ታላቁ ጠላት

የንባብ ክፍል፡- ዮሐንስ 11፡1-27

‹‹ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፣ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል›› ቁ. 25

የአልዓዛር እህቶች ማርታና ማርያም ወንድማቸው በታመመ ጊዜ፣ ኢየሱስ መጥቶ እንዲፈውስላቸው  መልእክተኛ ወደ እርሱ ላኩ፡፡ ይሁንና ኢየሱስ አልዓዛር ከመሞቱ በፊት ሊደርስላቸው የወደደ አይመስልም፡፡

አንዳንዴ እግዚአብሔር የተመኘነውን ነገር በፈለግነው ጊዜ አያደርግልንም፡፡ እንዲያውም በአልዓዛር ሞት ደስ ተሰኝቶአል (ቁ. 15)፡፡ ስለ ጠላው ወይም እነማርታን ለማሳዘን አልነበረም፡፡ ሆኖም ዓላማ ነበረው፤ ይኸውም የደቀ መዛሙርቱ እምነት ይፀና ዘንድ ነበረ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ጸሎታችንን ያልሰማ በሚመስለን ወቅት እንኳ፣ ለእኛ የተሸለ ነገር እንዳለው መገንዘብ አለብን፡፡

ማርታና ማርያም ወዳሉበት ቢታንያ በደረሰ ጊዜ፣ ‹‹እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ›› ሲል ታላቅ ምስጢር ገለፀላቸው፡፡ እርሱ ከሞት እንደሚነሣና ሌሎችንም ለማስነሣት ኃይል እንዳለው መናገሩ ነው፡፡ ይህንን እውነት ለማስረዳት አልዓዛር እስከሚሞት መዘግየትና ከመቃብር በማስነሣት ኃይሉን ማሳየት ነበረበት፡፡

በመጨረሻም ጌታ ወደ መቃብሩ በመሄድ ‹‹አልዓዛር ሆይ ተነስ›› ሲል ከታላቁ ጠላት ሞት አላቀቀው፡፡ ሞትም የእግዚአብሔርን ልጅ ታዞ አልዓዛርን ፈታው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ኃያል አምላክ ነው፡፡ እርሱ ‹‹ትንሣኤና ሕይወት ነው›› የሚያምንበት ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፡፡

ጸሎት፡- መድኃኒቴ ሆይ፡- ድነትን በዚች ምድር ላይ ብቻ ሳይወሰን ስለ ሰጠኸኝ ዘላለማዊ ተስፋም አመሰግንሃለሁ፡፡

የማርያም ሽቶ

 የንበብ ክፍል፡- ዮሐንስ 12፡1-26

‹‹የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፣ የሚያገለግለኝንም አብ ያከብረዋል›› (ቁ. 26)፡፡

ማርያም ለጌታዋ ያላትን ፍቅር ለመግለጽ ያለ የሌለውን ንብረትዋን በማፍሰስ እግሩን በሽቶ ቀባች፡፡ ባንፃሩ ግን የክርስቶስ ፍቅር ሳይሆን የገንዘብ ፍቅር ያሰከረው ይሁዳ፣ የማርያምን ድርጊት በማውገዝ ተቆጣ፡፡

አንዳንድ ጊዜ በሰይጣን የምንፈተንበት ዘዴ በጣም የረቀቀ ነው፡፡ ይህች ሴት በከበረ ዋጋ ለምትወደው አምላክ የገዛችው ሽቱ በአካባቢ ለነበሩት ሁሉ እንኳ መልካም መዓዛ ነበረ፡፡

በዚህ ድርጊቷ ግን ይሁዳ ተቆጣ፡፡ ዲያቢሎስም የሚቆጣው ሕይወታችን በጨለመ፣ ምስክርነታችን በቀዘቀዘ ጊዜ ሳይሆን፣ ብርሃናችን ሲታይ፣ ጨውነታችን ሲቀመስ፣ ምስክርነታችን ሲጎላ ነው፡፡ በዚህ ወቅት፣ ከጠላት በሚወረወርብን ተስፋ የሚያስቆርጥ አስተያየት ሳንደናገጥ መልካሙን ሽቶአችንን ማፍሰስ አለብን፡፡ መዓዛው የሚያስፈልጋቸው ሞልተዋል፡፡ ለክርስቶስ ያለንን ሁሉ ብንሰጥ፣ ካስፈለገ ሕይወታችንን እንኳ እስከ መሥዋትነት ብናቀርብ አይበዛብንም፡፡

    ‹‹ስለ ክርስቶስ ስም በትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ›› (1ጴጥሮስ 4፡14)፡፡

ከፍርሃት መጠበቅ

የንባብ ክፍል፡- ዮሐንስ 14

 ‹‹ልባችሁ አይታወክ፣ … አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና›› ቁ. 1-2

ደቀ መዛሙርት በክርስቶስ ከእነርሱ መለየት እጅግ በጣም አዝነውና ልባቸው ከብዶ ነበር፡፡ እርሱም ጭንቀታቸውንና ኀዘናቸውን በመረዳት በእግዚአብሔር ታምነው በእምነት ብቻ መቆም እንዳለባቸው ካስተማራቸው ቃል ያስታውሳቸዋል፡፡

ልባችን የእምነት ዙፋን ነው፡፡ ልባችንን በጭንቀት እንዲሞላ መፍቀድ ታዲያ እምነታችን እንዲናወጥ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ፈንታ ዘወትር ልባችን በእምነት፣ በትዕግሥት፣ በሰላም፣ በፍቅር በቃሉ እንዲሞላ መኰትኰት ይገባናል፡፡ ለልባችን ፅናት ዋናው መሠረት በእርሱ መታመን ነው፡፡ በዘላለም አምባ በእግዚአብሔር መታመን ነው፡፡ በአምላካችን በሚኖረን እምነት፣ ማናቸውንም የሕይወት ማዕበልና ዳገት ማሸነፍ እንችላለን፡፡ የትንሣኤው ኃይል ምርኵዛችን ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ችግርና ፈተና ወደሌለበት ዘላለማዊ አገራችን፣ ወዳዘጋጀልን ሥፍራ ለዕረፍት እንገባለን፡፡ እንደ ደቀ መዛሙርት ከጌታ የተማርነውን ረስተን ጭንቀት ውስጥ አንግባ፤ እርሱ አሁንም ሕያው ነው፤ ወዳዘጋጀልን ቤታችን ሊወስደን አንድ ቀን ይመጣል፤ በእምነትና በተስፋ እንጠብቅ፡፡ 

 በብፁዓን መኖሪያ፣ ነዋሪ ርስት አለን፣

 በየሱስ ደም ከዚያ ገብተን እንወርሳለን፡፡

     መስቀሉን ተሸክመን መከራም ታግሠን፣

     አክሊሉን እንድንጭን እንጓዝ ወደሰማይ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *