‹‹የምሕረቱ ብዛት››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 63 

  ‹‹ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላልና

    ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል›› ቁ . 5

የእግዚአብሔርን ምሕረትና ይቅርታ የሚበልጥ ምንም ነገር የለም፣ ሰዎች ይህን ነገር ካላስተዋሉና በሙሉ ልብ ካልተቀበሉት ትልቅ መንፈሳዊ ልምምድ ይጐድላቸዋል፡፡ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ይቅርታና ጸጋ በእውቀት ሳይሆን በሥራ እንዲያውቁት ያስፈልጋል፡፡

ክርስቲያኖች ስላገኙት በረከት ሆነ ኃይል ሊመሰክሩ ይችላሉ፤ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ስለ እግዚአብሔር ምሕረትና ጸጋ የሚናገር በታላቅ ልምምድ ውስጥ ያለፈ ሰው ነው፡፡ ዳዊት ስለምን በብዙ ሥፍራ ስለ እግዚአብሔር ምሕረት ይናገራል? ምክንያቱም ያለፈበት የሞት ሸለቆና ውድቀት ያስገድደዋል፡፡ ዳዊት እግዚአብሔርን አስቀይሞ በዚህ ተጸጽቶ ይቅርታ ሲጠይቅ የጌታን ምሕረት ወዶ ለልቡ ሰላም ለአእምሮው ዕረፍት ሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ ‹‹ምሕረትህ ከሕይወት ይሻላልና ከንፈሮቼ ያመሰግኑሃል›› ይላል፡፡

የእግዚአብሔርን ምሕረት ለማወቅ በኃጢአት ውስጥ መውደቅ የለብንም፡፡ ነገር ግን የምሕረቱን ስፋትና ጥልቀት መገንዘብ የምንችለው በድካማችንና በውድቀታችን ጊዜ ተስፋ ቆርጠን በምንገኝበት ወቅት ነው፡፡ ዛሬ ስለ ጌታ ስታስብ በአእምሮህ ቀድሞ የሚመጣው ምንድን ነው? ድንቆችና ተዓምራቶች ወይስ የጌታ ምሕረት?

ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! የምሕረትህን ጥልቀትና ስፋት እንዳስተውል እርዳኝ፡፡

‹‹መጠጊያዬ››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 71 

 ‹‹አምላክና መሸሸጊያ ሁነኝ፣

  ኃይሌ መጠጊያዬ አንተ ነህና›› ቁ . 3

በእግዚአብሔር መታመን ወይም እርሱን ተስፋ ማድረግ ጌታን ከሚወዱ የሚጠበቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከማስተዋላችንና ከኃይላችን በላይ ስለሆነ በሚገጥመን መከራችን ሁሉ መታመኛችን ነው፡፡

የኑሮን አዘቅት ችግር ለመወጣት በእግዚአብሔር መታመን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔርን በሰላም፣ በበረከት ጊዜ ተስፋዬ እግዚአብሔር ነው ብለን እንናገር ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይህ አባባላችን እውነተኛ መሆኑ የሚረጋገጠው በፈተናና በችግር ውስጥ ጌታን ስንታመን ነው፡፡ በጌታ ውስጥ ስንመላለስ በሕይወታችን ለሚሆነውና በሚደርስብን ‹‹ለምን?›› ብለን ለምንጠይቀው ጥያቄ መልስ አናገኝም፤ ነገር ግን ጌታን በማመን ለጥቅማችን እንጂ ለጉዳያችን እንዳላደረገው በመታመን እንቀበለዋለን፡፡

ሌላው ዳዊት በዚህ ክፍል የሚናገረው እግዚአብሔር መሸሸጊያና መጠጊያ መሆኑን ነው፡፡ ዳዊት ንጉሥ በመሆኑ ሊመካበት የሚገባው ብዙ ሥጋዊ ኃይል ነበረው፤ ሆኖም ከሕፃንነት ጀምሮ ወደ እግዚአብሔር ስላላሳፈረውና አሳልፎ ስላልሰጠው ‹‹ኃይሌና መሸሸጊያዬ አንተ ነህ›› ይላል፡፡ ዛሬ እኔና አንተ እንድንማረውና እንድናውቀው የሚያስፈልገው ተስፋ በቆረጥንና በፈተና ጊዜ የራሳችንን መንገድ ከመፈለግ ወደ እግዚአብሔር መሮጥን ነው፡፡ ያን ጊዜ ጌታ በእውነት መሸሸጊያችንና መጠጊያችን ይሆናል፡፡

 ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! አንተን ተስፋ ማድረግንና መጠጊያ መሆንህን አስተውል ዘንድ እርዳኝ፡፡

‹‹ከእርሱ በስተቀር››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 73

  ‹‹በሰማይ ያለኝ ምንድር ነው ?

   በምድር ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን አሻለሁ?›› ቁ .25

የዚህ ጥቅስ ሐሳብ ሊታወቅ የሚችለው በሚገባ ተተርጉሞ በሚገኘው በመደበኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው፡፡ የመደበኛው መጽሐፍ አነጋገር ይህን ይመስላል፣ ‹‹በሰማይ ከአንተ በቀር ማን አለኝ? በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም፡፡››

ዳዊት በላይ በሰማይ ከእግዚአብሔር ሌላ ሊረዳው የሚችል እንደሌለ ተስፋውና አለኝታው እግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ይናገራል፡፡ የእግዚአብሔርን ታማኝነት ወይም አዳኝነት ስንነጋገር ማወዳደር ያለብን በምድር ካሉት ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን በሰማያት ከሚገኙ ጭምር መሆን አለበት፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕይው እንዳየው ድነትን ለሰዎች የሚሰጥ በሰማያት ካሉት ቅዱሳን ሆኑ መላእክት እንዳቸውም አልቻሉም፣ ድነትን ሊሰጥ የቻለው የሰው ሁሉ አለኝታና ሕይወት የሆነው ጌታ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ ዳዊትም ማወዳደሩን በመቀጠል ‹‹በምድርም ከአንተ ሌላ የምሻው የለኝም››ይላል፡፡ ብዙዎች በማግኘት፣ በመማር፣ ለምድራዊ ክብር ጌታን ለውጠውታል፡፡

አንባቢ ወዳጄ ሆይ፡- ‹‹ዛሬ በምድር ያለው ሀብት፣ ክብርና እውቀት ከጌታ አይበልጥብኝም›› ብለህ እንደ ዳዊት ‹‹በምድርም ከአንተ ሌላ የምመኘው የለኝም›› ብለህ ለመናገር ትደፍራለህን? ጌታ የጊዜያዊ ችግርህ ማጽናኛ፣ ከችግር ወደ ማግኘት መሸጋገሪያ መሰላል ታደርገዋለህን? ወይስ ፍቅሩና ቸርነቱ ይበልጥብኛል ብለህ ከእርሱ ጋር ትኖራለህ? ዛሬ በዚህ ጥቅስ ራስህን መርምር ከጌታም ፍቅር ሊለየኝ ማን ይችላል? ብለህ ለመናገር እንድትችል ጌታ ጸጋውን ያብዛልህ፡፡  ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! የፍቅርህንና የቸርነትህን ስፋትና ጥልቀት አሳውቀኝ፣ በዓለም ምኞት እንዳልወሰድ ጠብቀኝ፡፡         


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *