ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት አምስት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እና የሶሻል ሚዲያ ቴሌግራምና ፌስ ቡክ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስናጋራ ቆይተናል፡፡ በዚህ በልደት ሰሞን ‹‹ስፍራ አልነበራቸውም›› በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍ ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እናጋራችኋለን፡፡ አሁን በዚህ ሳምንት ልደትን ልናከብር እየተዘጋጀን ባለንበት ጊዜ የዓለም አዳኝ ሆኖ የመጣው ጌታ ኢየሱስ በሚወለድበት ጊዜ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ እንዳጣ ታሪኩን አብረን እንድንካፈል ወደድን፡፡

አውግስጦስ ቄሣር ዓለሙን ሁሉ በሚገዛበት ጊዜ፣ የሚገዛውን የአንድ መቶ ሃያ አገሮች የሕዝብ ብዛት ለማወቅ የሕዝብ ቆጠራ እንዲደረግ ወሰነ፡፡ ይህን ታሪክ የምናገኘው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ሁለት ከቁጥር አንድ እስከ ሰባት ባለው ክፍል ውስጥ ነው፡፡ ‹‹በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች፡፡ ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ፡፡ ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ፡፡ ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነስቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ፡፡ በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፣ የኵር ልጅዋንም ወለደች፣ በመጠቅለያም ጠቀለለችው በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው›› (ሉቃ. 2፡1- 7)

Christmas

 ቀደም ባለው ምዕራፍ መልአኩ ገብርኤል ለማርያም የምሥራቹን ይዞላት በመጣ ጊዜ ስለዚህ ሕፃን ብዙ የተባሉ ነገሮች ነበሩ፡፡ ጌታ ካንቺ ጋር ነው፣ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻል፣ ታላቅ የልዑል ልጅም ይባላል፣ የአባቱ የዳዊት ዙፋን ይሰጠዋል፣ በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ይነግሣል ተብሎ ተነግሮለት ሳለ፤ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ግን የገጠመው የተለየ ነው፡፡

በአገራችን እንኳን ለወለደች ለነፍሰ ጡር በብዙ ነገር ቅድሚያ ይሰጣታል፣ በትራንሰፖርት ላይ እንኳን ወንበር ይለቀቅላታል፡፡ የእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ማለት በዘመናችን አጠራር ሆቴል ማለት ነው፡፡ ለማደሪያው የሚከፈል ከሆነ የሚከፍሉት አጥተው ሊሆን ይችላል፣ የማይከፈል ከሆነ ደግሞ ሞልቶባቸው ሊሆን ይችላል ማለት ነው፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ በየዘመናቱ ከሚወለዱት ሕፃናት ባነሰ መንገድ ተወልዶ፣ የዓለም አዳኙ ኢየሱስ የሚያድርበት ስፍራ ስላልነበረው እናቱ ማርያም በግርግም አስኛችው ይለናል ፀሐፊው ሉቃስ፡፡

ከዚህ ታሪክ በጣም ብዙ ነገር እንደምትማሩ በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡ እኔ ካየኋቸውና ከተማርኳቸው ጥቂቶቹን ብቻ ላካፍላችሁ፡፡ በመጀመሪያ ግርግማቸውን የፈቀዱለት የቤት ባለቤቶች በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተባረኩ መሆናቸውን አየሁ፡፡ ሁለተኛው ዮሴፍና ማርያም የመንግሥትን ትዕዛዝ በመታዘዛቸው ምን ያህል ታማኞች እንደሆኑ አየሁ፡፡ ማርያም እኔ ነፍሰ ጡር ነኝ ሄጄ መምጣት አልችልም ብላ ዮሴፍን ብቻ ለመላክ በቂ ምክንያት ነበራት፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ በቤተ ልሔም የመወለዱ ትንቢት አይፈጸምም ነበር፡፡ ሦስተኛው ልጇን እንደ ወለደች ዮሴፍን ‹‹የምበላው ሳጣ ልጄ ጥርስ አወጣ›› እንደሚባለው በምን አሳድገዋለሁ ውሰድና ወደ ጫካ ወይም ባሕር ጣልልኝ አለማለቷ ያስደንቀኛል፡፡      እናንተስ ምን ተማራችሁ? ጌታ በልባችሁ ስፍራ አለው? ቃሉ የሚላችሁን በታማኝነት ትታዘዛላችሁ? ዋጋ የሚያስከፍልም ቢሆን  ጌታ በቃሉ የተናገረው እንዲፈጸም በጸሎት ትተጋላችሁ?


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *