አስተምህሮተ ሥነ-ፍጻሜ (የመጨረሻ ነገሮች)

በአስተምህሮተ ሥነ-ፍጻሜ ርዕስ ሥር ስለ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት፣ ስለ መከራው ዘመን፣ ስለ ሺህ ዓመት ግዛት፣ ስለ ሙታን ትንሣኤና ፍርድ የምናይበት ይሆናል፡፡ ወደ ፊት ስለሚፈጸሙ ጉዳዮች ስናነሳ መቶ በመቶ እርግጠኛ የማንሆንባቸው ነገሮች ቢኖሩም፤ ከሃምሳ በላይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፡፡ ‹‹ምንም እንኳ ስለ ወደ ፊቱ ማንኛውንም ማወቅ ባንችልም፣ እግዚአብሔር ስለ ወደ ፊቱ ሁሉን ያውቃል፤ በቅዱሳት መጻሕፍት በአጽናፈ ዓለሙ ታሪክ ገና ስለሚመጡ ስለ ዋና ዋና ሁኔታዎች ነገሮናል፡፡ እነዚህ ነገሮች እንደሚሆኑ ፍጹም መተማመን ሊኖረን ይችላል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ተሳስቶ ወይም ዋሽቶ አያውቅም›› (ዌይን ገሩደም ስልታዊ ሥነ መለኮት ገጽ 1236)፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በቃሉ የነገር-ፍጻሜ እንደሚሆን ከተናገረ፣ እንደ ቃሉ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ማንኛውም ነገር ጅማሬ እንዳለው ሁሉ ፍጻሜም ይኖረዋል፤ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታ ሊያድን እንደ መጣ፣ ሊወስደንም ይመጣል፡፡ ጌታ የሚመጣው በመጨረሻው ዘመን ነው፤ መጨረሻ የሚሆነው ጌታ ሲመጣ ነው፣  ለመሆኑ ጌታ ለመምጣቱ ምን ያህል እርግጠኞች ነን?

  1. 1.       ዳግም ምፅዓት

እግዚአብሔር ሰዎች ቢቀበሉም ባይቀበሉም ስለ መጨረሻው ዘመን በነቢያቶቹ፣ በተለይም በነቢዩ ዳንኤልና በሐዋርያው ዮሐንስ በኩል ዋና ዋና ነገሮችን ተናግሮአል፡፡ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት አብዛኛው ሰው ሲቀበል ጥቂቶች ደግሞ የማይቀበሉ ይኖራሉ፡፡ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መምጣት ከሰባት መቶ ዓመት በፊት የተነገረ ቢሆንም፣ በሥጋ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው ሆኖ ሲመጣ፣ ሰዎች ግን አልተቀበሉትም ነበር፡፡ ሰዎች በትንቢት የተነገረውን ባይቀበሉትም፣ ጌታ ግን እኛን ለማዳን መከራ ተቀብሎ፤ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ እያንዳንዳችንን ከዘላለም ሞትና ኵነኔ አዳነን፡፡

       የዳግም መምጣቱ ዓላማ፡- ኢየሱስ ሥጋ ለብሶ ሰው የሆነበት ዋና ምክንያት ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ ነው፤ ሰው ከወደቀበት ወደ ነበረበት የክብር ሥፍራ እንዲመለስ ለማድረግ ሲሆን፣ ተልዕኮው አላለቀም፡፡ ስለዚህ ጌታ ዳግመኛ የሚመጣው፣ አማኞቹን ለመውሰድና በክብር ሥፍራ ከአባቱ ጋር እንዲኖሩ ለማድረግና ከዚህ ዓለም ሥቃይ ለማሳረፍና ወደ ተዘጋጀላቸው ቤታቸው ለመውሰድ ይመጣል፡፡ ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 13 ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ጌታ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ፣ የሞቱን መታሰቢያ የሆነውን ራት ከበሉ በኋላ፤ በሚቀጥለው ምዕራፍ በሚናገራቸው የማጽናናት ሐሳብ ውስጥ የመጀመሪያውን የሚመጣበትን ምክንያት እናገኛለን፣ ‹‹ልባችሁ አይታወክ በእግዚአብሔር እመኑ፣ በእኔም ደግሞ እመኑ፡፡ በአባቴ ቤት ብዙ መኖርያ አለ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፣ ሥፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና ሄጄም ሥፍራ ባዘጋጅላችሁ፣ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ›› (ዮሐ.14፡1-3)፡፡

ሁለተኛው ምክንያት በራዕይ 19፡11-16፣ 20፡7-10 ላይ እንደምናገኘው ጠላቶቹን ለመበቀል ለፍርድ ይመጣል፤ ‹‹እነሆ አምባ ላይ ፈረስ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፣ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም፡፡ …አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፣ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ …በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት፡-የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ ሦስተኛው ምክንያት ዓለምን ወደ ፍጻሜ ለማድረስና አዲስ ሥርዓት ለመዘርጋት (አዲስ ሰማይና ምድር) እንደሆነ ቃሉ ይናገራል (ራዕ፣21፡1)፡፡ የመጀመሪያው መምጣቱ ብዙ ዓመት ቢያስቆጥርም መምጣቱ እውነት እንደሆነ ሁሉ፤ ዳግመኛ መምጣቱንም ሰዎች ቢቀበሉትም ባይቀበሉትም እንደ ተስፋ ቃሉ ጌታ ተመልሶ ይመጣል፤ ቃሉ እውነት ስለሆነ እንደ ቃሉ ይፈጸማል፡፡ ታዲያ ቃሉ እውነት ከሆነ በእርግጥ መቼና  እንዴትስ ይመጣል?

       ዳግም የመምጣቱ ምልክቶች፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 23 መጨረሻው ላይ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ስላለማመናቸው ወቅሶ፣ በመቀጠልም ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም›› ብሎ ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፣ በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርት የመቅደሱን ግንቦች አሳዩት፡፡ ጌታም በመቀጠል ‹‹ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ›› እንደማይቀር በነገራቸው ጊዜ፣ የሚከተለውን ጥያቄ ጠየቁት፡፡ ‹‹ንገረን፡-ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?›› አሉት (ማቴ. 24፡1-14፣ ሉቃ. 21፡1-38)፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ስንመለከት ማቴዎስ ሲዘግብ ከመቅደስ ሲወጣ፣ ሲል ሉቃስ ደግሞ በመቅደስ ሰዎች ስጦታ ሲሰጡ፣ በነበረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርት ስለ ቤተ መቅደሱ ድንጋይ ይነጋገሩ እንደ ነበር ዘግቦአል፡፡ ደቀ መዛሙርትም በጠየቁት ጥያቄ ውስጥ ሦስት ዋና ዋና ነገሮችን ማየት ያስችለናል፤ የመጀመሪያው የመቅደስ መፍረስ ሲሆን፣ ሁለተኛው የጌታ መምጣትና ሦስተኛው የዓለም መጨረሻ የሚሉት ናቸው፡፡ የቤተ መቅደሱ መፍረስ በሰባ ዓመተ ምሕረት በጄኔራል ቲቶ (ታይተስ) በመፍረሱ ተፈጽሞአል፡፡ የቀሩት ሁለቱ ጥያቄዎች ሲሆኑ፣ እነርሱም መቼ እንደሚሆኑ ባናውቅም፣ በታቀደላቸው መሠረት ይፈጸማሉ፡፡

           የክርስቶስ መምጣትና የዓለም መጨረሻው ለመሆናቸው/ለመፈጸማቸው እርግጠኞች ከሆንን፣ ለመፈጸማቸው ምልክት ሆነው የተሰጡ ነገሮች ይኖሩ ይሆን? በእነዚህ በማቴዎስና በሉቃስ በተመለከትናቸው በሁለቱ ምዕራፎች ውስጥ ለቤተ መቅደሱ መፍረስ ምልክቶች ሆነው በተሰጡት ውስጥ ተሰባጥረው የተሰጡን ምልክቶች ለይቶ ማውጣቱ ከባድ ቢሆንም፤ ለጌታ መምጣትና ለዓለም መጨረሻ ምልክቶች የሆኑ አሉበት፡፡ የሐሰተኖች አስተማሪዎች መምጣት፣ የጦርነት መብዛት፣ የእሥራኤል ወደ መንግሥት መምጣት፣ የኃጢአት መብዛት፣ የዓለም በውጥረት ውስጥ መሆንና የፍቅር መቀዝቀዝ በየዘመናቱ የታዩ ቢሆኑም፣ መጠናቸው እየጨመረ በመሄዱና ወደፊትም ይበልጥ እየጨመሩ በመሄዳቸው፣ ዋና ዋና ምልክቶቹ እንደሚሆኑ ከቃሉ መረዳት እንችላለን፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ የተናገረውን እንመልከት፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ላይ ደቀ መዛሙርቱ  በሄሮድስ አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶ የተሠራውን አስደናቂ የሆነውን የቤተ መቅደሱን ድንጋዮች እያሳዩት ሳለ፣ መፍረሱ እንደማይቀር ተናገራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የሚኮሩበት ቤተ መቅደስ እንደሚፈርስ ሲነገራቸው፣ ደንግጠው ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?›› ባሉት ጊዜ በደቀ መዛሙርት ላይ ስለሚፈጸም መከራ፣ በሰባ ዓመተ ምህረት ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ራሱ በመጨረሻው ዘመን ዳግም ስለ መምጣቱ ሦስት ነገሮችን አደባልቆ ነገራቸው፡፡

 ‹‹ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም፡፡ የኖህ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፡፡ በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት ኖህ ወደ መርከብ እስከ ገባበት ቀን ድረስ ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፣ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል፡፡ …ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ፡፡

  ያን ጊዜ እወቁ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወም ነበር፡፡ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና … ከዚያችም ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፣ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፣ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ፡፡ በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፣ … የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል … ›› (ማቴ. 24፡32-44፣29-30)፡፡

     ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ ዮሐ. 14፡3 ላይ እንደ ገለጸው፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሦስት ዓመት ተኩሉን አገልግሎት ጨርሶ ወደ አባቱ እንደሚሄድ ሲነግራቸው ሐዘን ተሰምቶአቸው ሳለ እንደገና በመቀጠል እንዲህ አላቸው ‹‹እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ፡፡ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ›› በማለት ተመልሶ መምጣቱን በማሳሰብ አጽናናቸው፡፡ ከትንሣኤውም በኋላ በሚያርግበት ጊዜም እንዲሁ ዳግመኛ መምጣቱን እንዳይረሱት በመላእክቱ በኩል አሳስቦአቸዋል፡፡ ‹‹ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል›› አሉዋቸው (የሐዋ. 1፡11)፡፡

     ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ በመልእክቶቻቸው ሁሉም የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግመኛ መምጣት አረጋግጠው ጽፈዋል (1ተሰ. 4፡16፣ 2ጴጥ. 3፡10፣ ያዕ. 5፡8፣ 1ዮሐ. 3፡2)፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊም ስለ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት በምዕራፍ 9፡26 ላይ ‹‹… ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል›› ብሎ ጽፎአል፡፡ በመጨረሻም ሐዋርያው ዮሐንስ የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት በመናፈቅ ‹‹አሜን፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና›› (ራይ. 22፡20) በማለት መልእክቱን ይዘጋል፡፡

     ስለዚህ ይህን ሁሉ ማስረጃ ስንመለከት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ መምጣቱ የተረጋገጠ ነው፡፡ ነገር ግን መቼ እንደሚመጣ ከአባቱ በቀር የሚያውቅ እንደሌለ ቃሉ ይናገራል፡፡ ይህ ማለት ክርስቶስም አያውቅም ማለት ሳይሆን፣ ጌታ በሰብዓዊነቱ ሆኖ ሲናገር ልጅም ቢሆን አያውቅም አለ፣ እንጂ በመለኮታዊነቱ አያውቅም ማለት አይደለም፡፡ እኛ የሚመጣበትን ጊዜ ባናውቅም ምንም ችግር የለውም፡፡ ዋናው ነገር እኛ ይህን ታላቁን ተስፋችንን በቅድስና ሕይወት እየኖርን የዕለት ተግባራችንን እያከናወንን ‹‹ጌታ ሆይ ና!›› ‹ማራናታ› (1ቆሮ. 16፡22) እያልን ልንጠብቀው ይገባናል፡፡ (ቲቶ. 2፡12-13) ከዚህ ውጭ በዚህ ሰዓት፣ ቀንና ዓመት ይመጣል እያልን ማሰብና መጨነቅ የለብንም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በነበረበት ዘመን እንኳ፣ ‹‹… የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፣ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን›› ከሚለው አነጋገሩ ጌታ በዚህ ቀን ይመጣል ብለው የተናገሩ ሰዎች እንደ ነበሩ ከቃሉ ማየት እንችላለን፡፡ (2ተሰ. 2፡1-3)

     ዛሬም ጌታ የሚመጣበትን ቀን እናውቃለን ብለው የሚያስተምሩ እነርሱ የስሕተት አስተማሪዎች ናቸው፡፡ ልንሰማቸውም አይገባም፤ ባለፉት ጊዜያት በአገራችን እንኳ የሐሰተኛ ነብያትን ቃል በመስማት፤ ብዙዎች ከሥራቸው ተፈናቅለዋል፣ እምነታቸውን ጥለዋል ሥጋቸውም በጉስቁልና ውስጥ ወድቋል፡፡ እኛም የእነርሱ  ዕጣ ፈንታ እንዳይደርሰን በጸሎት ወደ ጌታ በመቅረብ፣ በኃጢአታችን ንስሐ እየገባንና በእርሱ በመታመን ቅድስናችንን ጠብቀን መኖር ይገባናል፡፡ እነዚህን ከመሰሉት ቃሉን በማጥናት በጸሎት እየተጋን ያልገባን ነገር ካለ የቤተ ክርስቲያን አስተማሪዎቻችንን በመጠየቅና በመረዳት መጠንቀቅና መራቅም ያስፈልገናል፡፡

     የወንጌል አማኞች ሁሉ በክርስቶስ መመለስ የመጨረሻ ውጤቶቹ ይስማማሉ፤ ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተ ልዩነት ቢኖራቸውም፤ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ መጨረሻ ሥልጣን ያለው አድርገው የሚቀበሉ ክርስቲያኖች ሁሉ የክርስቶስን መመለስ ይቀበላሉ፡፡ በመጨረሻው የመመለሱ ውጤት ላይም የማያምኑ ሰዎች ሁሉ እንደሚፈረድባቸውና አማኞች የመጨረሻውን ብድራት እንደሚያገኙ፣ እንዲሁም አማኞች በዐዲሱ ሰማይና ምድር ለዘላለም ከክርስቶስ ጋር እንደሚኖሩ ይስማማሉ፡፡      ስለዚህ አሁን ባለንበት ዘመን ለክርስቶስ ዳግም ምፅዓት መቃረብ ምልክት የሚሆኑ ነገሮች ከሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ላይ ማየት እንችላለን፡፡ የጦርነት መብዛት፣ የሰዎች ፍቅር መቀዝቀዝ፣ ሰዎች ምን ይመጣል ብለው በፍርሃት መድከምና የበለስ ማቆጥቆጥ ማለት የእሥራኤል መንግሥቷን መመሥረቷ (በ1948ዓ.ም) … የመሳሰሉት ምልክቶች ሁሉ የክርስቶስ ምፅዓቱ መቃረቡን ያመለክቱናል፡፡ 


1 Comment

Sami · April 1, 2022 at 1:45 pm

Trouth mesage

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *