ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት አምስት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እና የሶሻል ሚዲያ ቴሌግራምና ፌስ ቡክ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስናጋራ ቆይተናል፡፡ በዚህ በምንጀምረው አዲስ ዓመት ‹‹ደስታ›› በሚል የተዘጋጀ ጽሑፍ ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ እናጋራችኋለን፡፡ በቴሌግራምና በፌስ ቡክም ጊዜውን ጠብቆ እንለቃለን፡፡ አሁን በዚህ ሳምንት አዲስ ዓመትን ልናከብር እየተዘጋጀን ባለንበት ጊዜ፣ ‹‹መልካም አዲስ ዓመት›› እያልን ከቅዱስ ቃሉ የአንድ ግለሰብ ታሪክ አብረን እንድንካፈል ወደድን፡፡
የምንካፈለው ጽሑፍ ርዕሱ ‹‹ለእግዚአብሔር እንበርከክ›› የሚል ሲሆን፣ ታሪኩ የተመሠረተው በኤፌሶን መልእክት ምዕራፍ 3፡14-15 ላይ ‹‹የእግዚአብሔርን አባትነት›› ስለ ተረዳ ግለሰብ ታሪክ ይሆናል፡፡ እንደ ሰው በዚህ ዓለም ስንኖር በተለያየ ሁኔታ፣ በፈተና፣ በችግርና በመከራ ውስጥ እናልፋለን፤ ጌታም በምድር በነበረበት ጊዜ በዮሐንስ ወንጌል 16፡33 ላይ ‹‹በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ›› በማለት ለደቀ መዛሙርቱ እንደተናገራቸው እናነባለን፡፡ ሰው ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔርን ባለመታዘዙ ምክንያት ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ በችግር፣ በፈተናና በሥቃይ መኖር እንደ ጀመረ የታወቀና ሁላችንም የምናልፈበት ያለ ሐቅ ነው፡፡
አሁንም በዓለም ዙሪያና በአገራችን የምናየውና የምናረጋግጠው ይህንኑ እውነት ነው፡፡ ታዲያ ዓለም በዚህ የተሞላች ከሆነ ምን እናድርግ? በዚህ ጊዜ ልናደርግ የምንችለውን የምንማረው ከባለ ታሪኩ ከሐዋርያው ጳውሎስ ይሆናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በአይሁድ እምነት የሚኖርና በእምነቱ ጽኑ ሰው ነበር፤ ነገርግን የዓለም አዳኝ ሆኖ የመጣውን ክርስቶስን ማወቅና መቀበል አልቻለም፤ ምክንያቱም በሃይማኖት ወግና ሥርዓት ተይዞ ስለነበረ፣ ሊሞትለት የመጣውን አዳኙን መረዳትና ሕይወቱን አስረክቦ ጌታን ጌታ አድርጎ ማመን አልቻለም፡፡ የተለወጠበትን ታሪኩን በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 9 ላይ እንደምናገኘው ጌታ ራሱ አስደናቂ በሆነ መንገድ እንደተገናኘውና ሕይወቱ እንደ ተለወጠ ታሪኩ ይነግረናል፡፡
ዛሬ ከሐዋርያው ጳውሎስ ታሪክ እንድንማር የወደድኩት ስለ ወንጌል ሲል በታሠረበት ጊዜ የወሰደውን እርምጃ ነው፡፡ ለፊልጵስዩስ አማኞች በጻፈው መልእክቱ ‹‹ይህን ስል ስለ ጕድለት አልልም፣ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና፡፡ መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም፣ መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ፡፡ ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› (ፊልጵስዩስ 4፡11-12) በማለት ያለፈባቸውን የሕይወቱን ውጣ ውረዶች ይናገራል፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ከላይ ያሉትን ሐሳቦች እንዲህ እንዲል ያበቃው ዛሬ የምንመለከተው ክፍል ውስጥ ያለው የወሰደው እርምጃ እንደሆነ እንመለከታለን፡፡ ታሪኩ የተመሠረተው ከላይ እንደገለጽኩት በኤፌሶን መልእክት ላይ ነው፡፡ ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው በእስር ቤት ውስጥ ሆኖ እንደሆነ የሚከተሉት ጥቅሶች ‹‹… ስለ እናንተ እስር የሆንኩ›› (3፡1)፣ ‹‹… በጌታ እስር የሆንሁ›› (4፡1) የሚሉት ያረጋግጡልናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሕይወቱ ለገጠመው ችግር ሁሉ፣ እኛም ዛሬ ለሚገጥሙን ችግሮች ሁሉ፣ እርሱ የወሰደው የመፍትሔ እርምጃ ለእኛም መፍትሔ መሆን ይችላል፡፡ የወሰደው መፍትሔ የሚያመጣለት እርምጃ ምን ነበር?
ጳውሎስ በእስር ቤት በነበረበት ጊዜ ለኤፌሶን አማኞች ሲጽፍ ‹‹ስለዚህ ምክንያት በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ›› (ኤፌ 3፡14-15) በማለት የእርሱን ምሳሌነት እንዲከተሉ ይመክራቸዋል፡፡ ስለዚህ ምክንያት የሚለው የወንጌል አገልጋይ መሆኑንና የደረሰበት እስራትና መከራ በወንጌል ምክንያት እንደሆነ ያሳያቸዋል (3፡7-13)፡፡ የእግዚአብሔር አባትነት በሰማይና በምድር ሁሉ እንደሆነ ያሳስባል፣ ከአብ ፊት እንበረከካለሁ ሲል ማንንም መለማመጥና ደጅ መጥናት እንደማይሆንለት ያመለክታል፡፡ ስለዚህ በአባቴ ፊት ብቻ እንበረከካለሁ ሲል በአምላኩ ላይ ያለውን መታመን ታላቅ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በምዕራፍ 4፡6 ላይ (… የሁሉም አባት…) ነው በማለት ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለሚያምኑበት ሁሉ አባት እንደሆነም ገልጾአል፡፡
በሰሜኑ አገራችን ለአገልግሎት ሄጄ ሳለ፣ የአንድ ሰው ታሪክ ሰማሁ፤ ታሪኩ እንዲህ ነው፣ አንዱን ጌታን መስክረውለት ወደ ጸሎት ቤት ይዘውት መጥተው የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፡፡ ከቃሉ በኋላ ሕይወታችሁን ለጌታ የምትሰጡ ወደ መድረኩ ውጡ ሲባል ከሌሎች ጋር አብሮ ወጣ፡፡ ተንበርከኩና እንጸልይላችሁ ሲባሉ እርሱ ‹‹ለማንም ተንበርክኬ አላውቅምና አልበረከክም›› ብሎ ሳይጸለይለት ቀረ፡፡ በሌላ ጊዜ ከብዙ ቆይታ በኋላ እውነቱ ሲገባው መድረክ ላይ ወጥቶ ‹‹ኧረ ወንዱ ወንዳወዱ›› ብሎ መሸለል ጀመረ፡፡ አሁን ሰዎች ተንበርከክ ስላሉት ሳይሆን፣ በራሱ ጊዜ የክርስቶስ ጌትነት በደንብ ሲገባው በራሱ ፈቃድ ተንበርክኮ ‹‹እኔን የለወጠ ጌታ ጎበዝና ጀግና ነው ብሎ አወጀ፡፡
እኛም የጌታን ጀግንነትና ታላቅነት ረድተንና ተቀብለን ብንመላለስ አባትነቱን መረዳት እንችልለን፡፡ እግዚአብሔር ያድናል፣ ይሰማል፣ ይመልሳል፣ ይታደጋል፤ ስለዚህ በምናልፍባቸው ችግሮች ሁሉ በድል ለማለፍ በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፈት እንድንበረከክ እጋብዛችኋለሁ፤ እርሱ የሁላችን አባት ስለሆነ እንደ አባትነቱ ያደርግልናል፡፡ አባት በልጆቹ እንደማይጨክን እግዚአብሔርም አባታችን ስለሆነ አይጨክንብንም፡፡
እኔ ይህን ጽሑፍ ልጽፍ የቻልኩት ጳውሎስ ስላለ ብቻ ሳይሆን በራሴም ሕይወት ስለ አየሁት ነው፡፡ በዚህ ሁለት ዓመት ከአቅሜ በላይ በሆነ ችግር ውስጥ እያለፍኩ ነበር፤ በዚህ ሰማይንና ምድርን በፈጠረ አምላኬ ፊት መንበርከክም አስፈልጎኝ ነበር፡፡ በጉልበቴ መንበርከክ ብቻ ሳይሆን በልቤም በፊቱ የተንበረከኩባቸውና ያለቀስኩባቸው ጊዜያቶች ብዙ ነበሩ፤ እኔ ብቻ አልነበርኩም ብዙዎችም ስለ እኔ ተንበርክከው አንብተዋል፡፡ እግዚአብሔር በተቆረጠና ባለቀ ነገር ላይ መሥራት የሚችል ጌታ አስደናቂ በሆነ መንገድ ባልጠበቅሁት ጊዜ የፈተናዬን ገመድ ቆርጦ ዕንባዬን አበሰው፣ ተራራዬን አንከባለለው፣ ሸለቆዬን ሞላው፣ ልቤን በደስታ ሞላው፤ ስሙ የተመሰገነ ይሁን፡፡
ወንድሞችና እህቶች ይህ ዐዲስ ዓመት ‹‹በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት›› በጉልበታችንም፣ በልባችንም የምንበረከክበት ዓመት ይሁንልን፤ እያልኩኝ ዓመቱ የሰላምና የደስታ እንዲሆንልን ምኞቴና ጸሎቴ ነው፡፡
‹‹ መልካም አዲስ ዓመት ››
2015
0 Comments