‹‹በጊዜው እናጭዳለን››

 የንባብ ክፍል፡- ገላትያ 6፡9  

   ‹‹ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም

     ሥራ ለመሥራት አንታክት››

ሰው በሕይወቱ ዘመን እያለ መልካምም ይሁን ክፉ ብዙ የሚሠራውና የሚያከናውነው ይኖረዋል፤ ምንም ሳይሠራ ሕይወቱን የሚያሳልፍ ሰው የለም፡፡ የሥራው ውጤት ፍሬ አፍርቶ መልካም በመሆኑ ለሰዎች የሚተርፍና ምሥጋና፣ ክብርና ሹመት የሚያስገኝለት ሲሆን፤ ክፉ በመሆኑ ደግሞ ሰዎች የሚመረሩበትና የሚያለቅሱበት ይሆናል፡፡ ሰው በሕይወቱ ከእነዚህ ከሁለቱ ተግባራት ውጭ ሊያደርግ አይችልም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር ‹‹አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፡፡ ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፣ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፣ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል›› (ገላ. ቁ. 7-8)፡፡ ስለዚህ ዛሬ የምንዘራው ዘር የሥጋ ነው ወይስ የመንፈስ? የምንዘራው ራሳችንን ከፍ ለማድረግ ነው? ወይስ ጌታን ከፍ ለማድረግ? የምንዘራውስ ዘር ምንድን ነው? ክፋትን፣ ተንተኮልን፣ ጥላቻን፣ ምቀኝነትን፣ ራስ ወዳድነትን፣ ነው ወይስ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ትሕትናን፣ ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ የዋህነትን? በሁለቱም የምንዘራውን እናጭዳለን፡፡

መንፈሳዊ ዘርን ለመዝራት ከባድና አስቸጋሪ ቢሆንም ሳንደክም፣ ሳንዝል፣ ተስፋ ሳንቆርጥ እውነተኛውን የጽድቅን ዘር ብንዘራ አንድ ቀን ጊዜው ሲደርስ የዘራነውን እናጭዳለን፡፡ አሁን ባለን ጊዜ ከጌታ የተቀበልነውን ዘር ለመዝራት ሁላችን በያለንበት ቦታ መሰማራት አለብን፤ ለሰው ሁሉ መልካም የማድረግ ኃላፊነት አለብን፡፡ ዛሬ በችግርና በመከራ የምንዘራውን አንድ ቀን ጌታ ሲመጣ በደስታ እናጭዳለን፤ አንዳንዱ ዘር ጌታ እስኪ መጣ ድረስ ሳንጠብቅ በዚሁ በምድር የምናጭደው ይሆናል፡፡ ስለዚህ ስለ ምንዘራው የዘር ዓይነት ጥንቃቄ እናድርግ፡፡

 ጸሎት፡- ጌታ ሆይ የምዘራው ዘር መልካምና

 የሚታጨድ እንጂ መካን እንዳይሆንብኝ እርዳኝ፡፡

‹‹ዘመኑን ዋጁ››

 የንባብ ክፍል፡- ኤፌሶን 5፡16 

    ‹‹ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ››

የሕይወት ቀኖቻችን በአጠቃላይ ለክፋት የተጋለጡና አጭርም ናቸው፡፡ ያዕቆብም ይህንኑ በማስተዋል፣ ‹‹የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ›› ብሏል (ዘፍ. 47፡9)፡፡ ከዚህም ሌላ የፈለግነውን ልንሠራ የማንችልባቸው የተለዩ ክፉ ቀናት አሉ፤ ልባችን ለመሥራት እየጓጓ፣ የመሥራት ፍላጎት በልባችን እየተቃጠለ፣ ነገር ግን ጊዜ አልፎብን በምኞት ብቻ የምንኖርባቸው የመከራና የሥቃይ ጊዜያት ወይም በተለያየ የሥጋ ድካሞች፣ ለምሳሌ በበሽታ አልጋ ላይ የምንሆንበት ጊዜ፣ በእርጅና ሥር የምንወድቅበት (የምንያዝበት) ጊዜ ሊመጣ ይችላል፡፡

ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹ዘመኑን ዋጁ›› የሚል ማስጠንቀቂያ በዘመኑ ለነበሩ አንባቢዎችና ለእኛም ይሰጠናል፤ ሐዋርያው ይህን ሲል በጊዜው ሁሉ ተጠቀሙበት፣ እያንዳንዱን ሰከንድ፣ ደቂቃና ሰዓት አስቡ፣ በከንቱ የሚያልፈውን ጊዜ ተመልከቱ፣ የራሳችሁም አድርጉት ማለቱ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ እንድንሠራ የተሰጠንን አመቺ ጊዜ በሚገባ መጠቀም፣ ያ እውነተኛ ጥበብ መሆኑን ጨምሮ ያሳስበናል (ቁ. 15)፡፡ ሐሳቡም ሰፋ አድርገን ስናየው አንድ ሰው ድነትን ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ጊዜ በሙሉ እንዲዋጅ ማለት ይሆናል (2ቆሮ.6፡2)፡፡

‹‹ዋጁ›› የሚለው ቃል የጊዜውን አመቺነትና ከዚያም ይልቅ የጊዜውን ክቡርነት ያመለክታል፤ ጊዜ በተጠየቀው ዋጋ ሊገዛ የሚገባው ዕንቁ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ክርስቲያኖች ጊዜን በተለይም ያለንበትን ጊዜ ባለን ኃይል ሁሉ ልንሠራበት እንደሚገባን በማወቅ በቁጥጥራችን (በጥቅም ላይ) ሥር ማድረግ አለብን፡፡ ጊዜውን እንድናገለግለው ሳይሆን እንድንጠቀምበት፣ እንድናዘውና የምንፈልገውን እንድንሠራበት ለማድረግ ታጥቀን መነሣት ግዴታችን ነው፡፡ ዘመኑን መዋጀት ትልቅ ጥበብ ነውና፡፡

  ጸሎት፡- ጌታችን ሆይ የጊዜውን ክፋትና የቀኖቹን

        ማጠር እንድናይ ዓይኖቻችንን ክፈት፤

   እንድንሠራበትም ጥበብና ጉልበት ጨምርልን፡፡

‹‹በጥበብ ተመላለሱ››

 የንባብ ክፍል፡- ቈላስይስ 4፡5  

 ‹‹ዘመኑን እየዋጃችሁ በውጭ ባሉት ዘንድ

   በጥበብ ተመላለሱ››

የማያምኑ ዓለማውያን ስለ እምነታችን አሳምረን የምንናገረውን ብቻ መስማት አይፈልጉም፡፡ ነገር ግን እምነታችንን፣ ምን ያህል በኑሮአችን እንደምንተረጉመው አጥብቀው ይከታተላሉ፡፡ አንድ የሚያምን ወንድም ያለ ጥንቃቄ ለምንናገረው ቃል፣ ወይም በድርጊት ለምንገልጸው ስሕተት ሁሉ ይቅር ይለናል፤ ዓለማዊ የሆነ ሰው ግን እንደዚህ አይደለምና በጥንቃቄ መመላለስ ይገባናል፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ባነበብነው ክፍል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም መልእክቶቹ ይህንኑ ጉዳይ በማንሣት ክርስቲያኖችን በማስተዋል እንዲመላለሱ እንጂ፣ የጌታቸውንና የመድኃኒታቸውን ቅዱስ ስም እንዳያሰድቡ ይመክራቸዋል፡፡ ጌታም ራሱ ‹‹መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁእንዲሁ በሰው ሁሉ ፊት ይብራ›› በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስተምሮአል፡፡ ይህ ትእዛዝ ዛሬም ለእኛ ስለሚሠራ፣ ጳውሎስ በጥበብ ተመላለሱ የሚለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ይህ ጥበብ በምድራዊ ትምህርት የሚገኝ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርን በማወቅና በመፍራት የሚጀምርና እርሱን ከማያስደስተው ነገር ሁሉ በመራቅና በመመላለስ የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ ጥበብ ጥንቃቄና ማስተዋል ይጠይቃል፡፡ አንድ ክርስቲያን ደግሞ ይህን በጥንቃቄና በማስተዋል የመኖር ኃይል ማግኘት የሚችለው ከእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ለልጆቹ ጥበብና ማስተዋል የሞላበት፣ ሕፃናትን አስተዋይ የሚያደርገውን፣ ንጹሕ የሚያደርገውን ቅዱስ ቃሉን ለሕይወታችን መመሪያ እንዲሆን ሰጥቶናል፡፡ በዚህ ቃል ስንኖር በጥበብ እንኖራለን ማለት ነው፤ እንደሰማነውና እንዳነበብነው በቃሉ መሠረት ስንኖር፣ ሕይወታችን ብዙዎችን ወደ ክርስቶስ ይጠራቸዋል እንጂ እንዳያምኑ እንቅፋት አይሆንባቸውም፡፡

በዚህ ሰዎች እውነተኛ የሕይወት ትርጉም በሚፈልጉበት ዘመን በጥበብ እየተመላለስን ክርስቶስን ለማያምኑትና ከእግዚአብሔር መንጋ ውጭ ላሉት ሰዎች ሁሉ እርሱን ብናሳያቸው ብዙዎች ወደ ጌታ ሊመጡና ሕይወታቸውን ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ስንቶቻችን በችላ ባይነትና እግዚአብሔርን በማያስከብር ኑሮ እየኖርን፣ ስንቶቹን ጠባብ ወደ ሆነችው የሕይወት ጐዳና እንዳይገቡ መሰናክል ሆነንባቸው ይሆን?

 ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ዘመኑን እየዋጀሁ

       በጥበብ እንድመላለስ እርዳኝ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *