‹‹የተነገረው ትንቢት››
የንባብ ክፍል፡- ኢሳይያስ 9፡1-7
‹‹ስሙም… የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል›› ቁ.6
ስለ ኢየሱስ ከተነገሩት ትንቢቶች አንዱ ሰላምና ፍርድን በምድር ላይ የማምጣት ችሎታው ነው፡፡
አንድ ሰው የዓለም ካርታ የተሳለበትን አንድ ወረቀት ቆራረጠና ቁርጥራጮቹን እንዲያገጣጥማቸው ለልጁ ሰጠው፡፡ ሥራው ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ስለገመተ ልጁ ተዝናንቶ እንዲሠራ ለብቻው ተወው፡፡ ነገር ግን በጥቂት ደቂቃዎች ቁርጥራጮቹን በትክክል በማገጣጠም ወደ አባቱ አመጣ፡፡ ‹‹እንዴት በፍጥነት ልትሠራው ቻልክ?›› ብሎ አባቱ ጠየቀው፡፡ ልጁም ‹‹ከዚህ የዓለም ካርታ በስተ ጀርባ የአንድ ሰው ፊት ሥዕል አለ፡፡ የዚያን ሰው ምስል በትክክል ስሰበስብ የዓለም ካርታው በትክክል ሊገጥም ቻለ›› ሲል መለሰ፡፡
ዓለማችን በጦርነት፣ በጥላቻ፣ በዝብርቅርቅነትና በሕገወጥነት ተሞልታለች፤ በሺህ በሚቆጠሩ ቁርጥራጮች ልትመሰል ትችላለች፡፡ የዓለም መሪዎችና ገዢዎች የተሰባበሩትን ነገሮች ሁሉ በሰላም ስምምነትና ጉባኤዎች በማገጣጠም መፍትሔ ሊያገኙለት እጅግ ይጥራሉ፡፡ ከሺህ ዓመታት በፊት በእግዚአብሔር የተነገረ አንድ የማያዳግም መፍትሔ ብቻ አለ፡፡ መፍትሔውም ‹‹የሰላሙ አለቃ›› ነው፡፡ ሰዎች የኢየሱስን ፊት በመመልከት የተቆራረጠውን ለማጋጠም ቢሞክሩ ውስጣዊና ውጫዊ ሰላም ያገኛሉ፤ መፍትሔው ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡
ይህ የተነገረው ትንቢት ወደ አንተ፣ አንቺ፣ እናንተ ደርሷል? ካልደረሰ ዛሬውኑ ተቀበሉ፣ ጊዜ አትስጡት፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ትንቢት የተነገረለት ጌታ ወደ ልቤ እንዲገባ እርዳኝ፣ ልቤን ክፈትልኝ፡፡
‹‹የወደፊቱ ሲገለጽ››
የንባብ ክፍል፡- ኢሳይያስ 61፡1-11
‹‹የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው›› ቁ.1
‹‹ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፣ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፣ ለተማረኩትም ነፃነትን፣ ለታሠሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል›› በማለት ወደፊት የሚሠራውን ይናገራል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ውጤት በእነዚህ ድንቅ ቃሎች ተገልጾ ነበር፤ በአዲስ ኪዳንም የኢየሱስን ፈለግ ስንመለከት ሕይወቱና ሥራው ሁሉ በትክክል እንደ ተገለጸ እናያለን፡፡ አዳኛቸው መሆኑን ሥራው እንዲመሰክር አደረገ እንጂ ለአይሁዶች ክርክር አላቀረበላቸውም፡፡ የመለኰትነቱ ማረጋገጫ የዕለት ኑሮውና አረማመዱ ነበር፡፡ ስለ እርሱ የተገለጸው ነገር ሁሉ በእስራኤል ምድር ዙሪያ በሚያደርገው ነገር ግልጽ ሆኖ ይታይ ነበር፡፡
ክርስቲያን ወዳጄ ሆይ! የኢየሱስ መሆናችንን ለዓለም እንዴት እናሳያለን? አንዳንዶች የቤተ ክርስቲያን አባልነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን መንገዱ ያ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርና ዓለም ክርስቲያንነታችንን በዕለታዊ ኑሮአችን እንድንገልፀው ይጠብቁብናል፡፡ ኢየሱስ በዕለታዊ ኑሮው የተመረጠ የእግዚአብሔር ምስክር መሆኑን አሳየ፤ ለእኛም ያለን መንገድ ይህ ብቻ ነው፡፡ ለክርስቶስ ምስክር መሆን ፈለጉን በመከተል መራመድ ማለት ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን በነቢያቶች ወደፊት የሚሠራው ተገልጦ ከ700 ዓመት በፊት የተነገረው ትንቢት የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች በግልጽ መፈጸሙን ያሳዩናል (ሉቃ.4፡19-21)፡፡ እኛ በተፈጸም ትንቢት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡ ወደ ፊት የምንጠብቀው ትንቢት ቢኖር ዳግመኛ መምጣቱን ነው፡፡ ጌታ ሲመጣ እርሱን ፊት ለፊት ለማየት እንድንችል ዛሬ በቃሉ ታምነን እንመላለስ፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በአንተ የተገለጠ ጸጋ በእኔም እንዲገለጥ አርዳኝ፡፡
‹‹ኢየሱስ በምድረ ግብፅ››
የንባብ ክፍል፡- ማቴዎስ 2፡7-23
‹‹እነሆ የጌታ መልአክ …ተነሣ ሕፃኑንና እናቱንም
ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፣ እስክነግርህም ድረስ
በዚያ ተቀመጥ አለው፡፡ ቁ. 13
እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ለዮሴፍ ታየ፡፡ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ለማየት ወደ ተወለደበት በረት መጡ፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም ንጉሥ ሄሮድስ በኢየሱስ ላይ ያሰበውን ክፉ ተነተኮል ሊረዱና ዮሴፍን ሊያስጠነቅቁት አልቻሉም፡፡ በዚህን ጊዜ ከሰማይ የመመሪያ ቃል መጣ፡፡ ስለሆነም ሰውም ሆነ ሰይጣን እግዚአብሔር የእርሱ ምስክር አድርጎ ወደዚህ ዓለም ስለ ላከው ስለ ኢየሱስ ያለውን ዕቅድ ሊያግደው አልቻለም፡፡
በዓለም ላይ ያለው አደጋ ከሰው ዓይን ቢሰወርም፣ ሠፊዋን ዓለም በእጁ ያደረገ አምላክ መኖሩን ማወቅ ታላቅ መጽናናት ነው፡፡ ምናልባት አንዳንዶች ይህን በሚመስል የሕፃንነት እምነት ይበቁ ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን እውነት ሁሌ ትኖራለች፡፡ እኛ ራሳችን በሙሉ ልባችን በመንገዱ ለመሄድ ብንፈቅድ ምንም ወይም ማንም የእግዚአብሔር ዓላማ በሕይወታችን እንዳይፈጸም ሊያግድ አይችልም፡፡ የእኛ ተግባር ከሰማይ የሚመጣልንን ቃል መስማት፣ መረዳትና መታዘዝ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ሁልጊዜ ለኛ ሕይወት ጥቅም መሆኑን አስታውስ፡፡ ጸሎት፡- ጌታ ሆይ እንደ ፈቃድህ የሆነ ፈተና ለጥቅሜ እንደሆነ እንድረዳ እርዳኝ፡፡
0 Comments