ሰዎች በዚህ ዓለም ሲኖሩ በተለያየ ነገር ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ በክብር፣ በዝና፣ በገንዘብ፣ በዘር፣ በጐሣ፣ በቋንቋ እና በመሳሰሉት ነገሮች ሁሉ ላይ ትኩረት በማድረግ ጊዜያቸውን፣ ኃይላቸውንና ሕይወታቸውን ለዚያ ነገር ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ምድር በምንኖርበት ጊዜ ትልቅ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን ነገር ቢኖር የእግዚአብሔር ተልዕኮ መሆን አለበት፡፡ ሐዋርያት ለ3 ዓመት ተኩል በጌታ በራሱ እንኳን ሰልጥነው ልባቸውን በእግዚአብሔር ተልዕኮ ላይ ማድረግ ተስኖአቸው ነበር፡፡ በሐዋርያት 1፡6-8 ባለው ክፍል ውስጥ ስንመለከት፣ ተደብቆ ያለ ጥያቄ ከትንሣኤ በኋላ ወጣ፣ በልባቸው ውስጥ ትልቅ ትኩረት የሰጡት የእሥራኤልን መንግሥት ጉዳይ ነበር፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በሥጋ በመጣበት ጊዜ እስራኤላውያን በሮማውያን ቅኝ አገዛዝ ሥር ወድቀው ስለነበር፤ የራሳቸው የሆነ መንግስትና ነፃነት አልነበራቸውም፡፡ ክርስቶስም ሲመጣ ነፃነታቸውን ያስመልስልናል ብለው ሲጠብቁት፣ እርሱ ወደ መስቀል ሞት አመራ፡፡ እንደ ኤማሆስ መንገደኞች ጠውልገው፣ በአንድ በተዘጋ ቤት ውስጥ እያሉ ድንገት በመካከላቸው ተገኘ፡፡ ከእነርሱ ጋር እንደ በፊቱ ይሆናል ብለው ሲጠብቁ አልሆነም፤ ለዐርባ ቀን ያህል አልፎ አልፎ እየታያቸውና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሲነግራቸው ቆይቶ፣ በመጨረሻ በዕርገት ሊለያቸው ተሰብስበው እያለ ጥያቄአቸውን አቀረቡለት፡፡
“እነርሱም በተሰበሰቡ ጊዜ፡- ጌታ ሆይ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን ብለው ጠየቁት፡፡” ሐዋርያት ከዚህ በፊት ብዙ ጥያቄ ጠይቀውታል፤ እርሱም ለተጠየቀው ጥያቄ እንደሚገባ መልሶላቸዋል፡፡ አሁንም ከትንሣኤው በኋላ የመጨረሻቸውን ጥያቄ ይጠይቁታል፡፡ እርሱም ለጥያቄያቸው ቀጥተኛ ያልሆነ ምላሽ ከሰጣቸው በኋላ፣ ነገር ግን በማለት ለጠየቁት ጥያቄ ተቃራኒ የሆነ ምላሽ እንዲህ በማለት ይመልስላቸዋል፡- “እርሱም አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም፤ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ … ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡” (ከቁ.6-8)፡፡ ‹‹ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው፡፡ እነርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፣ እነሆ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፡- የገሊላ ሰዎች ሆይ፡- ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው፡፡›› (ከቁ.9-11) የተሰጣቸው መልስና ሁኔታው ቶሎ ባይገባቸውም፣ ከነበሩበት ደብረ ዘይት ከሚባለው ሥፍራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ በተነገራቸው መሠረት ከተቀበሉ በኋላ ትኩረታቸውን በወንጌሉ ላይ እንዲያደርጉ እንዳደረጋቸው እንመለከታለን፡፡
ዛሬ በግልም ሆነ በቡድን ትልቅ ትኩረት እየሰጠነው ያለ ነገር ምንድነው? ፡፡ ለዝና፣ ለክብር፣ ለስም፣ ለገንዘብ፣ ለዘር፣ ለጐሣችን ለቋንቋችን? ሁላችንም ራሳችንን እንጠይቅ? ራሳችንን እንደሚገባ እናውቀዋለን፡፡ ራሳችንን ከራሳችንና ከእግዚአብሔር መደበቅ አንችልም፤ እነዚህ እርሾዎች በውስጣችን ካሉ፣ ሕይወታችንን በክለው ከጥቅም ውጭ ሳያደርጉን፣ አውጥተን እንጣላቸው፡፡ ለመሆኑ፣ እንደ ሐዋርያት ጥያቄዎች ጠይቀን እናውቃለን? ከጠየቃችሁስ ምን ብላችሁ ጠይቃችሁ ነበር? ጌታስ ምን ምላሽ ሰጣችሁ? አወይ የሰው ድካም! ጌታ ለ 3 ዓመት ተኩል አሰልጥኖ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ሲጠይቁት ምን ይባላል? ሳይገረም አልቀረም፡፡ እኛም ዛሬ እንደ ሐዋርያት ምድራዊ አጀንዳ ውስጥ ገብተን፣ ሰማያዊ የሆነውን አጀንዳ ትተን ይሆን? የምንጠይቀው ጥያቄ ከተልዕኮ ጋር የተገናኘ ስለ ወንጌሉ ሥራ፣ ስለ መንግሥቱ መስፋፋት መሆን አለበት፡፡ ትኩረታችን በጊዜያዊና በሚጠፋ ነገር ላይ አይሁን፤ ትኩረታችን በእግዚአብሔር ተልዕኮ ላይ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ ስንት ወንጌል ያልደረሳቸው ሕዝቦች እንዳሉ ታውቃላችሁ? ማነው ትኩረት የሚሰጣቸው? የማን ኃላፊነት ነው? የሐዋሪያት ሥራ መጽሐፍን ስታነቡ፣ ይህን ጥያቄ ጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? ሐዋርያት የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከግቡ ለማድረስ ትኩረት ሰጥተው ተወጥተዋልን? ምን ጥርጥር አለው ተወጥተዋል፤ ልትሉ ትችሉ ይሆናል:: ምክንያቱም ወንጌል ወደ እኛ ዘመን ድረስ ስለ ደረሰ፡፡ አንዳንዶችም ደግሞ አይ እንደሚገባ አልተወጡም የምትሉበት ምክንያት ሊኖራችሁ ይችላል፡፡ ቶሎ ድምዳሜ ላይ ከመድረሳችን በፊት፣ ለመሆኑ የተሰጠው ተልዕኮ ምን ነበር? ብለን እንጠይቅ፡፡ በቁጥር 8 ላይ እንደምናገኘው ተልዕኮው እንዲህ ይላል “… መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም፣ በይሁዳም ሁሉ፣ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ” የሚል ነበር ፡፡ ሐዋርያት ወንጌሉን ይዘው ወደ ይሁዳ፣ ወደ ሰማርያና ወደ ዓለም ዳርቻ መውጣት ሲገባቸው፣ እነርሱ ግን ትኩረታቸውን በእስራኤል መንግስት ላይ አድርገው ስለ ነበር፣ በኢየሩሳሌም ከተማ ብቻ ሲሰብኩ ቆዩ፡፡
0 Comments