ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት አራት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እና የሶሻል ሚዲያ ቴሌግራምና ፌስ ቡክ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስናጋራ ቆይተናል፡፡ በዚህ በምንጀምረው አዲስ ዓመት ‹‹መና›› በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍ ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እናጋራችኋለን፡፡ በቴሌግራምና በፌስ ቡክም ጊዜውን ጠብቆ እንለቃለን፡፡ አሁን በዚህ ሳምንት አዲስ ዓመትን ልናከብር እየተዘጋጀን ባለንበት ጊዜ ከቅዱስ ቃሉ የአንድ ቤተሰብ ታሪክ አብረን እንድንካፈል ወደድን፡፡
የምንካፈለው ጽሑፍ ርዕሱ ‹‹እግዚአብሔርን መታዘዝ›› የሚል ሲሆን፣ ታሪኩ የተመሠረተው በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡1-15 ላይ ‹‹መልካም ጥበቃ›› ስለ ተደረገለት ቤተሰብ ታሪክ ይሆናል፡፡ እንደሰው በዚህ ዓለም ስንኖር በተለያየ ሁኔታ፣ በፈተና፣ በችግርና በመከራ ውስጥ እናልፋለን፤ ጌታም በምድር በነበረበት ጊዜ በዮሐንስ ወንጌል 16፡33 ላይ ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ›› በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሮአቸዋል፡፡ ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ ምክንያት ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ በችግር፣ በፈተናና በሥቃይ መኖር እንደ ጀመረ የታወቀና ሁላችንም የምናልፈበት ያለ ሐቅ ነው፡፡
በዚህ በማቴዎስ ወንጌል ላይ መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስንመለከት፣ ሄሮድስ ይሁዳን በሚገዛበት ጊዜ፣ ቃሉ እንደሚናገረው ‹‹… የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን… ልጁን ላከ›› ገላ. 4፡4 በሚለው መሠረት የጌታን መወለድ እንመለከታለን፡፡ የመወለዱን ታሪክ ስንመለከት በጊዜው ብዙ ሰዎች ያወቁ አይመስልም፣ ምክንያቱም እረኞች ያበሠሩት ዜና የሳምንት የልጆች ወሬ ሆኖ ቀርቶአል፣ ሄሮድስ፣ ካህናትና ጻፎች የዓለም አዳኙ ሕፃን እንደሚወለድ ትንቢቱን እንጂ በአካል መወለዱን እንዳላወቁ፣ ለንጉሡ ሄሮድስ በሰጡት ምላሽ መረዳት ይቻላል፡፡ በተወለደበት አካባቢና በናዝሬትም ያሉ ሰዎችም ከዐርባ ቀን የመንጻት ሥርዓት በኋላ ስለ ተወለደው ሕፃን፣ ከጥቂት ሰዎች በስተቀር የሚናገርና የሚያወራ ያለ አይመስልም፡፡ በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር አዳኙ የሚታወቅበትን መንገድ አዘጋጀ፡፡
በዚህ በማቴዎስ ወንጌል ዘገባ መሠረት ሰብአ ሰገል (ጠቢባን) የሚባሉት ሕፃኑን ለማየት በኮከብ እየተመሩ ከምሥራቅ እንዲመጡ አደረገ፡፡ እነርሱም ሕፃኑን ለማየት ሲመጡ የወሰደባቸው ጊዜ ቢያንስ ስድስት ወር ቢበዛ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ሳይሆን አይቀርም፤ ምክንያቱም የመጡት ከምሥራቅ እንደሆነ ቃሉ ይናገራልና፡፡ የመራቸው ኮከብ ኢየሩሳሌም ሲደርሱ የጠፋባቸው፣ መወለዱን ያላወቁት ሄሮድስ፣ ካህናት፣ ጻፎችና ሕዝቡ የአዳኙን መወለድ እንዲያውቁ ለማድረግ እግዚአብሔር ያደረገው የራሱ ሥራ እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡
ጠቢባኖቹ ኮከቡ በጠፋባቸው ጊዜ የአገሩን መሪ መጠየቅ፣ ግዴታ ስለሆነባቸው ወደ ቤተ መንግስቱ ሄደው፣ ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ልንሰግድለት መጥተናል›› በማለት ጥያቄአቸውን አቀረቡ፡፡ በዚህ ጊዜ በንጉሡና በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ወደቀባቸው፤ ምክንያቱም ንጉሡ ሄሮድስ ቄሣር በእኔ ላይ (ምትክ) ማንን ሾመ ብሎ ሲሆን፣ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ደግሞ ሄሮድስ የሚወሰደውን የጭካኔ እርምጃ ስለሚያውቅ ነበር፡፡ ሕዝቡ የፈራው አልቀረለትም፣ እናቱንና ወንድሙን በጭካኔ የገደለው ሄሮድስ፣ ከሁለት ዓመት በታች ያሉትን ሕፃናት ሁሉ በጭካኔ አስገደለ፡፡
ሕፃናት ሁሉ ከመገደላቸው በፊት እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ‹‹…እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታጥቶ ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው›› ቁ. 13፡፡ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ሄሮድስን ዲዳ፣ ሽባ፣ ዕውር ማድረግ ሲችል፣ ለዮሴፍ ‹‹ሽሽ›› ብሎ እንዲነግረው መላኩ እጅግ የሚገርምና የሚያስደንቅ ታሪክ ነው፡፡ ዮሴፍም ‹‹ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ›› ቁ. 15፡፡ ዮሴፍና ማርያም በመታዘዛቸው ምክንያት የዓለም አዳኝ የሆነው ጌታ ከሞት ሊድን ቻለ፡፡ ወላጆቹ ሄሮድስ ከሞተ በኋላ ከስደት አገር ወደ እስራኤል ተመልሰው መኖር እንደ ጀመሩ ቃሉ ይነግረናል፤ ጌታም ሠላሳ ዓመት ሲሞላው የአባቱን አገልግሎት ለሦስት ዓመት ተኩል ከፈጸመ በኋላ፣ የመጨረሻውን ተልዕኮ በመስቀል ላይ በመፈጸም ለሰው ልጆች ሁሉ የኃጢአተችንን ዋጋ በመክፈል አዳነን፡፡ የወላጆቹ እግዚአብሔርን መታዘዝ ለእኛ ድነትን አስገኘልን፡፡
በዚህ ባሳለፍነው በ2013 ዓ.ም በተለያየ ፈተና፣ ችግርና መከራ ውስጥ አልፈናል፤ እኔም ቤተሰቤም ለዚህ ምስክር ነን፡፡ አንዳንዱ ከጌታ፣ አንዳንዱ ከሰይጣን፣ አንዳንዱ ራሳችን ያመጣነው ሊሆን ይችላል፡፡ ለማንኛውም በዚህ ዓመት ማለቂያ ላይ በሃይማኖት መሪዎችና አባቶች አማካኝነት በታወጀው የአምስት ቀን የጾም ጸሎት ጊዜ ሁላችንም እንድንካፈል ጥሪ ተደርጐልን ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በተደረገው ጾም ጸሎት እግዚአብሔር ምን አለን? አለህ? አለሽ? በዚህ አዲስ ዓመት እግዚአብሔር ያለንን እንደ ዮሴፍ መታዘዝ ብንችል ዓመቱ ሁሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የበረከትና የመታደስ ዓመት ይሆንልናል፡፡ እግዚአብሔርን መታዘዝ (እንደ ስደት) ዋጋ የሚያስከፍል ቢሆንም እግዚአብሔርን በመታዘዛችን በዚህ በአዲስ ዓመት በሕይወታችን ‹‹መልካም ጥበቃ›› (አዳኙን እንደ ማዳን) ይሆንልናልና እግዚአብሔርን መስማት! መታዘዝ! ይሁንልን፡፡
**መልካም አዲስ ዓመት**
2014 EC
6 Comments
Chernet seifu · September 27, 2021 at 7:26 am
Amen
I am encouraged and learned a lot from the previous journey . I hope and pray to keep doing this great job .
May God bless you and your beloved family in Juses Name.
Chernet ,Hirut.,YeAmanuel and Ivan
Amberber Gebru · October 26, 2021 at 1:11 pm
Thank you Chere
ኃይሉ ደምሴ · October 1, 2021 at 5:44 am
በጣም ድንቅ ነው ትምህርቶች ይላኩልኝ
ኃይሉ ደምሴ · October 1, 2021 at 5:44 am
በጣም ድንቅ ነው ትምህርቶች ይላኩልኝ
Amberber Gebru · October 26, 2021 at 1:09 pm
Thank you
Amberber Gebru · November 9, 2021 at 7:04 am
Teleko.org ብለህ ብትገባ ታገኛለህ