በባለፉት ወራቶች ከመና የጸሎት መመሪያ ‹‹ዘመንን ስለ መዋጀት፣ ስለ ክርስቶስ ልደት ስለ ትንሣኤውና ወደ አባቱ ስለ መሄዱ ተመልክተን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በ‹‹ወንጌል አላፍርም›› በሚል በተከታታይ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ ተመሥርተን እንመለከታለን፤ ጌታ እንዲያስተምራችሁ በጸሎት ሆናችሁ አንብቡት፡፡
‹‹እመሰክርለታለሁ››
የንባብ ክፍል፡ ማቴዎስ 10
‹‹በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ›› ቁ. 32
በዚህ ዓለም ላይ ሰዎችን ከሚያረካቸው ነገሮች አንዱ ያዩትንና የሰሙትን ለሌሎች መመስከርና ማስተማር ነው፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አዲስ ፍጥረት የሆንን ሁላችን የእርሱ አምባሳደር እንደ መሆናችን መጠን በማንኛውም ጊዜ ስለ ጌታ ያየነውንና የሰማነውን በድፍረት ለመመስከር የተዘጋጀን መሆን አለብን፡፡ የአምላካችንን ማንነት ስንናገር በመጀመሪያ ምስክርነቱ እኛን ያረካና የለወጠን በልምምድም ያለፍንበት መሆን አለበት፡፡ እኛ በሕይወታችን ያልተለማመድነውንና ያላየነውን ለሌሎች ብንመሰክር ምንም የማይጠቅምና በረከት የሌለው ባዶ ቃል ብቻ ይሆናል፡፡ አምላካችን ሰዎች ለሚጠይቁን ምክንያት ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጀን ሆነን መጠበቅ እንዳለብን በቃሉ ተናግሯል፡፡
ያፈቀረን አምላካችን ምንጊዜም ቢሆን ከልብ ከወደድነውና ካፈቀርነው የትም ቦታ ሆነን እርሱን እናከብራለን፤ በእርሱም የምናፍርበት ምንም ምክንያት በሕይወታችን አይኖርም፡፡ በየዕለቱ የአምላካችን ፍቅር በቃልና በኑሮ በሰዎች ፊት ያለፍርሃት መመስከር አለብን፡፡ ለዚህ ሁሉ መሠረቱ እርሱን በሚገባ ማወቅና የመጨረሻ ዓላማችን ምን እንደሆነ ጠንቅቆ መረዳት ነው፡፡ የእርሱ መስካሪዎች ከመሆናችን በፊት የምስክርነቱን ቃል በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡
አንዳንዶቻችን ክርስቲያንነታችን እንዳይታወቅ የምንፈልግ ብዙዎች ነን፡፡ በቤታችን፣ በጎረቤታችን፣ በመሥሪያ ቤታችን… አማኝ መሆናችንን ደብቀን የምንመላለስ እንኖራለን፡፡ አንድ ቀን ግን ትልቅ ፈተና ውስጥ መግባታችን አይቀርም፤ ምክንያቱም ከእምነታችን ጋር የማይስማማ ነገር እንድናደርግ እንጠየቃለን፡፡ በዚህ ጊዜ እምነታችንን ለመግለጽ በጣም ይከብደናል፡፡ አስቀድመን ከገለጽነው ግን ለጊዜው ቢጠሉንም ትልቅ ችግርና መከራ ውስጥ የሚያስገባን አይሆንም፡፡ ስለዚህ እምነታችንን በየትም ቦታ ይሁን ወዲያውኑ እንግለጸው፡፡ በጊዜውም አለጊዜውም ቃሉን ለመመስከር የተዘጋጀን እንሁን፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በሰዎች ፊት እንዳላፍርብህ የድፍረት መንፈስ ስጠኝ፡፡
‹‹ምስክሮች ነን››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 3
‹‹… እርሱን ግን እግዚአብሔር ከሙታን አስነሣው፣ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን›› ቁ. 15
ጴጥሮስ በሚገባ ያውቀው የነበረውን ጌታውን በፍርሃት ተከቦ ‹‹ከየት እንደሆነ አላውቀውም›› ብሎ ቢናገርም፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ልቡን ከሰበረው በኋላ አምላኩን በተለያየ መንገድ ሲያከብረውና በድፍረትም ያለውን ፍቅር ሲገልጽ እንመለከታለን፡፡
ጴጥሮስ ሰማያዊውን ፍቅር በመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ፣ በተረዳ ጊዜ ለአምላኩ ያለ ፍርሃት ለመመስከር ቁርጥ ውሳኔ አደረገ፡፡ በምስክርነቱ ሁሉ ‹‹እኛ ምስክሮች ነን›› ማለት ጀመረ፡፡ ‹‹ትወደኛለህን››? ብሎ የጠየቀውን አምላክ ማንነቱን በድፍረትና በግልጽ ለወገኖቹ ያለምንም ችግር ተናገረ፡፡ ሕይወቱን ፍርሃት አስሮት የነበረው ጴጥሮስ በወገኖቹ መሐል የጌታውን ማንነት ማሳወቅ ጀመረ፡፡
የአምላካችንን ፍቅር በሚገባ ከተረዳን በየትም ቦታ ብንሆን በዚህ ዓለም ላይ እስካለን ድረስ ማንነቱን ከመናገር አንቆጠብም፡፡ ዓላማችንና ተልኮአችን የጌታችንን ፍቅር ሰዎች ሊገባቸው በሚችለው ቋንቋ መመስከር ነው፡፡ ምስክርነታችን ሞቶ መነሣቱን ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ያደረገውን ለውጥ ጭምር መሆን አለበት፡፡ ጴጥሮስ በድፍረት እንዲናገር ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያየውና የተለማመደው ስለነበረ ነው፡፡
እኛም ዛሬ ጌታችን በሕይወታችን ያደረገውን ያለ ፍርሃት ምስክሮች ነን እያልን መናገር አለብን፡፡ ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር ወደ ቤተ መቅደስ ሲሄድ ሳለ፣ በመንገድ ላይ ምፅዋት የሚለምን ሽባ አግኝቷቸው ለመናቸው፡፡ ጴጥሮስ የኢየሱስን ስም በሰጠው ጊዜ ፈውስን እንዳገኘ እናውቃለን፡፡ እኛም ኢየሱስ ለሥጋ ብቻ ሳይሆን የነፍስ አዳኝ እንደሆነ እኛም ምስክሮች መሆን አለብን፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ነፍሴን አድነሃል፣ ለዚህም ምስክር ነኝ፡፡
‹‹በጽናት መቆም››
የንባብ ክፍል፡- የሐዋርያት ሥራ 4
‹‹እግዚአብሔርን ከመስማት ይልቅ እናንተን እንሰማ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት የሚገባ እንደ ሆነ ቊረጡ፤ እኛስ ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም›› ቁ 19
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዐረገ በስድስተኛው ሳምንት በሐዋርያት መካከል ልዩ ሕይወት መታየት ጀመረ፡፡ ብዙ ድንቅና ተዓምራትም በኢየሩሳሌም አካባቢ በገሃድ መታየቱ ለብዙዎች ተረጋገጠ፡፡ ካህናትና አለቆችም በነገሩ በመደናገጥ ለአስተዳደራችንና ለእምነታችን መልካም አይደለም በማለት በሐዋርያት ላይ ምን እናድርግ ብለው ብዙ ከተመካከሩ በኋላ በመጨረሻ እንዳይናገሩ እንዳያስተምሩ አዘዙአቸው፡፡ ከሐዋርያትም መካከል ጴጥሮስና ዮሐንስ በካህናትና በአለቆች ፊት ከሰው ይልቅ የአምላካቸውን ድምፅ መስማትና እርሱን ብቻ መታዘዝ የሕይወታቸው መጀመሪያ መሆኑን ተናገሩ፡፡
ጴጥሮስና ዮሐንስ በሕይወትም በሞትም ቢሆን አምላካቸውን ለማስከበርና ለጽድቅ መቆማቸውን በቃላቸው ገለጹ፡፡ ከሰው ይልቅ እግዚአብሔርን መስማትና መታዘዝ ምርጫቸው እንደሆነ ተናገሩ፡፡ ፍቅሩን፣ ሥልጣኑንና ሰማያዊ ክብሩን እንኳ ሳይቀር ያሳያቸውን አምላክ፣ እነርሱም በፈንታቸው ለእርሱ መታዘዛቸውንና ምን ያህል እንደሚወዱት በቃልና በግብር ገለጡ፡፡
ሐዋርያት ከጴንጤቆስጤ ልምምድ በኋላ እግዚአብሔርን ማክበርና ለእርሱ በጽናት መቆም ምን እንደሆነ ስለ ተረዱ በየሄዱበት በኢየሱስ ስም ድልን እያገኙ ተመላለሱ፡፡ የጌታቸውን ፍቅር የሚሸፍን ምድራዊ ኃይልና ሥልጣን ስላላገዳቸው የአምላካችውን ማንነት ከመናገር አልተቆጠቡም፡፡ ለጽድቅ መሰደድ የተገባቸው እንደሆኑ ቆጠሩ፡፡ ስደቱንም መከራውንም እንደ ሙሉ ደስታ እየቆጠሩ መታዘዝና ለስሙ መቆምን መረጡ፡፡
እያንዳንዱ ክርስቲያን የቆመበትን ዓላማ በሚገባ የተረዳ ከሆነና ለቆመለትም ዓላማ የመጨረሻ ውጤቱ ምን እንደሆነ ከተረዳ የትም ቦታ ይሁን፣ ምንም ዓይነት ችግር ይድረስበት፣ ዓላማውን በጽናት ያንፀባርቅ ይሆናል እንጂ፤ በምንም ዓይነት መንገድ ከቆመለት ዓላማ ሊናወጥ አይችልም፡፡
ጸሎት፡- ጌታሆይ በእምነቴ ጕዞ ሁሉ አንተን እንድታዘዝና ለአንተ በጽናት እንድቆም ጸጋህን አብዛልኝ፡፡
0 Comments