‹‹የማስታረቅ ኃይል››

 የንባብ ክፍል፡- ኢዮብ 9 

   ‹‹እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር ዳኛ፣

    በመካከላችን ምነው በተገኘ፤ ቁ. 33

ኢዮብ ይህን ቃል የተናገረው መከራና ችግር እንደጐርፍ በከበበው ጊዜ ነው፡፡ ጓደኞቹም መጥተው ‹‹ይህ የደረሰብህ በኃጢአትህ ምክንያት ነው›› እያሉ የባሰ ፈተና ሲሆኑበትና በአምላኩም ላይ የስድብ ቃል እንዲናገርና እንዲበድል ሊያደርጉት ሳለ፤ እርሱ ግን በመፅናት ከመከራውም ብዛት የተነሳ አምላኩን እንዳይበድል በእግዚአብሔርና በእርሱ መካከል የሚሆን ዳኛ ወይም አስታራቂ ምነው በተገኘ ሲል ተናገረ፡፡ ዳኛ ሲል በኢዮብና በእግዚአብሔር መካከል ሆኖ ስለ ሁለቱም አቋም የሚረዳና ወደ ስምምነት አቅርቦ የሚያስታርቅ ማለቱ ነው፡፡

እኛም ዛሬ የክርስትናን ሕይወት ስንከተል ከአምላካችን ጋር እንድንጣላ የሚያደርጉንና የሚገፋፉን ብዙ ጠላቶች አሉብን፡፡ አምላካችንን በማምለካችንም ብዙ መከራና ችግር ሊመጣብን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔርን እንዳንበድል ሊረዳን የሚችል መካከለኛ ዳኛ ሞትን ድል አድርጐ በትንሣኤ የከበረው ክርስቶስ (አምላክና ሰው የሆነው) ብቻ ነው (1ጢሞ. 2፡5)፡፡ በክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት እንችላለን፡፡ ሰውንና እግዚአብሔርን ሊያስተርቅ ሥጋ (ሰው) ሆኖ ወደዚህ ዓለም የመጣ አዳኝ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር የማስታረቅ ኃይል ያለው ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ከአምላክህ ጋር ለመታረቅ ትፈልጋለህን? እንግዲያውስ ክርስቶስ ብቻ አማላጅህ ይሁን፡፡

 ጸሎት፡- ጌታዬ ሆይ በመከራና በችግር ደራሽ አንተ ብቻ ነህ፣ ሁልጊዜ ከእኔ አትለይ፡፡

የትንሣኤው ተስፋ

 የንባብ ክፍል፡- ኢዮብ 13   

‹‹እነሆ ቢገድለኝም እንኳን እርሱን በትዕግሥት

  እጠባበቃለሁ››  ቁ. 15

አንድ ሰው ሌላውን ተስፋ የሚያደርገውና በትዕግሥትም የሚጠብቀው ለመልካም ነገር እንጂ ለከፋ ነገር አይደለም፡፡ ኢዮብ ግን በሞትም እንኳ ቢሆን በተስፋ እንደሚጠብቀውና በትዕግሥት እንደሚቆይ ይናገራል፡፡ ማንም ሰው ቢሆን ሞትን ተስፋ የሚያደርግ የለም፡፡ እንዲያውም ለሰው የመጨረሻው ሞት እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ሰው በምድር ሕይወቱ እስካለ ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይወጣል፣ ይወርዳል ልቡ ያሰበውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ከሞት በኋላ ስላለው ምንም አያስብም፤ ሞትን የመጨረሻው በማድረግ ተስፋ በሌለው የገደል አፋፍ ላይ ተንጠልጥሎ ለጥቂት ጊዜ ይኖራል፡፡ በመጨረሻም ከዚህ ዓለም ያለ ተስፋ ይሄዳል፡፡ በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በዘመድ፣ በጉቦ… ሊመለስ የማይችለው ሞት መጥቶ በግድ እጅ ከፍንጅ ይዞት ይሄዳል፡፡

ኢዮብ ግን ‹‹ብሞትም እንኳ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ በትዕግሥት እጠብቃለሁ›› ብሎ ለመናገር ያበቃው ከሞት በኋላ ያለውን ሕይወት ስለሚያውቅና ስለ ተረዳ ነው፡፡ ሕይወቱን ለእግዚአብሔር ሰጥቶ አምኖ ለሚኖር ሰው ሞት እንቅልፍ ወይም ዕረፍት ሲሆን፣ በሌላም መንገድ ከአምላኩ ጋር የሚገናኝበት ድልድይ ነው፡፡

ለዚህም ማስረጃውና ማረጋገጫው ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱና በአብ ቀኝ መቀመጡ ነው፡፡ ወንድሜ ሆይ አንተስ ዛሬ የትንሣኤውን ኃይል ተስፋ አድገሃልን? የትንሣኤውን ተስፋ ተቀበል፡፡ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለህ ታረጋግጣለህ፡፡

ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ በሕይወት ብኖር ብሞትም ያንተው መሆኔን አስገንዝበኝ፡፡

‹‹የትንሣኤው እውነተኛነት››

 የንባብ ክፍል፡- ኢዮብ 14

 ‹‹በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው

  ይሆናልን?  ቁ. 14

ኢዮብ የጠየቀውን ጥያቄ ሰዎች በዘመናት ሁሉ እየጠየቁ ናቸው፡፡ ዛሬም እንኳን ብዙ ሰዎች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ለማረጋገጥና ከጥርጣሬ ለመውጣት ጥያቄ ይጠይቃሉ፡፡

ከሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ጥቂቶቹ ሰው ለምን ተፈጠረ? የመኖር ጥቅሙስ ምንድ ነው? ከሞት በኋላ ምን ተስፋ አለው? ሰው በእርግጥ እንደገና ተመልሶ በሕይወት ይኖራልን? ለምን እስከ ዛሬ ድረስ የሞቱት አልተነሱም? የሚሉ ናቸው፡፡

ኢዮብ ስለ ሰው ዕድሜ አንስቶ ሲናገር ሳለ ዛፍ እንኳን ቢቆረጥ እንደገና እንደሚያቆጠቁጥ ቅርንጫፉም እንደማያልቅ፣ ግንዱ ቢቆረጥና ቢሞት ሥሩ ከውሃ የተነሣ የለመለመ ተስፋ እንዳለው ይናገራል፡፡

ጳውሎስም ስለ ክርስቲያኖች ትንሣኤና ከትንሠኤ በኋላ ስለሚኖራቸው አካል፣ በቆሮንቶስ መልእክቱ በደንብ ገልጾ እናገኛለን (1ቆሮ. 15 ተመልከቱ)፡፡ እርሱም በበኩሉ ‹‹አንተ የምትዘራው ካልሞተ እንዴት ሊያድግ ይችላል?›› በማለት ስለ ሰው ትንሣኤ ያስረዳል፡፡ የትንሣኤውን እውነተኛነት የሚያረጋግጡ ብዙ ምስክሮች አሉ፡፡ ሐዋርያት  ከአምስት መቶ የሚበዙ ሰዎች እንዲሁም ዛሬ ሕይወታችንን ያዳነን ሰዎች ሁሉ ምሥክሮች ነን፡፡

ለሰው አንድ ጊዜ መሞት፣ ከሞት በኋላ ደግሞ ፍርድ ተመድቦበታል፡፡ ከዚህ ፍርድ ለመዳን ዛሬ በክርስቶስ በትንሣኤው ኃይል ማመን አለብን፡፡ ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለህ አረጋግጠሃልን? ጸሎት፡- ዓይኖቼ የትንሣኤውን ኃይል ከማየት፣ አእምሮዬም ከማስተዋል እንዳይደክም አንተ በመንፈስህ እርዳኝ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *