‹‹የጥበብ ድምፅ››
የንባብ ክፍል፡- ምሳሌ 8፡1-36
‹‹እናንተ አላዋቂዎች፣ ብልሃትን አስተውሉ፤
እናንተም ሰነፎች፣ ጥበብን በልባችሁ ያዙ›› ቁ. 5
ጥበብ ትጣራለች፤ የሚያገኛትም ሕይወትን ያገኛል፡፡ እግዚአብሔርም ያጸድቅለታል፡፡ ጥበብ ከፍጥረትና ዓለም በፊት በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረች፡፡ እኛ የምንኖርባት ዓለም እግዚአብሔር በጥበቡ ያዘጋጃትና የሠራት ነች፡፡ እግዚአብሔር የጥበብ ቃል ሲናገር ዓለም ወደ መኖር መጣች፡፡
የኢየሱስ አነጋገር በጥበብ የተሞላ ነበር፤ ጥበብን በሚገልጽበት ጊዜ ምን አደረገ? አስተማረ፤ የታመሙትን ፈወሰ፤ ከአጋንንት ኃይል አላቀቀ፤ ለኃጢአታችን ሞተ፤ ለጽድቃችን ተነሣ፤ ወደ አባቱ ወደ አብ ቀኝ ዐረገ፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው የእግዚአብሔርን ጥበብ ትልቅነትና ኃይል ነው፡፡ ጥበብ ድምፅ ካላት የእርሱ ድምፅ ነው፡፡ እኛም ድምፁን መስማት ይጠበቅብናል፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ሁልጊዜ ስትናገረኝ ድምፅህን ልስማ፣ ለምትናገረኝም ቃል መረዳትን ስጠኝ፡፡
‹‹የመለኰታዊ ጥበብ ውድነት››
የንባብ ክፍል፡- ሮሜ 11፡25-36
‹‹የእግዚአብሔር ባለ ጠግነትና ጥበብ እውቀቱም
እንዴት ጥልቅ ነው›› ቁ. 33
የእግዚአብሔር ትልቅ ጥበብ በወንጌል ውስጥ ተገልጾአል፤ ከዚያም የሚበልጥ ጥበብ የለም፡፡ እግዚአብሔር ካለፉት ዘመናት በፊትና ከሚመጡት ዘመናት በኋላ ያለውን ጊዜ ተመልክቶ፣ ዓለም ከመፈጠሯ በፊት ስለ ታረደው ኢየሱስ ሊናገር የሚችል እርሱ ብቻ ነው፡፡ የእርሱ መንገዶች እርሱ ካልገለጻቸው በስተቀር ፈልገን የማናገኛቸው ናቸው፡፡ እርሱ ለመደበቅ ካሰበ የጌታን ሐሳብ ፈልገን ለማግኘት አንችልም፡፡ በክርስቶስ እንዳደረገው ራሱን ሊገልጽ ሲፈልግ እኛ እንዳንመለከተው ልንከለከል እንችላለን፡፡
‹‹ሁሉ ከእርሱና በእርሱ ለእርሱም ነውና›› ሟች ሰው ትልቅ ነገር ለማድረግ በራሱ ይመካል፤ ነገር ግን ትምክህቱ ባዶ የሆነ ድምፅ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የተናገረውን ቃሉን ለመፈጸም ኃይልና ሥልጣን የለውም፡፡ እርሱ ያለውና እግዚአብሔር የሚፈልገው በአንድ ላይ ካልሄዱ (ካልተደረጉ) በስተቀር ሊሆንለት አይችልም፡፡ እግዚአብሔር የእርሱ ለሆኑት ነገሮች ሁሉ ምንጩ እርሱ ነው፤ በእርሱ ሁሉ ነገር አይቋረጥም፤ ሁሉ ነገር በእርሱ ፍጻሜ ያገኛል፡፡ እግዚአብሔር ጥበብን የሚሸጥ አይደለም፤ ነገር ግን ትሁታን ለሆኑት በነፃ ይሰጣል፡፡
ጸሎት፡- ያንተ ክብር፣ ግርማ፣ ኃይልና ጥበብ ለማየት እንድንችል፣ ጌታ ሆይ በምህረትህ ዓይኖቻችንን እንዲከፈቱ
አድርግ፡፡
‹‹የጥበብ መልእክት››
የንባብ ክፍል፡- 1ቆሮንቶስ 1፡18-31
‹‹ለተጠሩት ግን አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ
የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው
ክርስቶስ ነው›› ቁ. 25
ጥሪያችን የተቀደሰና በእግዚአብሔር ጥበብ ላይ የተመሠረተ እንጂ በሰው ጥበብ ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ የሰው ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው፡፡ ሰዎች በተፈጥሮአዊ መንገዶች እግዚአብሔርንና ጥበቡን ለማግኘት በመሞከር አይሆንላቸውም፤ ራሱን የሚገልጸው ለሚያምኑት ብቻ ነው፡፡ ትልቅ የተማረ፣ ያወቀና አንድ ትንሽ ልጅ የሚገቡት በአንድ በር ነው፡፡ በሩም የእምነት በር ነው፡፡
አዋቂዎችና መንፈሳዊ ያልሆኑ የመስቀሉ መልእክት እንዴት ሊገባቸው ይችላል? ምክንያቱም ለእነርሱ ሞኝነት ስለሆነ የማስተዋል ጥበብ የላቸውም፡፡ ትክክል ያልሆነ ሆኖ ሳይሆን የእግዚአብሐር ጥበብና የሰውም ዕውቀት የማይጨመርበት በጣም ጥልቅና ሰፊ ስለሆነ ነው፡፡ ሰው በራሱ ማየት አይችልም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እመንና ታያለህ ብሎአል፡፡ ሰው ከማመኑ በፊት ማየትና መረዳት ወደሚችልበት ሥፍራ መምጣት አለበት፡፡ በራሱ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ለማሳረፍ ችሎታ የለውም፡፡ ይሁንና የዓለምን ጥበብ ትቶ በክርስቶስ መስቀል ሲያምን፣ ያን ጊዜ የዓለም መቃብሮች ባዶ ሲሆኑና ዙፋኖች ሁሉ ሲወሰዱ እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ኃይልና ጥበብ ያገኛሉ፡፡ ጸሎት፡- ጌታ ሆይ የሁሉን ዓይኖች በመክፈት የሕፃናትን መንፈስ ስጣቸውና ወደ ድነትህ ይግቡ፡፡
0 Comments