‹‹በጌታ ውስጥ ራስን ማየት››

 የንባብ ክፍል፡- ኢዮብ 42

 ‹‹መስማትንስ በጆሮ በመስማት ሰምቼ ነበር፤

 አሁን ግን ዓይኔ አየችህ›› ቁ. 5

ኢዮብ ያ ሁሉ መከራ ሲደርስበት ሦስቱ ጓደኞቹ መጥተው ሲያፅናኑት የባሰ ራሱን ፃድቅ አድርጐ እንደ ተመጻደቀ አይተናል፡፡ ጓደኞቹም ‹‹ኃጢአት ሠርተህ ይሆናል›› እያሉ የባሰ እንዲሰበር አደረጉት፡፡ በዚህ ጊዜ ኤሊሁ መጥቶ ኢዮብም ራሱን ስለ ማመጻደቁ ሦስቱንም ጓደኞቹን ስለማይረባ ማፅናናታቸው በሰፊው ወቅሶ ስለ እግዚአብሔርም ታላቅነትና ቸርነት አስረዳቸው፡፡

ቀጥሎም እግዚአብሔር ኢዮብን ተናገረው፤ ለጥያቄውም መልስ እንዲሰጠው ቢጠይቀውም እንዳለፈው ጊዜ ሊናገር አልቻለም፡፡ በኢዮብ 40፡3-4 የሰጠውን መልስ ማየት እንችላለን፡፡ በመጨረሻም ንስሐ በመግባት ራሱን በመናቅና ዝቅ በማድረግ የእግዚአብሔርን ኃይል ብቻ ማየት ጀመረ፡፡ ለጓደኞቹ እንዲጸልይ በታዘዘም ጊዜ ጸለየላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ምርኮውን ቀድሞ በነበረው ፈንታ ሁለት እጥፍ አድርጐ ሰጠው፡፡

እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል ለማወቅ በብዙ መከራ ውስጥ እናልፍ ይሆናል፡፡ በዚህ ጓደኞቻችን እንኳን ፈተና ሊሆኑብን ይችላሉ፡፡ እኛ ግን ለእነርሱ እየጸለይን በትዕግሥት እግዚአብሔርን ብቻ ብንጠብቅ በረከትና ሰላም ሊበዛልን ይችላል፡፡

 ጸሎት፡- ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንክ አሳብህም ይከለከል ዘንድ እንደማይቻል አወቅሁ፡፡ በቃልህና በመንፈስህ ራሴን አይቼ ወደ አንተ በይበልጥ እንድጠጋ እርዳኝ፡፡  

‹‹በሕይወት ቢሆን በሞት››

 የንባብ ክፍል፡- ፊልጵ 1

 ‹‹በሕይወት ብኖር ወይም ብሞት ክርስቶስ

  … በሥጋዬ ይከብራል›› ቁ. 20

ሐዋርያው ጳውሎስ የፊልጵስዩስን መልእክት የጻፈው ከእስር ቤት ቢሆንም፣ በደረሰበት  መከራ ከማጉረምረም ይልቅ ‹‹በሕይወት ቢሆን በሞት›› ክርስቶስን ለማክበር ያለውን ምኞት ይገልጻል፡፡ ብዙ ሰዎች በእምነታቸው ምክንያት ትንሽ ችግር እንኳን ሲደርስባቸው ደስታቸው በኀዘን ይሸፈናል፡፡ መዝሙራቸው በእንጉርጉሮ ይለወጣል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ  ግን ስለ ክርስቶስ የሚደርስበትን ፍዳ ሁሉ የሚያነፃጽረው ከዘላለማዊ ደስታው ጋር፣ ለወንጌል መስፋፋት ከሚያስገኝለት በርና ለክርስቶስ ክብር ከሚያውልበት አጋጣሚ ጋር ነበር፡፡ ስለሆነም ናፍቆቱ ምንጊዜም የአዳኙን ፈቃድ መፈጸም እንጂ፣ ለእርሱ ድሎት ቅድሚያ መስጠት አልነበረም፡፡

ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ የእምነት አርበኞች ሁሉ ራሳቸውን ንቀው ለዚህ እውነት፣ ማለትም ለአምላካቸው ክብር በሰማዕትነት አልፈዋል፡፡ እንደ ሻማ እየነደዱ ሌሎች በብርሃናቸው የዘላለምን ሕይወት ለማየት በቅተዋል፡፡

ሞት በመሠረቱ ለክርስቲያን የሚያስፈራው ጠላት አይደለም፡፡ ሞት በጌታ ላመነ ወደ ዘላለማዊ የዕረፍት ቦታው የሚያሸጋግረው ድልድይና አምላኩን ፊት ለፊት ለማየት የሚያስችለው አጋፋሪ (አስተናጋጅ) ነው፡፡ ይሁንና ክርስቲያን በዚች ምድር ላይ እስካለ ድረስ አዳኙን ለማገልገል ታላቅ ተልዕኮ ያለው ሰው ነው፡፡ ስለዚህም የሰው ልጆችን ወዶ ለተሠዋው ጌታ፣ ዘላለማዊ ተስፋ ላቀዳጀው አምላክ ምስክር በመሆን በሞት ቢሆን በሕይወት ለእርሱ ክብር ይኖራል፡፡

ጸሎት፡- መድኃኒቴ ክርስቶስ ሆይ! በሞት ላይ ድል ስለ ሰጠኸኝና የክብርህ መግለጫ እንድሆን ስለ መረጥከኝ ምስጋና ላንተ ይሁን፡፡

‹‹ለሞትም የታዘዘ ሆነ››

የንባብ ክፍል፡- ፊልጵስዩስ 2፡1-18

‹‹ እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ›› ቁ. 6-7

በ2ኛ ቆሮንቶስ 8፡9 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ጌታ ኢየሱስ ሲናገር፡- ‹‹እናንተ በእርሱ ድኅነት ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለ እናንተ ድሃ ሆነ›› ይላል፡፡ በዛሬው ንባባችን እንዳየነው ደግሞ ከዚህ የጠለቀ ምስጢር እንረዳለን፡፡

ጌታ ኢየሱስ በተፈጥሮ የመለኮት ባሕርይ ተካፋይ የሆነ፣ በመለኮትነት ሥልጣኑም የሚጋፋው የሌለ ጽኑ ነው፡፡ ዳሩ ግን በውዴታው ሥልጣኑን ትቶ፣ ክብሩን ጥሎ (እያለው እንደሌለው ሆኖ) ራሱን ባዶ በማድረግ መጣ፤ ሰው ይሆን ዘንድ ፈቀደ፡፡ እኛን ምስኪን ኃጢአተኞችን ሊያድን ባለጠጋው ደኸየ፡፡ የአገልጋይን መልክና ተግባር ወሰደ፡፡ ራሱን በሰው አምሳል ገለጠ፡፡ በውርደቱ፣ በመስዋዕትነቱና በትህትናው እኛ ሕይወትን አገኘን፡፡ የዓለም ፈጣሪ ሆኖ ሳለ ሰው ሊያገለግል እንጂ ሊረግጥ አልከጀለም፡፡ የአባቱን ፈቃድ መፈጸም እንጂ የግሉን መንገድ አልተከተለም፡፡ ለሰው ልጆች ድነት ሲል ክብሩን ሁሉ ጣለ እንጂ ክብርን በምድር ላይ አልጠየቀም፡፡

አንባቢ ወዳጄ ሆይ፡- እርሱ ይህን ያህል ዝቅ ካለ፣ እኛስ የቱን ያህል ስለ እርሱ ለመዋረድ ፈቃደኞች ነን፡፡

  ጸሎት በመዝሙር፡-   ራስን ዝቅ የማድረግ (3) መንፈስ ስጠኝ ጌታ፡፡     


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *