‹‹መግቢያ››
ባለፉት ሦስት ወራት በደርግ ዘመን በሠፈረ ገነት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን (በኢትዮጵያ ገነት ቤተ ክርስቲያን) ‹‹መና›› ከሚል ለግል፣ ለቡድን እና ለቤተሰብ የሚሆን ዕለታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የጸሎት መምሪያ እንዲሆን ከተዘጋጀው ‹‹ዘመኑን ዋጁ›› በሚለው ርዕስ ሥር የተዘጋጁትን ስናካፍላችሁ ቆይተናል፡፡
አሁን ደግሞ ልደቱን አስመልክቶ ለአንድ ወር ያህል ተዘጋጅተው ከነበሩትና በተለያየ ርዕስ ለየቀኑ ተዘጋጅተው የተነበቡትን ለአሥር ሳምንት ያህል እናቀርብላችኋለን፡፡ ጥበብኛው አምላክ፣ በጥበቡ የሰውን ልጆች ለማዳን መለኰታዊነትንና ሰብዓዊነትን በጥበቡ አዋህዶ ከድንግል ማርያም ሥጋ ነስቶ እንዲወለድ አደረገው፡፡ እኛም በመለኰታዊ ጥበቡ በመረዳት፣ ይህን ጌታ ልናመልከው ይገባናል፤ የልደቱ ጮራ በልባችሁ በጥበቡ ይብራ፡፡
እግዚአብሔር በጥበቡ ካዘጋጀልን የጥበብ መንገዶች አንዱ ጸሎት ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ዘወትር ሳናቋርጥ እንድንጸልይ ያሳስበናል፡፡ የእምነት አርበኛ የነበረው ነቢዩ ዳንኤል፣ ችግርና ፈተና ወይም ሥራ ብዛት ሳይገታው በዕየለቱ ሦስት ጊዜ ይጸልይ እንደነበር ታሪኩ ያሳየናል፡፡
ይህ እኛ ያለንበት ዘመንም ከምንጊዜውም ይልቅ ወደ አምላክ ዙፋን በዚህ ጥበብ፣ በምልጃ እንድንቀርብ የሚያስገድደን ጊዜ ነው፡፡ የጌታ ፍርድ በዓለማችን ላይ ባንዣበበበት መጨረሻ ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ይህም ዕለት በዕለት በፊቱ እየቀረብን ፈቃዱን እንድንፈልግ፣ በቃሉ እንድንመራና በጸሎት መንፈስ እንድንኖር ያስገድደናል፡፡ ለዚህ ዓላማ ይጠቅማችኋል ብለን በማሰብ ለየዕለቱ የንባብ መምሪያና የጸሎት መነሻ እንዲሆናችሁ አቅርበናል፡፡
‹‹ለጥበብ መጸለይ››
የንባብ ክፍል፡- 1ኛ ነገሥት 3፡3-15
‹‹… ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ›› ቁ 14
ሰሎሞን ጥበብን ፈለገ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ሕዝቦች እንደ ንጉሥና ዳኛ ሆኖ ይመራ ስለ ነበር ትልቅ ኃላፊነት ነበረበት፡፡ አንድ ጉዳይ ወደ እርሱ ዘንድ ሲቀርብ ያ የመጨረሻው ውሳኔ ይሆናል፤ ብዙ ጊዜ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነበር፤ እርሱም እውነቱን ማግኘት አለበት፡፡ ሰዎች የደበቁትን እውነት ፈልጎ ውሳኔ መስጠት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የሰሎሞን ጥበብ በልጅ በተጣሉት ሁለት ሴቶች ላይ በሰጠው ውሳኔ ታይቶአል፡፡ ሁለቱም የእኔ ነው በማለት አጥብቀው ይከራከሩ ነበር፡፡ ክርክሩን እንዴት ውሳኔ ሰጠው? እውነተኛዋ እናት ልጇ እንዲሞትባት እንደማትወድ በማወቁ፣ ልጁ ለሁለት እንዲከፈል ውሳኔ ሰጠ፡፡ እውነተኛዋ እናት የልጁ መከፈል ጉዳት መሆኑን ስለ ተረዳች ለሌላዋ ተወችላት፡፡ በዚህ ጊዜ ሰሎሞን እውነተኛዋ እናት መሆንዋን ተረዳ፡፡
ዛሬ ለእኛስ በበጎና በክፉ ላይ ለመፍረድ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዴት አያስፈልገንም? ስለዚህ በያዕቆብ እንደምናነበው ‹‹ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጐድለው ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን›› (ያዕ. 1፡5)፣ የምንፈልገው ጥበብ ንፁሕ፣ ታራቂ፣ ገር፣ እሺ ባይ፣ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላበት፣ ጥርጥርና ግብዝነት የሌለበት ነው፡፡ ጥበብን በሥራ ላይ ማዋል ማወቅ የምንቸለው የእግዚአብሔርን ቃል ስናውቅ ነው፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ መለኰታዊ ጥበብን ስጠኝ፡፡
‹‹የመለኰታዊ ጥበብ ፍጹምነት››
የንባብ ክፍል፡- መዝሙር 19፡7-14
‹‹የእግዚአብሔር ምስክር (ቃል) የታመነ ነው፣
ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል›› ቁ. 7
የእግዚአብሔር ፍጹም ጥበብ በፍጹም ሕጉ ታይቶአል፡፡ ሞኞች መልካሙንና ክፉውን መለየት አይችሉም፡፡ ጥበበኞች ማንኛውንም ሐሳብ ለመቀበል ልባቸው የተከፈተ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚያውቁት በክፉ ሰዎች ሐሳብ አይታለሉም፡፡ የእግዚአብሔር ሕግ በፍርድ ጥበበኞች ያደርጋል፡፡
‹‹እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው››፣ በእውነት ጌታን የምንፈራ ከሆነ ክፉ ነገሮችን ከማድረግ እንቆጠባለን ፡፡ መዝሙረኛውም ኃጢአት እንዳይገዛው ይፈልጋል፡፡ ጥበበኛ ሰው ከኃጠአት ነፃ መሆንን እንጂ ሕይወቱን ኃጢአት እንዲገዛው አይፈልግም፡፡ ስለዚህም መዝሙረኛው ባለማወቅ ኃጢአት እንዳይሠራና ከተደበቀም ኃጢአት እንዲነፃ እግዚአብሔር እንዲጠብቀው ይጸልያል፤ በእርግጥ የጥበብ ጸሎት ነው፡፡
እኛ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደለንም፤ ስለዚህ ምክንያት ከኃጢአት እርግማንና ቅጣት ድነናል፡፡ የሞራልን ሕግ ለመጠበቅ ኃይል አለን፡፡ ኃይሉም መለኮታዊ የሆነውን አስፈላጊ ጥበብ የያዘ ነው፡፡ ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ቃልህን እንድመለከት ጥበብን ስጠኝ፣ ሕግህም አንተን እንዳልበድል ይጠብቀኝ፡፡
0 Comments