‹‹የመጽናናት ዘመን››
የንባብ ክፍል፡- ሐዋርያት ሥራ 3፡19-20
‹‹እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ
አስቀድሞ ለእናንተ የመረጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን
እንዲልክላችሁ ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ
ንስሓ ግቡ ተመለሱም፡፡››
‹‹መዳን በሌላ በማንም የለም፣ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና›› (የሐዋ. 4፡12)፡፡ እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸውን ጥቅሶች ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ለአይሁድ አለቆችና ሽማግሌዎች ተናገራቸው፡፡ ምንም እንኳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ ወደ ገዛ ወገኖቹ ቢመጣም የእርሱ የሆኑት አልተቀበሉትም፡፡ ጌታ ኢየሱስ በተበላሸው ኅብረተ ሰብ መካከል ምልክትና ድንቅ ነገር እያደረገ ብዙ ተአምራቶችን ሠርቷል፤ ይሁን እንጂ በአንፃሩ ልዩ ልዩ የሐሰት ክስ እያቀረቡ ይወነጅሉት ነበር፡፡ በዚህም ሳይወሰኑ አዳኛቸውን ለሞት አሳልፈው በመስጠት አሰቅለዋል፡፡
በሐዋርያት ዘመን እንደዚሁ ከጌታቸውና ከአምላካቸው በተቀበሉት መመሪያ መሠረት ቃሉን ካስተማሩና ከመሰከሩ በኋላ ቃሉን ለማጽናት በኢየሱስ ስም አጋንንትን ያስወጡ ነበር፣ ሽባዎችን በመፈወስ፣ የሞቱትን በማስነሣት ብዙ ተአምራት ያደርጉ ነበር፡፡ በአንፃሩ ግን ግርፋት፣ እስራት፣ ስደት፣ መገደል ደርሶባቸዋል፤ ሆኖም ግን በዚህ ሁሉ በመጽናናት በብርታት ራሳቸውን እየሰጡ ያልፉ ነበር፡፡ ምክንያቱም መሪያቸው ኢየሱስ ሞትን ድል ነስቶ ሕያው ሆኖ መነሣቱን ስላረጋገጡ ነው፡፡
እኛም ዛሬ ለኅብረተ ሰቡ የመጽናናት ዘመን እንደሆን በሚደርስብን ሁሉ እየተጽናናንና ዘመኑን እየዋጀን ሰዎች በንስሓ ወደ አምላካቸው እንዲመለሱ ቃሉን እናስተምር፣ አዳኝነቱን እንመስክር፡፡ በዚህ በመጽናናት ዘመን ንስሓ በመግባት ወደ እርሱ እንዲመለሱ በጸሎት ወደ አምላካችን እናቅርብ፡፡ ለእኛም የመጽናናት ዘመን እንዲሆንልን የተሰጠንን ተስፋ በመያዝ ወደ ፊት እንጓዝ፤ የጌታንም ፊት አንድ ቀን ስናይ፣ ዛሬ እንደሆነልን ትልቅ መጽናናት ይሆንልናል፤ ትልቁ ተስፋችንም በዳግም ምፅዓቱ ከእርሱ ጋር መሆን ነው፡፡
ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ ተስፋ ስቆርጥና ስዝል መጽናናትን ስጠኝ፡፡
‹‹ዘመኑን እወቁ››
የንባብ ክፍል፡- ሮሜ 13፡12
‹‹ሌሊቱ አልፎአል፣ ቀኑም ቀርቦአል፡፡
እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን
የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ››
የቀን ብርሃን እንዳያጋልጣቸው ጠላቶቻቸውን ለመከላከል በየዋሻውና በየጉድጓዱ ተደብቀው ከዋሉ በኋላ የቀኑ ብርሃን አልፎ የሌሊቱ ጨለማ ሲተካ፣ ጨለማውን ተገን አድርገው ከየዋሉበት ዋሻና ጉድጓድ ወጥተው በሰውና በእንስሳት ላይ አደጋ የሚያደርሱ አውሬዎች አሉ፡፡ ከሰዎችም እንደዚሁ ሊያርፉበትና ሊተኙበት ሲገባ የሌሊቱን ጨለማ ተገን በማድረግ የሰውን ሕይወት በማጥፋት፣ ቤቶችን በመሰርሰርና ንብረቶችን በመስረቅ፣ በመስከርና በማመንዘር ከአውሬዎች ጎን ተሰልፈው በኅብረተ-ሰቡ ዘንድ ጉዳት የሚያደርሱ አሉ፡፡ ብርሃንና ጨለማ ፍጹም ተቃራኒዎች ናቸው፤ ብርሃን የሚገልጻቸውን ነገሮች ሁሉ ጨለማ ይደብቃቸዋል፡፡ ይህ በቀጥታ ሲታይ የብርሃንና ጨለማን ምንነት ያመለክታል፡፡
በመንፈሳዊ አመለካከት ግን ብርሃን የጽድቅ፣ የቅድስና የሕይወት መንገድ ሲሆን፣ ጨለማ ደግሞ የኃጢአት መንገድ ነው፡፡ ዛሬ በሥጋ ሕያዋን ሆነው በመንፈሳቸው ግን የሞቱ ሰዎች ከእንቅልፋቸው ያልነቁና ሕይወት ያላገኙ፣ አካሄዳቸውና አሠራራቸው ከጨለማ ሥራ ተባባሪነት ያለው ነው፡፡ ስለዚህ ነው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት አሁን እንደ ደረሰ ዘመኑን እወቁ፣ ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና›› የሚለው፡፡ ክርስቲያኖች በአካሄዳችንና በአሠራራችን እውነትን እየገለጽን በብርሃን እየተጓዝን ከእንቅልፋቸው ያልነቁትን የምንቀሰቅስበት ዘመን እንደሆነ አውቀነዋል? ወይስ በጨለማው ውስጥ ተኝተናል?
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በኃጢአት እንቅልፍ ውስጥ
ተኝቼ ድንገት እንዳትገለጽ እባክህ ቀስቅሰኝ፡፡
‹‹የመዳን ቀን››
የንባብ ክፍል፡- 2ቆሮንቶስ 6፡2
‹‹በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ››
የሰው ልጆች በአዳም ምክንያት ወደ ዓለም የገባው የትእዛዝ መተላለፍ ያስከተለውን የሞት ዕዳ ተሸክመው ስለሚኖሩ፣ ሁልጊዜ በሞት ጥላ ሥር ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ሰው ምክንያት ወደ ዓለም የገባውን የሞት ዕዳ በአንድ በሕያው በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተከፍሎአል፡፡ የተከፈለውን የሞት ዕዳ ተሸክመው የሚኖሩ ሁሉ ‹‹በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ›› ይላልና ዛሬም እነሆ የተወደደ ሰዓት አሁን ነው፣ የመዳንም ቀን አሁን ነው፤ እያለ የእግዚአብሔር ቃል ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ለእያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ የተወደደ ሰዓት፣ የራሱ የሆነ የመዳን ቀን አለው፡፡ ሆኖም ግን የተወደደው ሰዓትም ሆነ የመዳኑ ቀን በእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ውስጥ ሊሠራ የሚችለው እንደ ፈቃደኛነቱና እንደ እምነቱ ነው፡፡ ዛሬ ከምንጊዜም ይበልጥ የእግዚአብሔር ፍርድ በደጅ እንደ ቀረበ ለማሳሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በትራክት፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን እንዲሁም በሶሻል ሚዲያ አማካይነት የወንጌሉ ምሥራች እየተሠራጨ ነው፡፡
ይህን የወንጌል የምሥራች ስርጭት ሰምተው ልባቸውን የሚያደነድኑ ሁሉ የተወደደውንና የመዳኑን ቀን በዋዛ ፈዛዛ ስለሚያሳልፉት ለፍርድ ያዘጋጃቸዋል፡፡ ስለዚህ ነው የዕብራውያኑ መጽሐፍ ጸሐፊ ‹‹በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ መተላለፍና አለመታዘዝም ሁሉ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ መዳን ቸል ብንለው እንዴት እናመልጣለን?›› (ዕብ. 2፡2-3) ብሎ የሚጠይቀው፡፡
ወንድሞችና እህቶች በችግራችሁ ሁሉ ረዳታችሁ ማነው? የነፍስ ድነት ሊሰጣችሁ የሚችል ማን አላችሁ? ዛሬ የተሰጠንን ይህን የመዳን ቀን ቸል እንዳንለው፣ ዛሬውኑ ሊረዳንና ሊያድነን ወደሚችለው አምላካችን እንቅረብ፡፡ እርሱም እጆቹን ዘርግቶ ይቀበለናል፡፡
ጸሎት፡- መድኃኒቴ ሆይ በመዳን ቀን ወደ አንተ
መጠጋትና ድነትን ማግኘት ይሁንልኝ፡፡
0 Comments