፡23) ይላል፡፡  ስለዚህ ያንን ሞት ራሱ መሞት እንዲችል የሚሞት ሰው ሆኖ  መምጣት ነበረበት፡፡

የዕብራውያን ጸሐፊም መሞት እንዲችል በሥጋና በደም ተካፍሎ ወንድሞቹን ሊመስል እንደ ተገባው በመናገር፣ እንዲያውም የአብርሃምን ዘር ይዞ እንደመጣ ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ እንዲህ ሲል ጽፎአል፡፡ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣… በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም፡፡ ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፣ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው›› (ዕብ.2፡14-18) በማለት ሥላሴ ያወጡትን ዕቅድ ለመፈጸም ወልድ/እግዚአብሔር የሚሞት ሰው ሆኖ መጥቶ ለሰው ልጆች ድነት ማስገኘቱን ይናገራል፡፡

2) በችግራችን ሊረዳን፡- ሁለተኛው እግዚአብሔር (ኢየሱስ) ሰው የሆነበትን ምክንያት የዕብራውያን ጸሐፊ አስቀምጦታል፡፡ ሰው ያልሆነ ፍጡር ሁሉ እንሰሳትም፣ መላእክትም… ሰው ስላይደሉ የእኛ ችግር ፈጽሞ አይገባቸውም፡፡ አንድ በጣም የምወዳትና የምትወደኝ የቤተ ክርስቲያን ድመት ነበረች፤ በሚርባት ጊዜ በጩኸት አዳራሹንና ግቢውን ታናውጠዋለች፣ እኔ ወደማድርበት ክፍል ስገባ፣ አይታ ቶሎ ብላ ወደ ክፍሌ ትገባለች፡፡ ከዚያ ቀስ ብላ አንድ እግሯን ጭኔ ላይ ታስቀምጥና ፊቴን ታያለች፣ ቀጥላም ሁሉንም እግሮቿን አውጥታ አርፋ ትቀመጣለች፡፡ እኔም ታሳዝነኝና ወጥቼ ሳምባ ገዝቼላት እመጣለሁ፤ ታዲያ እንዲህ እየተዋደድን አንድ ቀንም ችግሬን ነግሬአት አላውቅም፤ ምክንያቱም ሰው ስላይደለች ችግሬ አይገባትም፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ችግራችን አስቀድሞ የሚገባው አምላክ ቢሆንም የችግራችን ተካፋይ መሆኑ እንዲገባን የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚደክም፣ የሚያንቀላፋና የሚያዝን ሰብዓዊነትን ይዞ በመምጣት የኃጢአታችንን ዋጋ በሞቱ በመክፈል የችግራችን ረዳት መሆኑን አረጋግጦአል፡፡ አሁን ባየነው የዕብራውያን መልእክት ላይ ‹‹እርሱ ራሱ ተፈትኖ መከራን ስለ ተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና›› (ቁ.18) በማለት ሰው ሆኖ የመጣበትን ሁለተኛውን ምክንያት በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የሚደርሱትን ችግርና መከራ ሁሉ ስለ ቀመሰ በችግራችን ሁሉ ሊረዳን የሚችል ‹‹ … የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት›› እንደሆነ ያስረዳናል (ቁ.17)፡፡ ለዚህ ነው ኢየሱስ የምትለምኑትን ሁሉ በስሜ ለምኑ ብሎ የተናገረው፡፡ ዛሬ በዚህ በልደት ቀን ‹‹ደስ ይበላችሁ›› የችግራችሁ ረዳት ሆኖ ጌታ በውስጣችሁና በአጠገባችሁ  አለ፡፡ በዚህ እውነት ምስጋና ይሙላባችሁ፡፡

3) ምሳሌ ሊሆነን፡- ሦስተኛው እግዚአብሔር(ኢየሱስ) ሰው የሆነበትን ምክንያት ሐዋርያው ጴጥሮስ በስደት ላይ ለነበሩት እንግዶችና መጻተኞች ለነበሩት የማጽኛኛ መልእክት ሲጽፍላችው፣ ኢየሱስ ምሳሌአቸው እንደሆነ ያሳያቸዋል፡፡ የእግዚአብሔር ወልድ ሰው ሆኖ መምጣት ለእኛ በአራት መንገዶች ልንከተለው የሚገባን ምሳሌያችን ነው፡፡ ሰው በዚህ ምድር ሲኖር የማይቀበላቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ጥቂቶቹን እንመለከታለን፡፡ የመጀመሪያው በተለያየ ምክንያት ራስን ያለ መቀበል ችግር ይታይብናል፤ ከዚህ ተነሣ ራሳቸውን በተለያየ መንገድ የሚያጠፉ አሉ፡፡ ስለዚህ ይህን የምንጠላውን ማንነት፣ የራሱን ሰብዓዊነት ተቀብሎ፣ የአዳምን አስቸጋሪና ደካማ ሰብዓዊነት ይዞ ለሠላሳ ሦስት ዓመት ተኩል በዚህ ምድር ላይ በመኖሩ፣ ራስን በመቀበል ታላቅ ምሳሌያችን ነው፡፡ ሁለተኛው ችግራችን የተወለድንበትን ቤተሰብ ያለ መቀበል ነው፤ ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ ቤተ ሰብ ነበረው፡፡ ቤተ ሰቦቹ ድሆች ስለ ነበሩ፣ በስምንተኛው ቀን የመንፃት ሥርዓት ለመፈጸም ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄዱ፣ ለመሥዋዕት ይዘውት የሄዱት፣ ድሆች የሚያቀርቡትን ርግብ ነበር፡፡ ከአስራ ሁለት ዓመቱ ጀምሮ ሰማያዊ አባቱን ለማገልገል ቢጀምርም፣ ሠላሳ ዓመት ሞልቶት ሙሉ በሙሉ ማገልገል እስከሚጀምርበት ጊዜ ድረስ፣ ቤተሰቡ ምንም እንኳ ድኃ ቢሆኑም ሳያፍርባቸውና ሳይሸማቀቅባቸው እያገለገላቸው አሳልፎአል፡፡ ይህንንም ማርቆስ በወንጌሉ ‹‹የአናጺው ልጅ›› (ማር. 6፡3) በማለት ቤተ ሰቡን በአናጺነት ማገልገሉን ይገልጻል፡፡ የጌታ ሕይወት ቤተሰብን በመቀበልና በማገልገል ታላቅ ምሳሌያችን ስለሆነ፣ እኛም ወላጆቻችን በምንም ዓይነት ድህነት ውስጥ ይሁኑ መቀበል፣ መውደድና ማገልገል ይጠበቅብናል፡፡

ሦስተኛው ችግራችን ኅብረተ ሰባችንን ያለመቀበል ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ አይሁዶች በሮማውያን ቅኝ አገዛዝ ሥር ነበሩ፡፡ ከባቢሎን ምርኮ ጀምሮ እስከ ዘመናችን 1948 ዓ.ም በተለያዩ መንግሥታት ሲገዙ ቆይተዋል፤ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔርን ባለ መታዘዝ ባሳለፉት ሕይወት ለአሕዛብ መንግሥታት አልፈው የተሰጡ ነበሩ፡፡ በየዘመናቱ አሳዛኝ ሕይወት አሳልፈዋል፤ ኢሱስም ወደዚህ ምድር በሥጋ በመጣበት ጊዜ በጠላት አገዛዝ ሥር ስለ ነበሩ፣ የራሳቸው መንግሥት፣ መሪና ገንዘብ (currency) አልነበራቸውም፡፡ ጌታም ከዚህ ትውልድ በመገኘቱ፣ ይህን ኅብረተሰብ ተቀብሎ፣ ቤተ መቅደስ በመሄድና የሚገባውን በማድረግ፣ ግብር ገብር ሲሉት በመገበር ኖሮአል፡፡ ከአባቱ የተላከበትን ተልዕኮ ጨርሶ እስከ ሄደ ጊዜ ድረስ እያገለገላቸው ተመላለሰ፤ በዚህ ምክንያት በእርሱ ላይ ክስ የሚያቀርቡበት በቂ ምክንያት ማግኘት አልቻሉም፡፡ ጌታ የተወለደው ከዚህ በቅኝ አገዛዝ ሥር ከወደቀው ሕብረተ ሰብ ነበር፡፡ ጌታም ይህንን ሕብረተ ሰብ በማክበርና በማገልገል ትልቅ ምሳሌያችን ነው፡፡ ስንቶች እንሆን ድኃ  ሕብረተ-ሰባችንን ተቀብለን የምንኖር?

አራተኛው የምንኖርባትን አገር ያለመቀበል ችግር ነው፤ ኢየሱስ ግን መንግሥትን በመቀበል ምሳሌያችን ነው፤ ከላይ እንደ ተገለጠው ኢየሱስ በተወለደበት ጊዜ አይሁዶችን ይገዛ የነበረው የሮም መንግሥት ነበር፡፡ ሕዝቡ ለሮም መንግሥት ይገብርና ይታዘዝ እንደነበረ ሁሉ ጌታም እንደ ሕዝቡ የሚጠበቅበትን ሁሉ እያደረገ ምሳሌነቱን አሳይቶአል፡፡ አንድ ጊዜ የሚገብረው ሲያጣ ጴጥሮስን ዓሣ አጥምዶ ከሆዱ ውስጥ የሚያገኘውን ገንዘብ ሄዶ እንዲከፍል ትእዛዝ ሲሰጠው መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል (ማቴ. 17፡27)፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያኖች ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በትምህርት በሥራ በስደትም ወጥተው ለረጅም ጊዜ ሲቆዩ የአገር ፍቅር የሌላቸው ይመስለኝ ነበር፡፡ አሁን ግን በዚህ በችግር ጊዜ አገራቸውን በውደዳቸውን ‹‹በቃ›› (NO MORE) በሚለው ሞፈክራቸውና ተመው ወደ አገራቸው በመግባታቸው ዓለምን አስደንቀዋል፤ የእኔም አመለካከት ተለውጧል፡፡ በውጭም በአገር ውስጥም ያለን አገራችን ኢትዮጵያን እንደምንወድ አስመስክረናል፡፡  

ከዚህ በላይ ያሉትን ስንመለከት ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ የመጣው፣ ሥላሴ በአንድነት ሆነው ያቀዱትን (እግዚአብሔር አብ ያቀደውን) ለመፈጸምና ሁሉን በክርስቶስ ለመጠቅለል፣ አስታራቂ ለመሆን፣ ሊቀ ካህናችን ሆኖ ከአባቱ ጋር ለማስታረቅና  በምሳሌነት ኖሮ ሕይወትን ለማሳየት ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ ከፈጣሪነት ወደ አዳኝነት ለመምጣት ሰው ሆኖ እንደመጣ በሰፊው ተመልክተናል፡፡ ከእነዚህም ውጭ ብዙ ምክንያቶችም ቢኖሩም፣ ለዚህ ሰሞን ለምናከብረው የጌታ ልደት ‹‹መልካም ልደት›› ብዬ ልደቱንየምናከብርበትን ዋና ምክንያቶች ለመጠቆም ነው፡፡ ጌታ ይባርካችሁ!


2 Comments

Pa Shiferaw Demeke · January 9, 2022 at 7:45 am

Dear Ambe,

I am very to have read a sound doctrine on humanity of Christ. This is what the world needs to know. We need to know who Christ is rather than celebraing Christmas without Christ. God bless you. እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርክህ ግሩም ስነመለኮታዊ ትምህርት ነው። አገልጋይ ሽፈራው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *