ሐዋርያት በጌታ የተሰጣቸው ትዕዛዝ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ፣ አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል እንዲጠብቁና በመንፈስ ቅዱስ እንዲጠመቁ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ብዙ የገባቸው አልመሰለኝም፣ ይህን ያልኩበት ምክንያት የሐዋርያት ሥራ 1፡6 ላይ ከትንሣኤ በኋላ ስለ ምድራዊ መንግስት ሲጠይቁት ይታያሉ፡፡ ለነገሩ ባይገባቸውም የሚያስደንቅ አይደለም፣ ምክንያቱም በብሉይ ኪዳን ስለ መንፈስ ቅዱስ ብዙ ተጽፎ የምናገኘውና ግልጽ የሆነ ነገር ባለመኖሩ ነው፡፡ በዘፍጥረት 1፡2 ላይ በውኃ ላይ መስፈፉ፣ በኢዮብ 33፡4 ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጠረኝ ሁሉንም የሚችል አምላክ እስትንፋስ ሕይወትን ሰጠኝ በማለት ከሚናገሩ ጥቅሶችና አልፎ አልፎ በካህናት፣ በነብያትና በነገሥታት ላይ እየመጣ አንዳንድ ሥራዎችን አሠርቶአቸው ከመሄዱ በስተቀር፣ እንደ አዲስ ኪዳኑ ስለ መንፈስ ቅዱስ በስፋት የምናውቀው ነገር የለም፡፡

 አይደለም ስለ መንፈስ ቅዱስ፣ ስለ ሥላሴም ቢሆን ግልጽ ያለ ነገር ያወቅነው በአዲስ ኪዳን ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር በብዙ ቁጥር ሲነግረን ሳለ ሁለት፣ ሦስት፣ አምስት ይሁን አሥር የምናውቀው ነገር የለም፡፡ የአዲስ ኪዳንን ባትሪይ በብሉይ ኪዳን ላይ ስናበራበት ነው ስለ ሥላሴ ሙሉ ትምህርትና ዕውቀት ይሰጠናል ማለት የምንችለው፡፡ የሥላሴ ነገር ቀስ በቀስ እየተገለጠ (Progressive Revelation) የመጣ እውነት ነው፡፡ ብሉይ ኪዳን ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚያስተምረው ትምህርት ግልጽ ቢሆንም ባይሆንም፣ በአዲስ ኪዳን በግልጽ ተቀምጦአል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታላቁን ተልዕኮ በሰጠበት በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28፡18-20 ባለው ክፍል ውስጥ፣ ‹‹… በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ …›› ብሎ ስሞች ሳይሆን ስም ነው የሚለው፣ ጳውሎስም በ2ኛ.ቆሮ.13፡14 ላይ ቡራኬ በሚሰጥበት ጊዜ፣ “የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኀብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን” በማለት በሚናገርበት ክፍል በግልጽ ሥላሴን ማየት እንችላለን፡፡

 ይህ የሚያሳየን መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ አንዱ አካል መሆኑን ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ሆኖ ሳለ ራሱን በሦስት መንገድ ገልጾአል፡፡ የምናመልከው አምላክ አንድ እንጂ፣ ሦስት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በማለት እንጠራቸዋለን፡፡ ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ የሥላሴ አንዱ አካል ከሆነ፣ አምላክ ነው፡፡ አምላክ ከሆነ ደግሞ በየሰው ኪስ የሚከተትና በእጅ መዳፋችን ውስጥ ይዘን የምንበትነው አየርም አይደለም፡፡ እኛ እርሱን የምናዘው ሳይሆን፣ እርሱ እኛን የሚያዘን ነን፡፡ የምንቆጣጠረው ሳንሆን፣ የሚቆጣጠረን፣ የምንመራው ሳንሆን፣ የሚመራን እርሱ ነው፡፡ ስለ መንፈስ ቅዱስ ያለን መረዳት ዋናው የክርስትና ትምህርታችን መሠረት ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስን መለኮታዊነት ከተረዳን፣  በኃጢአታችን ሲወቅሰን ንስሐ ልንገባ፣ ሲመራን ልንመራለት፣ ሲናገረን ልንሰማው እንችላለን፡፡        

እነዚህ ነገሮች በእኔና በእናንተ ሕይወት ምን ያህል ተፈጻሚነት አግኝተዋል፡፡ እኛ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ ሳያስፈልገን ባለንበት ቦታ ሆነን የተስፋውን ቃል፣ ‹‹በመካከላችሁ እገኛለሁ›› ብሎ ተስፋ በገባልን መሠረት ልንቀበል እንችላለን፡፡ ስለዚህ በግልም ሆነ በቡድን ሆነን በበዓለ ሃምሳ ቀን የወረደውን መንፈስ ቅዱስ  እንደ ሐዋርያት መጠመቅና መሞላት ይገባናል፡፡ ያለ መንፈስ ቅዱስ ድነት የለም፤ የኃይል አገልግሎትም የለም፡፡ እነርሱ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ በታዘዙት መሠረት አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል ተቀብለው፣ በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀውና ተሞልተው እንዳገለገሉ ሁሉ፣ እኛም ይህን የተስፋ ቃል ተቀብለን ሕይወት ልናገኝበትና ልናገለግልበት ይገባናል፡፡ ታዲያ! እየተጠቀምንበት ነው? ወይስ እንዳለ እንኳን ሰምተን አናውቅ ይሆን? ወይም የሰዎች ትምህርት ግራ አጋብቶን ሁሉን ነገር ትተን ተቀምጠን ይሆን? አስቡበት:: 

የማንወደደውን ወዶን፣ ከእርሱ የራቅነውን አቅርቦን፣ የተጣልነውን አንስቶን፣ የማንፈቀረውን አፍቅሮን፣ እንዲህ ዓይነት ሕይወት ከሰጠን ጌታን ከልባችን ልናከብረውና ልንወደው፣ ልንገዛለትና ልናገለግለው ይገባናል፡፡ ይህን የተስፋ ቃል ተቀብለን እንደ ዮሐንስ 1፡12 አባባል፣ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው” እንደሚለው ልጅ በመሆናችን ጌታን እናመስግን፡፡ ይህ በሕይወታችን የታየው ለውጥ የመንፈስ ቅዱስ የሥራ ውጤት እንጂ፣ እኛ ያመጣነው ለውጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ ለሕይወታችንና ለአገልግሎታችን ሁልጊዜ የመንፈስ ቅዱስን ድምፅ መስማትና ዕለት በዕለት ኃይሉን መቀበል ይገባናል፡፡  


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *