ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን (online) አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት አምስት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እና የሶሻል ሚዲያ ቴሌግራምና ፌስ ቡክ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስናጋራ ቆይተናል፡፡ በዚህ በትንሣኤ ሰሞን ‹‹መልካም ትንሣኤ›› በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍ ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እናጋራችኋለን፡፡ አሁን በዚህ ሳምንት ትንሣኤን ልናከብር እየተዘጋጀን ባለንበት ጊዜ ከቅዱስ ቃሉ ‹‹እርሱን ግን አላዩትም›› ያሉትን ሰዎች ታሪክ አብረን እንድንካፈል ወደድን፡፡
የምንካፈለው የጽሑፍ ርዕስ ‹‹ተስፋ አድርገን ነበር›› የሚል ሲሆን፣ ታሪኩ የተመሠረተው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 24፡13-27 ባለው ሲሆን ስለ ሁለቱ የኤማሆስ መንገደኞች የሚተርክ ክፍል ነው፡፡ ‹‹እነሆም ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር›› በማለት ታሪኩን ይጀምራል፡፡
ከዚያ በፊት ይህ ምዕራፍ ከቁጥር አንድ ጀምሮ እስከ አስራ ሁለት ድረስ ያለው ታሪክ የሚተርከው ስለ መግደላዊት ማርያምና ዮሐና የያዕቆብም እናት ማርያም ሌሎችም ሴቶች ሆነው በሌሊት ወደ መቃብሩ ሄደው፣ ሽቶ ለመቀባት ሲዘጋጁ ሳለ፣ መቀብሩ ባዶ ሆኖ ማግኘታቸውን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሱ ወደፊታቸው ቀርበው ‹‹ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቷአል እንጂ በዚህ የለም›› ብለው መነሣቱን አበሰሩዋቸው፤ ‹‹እርሱን ግን አላዩትም››፡፡ ይህንም መነሣቱን ለአሥራ አንዱ እና ለሌሎችም ቢነግሩዋቸውም ቅዠት መስሎ ታያቸው፡፡ ጴጥሮስ ግን ለማረጋገጥ ሄዶ ሬሳው እንኳን እንደሌለ፣ መቃብሩ ባዶ መሆኑን አይቶ እንደ ተመለሰ ክፍሉ ይተርክልናል፡፡
ሴቶቹ የምሥራቹን ካበሰሮአቸው መካከል ቁ. 13 ላይ ‹‹ከእነርሱ ሁለቱ›› በተለይም ‹‹በዚያን ቀን›› ማለት ክርስቶስ ከሞት በተነሣበት ቀን ማለት ነው፡፡ በዚህ ቀን እነዚህ ሁለት መንገደኞች ከኢየሩሳሌም ወደ ኤማሆስ ሲጋዙ ሳለ፤ ‹‹ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር›› ይላል፡፡ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ አብሮአቸው መሄድ ጀመሮ ሳለ፣ ዐይናቸው ተይዞ ስለ ነበረ አላወቁትም፡፡ ‹‹እርሱም፡- እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፣ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው ? ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ከእነርሱም አንዱ መልሶ፡- ‹‹አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? ብለው ጠየቁት፡፡
‹‹ለቀባሪው አረዱት›› እንደሚባለው ለታሪኩ ባለቤት የሆነውን ሁሉ ማስረዳት ጀመሩ፤ እንዲህ ሲሉ ‹‹በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ እርሱንም የካህናት አለቆችና መኳንንቶቻችን ለሞት ፍርድ እንዴት አሳልፈው እንደ ሰጡትና እንደ ሰቀሉት ነው›› ብለው አስረዱት፡፡ እነርሱም ራሳቸው እስራኤልን ይቤዣል ብለው ተስፋ አድርገው እንደ ነበረና ደግሞም ሦስተኛው ቀን ሆኖታል፣ ምንም የለም ብለው ነገሩት፡፡
ደግሞ ይበልጥ የሚገርመው ነገር ከመካከላችን ወደ መቃብሩ ሄደው የነበሩት ሴቶች ሥጋውን አጣነው ብለው መመለሳቸው፣ ‹‹ሕያው ነው የሚሉ የመላእክትን ራዕይ ደግሞ አየን››፣ ‹‹እርሱን ግን አላዩትም››፡፡ ከመካከላችንም አንዳንዶች ወደ መቃብሩ ሄደው ሴቶች እንዳሉት ሆኖ በመገኘቱ መገረማቸውንና መደነቃቸውን ነገሩት፡፡
በዚህ ጊዜ ክርስቶስ ‹‹እናንተ የማታስተውሉ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ፤ ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው››፡፡ በመቀጠልም በሙሴና በነቢያት ስለ እርሱ የተነገረውን ሁሉ አንድ በአንድ በመተርጐም አስረዳቸው፡፡ በመጨረሻም ቀኑ መሽቶ ስለነበረ፣ ወደ ቤት ገብቶ እንዲያድር ለመኑት፤ እርሱም ወደ ቤታቸው ገባ፤ ማዕድም ቀርቦ ሳለ፣ ጸልዮ ባረከና ሰጣቸው፤ ወዲያውም ተሰወረባቸው፡፡
በዚህ ጽሑፍ ላካፍላችሁ የፈለግሁት ዋናው ነገር በርዕሱ ላይ ያለውን ሐሳብ ነው፡፡ በሩሲያና በዩክሬን መካከል፣ በእስራኤልና በሀማስ መካከል ባለው ጦርነት እንዲሁም በሌሎች የዓለም ክፍሎች ሁሉ የምናያቸው፣ በአገራችንም እየሆነ ባለው የእርስ በርስ መጠላላትና ግድያ ሁሉ ስንመለከት፤ አሁንም በኢየሱስ ተስፋ አለን ወይስ እንደ ኤማሆስ መንገደኞች ተስፋ አድርገን ነበር እንላለን፡፡ በዚህ ዘመን ኢየሱስ ተስፋችን ነው ወይስ እንደ ሁለቱ መንገደኞች ተስፋ አጥተን ይሆን?፡፡
ጌታ እንደ ቃሉ ተነስቷል፤ ‹‹እርሱን ግን አላዩትም››፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘላለም ያው ነው፤ እነሆ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፣ ብሎ ቃል የገባው ጌታ ቃሉን በመጠበቅ ታማኝ ነው፡፡ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው እንደ ተባለው ሆነን አንገኝ፡፡ ጌታ ሳናሰበው በድንገት ሊወስደን ይመጣል፤ አሜን ማራናታ ቶሎ ና፡፡
በጌታ ወንድማችሁ ወ/ዊ አምበርብር ገብሩ
0 Comments