‹‹የተከፈተ በር››

የንባብ ከፍል፡- 1ቆሮንቶስ 16

‹‹ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛል…›› ቁ. 9

በሰው ልጆች የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ የእግዚአብሔርን ሥራ የተቃወሙ ሰዎች እጅግ ብዙ ቢሆኑም አንድ ጊዜም እንኳን ተሳክቶላቸው እግዚአብሔርን ከዘላለማዊ የሥራ ዕቅዱ አውርደውት አያውቁም፡፡ ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ እርሱን የሚወዱና የእርሱ አገልጋዮች የሆኑ የሚደርስባቸውን ተቃውሞና ስደት ተጋፍጠው ድል በማድረግ፣ እነሆ ዛሬ ወንጌላችንን አስረክበውን አልፈዋል፡፡

የእግዚአብሔርን ሥራ የሚዘጋ በሰማይም ሆነ በምድር ምንም ኃይል እንደሌለ ለመረዳት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ‹‹ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ›› ስላለ ነው፡፡ ‹‹እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼሃለሁ ማንም ሊዘጋው አይችልም›› (ራዕይ 3፡8)፡፡ ጌታ ሊያገለግሉት ለሚወዱ ልጆቹ እንደ ፍቃዱ የተከፈተን የሥራ በር ይሰጣል፡፡ ስለሆነም የእግዚአብሔር አገልጋዮች ይህንን የወንጌል ሥራ በር እንዲገልጽላቸው በጸሎት መጠየቅ ይገባቸዋል፡፡

እግዚአብሔር ላሳያቸው የሥራ መስክ ራሳቸውን አሳልፈው መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም በዚያ ውስጥ ተቃውሞ፣ ስደት፣ ፈተና… ስላለ ለዚህ አገልግሎት እስከ መጨረሻ ራስን ለመሰዋትና ታማኝ ለመሆን መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ማንም ክርስቲያን ራሱን ለመከራ ማጋለጥ ወይም ስደትን በራሱ እንዲመጣበት ማድረግ የለበትም፡፡ ነገር ግን በተከፈተ የወንጌል በር ውስጥም ተቃውሞና ስደት መኖሩንም ማወቅና እንደ ርግብ የዋህ እንደ እባብ ብልህ ሆኖ ዓላማውን ሳይስት መራመድ ይገባዋል፡፡

ታዲያ ስንቶች ነን ጌታ የተከፈተ በር እንዲሰጠን የምንጸልይ? ስንቶችስ እንሆን የተከፈተ በር እያለ ቃሉን ከመናገርና ከመመስከር ችላ ያልን?

ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! ዛሬ በሰጠኸኝ በር መሥራት እንድችል ኃይልን ስጠኝ፡፡

‹‹ከሞትም ያድናል››

የንባብ ክፍል፡-2ቆሮንቶስ 1

‹‹… ከአቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር›› ቁ. 8

ሞት ሰው ሁሉ ሊቀምሰው የማይፈልገው መሪር የሆነ ጽዋ ነው፡፡ ከሞት በኋላ ስላለው ሞት በምናስብበት  ጊዜ፣ ሰው፣ በኢየሱስ ካላመነ በስተቀር ወደ በለጠው ዘላለማዊ ሞት የሚሸጋገርበት እጅግ የከፋና የመረረ መሆኑን ልንረዳ እንችላለን፡፡

የቱንም ያህል በምድር ላይ የተከበር ሰው ቢሆን ከሞተ በኋላ ሬሣ መባሉን ማወቅ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ የመኪና አደጋ ሰዎችን አጋጥሞአቸው ሳለ የሚጠየቀው ጥያቄ ‹‹ሰው ተረፈ›› የሚል ነው፡፡ ይህም የሰው ሕይወት ከማንኛውም ሀብትና ንብረት ይልቅ የከበረ መሆኑን ነው፡፡

ሐዋርያው ጰውሎስም ይህንኑ በማስመልከት እግዚአብሔር እንዴት ከሞት እንዳዳነውና እንዳተረፈው ይናገራል፡፡ በእርግጥ ለሚታመኑበት ሰዎች ያለ እርሱ ፈቃድ አንዳች ነገር እንኳን እንደማይደርስባቸው እናውቃለን፡፡ ጌታ ከሞትም የሚያድን አምላክ ነው፡፡ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ በሞት ጥላ ውስጥ እንኳን ባልፍ አንተ ከእኔ ጋራ ነህና ክፉን አልፈራም›› በማለት ይናገራል፡፡ ከዚህም ይልቅ እጅግ የምንደሰተው ከሞት በኋላ ስላለው ትንሣኤና የዘላለም ሕይወት በምናስብበት ጊዜ ነው፡፡ ትንሣኤው ለክርስቲያኖች እምነት መሠረታቸውና ተስፋቸው የወንጌልም እውነት ነው፡፡

ክርስቲያኖች በሞት ላይ ሙሉ ሥልጣንና ድፍረት አለን፡፡ ሞት ለአማኞች ወደ ፍጹም ደስታ ወደ አምላካችን ቤት የሚያደርሰን ድልድይ ሆኖ ያገለግለናል፡፡ በሞትና በሲዖል ላይ ሥልጣን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን በመያዛችን ሞት በእኛ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡ ከዚህ ዓለም በምናልፍበት ጊዜ በብዙ መላእክት ዝማሬ ነፍሳችን በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር ትደርሳለች፡፡ ታዲያ የሞት ጌታ የሆነው ከእኛ ጋር ከሆነ የምሥራቹን ለመናገር ለምን እንፈራለን?

ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! ሩጫዬን ጨርሼ ገድሌን ተጋድዬ፣ አንተን አስከብሬ በፊትህ እንድቆም ጸጋህን አብዛልኝ፡፡

                                                 ‹‹የአዲስ ኪዳን አገልጋዮች››

የንባብ ክፍል፡- 2ቆሮንቶስ 3

‹‹በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን›› ቁ. 6

የቀደመው የኪዳን ትዕዛዝ የእግዚአብሔርን ፍጹም ቅድስና ሲያሳየን፣ የሰውን ሕግ ተላላፊነትና ኃጢአተኛነት ያሳያል፡፡ ሰውም በኃጢአቱ ምክንያት የሞት ፍርድ ተፈረደበት፡፡ ‹‹ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጽ ነው (ገላ. 3፡11)፡፡ ስለዚህም ማንም ሰው አድርግ አታድርግ የሚለውን ሕግ በሥጋው ኃይል ለመፈጸም ካለበት የሞት ፍርድ ሊያመልጥ የቻለ ማንም የለም፡፡

አዲሱ ኪዳን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባደረገው ቤዛነት ከሕግ እርግማን እንድንዋጅ፣ ክርስቶስን በማመን ሕይወትን እንድናገኝ እግዚአብሔር ያዘጋጀልን የጽድቅ መንገድና ቃል ኪዳን ነው፡፡ እኛንም ለዚህ አዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፡፡ በመንፈስ ብንኖር ከሕግ በታች አይደለንም፤ የአዲስ ኪዳን አገልጋዮች ከሕግ በላይ መሆናችንንና እንድንሆንም ያደረገ በውስጣችን የሚኖረው የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ነው፡፡ የምናደርጋቸው መልካም ሥራዎች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በእኛ ውስጥ የሚሠራቸው ናቸው፡፡ በሕግ ውስጥ ሆነን መፈጸም ያቃተንን አሁን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንፈጽማለን፡፡

ሕግ ከሚጠይቀንና ከሚፈልግብን የበለጠ በዚህ በአዲስ ኪዳን በፍቅር ማድረግ እንችላለን፡፡ ለዚህም ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ ከተመረጥን ዘንድ ያለብንን ኃላፊነትና ግዴታ መፈጸም አለብን፡፡ ሞት ከሚሆን ሕግ አውጥቶ በመንፈስ እንድንመራ የአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንድንሆን ላበቃን አምላካችን ክብር፣ ምስጋናና ውዳሴም ገናንነትም ሁሉ ይድረሰው፡፡ ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! የምሥራቹን ቃል ለማድረስ እግሮቼ የፈጠኑ፣ እጆቼ የተዘረጉ፣ አንደበቴ የተከፈተ ይሁን፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *