‹‹የሐና ውዳሴ››
የንባብ ክፍል፡- 1 ሳሙኤል 2፡1-10
‹‹የመሲሁንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል›› ቁ.10፡፡
በጥንቱ እስራኤላውያን ባሕል የታመመ ሰውና ልጅ ሲወለድ የምሥጋና ጸሎት ማቅረብ የተለመደ ነበር፡፡ ሕዝቅያስ ከሞት አፋፍ ሲመለስ የምሥጋና ጸሎቱን ደርድሯል (ኢሳ 38፡10-20)፡፡ በዛሬው የንባብ ክፍል የምንመለከተው ሐና ሳሙኤልን በወለደች ጊዜ ያደረገችውን የምሥጋና ጸሎት ነው፡፡
ሐና ለብዙ ዘመን መካን ነበረች፤ ጣውንትዋ በመካንነትዋ ታበሳጫት ስለ ነበረ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሄዳ የልቧን በማፍሰስ ጸለየች (1ኛ ሳሙ.1፡10)፡፡ እግዚአብሔር ጸሎቷን ሰምቶ ልጅ ሲሰጣት ዝም ለማለት አልቻለችም፡፡ ‹‹ልቤ በእግዚአብሔር ፀና ቀንዴም በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ›› አለች፡፡ እግዚአብሔር ጸሎትዋን ሰምቶ ከፍ ከፍ ሲያደርጋት ያገኘችው ልጅ ለጌታ አገልጋይ እንዲሆን ሰጠች፡፡
የሐና ጸሎትና አድራጐት በጐ ለሚያደርግ አምላክ ምን ማድረግ እንደሚገባን ያስተምረናል፡፡ እርሱ ተስፋ የሚያደርጉበትን ሁሉ አያሳፍርም፡፡ ሐና በምሥጋና በተሞላችበት ጊዜ ‹‹በማዳንህ ደስ ይለኛል›› ብላ ትንቢታዊ ቃል ትናገራለች፡፡ እኛም ዛሬ ብዙዎች ሊያዩትና ሊሰሙት የተመኙትን የድነታችን መሠረት አግኝነተዋልና እንደ ሐና ‹‹ ቀንዴ ከፍ ከፍ አለ በማዳንህ ደስ ብሎኛል›› ለማለት እንችላለን፡፡
ጸሎት፡- ‹‹እግዚአብሔር ሆይ፤ ማዳንህን ስላሳየኸን እናመሰግንሃለን››
‹‹ከድንግል የመወለዱ ተስፋ››
የንባብ ክፍል፡- ኢሳይያስ 7፡14
‹‹እነሆ፡-ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች››፡፡
የሰው ልጅ በኃጢአት ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ ብዙ ጊዜ ስለ ክርስቶስ መሞጣት ተስፋ ሰምቷል፡፡ የኤደን ገነትን ሲለቅ የእባቡን ጭንቅላት የሚቀጠቅጥ እንደሚመጣ እግዚአብሔር ነግሮታል፡፡ የዛሬው የንባብ ክፍል ኢየሱስ ከመወለዱ ከ700 ዓመታት በፊት የተተነበየ ትንቢት ነው፡፡ በዚህ ክፍል ኢየሱስ ከድንግል ስለ መወለዱ ተገልጦአል፡፡ የሰው ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰማው ተስፋ ውስጥም ‹‹የሴቲቱ ዘር›› የሚል ቃል ነበር፡፡ ይህም የኢየሱስ መወለድ ከወንድ ፈቃድ (ከወንድ ዘር) ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መሆኑን ያስረዳል፡፡
አዲስ ኪዳን ይህ እውነት ተፈጽሞ ኢየሱስ ከድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ተጸንሶ መወለዱን ያሳያል፡፡ ይህ ተስፋ በተፈጸመ ጊዜ የድነታችን መንገድ ተስተካከለ፡፡ ዘላለማዊ ጌታ በሰው ሥጋ በሰዎች መካከል አደረ፡፡ እስከ መስቀል ሞት ተጉዞ የአዳም ልጆችን ሁሉ ከኃጢአት ባርነት አላቀቀ፡፡ መላው የሰው ዘር ‹‹ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል ትርጓሜውም እግዚአብሐር ከእኛ ጋር ነው›› በሚለው ተስፋ መፈጸም ተባረከ፡፡
ዛሬ ከድንግል የመወለዱ ተስፋ ወደ እኛ ደርሶአል? ተስፈው ከደረሰ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፤ ያ ቀድሞ የነበረ፣ ሁሉ በእርሱና ለእርሱ የተፈጠረው መጥቷል፤ አብሮን ይኖራል ኦ! አማኑኤል!!
ጸሎት፡- ‹‹ሁሉን የምትችል ጌታ ሆይ!! ቃል ኪዳንህን ስለማትረሳ እናመሰግንሃለን፤ አሜን››፡፡
‹‹እርሱ ብቻ ታላቅ››
የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 1፡26-37
‹‹…ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና
ስሙም ቅዱስ ነው›› 2፡49
ሰዎች በተፈጥሮ ባለ ዝናና ገናና መሆንን ይወዳሉ፤ ጥቂቶች ጊዜያዊ ዝና ቢያገኙም ታላቅ መባላቸው ለዘላለም አይቆይም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ታላቅነት ግን ዘላለማዊ ነው፡፡ መልአኩ ለማርያም ባበሠረው ቃል ውስጥ ‹‹ታላቅ ይሆናል›› ብሎ ተናግሯል፡፡ ነቢያትም ከቀድሞ ጀምሮ ‹‹እግዚአብሔር ራሱ ታላቅ የሆነውን ይልክላችኋል›› ብለው ጽፈዋል(ኢሳ. 19፡20)፡፡
ሶቅራጥስ ታላቁ ፈላስፋ 40 ዓመት በምድር አስተምሯል፡፡ እንደዚሁም ፕላቶ ለ50 ዓመት ሲያስተምር፣ አሪስጣጣሊስ ደግሞ 40 ዓመት አስተምሯል፡፡ ክርስቶስ ግን ያስተማረው ለ3 ዓመት ተኩል ብቻ ነበር፡፡ ቢሆንም እነዚያ ፈላስፎች በአንድ ላይ ያስተማሩትን የ130 ዓመት አገልግሎት፣ የእኛ ጌታ የ3 ዓመት ተኩል ትምህርት ይሸፍናቸዋል፡፡ ሰዓሊዎች፣ ሙዚቀኞች፣ ባለቅኔዎች፣ ተናጋሪዎችና ጸሐፊዎች ሁሉ የክብሩን አንፀባራቂነት ገልጾውታል፡፡ ኢየሱስ ለዓለም ሕዝብ የሰጠው ባዶ የፍልስፍና ቃላት ሳይሆን ድነትን ያጐናጸፈንን መሥዋዕት ራሱን ነበር፡፡ ኃጢአትንና ሰይጣንን በመስቀሉ ላይ ወግቶ ነፃ አደረገን፡፡ እንደ እርሱ ታላቅ ማንም የለም፡፡
ዛሬም ከድንግል የመወለዱ ተስፋ ለእኛ ነው፤ በዓለም ላይ ከእርሱ ሌላ ታላቅ የምናደርገውና የምናመልከው፣ የምንሰግድለትና የምንገዛለት ማንም የለም፤ ሞታችንን ሞቶ ሕይወት የሰጠን፣ ታላቁ አዳኛችን እርሱ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ሐና ልናወድሰው ይገባናል፡፡ ጸሎት፡- ኦ! ጌታችን ሆይ!! ያንተ መሆን ምንኛ ታላቅ ደስታ ነው፤ የኛ ጌታ ነህና ስምህን እናወድሳለን፡፡
0 Comments