‹‹የእግዚአብሔር በረከት››
የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 103
‹‹ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፣
ጕልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል›› ቁ .5
እግዚአብሔር ስለ ጸጋው ስጦታ አይጸጸትም፡፡ ከጌታ ዘንድ ነፍስን ሞልቶ የሚተርፍ በረከት አለ፡፡ ስለዚህ በድርቀት ሕይወት ውስጥ ያሉ ሁሉ ጌታ የበረከት ጌታ መሆኑን በመረዳት በፊቱ ሲቀርቡ በረከትን ያገኛሉ፡፡ ብዙውን ጊዜ ከእኛ አለመስተካከልና በጌታ ፊት አለመቅረብ እንጂ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስሕተት ተደርጐ አያውቅም፡፡ ‹‹አስቀድሞ ጽድቁንና የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ ከዚያም ሁሉ ይጨመርላችኋል›› የሚለው የጌታ ቃል፣ ከሁሉ በፊት የእግዚአብሔርን መንግሥትና ሰማያዊውን በረከት እንድንሻ ያስተምረናል፡፡
‹‹ጐልማሳነትሽን እንደ ንስር ያድሳል›› ሰማያዊው በረከት የደከመውን ሕይወት ሲያበረታ በድንቅ አኳኋን ነው፡፡ ንስር ከየትኛውም አእዋፍ ይልቅ እጅግ ወደ ከፍታ ሊነጠቅ የሚችል ፍጥነት ያለው ነው፡፡ ጌታ የተሰበረውን ሕይወት ሲጠግን የደከመውን ሲያበረታ በዚህ ዓይነት ነው፡፡ ዛሬ ሕይወትህ ደክሞ ተስፋ ቆርጠህ በጠወለገ ሕይወት ውስጥ ካለህ ጌታ እንዲባርክህ ጠይቀው፤ እርሱም ሕይወትህን ያድሳል፡፡ ለቃሉ ታማኝ ነው፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! ሕይወቴን ታድሰኝና ታበረታኝ ዘንድ በፊትህ ቀርቤአለሁ፡፡
‹‹የተራበችን ነፍስ የሚያጠግብ››
የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 107
‹‹እግዚአብሔር … ከጠላቶች እጅ ያዳናቸው ይናገሩ›› ቁ .22
በዚህ ክፍል ውስጥ የምንመለከተው ስለ እስራኤላውያን ታሪክ ነው፤ ታሪኩም የተፈጸመው በግብፅ ባርነት ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ በጉዞአቸው ሁሉ የተፈጸመውን መውደቅና መነሳት፣ ጩኸትና ዝለት ሁሉ ያሳያል፡፡
መዝሙረኛው በመዝሙሩ ከመጀመሪያ ጀምሮ እስራኤላውያን ያለፉበትን ይገልፃል፡፡ ከግብፅ ባርነት እንዴት እንዳወጣቸው፣ የኤርትራንም ባሕር አሻግሮ በምድረ በዳ እንዴት እንደ መገባቸውና ውኃንም እንዳጠጣቸው፣ በኃጢአታቸውም እየተጨነቁ ወደ እግዚአብሔር ሲጮሁ እንዴት እንዳዳናቸው፣ ከጠላቶቻቸው እጅ እንዴት እንደታደጋቸው ይዘረዝራል፡፡
ዛሬ የሰው ልጅ ትልቅ ችግሩ ምግብ ማጣት፣ በውኃ ጥም መቸገር፣ ትምህርት አለማግኘት እውቀት ማነስም የመሳሰሉት አይደሉም፡፡ ሰው ጤና ከሆነ ሥጋውን በማብላትና በማጠጣት ሊመግብ ይችላል፡፡ ትምህርትና እውቀት የሌላቸው ሰዎች እንኳን ባላቸው ትጋትና ታማኝነት ተቀጥረው ሥጋቸውን እየመገቡ ይኖራሉ፡፡ ሰው ነፍሱ አምላኳንና ቃሉን ከተጠማች ግን በምን ልትረካ ትችላለች?
ጌታ ዛሬም ቢሆን በሥጋም በነፍስም የተራቡትን ሊያጠግብ የተጠሙትን ሊያረካ የተራቆቱትን ሊያለብስ ይችላል፡፡ ለዚህ ግን እኛ አስቀድመን እርሱንና ኃይሉን ልናውቀው ይገባናል፡፡ ለእስራኤላውያን ያደረገ አምላክ እኛም ብንተማመነው ሊያደርግ ይችላል፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! የተራበች ነፍሴን ከቃልህ መግባት፡፡
‹‹በአምላክ ኃይል መታመን››
የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 108
‹‹በእግዚአብሔር ኃይልን እናደርጋለን›› ቁ .13
ዳዊት በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በራሱ ኃይልና ሠራዊት የማይታመንና የማይመካ ነበር፡፡ ስለሆነም በመዝሙር አምላኩን እያመሰገነ አሁንም የእግዚአብሔርን ርዳታ በጸሎት ይጠይቃል፡፡
ዳዊት ጸሎቱንም ሆነ ምሥጋናውን በሚያቀርብበት ጊዜ ልቡ ጽኑ ሆኖ በአምላኩ ላይ የተመሠረተና የቆመ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በአህዛብ መካከልም በድፍረት ለማመስገን የቆረጠ ልብና እውነተኛ ፍቅር እንዳለው ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ዳዊት ለአምላኩ ያለውን ምሥጋና ለመግለፅ ሲል በሕዝብ ፊት በታቦቱ ዙሪያ በጭብጨባና በሽብሸባ የዘለለ ንጉሥ ነው፡፡
ይህንን እንዲያደርግ ያስገደደው አምላኩ ያደረገለትን ታላቅ ውለታ በማሰብ ነበረ፡፡ ከዚህ በፊት ላደረገለት በማመስገን አሁንም ከጠላቶችቸው እንዲያድናቸው ኃይልን ይለምናል፡፡ ያለ እግዚአብሔር መዋጋት ዋጋ እንደሌለው ስለ ተረዳ አምላኩ ከሠራዊቱ ጋር እንዲወጣ ይለምናል፡፡ ቁ .11
እኛም ዛሬ በክርስቶስ ኃይል ካልተማመንን በስተቀር በራሳችን ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ስለዚህም ኃይላችንና ብርታታችን የሆነውን አምላክ እንድናስቀድመው ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ሁሉን ለማድረግ እንደሚችል ከተማመንን፣ እኛ እርሱን ሳንቀድም ሁሉን ከመስቀሉ በታች በማስቀመጥ፣ እንድናስረክበው ያስፈልጋል፡፡ ሁሉን አስረክበን እና ዝም ብንል ኃይሉን ለማየት እንችላለን፡፡ ስንት ነገር በኃይልህ ሞክረህ አቅቶሃል? እርሱን አስቀድመህ፣ አንተ እርሱን እየተከተልህ፣ በጌታ መታመኑ ይሻልሃል፡፡ ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ! በመከራችን ኃይልን ስጠን የሰው ማዳን ከንቱ ነውና፡፡
0 Comments