አሁን የሚቀጥለው ጥናታችን ስለ አስተምህሮተ ድነት ይሆናል፤ ድነት ያገኘነው በዚህ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ለሚመጣውም ሕይወት ስለሆነ፤ በዚህም ሆነ በሚመጣው ሕይወት አግኝተን እንዴት መኖር እንዳለብን እናጠናለን፡፡
ድነት/ደህንነት (Salvation) በውስጡ ሦስት ነገሮችን ያካትታል፤ ቃሉ የግዕዝ ቃል ሲሆን ‹መዳን› የሚለውን ሐሳብ ያመለክታል፡፡ መዳን በመጀመሪያ ችግሩን (ሰውን ያሰመጠ ውኃ)፣ በሁለተኛ የሚድነውን (በውኃ ውስጥ የሰመጠ ሰው)፣ በሦስተኛ አዳኙን (ሰውን ከውኃ መስመጥ የሚያድን ዋናተኛ) ያካትታል፡፡ ውኃ ውስጥ የገባ ሰው ቢኖር፣ ከውኃ ውስጥ የሚያወጣው ሌላ ሰው ያስፈልገዋል፤ የታመመ ካለ የሚያድን ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ወድቆ የተሰበር ካለ ጠግኖ የሚያድነው ይፈልጋል፡፡
ኃጢአት ካለ ኃጢአተኛ ይኖራል፣ ኃጢአተኛ ካለ ከኃጢአት የሚያድን አዳኝ መኖር አለበት፡፡ አዳምና ሔዋን ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ኃጢአተኛ እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ እግዚአብሔር የወሰደው የፍርድ እርምጃ ሞት ነበረ፡፡ ነቢዩ ሕዝቅኤል በመልእክቱ ምዕራፍ 18፡4 ‹‹ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች›› ሲል፤ ሐዋርያው ጳውሎስም በሮሜ መልእክቱ ደግሞ ምዕራፍ 6፡23፣ እና 3፤23 ‹‹ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል›› ‹‹የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና›› በማለት የሰው ልጆች ሁሉ ኃጢአተኛ እንደ ሆኑ በጽሑፉ አስቀምጦት እናገኛለን፡፡ የአዳምና የሔዋን ኃጢአት ለትውልድ ሁሉ ተላልፎ እስከ ዘመናችን ድረስ ደርሷል፡፡ ከእነዚህ ጥቅሶች የምንረዳው ነገር ቢኖር ሰው ሁሉ በኃጢአት ምክንያት የታመመና ሞት የተፈረደበት መሆኑን ነው፤ ስለዚህ ከዚህ ሞት ሊያድነው የሚችል አዳኝ ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ መሠረት እግዚአብሔር ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን የዚህ ዓለም አዳኝ አድርጎ የላከው ለዚህ ነው፡፡ አንተም በኃጢአትህ መታመምህን አውቀህ ከሆነ አዳኝ ያስፈልግሃልና ወደ አዳኙ ቅረብና ከሞት የሚያድነውን ሕይወት ተቀበል፡፡ አዳኙን ያገኛችሁ (ልጁን) እግዚአብሔር ስለ ሰጣችሁ ድነት ዕለት ዕለት አመስግኑት፡፡
ድነት ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ሰው ኃጢአተኛ ነው እንደሚል ከኃጢአቱም ሊድን የሚችልበትን መድኃኒት እንዲህ በማለት ያስቀምጣል፡፡ ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲው በጸጋው ይጸድቃሉ›› (ሮሜ 3፡24)፣ ‹‹የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው›› (ሮሜ 6፡23)፡፡ ድነት ስንል ኃጢአትን፣ ኃጢአተኛንና አዳኝን ሦስቱንም ሐሳቦች እንደሚያጠቃልል አይተናል፡፡ ድነት ኃጢአት ከሚያመጣው ሞት ድኖ በሕይወት መኖር ማለት ነው፡፡ ከአዳምና ሔዋን ውድቀት በፊት ወደ ነበረው ክብር፣ ወደ እግዚአብሔር ኅብረት መመለስና እንደ ቀድሞ መሆን ማለት ነው፡፡
ድነት ለምን አስፈለገ?፡- በመግቢያችን ላይ እንዳየነው የመጀመሪያው ሰው ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት፣ እግዚአብሔር ሞት እንደ ፈረደበት ተመልክተናል፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ በመልእክቱ ምዕራፍ 9፡27 ላይ ‹‹ለሰዎችም አንድ ጊዜ መሞት ከእርሱ በኋላም ፍርድ እንደ ተመደበባቸው…›› ብሎ እንደሚናገረው ለሰው ሥጋዊ ሞት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ሞት ጭምር እንደ ተፈረደበት ያመለክተናል፡፡ ከእግዚአብሔር ተለይቶ ለዘላለም የሥቃይ ኑሮ እንዲኖር ተወስኖበታል፡፡ ስለዚህ የሰው ልጅ ከዚህ የኃጢአት አዘቅት መውጣትና ከፍርድ ነፃ መሆን ስላለበት ድነት አስፈለገው፡፡ ሰው ኃጢአተኛ ሆኖ መገኘቱና የኃጢአት ዘር ከአዳም የወረሰው በውስጡ መኖሩ የግድ ድነትን መቀበል እንዳለበት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ድነትን አግኝቶ የዘላለምን ሕይወት ካልተቀበለ በስተቀር በሮሜ ምዕረፍ 3 እና ኤፌሶን 2 ላይ እንደሚናገረው አስቀድሞ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፡፡ ደግሞም ሰው ይህን አቋሙን በእምነት ካለወጠ ለዘላለም የጠፋ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ቢወድም፣ በቅድስናው ከኃጢአት ጋር ስለማይተባበር፣ ሰውን የግድ ድነት እንዲኖረው ይጠይቀዋል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን በፈቃደኝነት እንዲመጣ እንጂ፣ ለአገልግሎት እንደ ፈለገው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ማንንም በግድ ወደ ድነት እንዲመጣ አያስገድድም፡፡
ሰው ራሱን ማዳን ይችላል?፡- ሰው ድነት ቢያስፈልገውም ራሱን ማዳን በፍጹም አይችልም፤ ምክንያቱም የኃጢአት ዋጋ ሞት ስለሆነ ሰው ያንን ዋጋ ሊከፍል በፍጹም አይችልም፡፡ ፤ ሰው ኃጢአት ካመጣው ፍርድና ሞት ለመዳን ሕግን ቢጠብቅም፣ የሥነ ምግባር ሕይወትን ለመኖር ቢሞክርም፣ እንዲሁም የተለያዩ ሃይማኖቶችን መሥርቶ ቢከተልም ራሱን ማዳን በፍጹም አልቻለም፡፡ የሰው ልጅ ከወደቀበት ውድቀት ለመነሳትና ከተፈረደበት ፍርድ ነፃ ለመሆን በራሱ ሞክሮ አቅቶታል፤ ለዚህ ነው አዳኝ ያስፈለገው፡፡
የሰው ልጅ መዳን የሚችለው እንዴት ነው?፡- የሚለውን ጥያቄ፣ ብዙዎቻችን መጠየቃችን ተገቢ ነው፡፡ እኛ የሰው ልጆች ከኃጢአት ፍርድና ቅጣት እንድን ዘንድና መንግሥቱን እንድንወርስ፣ እግዚአብሔር የምንታረቅበትን መንገዱን ያቀደውና ያዘጋጀው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ጊዜ እሥራኤላውያን የሞት መልአክ ከሚያመጣው መቅሠፍት ለመዳን እግዚአብሔር ባዘጋጀላቸው መንገድ፤ የፋሲካውን በግ መሥዋዕት በማድረግ የበራቸውን መቃን የበጉን ደም በመቀባት ከጥፋት ዳኑ (ዘፀ. 12፡1-20)፡፡ እንዲሁም በአዲስ ኪዳን ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ ምዕራፍ 1፡14 ላይ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ለመታረቅ ሰው ሆኖ በሰዎች መካከል መገኘት እንዳስፈለገው ይናገራል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከእግዚአብሔር ጋር ለማስታረቅ እኛ መፈጸም የሚገባንን ሕግ እርሱ ፈጸመ፤ መክፈል የነበረብንን ዕዳ እርሱ ስለ እኛ በሞቱ ከፈለው፡፡ ስለዚህ ድነት የተፈጸመው በክርስቶስ የመስቀሉ ሥራ ብቻ ነው፤ ‹‹የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ…›› (ሮሜ. 10፡4)፣ ‹‹…ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን›› (ገላ. 3፡13)፡፡ ስለዚህ ከኃጢአት መዳን የምንችለው ጌታ በመስቀሉ ላይ በፈጸመው የድነት ሥራ በማመን ብቻ ነው፡፡
2.1 የእግዚአብሔር ድርሻ
ስለ ድነት መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የእግዚአብሔርና የሰው ድርሻ እንዳለ ያስገነዝበናል፤ ሰው የተሰጠውን ትእዛዝ ተላልፎ በኃጢአት በወደቀና በገነት ዛፎች መካከል ተሸሽጎ ባለበት ጊዜ፤ እግዚአብሔር የራሱ ጉዳይ ባዘጋጀሁለት በገነት መኖርና መጠቀም አልቻለም በማለት ዝም ብሎ አልተመለከተውም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሔዋን በሰይጣን ተታላ፣ እንደ እግዚአብሔር ለመሆን አሰቡ፤ አዳምና ሔዋን ሐሳባቸው ሳይሳካ ቀርቶ፣ በኃጢአት በወደቁ ጊዜ ስለ ነበረው የውድቀት ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ይላል፣ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ ወዴት ነህ? አለው›› (ዘፍ.3፡9)፡፡ አዳም ያላሰበው ውድቀት ደርሶበት፤ ራሱን ከደረሰበት የኃጢአት ውድቀት ለማውጣት አልቻለም፤ ነገር ግን እየፈራና እየተንቀጠቀጠ ምላሽ መስጠቱ ለውድቀቱ መፍትሔ ሊያስገኝለት ችሎአል፡፡
ሰው ሲፈጠር በተሰጠው ነፃ ፈቃድ ተጠቅሞ ኃጢአት ሲሠራና ሲወድቅ፤ እግዚአብሔር ደግሞ በድርሻው የወደቀውንና የጠፋውን ሰው ወደ ራሱ ለማስጠጋትና የመጀመሪያውን ኅብረት እንደገና ለመመለስ እርምጃ ሲወስድ እንመለከታለን፡፡ ስለ ወሰደውም እርምጃ ቃሉ እንዲህ ይላል፣ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፣ አለበሳቸውም›› (ዘፍ. 3፡21)፡፡ ይህም ወደፊት በክርስቶስ (በሁለተኛው አዳም) በኩል እንደሚያድነው ተስፋ የሚሰጥ ጥላ ነበር፡፡
የአብ ድርሻ፡- ስለ እግዚአብሔር አብ የማዳን ሥራ ስናነሣ ጸጋው በአዲስ ኪዳን ብቻ የተገለጠ ይመስለናል፤ ጸጋውን በብሉይ ኪዳንም ጊዜ በስፋት ማየት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር አዳም በኃጢአት በወደቀበት ጊዜ፣ በቃ ያንተ ጉዳይ ብሎ ከገነት ማባረር ብቻ ሳይሆን፣ በመንፈሱ እንደ ሞተ በሥጋውም እንዲሞት ማድረግ ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር በጸጋውና በምሕረቱ ባለጠጋ በመሆኑ አንድ እንስሳ ወስዶ ደም በማፍሰስ ቁርበት እንዳለበሰው በቃሉ ቀደም ብለን አይተናል፡፡ በዘፍጥረት ምዕራፍ 3፡21 ላይ ‹‹እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበትን ልብስ አደረገላቸው፣ አለበሳቸውም›› በማለት የሚናገረው ሐሳብ አዳም በሠራው ኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ኅብረቱ ተቋርጦ እንዳይቀር ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ ነው፡፡ የኃጢአት ዋጋ ሞት ስለሆነ አዳም በኃጢአቱ ሞቶ እንዳይቀር፣ ወደፊት በክርስቶስ ሞት በደሙ ተዋጅቶ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም መታረቅ እንዲሆንለት በጊዜአዊነት በእንሰሳ ደም አማካኝነት ኃጢአቱ እንዲሸፈንለት (ኅብረቱ እንዲቀጥል ምልክት እንዲሆንለት) አደረገ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በዕብራውያን መጽሐፍ 9፡22 ላይ ‹‹ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም›› ስለሚል እግዚአብሔር አዳምን ደም በማፍሰስ ኃጢአቱን ቁርበት (የጸጋ ልብስ) በማልበስ ሸፈነለት፡፡
የእግዚአብሔር አብ ድርሻ ይህ ሲሆን የአዳምም ድርሻ የተደረገለትን እሺ ብሎ መቀበልና መልበስ ነበረበት፡፡ ይህን ባያደርግ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ኅብረት እንዲቀጥልና እንደገና በክርስቶስ ደም በኩል ለሚደረገው የምሕረት ቃል ኪዳን ኅብረት የማድረግ ዕድልና ፈንታ አይኖረውም ነበር፡፡ በለበሰው ቁርበት አማካኝነት ኅብረቱ እንዲቀጥል ቢደረግም፤ በክርስቶስ ደም ተዋጅቶ ፍጹም እስከሚሆንበት ድረስ በኃጢአተኛ ሥጋው በኤደን ገነት እንዳይኖር ተባረረ፡፡ ስለዚህ በብሉይ ኪዳንም ጊዜ ከአዳም ጀምሮ በሙሴ ሕግ በተሰጠበትም ጊዜ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ በስፋት ከሕዝቡ ጋራ ስለ ነበረ፣ በመሥዋዕት አማካኝነት ኃጢአታቸው በደም እየተሸፈነላቸው ይኖሩ እንደነበረ ማየት ይቻላል (ዘዳ. 4፡31፤ መዝ. 86፡5፣15፤ 103፡8፣ 51፡1)፡፡ የእግዚአብሔር አብ የጸጋ ስጦታ ለአዳምም ሆነ ለእኛ የማይገባን፣ ልንከፍለው የማንችል፣ ነፃ ስጦታ ነው፡፡ አዳምም በነፃ ቁርበቱን በመልበስ፤ እኛም በነፃ በመስቀል ላይ በፈሰሰው በክርስቶስ ደም በነፃ ድነትን አገኘን፡፡
ወደ አዲስ ኪዳንም ስንመጣ የሚያሳየን እውነት ይህንኑ ነው፤ የእግዚአብሔር አብ ጸጋ በስፋት መገለጡን ያሳየናል፡፡ በሥላሴ የሥራ አመዳደብ መሠረት እግዚአብሔር አብ ለኃጢአተኛው ሰው ምሕረቱንና ፍቅሩን ማሳየቱን ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ ምዕራፍ 3፡16 ላይ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና›› በማለት የእግዚአብሔርን ፍቅር በግልጽ ያሳየናል፡፡ የአብ ጸጋ የተገለጠው በፍቅሩ ነው፣ ፍቅሩ ደግሞ የተገለጠው ልጁን በመስጠቱ ነው፡፡
ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ምዕራፍ 2፡4-5 ላይ ‹‹ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሳ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን ›› እንዲሁም በሮሜ. 5፡8 ላይ ‹‹ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል›› በማለት እግዚአብሔር ሰውን ሁሉ እንደ ወደደ ያሳያል፡፡
ጌታም በምድር በነበረበት ጊዜ አብ ለሰዎች ፍቅር እንዳለው ሲገልጥ ‹‹እናንተ ስለ ወደዳችሁኝ … አብ እርሱ ራሱ ይወዳችኋልና›› (ዮሐ. 16፡27) ‹‹…የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል… የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖርያ እናደርጋለን›› (14፡21-23) በማለት ገልጦአል፡፡ ይህ የአብ ፍቅር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እኔ አንተ/አንቺ ደርሷል? ካልደረሰ አሁን እርምጃ ለምን አንወስድም?
ሀ) የአብ ምርጫ፡- በዚህ በድነት ትምህርት የእግዚአብሔር አብ ጸጋ ሥራ ከሚነሡት ነገሮች አንዱ ነገር ቢኖር የእግዚአብሔር ምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ስለ ምርጫ በመደገፍ የሚያስተምሩና በመቃወም በሚያስተምሩት መከከል የተራራቀ ጥንፍ (አመለካከት) በመያዝ የየራሳቸውን ትምህርት ያራምዳሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምርጫ መናገሩ እውነት ነው፤ ነገር ግን በቃሉ ውስጥ የተነገሩትን ጥቅሶች የምንረዳበትና የምንተረጉምበት መንገዶች የተለያዩ ናቸው፡፡ እንዴት ነው የምንረዳቸው? የሚለው ዋናው ጥያቄ ነው፡፡
በመጀመሪያ ሰው ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ የእግዚአብሔር ምርጫ እንጂ የሰው ምርጫ የለበትም፤ ምክንያቱም ሰው ገና አልተፈጠረምና ነው፡፡ ሰው ከተፈጠረ ከብዙ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አብርሃም ምርጫ የሚናገረውን በዘፍጥረት 12 ላይ እናገኛለን፡፡ ይህ ምርጫ የድነት ነበር ወይስ የአገልግሎት? የሚለውን መመለስ አለብን፤ ከቃሉ እንደምንረዳው አብርሃም የተመረጠው ‹‹የምድር ነገዶች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ›› (ዘፍ. 12፡3) በሚለው መሠረት የዓለም ሕዝብ እግዚአብሔርን እንዲያውቅ ማወጅ ነበር፡፡ አብርሃም የተመረጠው ከእርሱ ዘር የዓለም አዳኝ የሆነውን ዘር (ክርስቶስን) ለማስገኘት ነበር፡፡ ‹‹…ለዘሮቹም አይልም ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፡- ለዘርህም ይላል እርሱም ክርስቶስ›› (ገላ. 3፡16) በማለት የዓለም አዳኝ የሆነው ክርስቶስ፣ ከአብርሃም ዘር መምጣቱን ያመለክተናል፡፡ ስለዚህ የአብርሃም መመረጥ ለድነት ሳይሆን ለአገልግሎት ነው፡፡
የምርጫ ጉዳይ ሲነሳ መላእክት፣ እስራኤል፣ ክርስቶስና ሰዎች (ደቀ መዛሙርት) ለተለየ አገልግሎት እንደተመረጡ ቃሉ ይናገራል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው በጢሞቴዎስ መልእክቱ ጢሞቴዎስን ሲመክረው፣ ‹‹አንድን እንኳ በአድልዎ ሳታደርግ እነዚህን ያለ መዘንበል (ማበላለጥ) እንድትጠብቅ በእግዚአብሔርና በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በተመረጡትም መላእክት ፊት እመክርሃለሁ›› (1ጢሞ. 5፡21) ሲለው፤ ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ በአንደኛው መልእክቱ ‹‹እነሆ የተመረጠና የከበረን የማዕዘን ራስ ድንጋይ በጽዮን አኖራለሁ በእርሱም የሚያምን አያፍርም›› (1ጴጥ. 2፡6) በማለት በነቢዩ ኢሳይያስ የተነገረውን ትንቢት በመጥቀስ የክርስቶስን መመረጥ ያመለክታል (ኢሳ. 28፡16)፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገራቸውን ሲጽፍ ‹‹እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፣… ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ›› (ዮሐ. 15፡16) በማለት ለአገልግሎት መመረጣቸውን ያመለክተናል፡፡
ለአገልግሎት መመረጥና ለድነት (ደህንነት) መመረጥ ልዩነት እንዳላቸው አስቀድመን መረዳት ይኖርብናል፤ ጳውሎስም ‹‹ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን›› ሲል፤ ክርስቲያኖችም በዚህ የምርጫ መደብ ውስጥ በኤፌሶን 1፡4 መሠረት መግባታችንን ያመለክታል፡፡ ይህን ጥቅስ የበለጠ ለመረዳት ወደ አንደኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 1፡1-2 ላይና ወደ ሮሜ 8፡28-30 ላይ ያለውን አዛምደን በመመልከት ግልጽ ለማድረግ ያስፈልጋል፤ ‹‹…እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ እንዳወቃቸው በመንፈስም እንደሚቀደሱ፣ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡት…›› ‹‹እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን፡፡ ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፣ እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው›› ብሎ በሚናገራቸው ላይ ትኩረት ልንሰጥ ይገባናል፡፡ ትኩረት የምንሰጣቸው ቃላቶች የሚከተሉት ሲሆኑ፤ እነርሱም አስቀድሞ መታወቅ፤ መወሰን፤ መጠራት፤ መጽደቅና መክበር የሚሉት ሲሆኑ፤ ሁለቱን ጥቅሶች በጥምረት ስንመለከት፤ ‹‹ይታዘዙ ዘንድ›› እና ‹‹ለሚወዱትና ለተጠሩት›› የሚሉትን ቃላቶች ስንመለከት የሚጠቁሙን ነገር አላቸው፡፡ ሰዎች በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት ይታዘዙ አይታዘዙ፤ ይውደዱ አይውደዱ፤ ይቀበሉ አይቀበሉ፣ እግዚአብሔር በመለኮታዊነቱ አስቀድሞ ያውቃል ማለት ነው፡፡ አስቀድሞ ያወቃቸውን በዳግም ልደት፣ ልጆቹና አዲስ ፍጥረት እንዲሆኑ መወሰን የእርሱ መብትና ሥልጣን ነው፡፡ ሰዎችም እነዚህን ነገሮች ለማግኘት ሊያደርጉት የሚገባቸውን ነገሮች ወደፊት እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው በራሱ ለመዳን ብቁ አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጥሪ ሰምተው የተቀበሉትን አድኖ፣ ያልተቀበሉትን ቢያጠፋቸው ፍርድ አዛብቶአል አድልዎም አድርጐአልም አይባልም፡፡ እግዚአብሔር ፍቅር ሆኖ ሳለ አንዱን ለመዳን አንዱን ለጥፋት ወይም አንዱን ለጽድቅ አንዱን ለኵነኔ ይመርጣል ብሎ ማሰብ ፍቅሩን ማጥፋት ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱ በመለኮታዊነቱ በወንጌሉ በኩል በሚያደርገው ጥሪ አማካኝነት፤ ሰዎች በወንጌሉ በኩል ጥሪ ሲደርሳቸው፤ ማን እንደሚታዘዝና እንደማይታዘዝ ያውቃል፡፡ በዚህም መሠረት ጥሪውን ሰምተው የሚድኑትን በክርስቶስ መርጫችኋለሁ ብሎ እንዳይናገር የሚከለክለው የለም፡፡ ጳውሎስም ‹‹ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን›› በኤፌሶን 1፡4 ላይ ያለው ለዚህ ነው፡፡ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን መረጣቸው ማለት ሌሎች እንዳይድኑ ከለከላቸው ማለት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ላለማዳን በማንም ላይ ፈርዶ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ለመዳን የተሰጣቸውን ዕድል ሳይጠቀሙበት ጸጋውን ቸል በማለታቸው ሊጠፉ ያሉትን አስቀድሞ አወቃቸው ማለት ነው፡፡
2 Comments
Derese Dercha · November 5, 2021 at 8:14 am
ትምህርቱን መከታተል እፈልጋለሁ
Amberber Gebru · November 9, 2021 at 7:01 am
Teleko.org ብለህ ግባ ታገኛለህ