‹‹በኃያሉ አምላክ እጅ መውደቅ››

  የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 119፡65-80 

      ‹‹በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ›› ቁ .10

 እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፡፡ በዘመናት ሁሉ ያዋረዳቸውን ትዕቢተኞች በመጽሐፍ  ቅዱስና በዓይናችንም ከምናያቸው ብዙ ማስረጃዎችን ማግኘት እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር የእርሱን ማንነትና ኃይል ተረድተውና በደንብ ገብቶአቸው ራሳቸውን አዋርደው ወደ እርሱ ቢቀርቡ ጸጋውንና ምሕረቱን ሊያበዛላቸው ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ እኛም በሥጋችን፣ በነፍሳችንና በመንፈሳችን መቀደስ አለብን፡፡ ያለ ቅድስና እግዚአብሔርን ማየትና የእርሱን ኃይል መለማመድ አይቻልም (1ተሰ. 5፡23)፡፡

በዚህ በንባብ ክፍላችን ንጉሡ ዳዊት ምንም ሳይቸገር ወደ ጥፋት ጐዳና እንዳዘነበለ ይናገራል፡፡ ከአምላኩ ርቆ በኃጢአት መንገድ ከሄደ በኋላ እንደገና ቃሉን እንደ ጠበቀ እንመለከታለን፡፡ በእውነትም በንስሐ በፍጹም ልቡ ቃሉን ይፈልግ ጀመር፡፡ ዳዊት በውድቀቱ በዚያው ሊቀር አልፈለገም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ማን እንደሆነ በደንብ ስለሚያውቅ ከእርሱ እጅ ወጥቶ ለመቅረት አልፈለገም፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ ከወርቅና ከብር ይልቅ እንደሚበልጥበት ስለሚያውቅ ‹‹በፍጹም ልቤ ፈለግሁህ›› በማለት ይናገራል፡፡

ወንድሞችና እህቶች ይህን የክርስትና ሕይወት ጉዞ ከጀመራችሁ ስንት ጊዜ ወድቃችኋል? ወይም ስንት ጊዜ ለመውደቅ ልባችሁ አወላውሏል? እስቲ ትንሽ ጊዜ ከማንበብ ቆም ብላችሁ ፀጥ ባለ መንፈስ ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ ጌታን ብትተውት መውደቂያችሁ የት ነው?

 ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! በትዕቢት ኃጢአት ተይዤ እንዳልበድልህና እንዳልወድቅ እርዳኝ፡፡

‹‹በክንዱ መታመን››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 121 

  ‹‹እግዚአብሔር መውጣትና መግባትህን ይጠብቃል›› ቁ .8

በዓይን አይተው መኖሩን የተናገሩለት ሲጠፋ፣ በልባቸው አምነውት የነበረው ሲከዳቸው፣ በእጃቸው ጨብጠውት የነበረው ሲበን፣ በወረቀትና በቀለም አስፍረውት የነበረው ሁሉ ትርጉም ሲያጣ… በሕይወታቸው ውጣ ውረድ የሚቸገሩ በዓለም ዙሪያ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡

አንድ በጣም የታወቀ የአንድ አገር ፈላስፋ ስለ ሕይወቱ አቋም ተጠይቆ የሚከተሉትን መልስ ሰጥቶአል፡፡ ፈላስፋው ብዙ የተማረና ብዙ ነገር የሚያውቅ ስለነበረ፣ ሰዎች ወደ እርሱ እየመጡ ብዙ ጥያቄዎችን ይጠይቁታል፡፡ እርሱም ለብዙዎች ጥያቄዎች ተጨባጭ የሆነ መልስ ሲሰጥ፣ ስለ ራሱ ሕይወት በተጠየቀ ጊዜ ግን የሚከተለውን አስተማማኝ ያልሆነ መልስ ሰጥቶአል፡፡ ‹‹ቀን ሲሆን እጠራጠራለሁ፣ በሌሊት ደግሞ እጨነቃለሁ›› ሲል ያለበትን ሰላም ያጣ ሕይወቱን ገልጾአል፡፡

መዝሙረኛው ግን ምንም እንኳን በዙሪያው በሚደርስበት ነገር ሁሉ ለማምለጥና ለመሸሽ ወደ ተራሮች በማየት ረዳት ለማግኘት ባይችልም፣ በመጨረሻ ረዳቱ ሰማይና ምድርን ከሠራ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ረዳቱ የማይተኛ የማያንቀላፋ፣ የማይደክም፣ እንደሆነና በቀንና በሌሊት ከክፉ ሁሉ ስለሚጠብቀው መውጣትና መግባቱ፣ መኝታውና ሥራው ሁሉ የሰላም እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ምክንያቱም የሚታመኑ በራሱ ሳይሆን በአምላኩ ክንድ ስለሆነ ነው፡፡ እኛስ?

ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! የጥበቃህን ኃይል በይበልጥ እንድረዳ፣ በክንድህም እንድታመን እምነትን ጨምርልኝ፡፡

‹‹በጸሎት ኃይል ማግኘት››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 143 

 ‹‹እጆቼን ወደ አንተ ዘረጋሁ፣

  ነፍሴም እንደ ምድረ በዳ አንተን ተጠማች›› ቁ.6

አንድ ሰው ወደ ሌላው ሰው ለእርዳታ የሚጮኸውና የሚለምነው ኃይል ወዳለው እንጂ ኃይል ወደሌለውና እርዳታ ለሚያስፈልገው እርዳታ ማድረግ ወደማይችለው አይደለም፡፡

ዳዊት በዚህ ሥፍራ ልጁም አቤሴሎም ባሳደደው ጊዜ ጥበቃና እርዳታ እንዲያገኝ በጸሎት ወደ አምላኩ ሲለምን እናያለን፡፡ ዳዊት ለደረሰበት ችግር ሁለት ነገሮችን አድርጐአል፡፡ ይህም እግዚአብሔር ከዚህ በፊት የሠራለትን ሥራና የእጁን ሥራ ተመለከተ፡፡ በዚሁ ጊዜ የአምላኩን ታላቅነት ስለ ተመለከተ እጆቹን ወደ እርሱ ዘረጋ፡፡

ብዙ ጊዜ የእኛ ችግር ይህ ነው፤ ዝም ብለን ችግራችንን ብቻ ስንመለከት የባሰ ችግር እንፈጥራለን፡፡ በዚህ ፈንታ ኃያሉን ጌታ ማየትና እጅን በጸሎት ወደ እርሱ መዘርጋት አስፈላጊ ነው፡፡ ያን ጊዜ ለችግራችን መፍትሔው ይመጣል፡፡ ስለዚህ እንደ ዳዊት በአምላካችን ኃይል እንድንታመን፣ በእርሱም እንድንማፀን ፈቃዱንም እንዲያስተምረን በጸሎት መጠየቅ አለብን፡፡

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ስንመለከት የእምነት አርበኞች ሆነው ያለፉት የእግዚአብሔር ሰዎች ኃይልን ያገኙት በጸሎት ነው፡፡ በጸሎት እምነትን አገኙ፡፡ በእምነትም ለአምላካቸው በመከራና በችግር ውስጥ ሁሉ ቆሙለት፡፡  የአንበሳን አፍ ዘጉ፤ የእሳትን ኃይል አበረዱ፡፡ ሰንሰለትንም በጣጠሱ፤ እሥር ቤትን አናወጡ፡፡ ይህ ሁሉ በጸሎት የተገኘ ኃይል ነው፡፡ አንተ በጸሎት የተገኘ ኃይል አለህን?

 ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ችግሬን ብቻ እንዳልመለከት፣      መንፈሳዊ ዓይኔን ከፍተህ ኃይልህን አሳየኝ፡፡   


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *