በታላቁ ተልዕኮ ውስጥ ሦስተኛው ሀሳብ “ምስክሮቼ ትሆናላችሁ”  የሚል ነው፤ መንፈስ ቅዱስን መስጠትና ኃይል መስጠት የእግዚአብሔር ድርሻ ሲሆን፣ ምስክር መሆን የሐዋርያት ድርሻ ነበር፡፡ ጌታ ተልዕኮውን ለመወጣት የተጠቀመበት ስልት ሐዋርያትን መጠቀም ነበር፤ በምድር በነበረበት ጊዜ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች አድርጎአል፡፡ የመጀመሪያው ለአባቱ ክብር መስጠት፣ ሁለተኛው ጥቂቶችን በማሰልጠን  ጊዜ መውሰድ ሲሆን፣ ሦስተኛው ተልዕኮውን ለእነርሱ አሳልፎ በመስጠት ወደ መጣበት ተመልሶ መሄድ ነበር፡፡ ይህን በሚያደርግበት ጊዜ ለሰጣቸው ተልዕኮ ድንበር ነበረው፣ የድንበሩም ስፋት         (1) በኢየሩሳሌም፣ (2) በይሁዳ፣ (3) በሰማርያ፣ እና (4) እስከ ምድር ዳርቻ የሚል ነበር፡፡

ሐዋርያት በተሰጣቸው የተልዕኮ ድንበር መሠረት ተልዕኳቸውን ተወጥተው ይሆን? ቃሉ ምን ያስተምረናል? እኛስ ምን እንረዳለን? ተልዕኮውን ስንመለከት፣ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያና በዓለም ዳርቻ በማለት በቅደም ተከተል ያስቀምጣል፡፡ ሀሳቡ ምንም እንኳ እንዲህ ቅደም ተከተል ያለው ቢመስልም፣ ወንጌሉ መስፋፋት ያለበትና ወንጌልን ማሠራጨት ያለባቸው በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ እንደሆነ  የምትጠቁም ፊደል አለች፡፡ ‹‹ም›› የምትለው ፊደል የምታመለክተው ወንጌሉን በአንድ ጊዜ በኢየሩሳሌምም፣ በይሁዳም፣ በሰማርያምና በዓለም ዳርቻም፣ ማለትም በሁሉም ቦታ፣ ማሠራጨት እንዳለባቸው  ነው፡፡

 በምዕራፍ 2 ላይ እንደምናገኘው፣ ሐዋርያት ጠብቁ በተባሉት መሠረት የተሰጣቸውን ትዕዛዝ በጸሎት እየተጉ ሲጠብቁ ሳለ፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ፈሶላቸው በኃይል ከተሞሉ በኋላ፣ ከመካከላቸው ፈሪ የነበረው ጴጥሮስ ተነሰቶ ለበዓለ ኀምሳ በዓል ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች ድምጹን ከፍ አድርጎ ወንጌልን ሰበከላቸው፡፡ በዚያም ቀን በተደረገው ስብከት ወደ ሦስት ሺ የሚሆኑ ሰዎች በጌታ አመኑ፡፡ (2፡41)

ወደ የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 3 መጥተን ስንመለከት፣ ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ ሽባ የነበረውን ሰው ምፅዋት ሲለምናቸው ሳለ እነርሱ ክርስቶስን ሰጥተውት በመፈወሱ ምክንያት መከራ ሲቀበሉ፣ ሲታሠሩ፣ ሁለተኛ በዚህ ስም እንዳትናገሩ ተብለው በማስጠንቀቂያ ከእስር ሲፈቱ እናያለን፡፡ እነርሱም “ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን እንሰማለን፣ እንታዘዛለን” በማለት ውሳኔያቸውን ያሳውቃሉ፡፡ በመቀጠልም በጌታ ፊት በጸሎት በመቅረብና በመጠየቅ የእግዚአብሔርን ኃይል ከተሞሉ በኋላ፣  አገልግሎታቸውን በድፍረት ይቀጥላሉ፡፡ በቀጣይ እንቅስቃሴአቸው ወደ አምስት ሺ ሰዎች አምነው መጠመቃቸውን በምዕራፍ 4፡4 ላይ እናነብባለን፡፡ ሐዋርያት በቆራጥ ውሳኔያአቸውና በከፈሉት  መከራ (ዋጋ) አማካኝነት በምዕራፍ 6፡6 ላይ የእግዚአብሔር ቃል እየሠፋ ሄደ፣ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቁጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፡፡ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ፣ በማለት ሐዋርያት በወንጌሉ ሥራ ብርቱ የሆኑበትን ጎናቸውን ያሳየናል፡፡    ተልዕኮን ስለ መወጣት በሐዋርያት ሕይወት የነበረውን ብርቱ ጎን ተመለከትን፡፡ እኛስ እንዴት ነን? ጌታ የሰጠንን ትዕዛዝ ምን ያህል ትኩረት ሰጥተነው  ተወጥተን ይሆን? ‹‹አይ፣ እኔ መጋቢ፣ ወንጌላዊ፣ የሙሉ ጊዜ አገልጋይና ሽማግሌ አይደለሁም›› ብለን የተለያዩ ምክንያቶችን መደርደር እንችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ምክንያት መስጠት አያዋጣንም፡፡ ጌታ ታላቁን ተልዕኮ የሰጠው ለሁላችንም ስለሆነ፣ እያንዳንዳችን እንደሚገባ ልንወጣው ይገባናል፡፡ ይህን ትዕዛዝ ለመወጣት የግድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ ተማሪና አስተማሪ በት/ቤቱ፣ ነጋዴም በንግዱ፣ ገበሬም በግብርናው …ሁሉም በተሰለፈበት የሥራ መስክ ለክርስቶስ ምስክር በመሆን ተልዕኮአችንን መወጣት ይቻለናል፡፡ በሥራችን፣ በቃላችንና፣ በድርጊታችን፣ ታማኝና ቅን ሆነን ልንገኝና ለተልዕኮአችን ትኩረት በመስጠት እንደ እሥራኤላውያን በልብ መያዝ፣ ለልጆች ማስተማር፣ በቤትም ስንቀመጥ፣ በመንገድም ስንሄድ፣ ስንተኛም፣ ስንነሣም ልንጫወተው ይገባናል፡፡ በእጃችንም ምልክት አድርገን በማሠር፣ በዓይኖቻችንም መካከል እንደ ክታብ በማድረግ፣ በቤታችንም መቃኖችና በደጃፋችንም በሮች ላይ በመጻፍ ተልዕኮአችንን  ልንወጣው ይገባናል፡፡ (ዘዳ. 6፡6-9፤ ማቴ 24፡45-51) ተልዕኮን በሁሉ ሥፍራ በቤት፣ በሥራ፣ በገበያና በሌላም ቦታ መናገር፣ ማወጅና መኖር ይጠበቅብናል፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *