‹‹መጐብኘት ዘመን››
የንባብ ክፍል፡- ሉቃስ 19፡41-44
‹‹ሲቀርብም ከተማይቱን አይቶ አለቀሰላት፣
እንዲህ እያለ፡- ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን
አንቺስ እንኳ ብታወቂ፣ አሁን ግን ከዓይንሽ
ተሰውሮአል …የመጐብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና፡፡››
ጌታ ኢየሱስ ስለ ራሱ ያለቀሰበት ጊዜ የለም፤ ሰዎችን ለማዳን ሰው ሆኖ በዚች ምድር በተመላለሰባቸው ዓመታት፣ በዚህ ክፍል እንደምንመለከተው የኢየሩሳሌምን ከተማ አይቶ አለቀሰ፡፡ በሐሰት ሲከሱት፣ ሲተፉበትና ሲሳለቁበት፣ ሲገርፉትና ሲሰቅሉት አላለቀሰም፤ ነገር ግን የመቤዠትዋንና የመዳንዋ ቀን በደጅዋ እያለ ይህን የመዳን ቀን አውቃ የንስሓ ፍሬ ባለማግኘቱ አለቀሰላት (ሉቃ. 13፡34)፡፡
የእስራኤል ሕዝቦች አስቀድሞ ትንቢት የተነገረላቸው፣ እግዚአብሔር የመዳን ቀን እንዳዘጋጀላቸው በተለያዩ ነቢያትና በተለያየ መንገድ ገልጾላቸዋል፡፡ እነርሱም መሲህ መጥቶ ካለንበት መከራና ሥቃይ ሁሉ ነፃ ያወጣናል እያሉ ተስፋ ያደርጉ ነበር፡፡ ይህ የጨለማ ጊዜ አልፎ ወርቃማ ዘመን ይመጣል እያሉ ተናግረዋል፡፡ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ በተስፋ፣ ይህን ዘመንና ጊዜ ጠብቀዋል፡፡ ነገር ግን ዘመኑን ወርቃማ የሚያደርገው ጌታ በመጣ ጊዜ አልተቀበሉትም፡፡ ስለዚህም ከላይ የተመለከትነውን ቃል ክርስቶስ የተናገረው ከተማይቱን እያየ ነው፡፡ እነርሱ ግን በክርስቶስ የመጐብኘታቸው ዘመን እንደ ሆነ አላወቁም፡፡
ዛሬም የተወደደው ቀንና የመዳን ቀን በደጃቸው እያለ፣ በጨለማ ገዥ ሥር የሆኑና የመቤዠታቸውን ዘመን ባለማወቅ፣ የንስሓ ፍሬ ሳይገኝባቸው፣ የሞት ኃይል በላቸው ላይ ነግሦባቸው በመባዘን ለሚገኙትና ለሚመላለሱት ወገኖቻችን ልናለቅስላቸው ይገባናል፡፡ ስንት ጊዜ ለወገኖቻችን የእውነት ዕንባችንን አፍስሰን ይሆን?
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ዛሬም ቢሆን የመጐብኘትህ
ዘመን ስላላለቀ አመሰግንሃለሁ፡፡
‹‹በዚህ ዘመን››
የንባብ ክፍል፡- ዮሐንስ 9፡4
‹‹ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤
ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ትመጣለች፡፡››
ባለፈው ምንባብ ኢየሩሳሌም የንስሓ ፍሬ ስላልተገኘባትና የመጐብኘቷን ቀን ባለማወቋ ጌታ እንዳልተቀበላት ተመልክተናል፡፡ በዛሬው ክፍል ደግሞ ዘመናትንና ዓመታትን የመዋጀት ኃይል ያለው ጌታ በልቅሶ ብቻ ሳይወሰን የተላከበትን ተልዕኮ ቸል ሳይል፣ ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፣ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች በማለት የአባቱን ተልዕኮ በሥራ ለመተግበር እንደ ተነሣ እንመለከታለን፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ሁልጊዜ በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ ለአባቱ ለመታዘዝና ፈቃዱን ለመፈጸም ሲያስብ ብዙዎች ጣልቃ እየገቡ ቢያስቸግሩትም፣ የመጀመሪያ ዓላማው ስለ ነበረ እስከ መጨረሻው በመታገስ ድል አድርጓል፡፡ ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የነበረውን ሰው ሲፈውስ ብዙዎች ቢቃወሙትም፣ ተልዕኮውን ከመፈጽም ወደ ኋላ አላለም፡፡
እኛም ክርስቲያኖች ተልዕኮአችንን ሳንረሳ ባለንና በተሰጠን ጊዜ ልንሠራበት ይገባናል፡፡ ዛሬ ሰዎች በጎውን ማን ያሳየናል? ረዳታችን ከወዴት ይምጣ? እያሉ ፈዋሽና አዳኝ አጥተው በሚቅበዘበዙበት በዚህ ጊዜ፣ የማዳኑን ኃይልና የምሥራቹን ወንጌል ልንሰብክላቸው ይገባል፡፡ ያየነውን የማዳን ኃይልና የቀመስነውን የክርስቶስ ፍቅር ለሰዎች ካልተናገርን፣ ካልመሠከርን ሰዎች ካሉበት የጨለማ ሥራ ወደ ብርሃን ሊወጡ አይችሉም፡፡ ልንሠራ የሚገባንን ስንት ቀኖችን ችላ ብለን ይሆን? ራሳችንን ለምን ብለን እንጠይቅ፡፡ ዛሬ ቀን ሳለ ልንሠራ የሚገባንን፣ በዚህ ቀን ለመሥራት እንነሣ፡፡ ጌታም ጸጋውንና ብርታቱን ይሰጠናል፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በሰጠኸኝ ‹‹በዚህ ቀን›› ልሠራ
የሚገባኝን እንድሠራ ሸክሙንና ጸጋህን አብዛልኝ፡፡
‹‹ጥቂት ጊዜ››
የንባብ ክፍል፡- ዮሐንስ 12፡35
‹‹ጨለማ እንዳይደርስባችሁ
ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ››
የዓለም ብርሃን፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በጨለማ ውስጥ ያሉትን ወደ ብርሃን ለማምጣት፣ በኃጢአት እሥራት የታሠሩትን በንስሓ ከእሥራታቸው ለመፍታት፣ በሞት ጥላ ሥር ያሉትን የሞትን ዕዳ በሕይወቱ ከፍሎ ወደ ዘላለም ሕይወት ለማምጣት ወደ ዓለም መጣ፡፡ ይሁን እንጂ ሰዎች ሥራቸው ክፉ ስለ ሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን፣ ከመፈታት ይልቅ መታሰርን፣ በሕይወት ከመኖር ይልቅ ሞትን መረጡ፡፡ ስለዚህ የሰው ሕይወቱን እንጂ ሞቱን የማይወድ ጌታ ‹‹ገና ጥቂት ጊዜ ብርሃን ከእናንተ ጋር ነው፡፡ ጨለማው እንዳይደርስባችሁ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፣ በጨለማም የሚመላለስ ወዴት እንዲሄድ አያውቅም›› ብሎ ተናገረ፡፡
የወንጌሉ ጥሪ ዛሬም ቢሆን ‹‹አንተ የምትተኛ ንቃ ሀሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል›› ይላል፡፡ ስለሆነም በብርሃኑ የምንመላለስና ሕይወቱን የተቀበልን ሁሉ ከእንቅልፋችን ነቅተን በጨለማ ውስጥና በሞት ጥላ ሥር ያሉትን ወደ ብርሃንና ወደ ሕይወት እንዲመጡ፣ የወንጌሉን ምሥራች እናውጅላቸው፡፡ የእግዚአብሔር የምሕረት ጊዜ በጣም ሰፊና ብዙ ነው፤ ልጁን ወደ ዓለም ከላከበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የምሕረት ጊዜ ሲሆን ወደፊትም የምሕረቱ ጊዜ የሚቀጥል ቢሆንም፣ ጥቂት የብርሃን ጊዜ ስለ ቀረ፣ ለጥቂት ጊዜ ብቻ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በዚህ በጥቂት የብርሃን ጊዜ ሳንጠቀምበት ደህንነትን ሳናገኝበት፣ ካምላካችን ጋር ሳንታረቅበት እንዳያልፍብን ዛሬውኑ እንዋጀው፡፡ ጥቂቷን ጊዜ ለመዋጀት ስንቶቻችን ተነስተናል?
ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ የጨለማው ጊዜ ሳይመጣ
ዛሬውኑ ወደ ብርሃን የሚወጡትን እርዳቸው፡፡
0 Comments