የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 1፡57-66

  ‹‹አፉ ተከፈተ መላሱም ተፈታ እግዚአብሔርንም

    እየባረከ ተናገረ›› ቁ.64

‹‹አስደናቂ ነገሮች በዓለም ላይ›› በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ስለ አንዳንድ አጋጣሚና እንግዳ ነገሮች መፈጸም ይገልጻል፡፡ ለምሳሌ ያህል፣ በ57 ዓመታቸው የመጀመሪያ ልጅ ስለ ወለዱት ስለ አንዲት ሴት ያወራል፡፡ እንደዚሁም የዮሐንስ መወለድ በጊዜው ለነበሩ ሰዎች እጅግ አስደናቂ ነበር፡፡ ሆኖም በዚህ ዕድሜያቸው ቤተሰቡ ዮሐንስን መውለዳቸው አጋጣሚ ሳይሆን በእግዚአብሔር ዓላማ ሥር ነበር፡፡ አባቱ የተላከውን የእግዚአብሔርን መልእክተኛ ባለማመኑ ዲዳ ሆኖ ነበር፡፡ የሰው አስተሳሰብ በስተ እርጅና መውለድ አይቻልም የሚል ነውና፡፡

ነገር ግን ዮሐንስ ተወለደ፤ ዮሐንስ ከተወለደ በኋላ ስም እንዲወጣለት አባቱን ጠየቁት፣ አባቱም ‹‹ዮሐንስ›› ብሎ ስም ሲያወጣ አፉ ተከፍቶ መናገርም ጀመረ፡፡ የነበሩትም ሰዎች እግዚአብሔርን አከበሩ፡፡ ዛሬም ደግሞ እግዚአብሔር ከመንፈስ በሚወለዱና ንስሓ ገብተው የጽድቅን መንገድ በሚከተሉ ይከብራል፡፡ የጌታም እጅ ከዮሐንስ ጋር እንደነበረች፣ ከእነዚህም ጋር ይሆናል፡፡

 ዛሬም በእኛ መዳን እግዚአብሔር ይከብራል፤ ወላጆቻችንም ከተለያየ የመጠጥ፣ የሲጋራ፣ የሐሺሽና የኃጢአት ሱስ በመላቀቃችን ጌታን ባይቀበሉትም፣ ስለ እኛ መለወጥ እፎይ ብለው ጌታን ያመሰግናሉ፡፡

‹‹የጌታ ስም ብሩክ ይሁን፣ እኔን የተቀበለኝ፤

በደሌን ይቅር ብሎኛል፣ ከኃጢአት አንጽቶኛል››፡፡

‹‹ክርስቲያናዊ ግዴታ››

 የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 3፡3-14 

 ‹‹የጌታን መንገድ አዘጋጁ፣ ጥርጊያውንም አቅኑ›› ቁ.3

በዮሐንስ መጥምቁ ዘመን ኅብረተ ሰቡ በኃጢአት ምክንያት ከአምላኩ ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከመሰሉም ጋር ኅብረት አልነበረውም፡፡ በሐሰት መክሰስ፣ ግፍ መሥራት፣ ጉቦ መቀበልና ድሆችን ችላ ማለት የዕለት ተግባር ነበር፡፡ ታዲያ ይህንን ኅብረተሰብ ከአምላኩ ጋርና ከመሰሉ ማለትም  ከወንድሙ ጋር ለማስታረቅ ራሱን የሰጠ አገልጋይ ያስፈልግ ነበር፡፡ ብዙ ውጣ ውረድን የሚጠይቅ ከባድ ሥራ ነው፡፡

መሥዋዕትነትም ከራስ የሚጀምር ነው፤ የሚሉትን ሆኖ መገኘትና በምሳሌነት መኖርን የሚጠይቅ ነው፡፡ በጊዜው ዮሐንስ መጥምቁ ነበር፤ ዮሐንስ ሁለት ዓይነት መልእክት ነበረው፡፡ ሰው ከአምላኩ ጋር እንዲታረቅና እንደሁም ከወንድሙ ጋር እንዴት መኖር እንደሚገባው ማመልከት፡፡ ታዲያ ከዮሐንስ ብዙ ጠይቆበታል፤ አደራውን ግን በድል ጠብቋል፡፡ ጳውሎስም በመልእክቱ አክሪጳን ሲመክር ‹‹በጌታ የተቀበልኸውን አገልግሎት እንድትፈጽመው ተጠንቀቅ›› ይላል፡፡

ዘማሪው፡-‹‹ቃሉን ጠማን ብለው በጣም ይጮሃሉ፣

    ድረሱልን ዛሬ ነፃ አውጡን ይላሉ፣

    የመስካሪ ያለህ ፈጥናችሁ ኑ ሲሉ፣

    እንሂድ እንድረስ በእሳት አይበሉ››፡፡ 

‹‹መጠራጠር››

 የንባብ ክፍል፡- ማቴዎስ 11፡1-6

  ‹‹የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ?››

የሰው ሕይወት ከአዳም ውድቀት አንስቶ በጥርጣሬ የተሞላ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰው አምላኩን ተጠራጠረ፡፡ እንደገናም በአዲስ ኪዳን ቶማስ የጌታን መነሣት ስላላመነ ካልዳሰስኩት አላምንም እስከ ማለት ደርሶ ነበር፡፡ ጥርጣሬ የእምነትን ሥር የሚበላ የእንጨት ምስጥ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ብርቱ አይደለምና መጥምቁ ዮሐንስም በትንቢት የተነገረለት ይህ ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ የክርስቶስን የድነት ወንጌል ሥራ ይጠባበቅ ነበርና በዓይኑ ስላላየ እስር ቤት ስለነበር አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ? ብሎ ተማሪዎቹን ላከ፡፡ በእርግጥ ይህንን ጌታ አምኖ ነበር ሲሰብክና ሲያስተምር የነበረው፡፡ አዎን ለጥርጣሬው ሁለት ምክንያቶች ነበሩ፤ የራሱ አመለካከትና የአካባቢው ድምፅ፡፡

በማቴዎስ 3፡11-12 እንደ ተገለጸው ለፍርድ የሚመጣው መሲህ ስንዴውን ከእንክርዳድ ለመለየትና ወዲያው ፍርድ ለመስጠት መስሎት ነበር፡፡ ጌታም በተዘዋዋሪ መንገድ መለሰለት፡፡ የእግዚአብሔርን መኖርና ከእርሱ ጋር የመሆኑ ምልክቶች ማለትም የሰዎችን አካል መፈወስና መልካሙን የምሥራች ወንጌል መስበክ ከተቀባው ሌላ እንደማያደርግ መለሰለት፡፡ ዮሐንስም በመልእክቱ ታድሶ፣ ለተጠራጠረው ጌታ አንገቱን ሰጠ፡፡

እኛም የተረዳነውን እውነት ሳንጠራጠር፣ ክርስቲያናዊ ግዴታችንን በመወጣት መልካም ምሳሌዎች በመሆን እግዚአብሔርን እናክብር፡፡

 ጸሎት፡- ‹‹ጌታ ሆይ እንዳልሰናከል የቃልህን ብርሃን ግለጥልኝ››፡፡

‹‹ጌታን ማስከበር››

የንባብ ክፍል፡- ማቴዎስ 14፡12 

  ‹‹… እርሱ ከሙታን ተነስቷል››

በአንድ ሀገር ውስጥ ክርስቲያኖች ይሰደዱና ቀንደኛ የተባሉትም ተይዘው ይጐሳቆሉ ነበር፡፡ ኃይለኛ ቅዝቃዜና በረዶ የክረምት ወር መግባት ምልክቱ ስለሆነ ሰው ሁሉ ወደ ጉዳዩ ሲሄድ፣ ያለውን ልብስ ደርቦ ነው ከቤቱ የሚወጣው፡፡ እነዚህ ግን ጌታን በማመናቸው ብቻ ከበረዶ ላይ ያለ ልብስ ተጥለው ያመኑትን እንዲክዱ ይጠየቁ ነበር፡፡ ብዙ ሰዓቶችም አለፉ፤ ወታደሮችም ተለዋወጡ፡፡ በመጨረሻም ከአማኞቹ አንዱ ሥቃዩን አልቻለም ነበርና ይጠብቀው የነበረውን ዘብ ጠርቶ ‹‹እባክህን ሥቃዩን አልቻልኩምና ጌታን እክደዋለሁ እንዲለቀኝ ለሚመለከተው አመልክትልኝ›› አለው፡፡ ዘቡም የሁሉም ሐሳብ እንደሆነ ጠየቃቸው፡፡ ሌሎቹ ግን በእምነታቸው እንደሚጸኑ ነገሩት፡፡ ዘቡም መልሳቸውን ሰምቶ በጣም ካዘነ በኋላ ‹‹እምነቴን አክዳለሁ›› ላለው ክርስቲያን የማዕረግ ልብሱን አልብሶ በምትኩ ገባ፡፡ ዘቡ ጌታን አምኖ በብርዱና በቅዝቃዜው ሥቃይ ሞተ፡፡

ዮሐንስ ጌታን ያሳወቀ ፅኑ አማኝ ነበር፤ አገልገሎቱ ‹‹በፍሬያማነትና ጌታን በማስከበር›› አብቅቶአል፡፡ ስለዚህ ነበር ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና በሰማ ጊዜ የገደለው፡፡ ዮሐንስ መስሎት፣ ዮሐንስ ከሞት ተነሣ ወይ ያለው፡፡ አገልግሎቱ ሞትን ቢጠይቅበትም እግዚአብሔርን አስከብሮ አልፎአል፡፡  ጸሎት፡- ‹‹ጌታ ሆይ ዮሐንስን አድርገኝ አልልህም፤ ነገር ግን እርሱ የነበረውን ፅናት በእኔ አኑር››፡፡       


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *