ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት ስድስት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እና የሶሻል ሚዲያ ቴሌግራምና ፌስ ቡክ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስናጋራ ቆይተናል፡፡ በዚህ በምንጀምረው አዲስ ዓመት ‹‹እግዚአብሔርን ማወቅ›› በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍ ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እናጋራችኋለን፡፡ በቴሌግራምና በፌስ ቡክም ጊዜውን ጠብቆ እንለቃለን፡፡ አሁን በዚህ ሳምንት አዲስ ዓመትን ልናከብር እየተዘጋጀን ባለንበት ጊዜ፣ ‹‹መልካም አዲስ ዓመት›› እያልኩ ከቅዱስ ቃሉ አብረን እንድንካፈል ወደድሁ፡፡
በዚህ የአዲስ ዓመት መግቢያ ላይ የማካፍላችሁ ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብዓውን ደቀ መዛሙርት ለአገልግሎት በላከበት ጊዜ የተናገራቸውን ከሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10፡21-22 ያለውን ይሆናል፡፡
‹‹በዚያን ሰዓት ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ሐሤት አደረገና፡-የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፡- ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግናለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፡- ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና፡፡ ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፣ ወልድንም ማን እንደ ሆነ ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም፣ አብንም ማን እንደ ሆነ ከወልድ በቀር ወልድም ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በቀር የሚያውቅ የለም አለ፡፡››
በዚህ ሥፍራ ትንሽ ልጠቁማችሁ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር ስለ ‹‹እግዚአብሔር›› ምን ያህል እንደምናውቅ ራሳችንን እንድንጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ሥፍራ አብን ከወልድ በቀር የሚያውቅ የለም፤ ወልድንም ከአብ በቀር የሚያውቅ የለም ይላል፤ ታዲያ እግዚአብሔር አብን እንዴት ነው የምናውቀው? እግዚአብሔር አብ ራሱን ያሳወቀበት መንገድ ሁለት ናቸው፣ ወልድና ቃሉ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ በምዕራፍ 1:18 ላይ ‹‹መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው (ገለጠው) ይላል፡፡ በሕያው ቃል ትርጉም ‹‹አብን የሚያውቁ ቢኖሩ ወልድ የገለጠላቸው ብቻ ናቸው›› ሉቃስ 10፡22 ይላል፡፡
አብን ምን ያህል እናውቀዋለን? እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ባይሆንም እንካን እንደ ሙሴ በከፊል ለማየት ወልድን(ኢየሱስን) ማወቅ ይጠይቃል፤ ኢየሱስን ለማወቅ የምንችለው በቃሉ በኩል ነው፡፡ ቃሉ በ1ኛ ዮሐንስ 5፡12 ‹‹ልጁ (ኢየሱስ) ያለው ሕይወት አለው፣ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም›› ይላል፡፡ ስለዚህ አብን ማወቅ የምንችለው የሰውን ሥጋ ይዞ በመጣው በኢየሱስ ነው፡፡ ዮሐንስ በወንጌሉ 1፡1፣14 ላይ ሲናገር ‹‹በመጀመሪያው ቃል ነበረ፣ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፣ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡… ቃልም ሥጋ ሆነ…›› ይላል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል 14፡9 ላይ ‹‹እኔን ያየ አብን አይቶአል›› ብሎ እንደ ተናገረው እግዚአብሔር አብን ማወቅና ማመን የምንችለው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው፡፡
ይህ አዲስ ዓመት እግዚአብሔርን የምናውቅ የበለጠ ማወቅ፣ ያላወቅን ደግሞ ማወቅ ይሁንልን፡፡ እግዚአብሔርን ካወቅን ፍቅርና ሰላም ይኖረናል፣ ፍቅርና ሰላም ከኖረን አንሰዳደብም፣ አንጠላላም፣ አንሰራረቅም፣ አንገዳደልም፡፡ ስለዚህ ይህ አዲስ ዓመት ለሁላችንም እግዚአብሔርን የምናውቅበት የፍቅርና የሰላም ዓመት ይሁንል፡፡ መልካም አዲስ ዓመት
0 Comments