‹‹የጌታን ክብር ማየት››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 17  

   እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፣

   ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ›› ቁ. 15

በባለፉት ወራቶች ከመና የጸሎት መመሪያ ‹‹ዘመንን ስለ መዋጀትና ስለ ክርስቶስ ልደት በሥጋ ወደ ምድር ስለ መምጣቱ ተመልክተን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የምድር የአገልግሎት ዘመኑን ጨርሶ በትንሣኤ ወደ አባቱ መሄዱን እንመለከታለን፤ ጌታ እንዲያስተምራችሁ በጸሎት ሆናችሁ አንብቡት፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ቅድስና እግዚአብሔርን ማየት እንደማይቻል ይገልጽልናል፡፡ ዳዊትም ስለዚህ ሲናገር ‹‹በጽድቅህ ፊትህን አያለሁ›› ይላል፤ ይህ ጽድቅ ከእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የምናገኘው እንጂ በራሳችን ድካም የምናገኘው አይደለም፡፡ ይህ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የምናገኘው ጽድቅ በእግዚአብሔር ፊት እንድንቆም ያስችለናል፡፡ ይህ ጽድቅ ኃጢአታችንን ሁሉ በመደምሰስ በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ ያቆመናል፡፡

ብዙ ጊዜ በሕይወታችን ድካም ሲይዘን ተስፋ ቆርጠን ወደ ዓለም የምንመለሰው የእግዚአብሔርን ጸጋ ታላቅነት ባለማስተዋል ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ የጌታን ክብር እንድናይ ያደርገናል፡፡ ማንም ሰው የእግዚአብሔርን ክብር ካየ በኋላ እንደ ቀደመው ሊሆን አይችልም፡፡ ነቢያት የእግዚአብሔርን ክብር ባዩ ጊዜ የራሳቸውን ድካም የእግዚአብሔርን ታላቅነት አስተዋሉ፡፡

ዛሬም ክርስቲያኖች ሊረዱት የሚያስፈልግ ዋና ነገር ቢኖር የእግዚአብሔር ክብር ነው፤ በመንፈስ ተሞልተን የጌታን ታላቅነት ለመመስከር የምንችለው ክብሩን ስናይና ስንረዳው ነው፡፡ ከአምና ይልቅ ዘንድሮ የጌታን ታላቅነት አውቀሃልን? ዛሬ በጸሎትህ ጊዜ ቃሉን እያነበብክ፣ አንድ ዋነኛ ዓላማህ ሊሆን የሚገባው የጌታን ክብር ለማወቅና ለማየት መሆን አለበት፡፡

   ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ክብርህን ትገልጥልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ        

‹‹ኃይሉን መታጠቅ››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 18  

 ‹‹ኃይልን የሚያስታጥቀኝ መንገዴንም የሚያቀና

   እግዚአብሔር ነው›› ቁ . 32

ሰባኪያን ‹‹የክርስትና ሕይወት የጽጌረዳ ፍራሽ አይደለም ›› ይላሉ፤ በሌላ አነጋገር ለማስረዳት የሚፈልጉት ክርስትና የሠልፍ የጦርነት ሕይወት መሆኑን ነው፤ ጌታን የተቀበልነው ሰላምን ዕረፍትን ለማግኘት ይሁን እንጂ መንገዱ ለስላሳና ቀላል አይደለም፡፡ ይህን ካለፉበት ቅዱሳን መማር እንችላል፡፡

አንዳንድ ክርስቲያኖች በሸለቆ ውስጥ እንድናልፍ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይመስላቸውም፤ በቁልቁለት ውስጥ ሲያልፉ ሰይጣንን ይከሳሉ እንጂ ‹‹ለምን›› በማለት ትምህርት ለማግኘት አይሞክሩም፡፡ የክርስትና ውበት የሚታየው በሸለቆ ስናልፍ ነው፡፡ ስንወድቅ፣ እግዚአብሔር በጸጋው ደግፎ ሲያነሣን፣ ጠላት እንደ ውሃ ሙላት ሲመጣ፣ ኃይልን ሲያስታጥቀን ያን ጊዜ ኃይልን በሚያስታጥቀን ጌታ ላይ እንታመናለን፡፡

እግዚአብሔር ባሪያዎቹ በፈተና መካከል በወደቁበት ወቅት ጥሎአቸው የሄደበት ጊዜ የለም፡፡ ነገር ግን ባሪያዎቹ ከጌታ ዘንድ ኃይል እንደሌለ ከፈተና የሸሹበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ዛሬም ሆነ ነገ በሕይወትህ የተደቀነውን ፈተና ለማለፍ የምትችለው ኃይልን በሚያስታጥቅህ ጌታ ፊት ስትቀርብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለልጆቹ ኃይልን እንደሚሰጥ በቃሉ ግልጽ አድርጓል፡፡ እስከ ዛሬ ስለ ብዙ ነገሮች ጸልየህ ይሆናል፤ ግን ኃይልን ለመቀበል ጸልየህ ታውቃለህ? ይህን አላደረግህ እንደሆነ፣ ዛሬ አሁን ጌታን ጠይቀው፡፡

 ጸሎት፡- ጌታ ሆይ! ኃይልህ እጅግ ያስፈልገኛልና እባክህ ኃይልህን አልብሰኝ፣ አስታጥቀኝ፡፡

‹‹የዳዊት ልመና››

 የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 27 

 ‹‹እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት

 እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ

 በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣

  እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን አይ ዘንድ፣

  መቅደሱንም እመለከት ዘንድ›› ቁ. 4

 ንጉሡ ዳዊት፣ ብዙ ሀብት ያለው፣ ሰው ሆኖ ሳለ በሕይወቱ አንድ ታላቅ ምኞት ነበረው፡፡ ያ ምኞቱ አስካልተሟላ መንፈሱ እጅግ ይናፍቅ ነበር፤ ይህም በእግዚአብሔር ቤት መኖርን ነበር፡፡ ዛሬ እኔና አንተ እጅግ የምንጓጓው ለምንድን ነው? ትዳር ለመያዝ? ቤት ለመሥራት? መኪና ለመግዛት? ሀብት ለማከማቸት? ወይስ የጌታን ፊት ለማየትና በእግዚአብሔር ቤት ለመኖር? ጌታ ኢየሱስ ሲያስተምር ‹‹አስቀድማችሁ ጽድቁንና የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈልጉ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል›› ይላል (ማቴ. 6፡33)፡፡ እግዚአብሔርን በሕይወታቸው ያስቀደሙ ሰዎች ከመልካም ነገር ጐድለው አያውቁም፡፡ ዛሬ በሕይወትህ ጌታን ብታስቀድም፣ እርሱ ስሌላው ያስባል፡፡

ዳዊት በእግዚአብሔር ቤት መኖር የሚፈልገው እግዚአብሔርን ለማየት ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ለማየትና ለማወቅ ነው፡፡ በሕይወትህ ጌታን ደስ የሚያሰኘው ምንድን ነው ብለህ ጠይቀህ ታውቃለህ ጌታን በሕይወትህ ስትቀበልና የሕይወትህ መሪ ስታደርገው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ፈጽምህ ማለት ነው፡፡ ከዚያም ጌታ በሕይወትህ የጀመረውን ሥራ ከፍጻሜ ያደርሰዋል፡፡  ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ! እስከ መጨረሻው ጸንቼ በቤትህ እኖር ዘንድ እርዳኝ፡፡    


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *