‹‹ፈልጉት››

 የንባብ ክፍል፡- ኢሳያያስ 55፡6

   ‹‹እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣

    ቀርቦም ሳለ ጥሩት››፡፡

 የሰው ልጆች እግዚአብሔርን በተለያዩ ጊዜያት ይጠሩታል፤ ለአንዳንዶች ሲደርስላቸው፣ ለአንዳንዶች ደግሞ ዝም ስለሚል፣ ፈጽሞ የማይሰማ ወይንም የሌለ የሚመስላቸው ጊዜ አለ፡፡

የንባብ ክፍላችን ‹‹እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፣ ቀርቦም ሳለ ጥሩት›› ብሎ ይላል፤ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ይወዳል፣ ያፈቅርማል፡፡የማይታየውንም  ባሕርዩን በተፈጠረው ፍጥረቱ በኩል እንድናየው፣ እንድናውቀው መንገድን አዘጋጅቶአል፡፡ እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ጓደኝነት ይወዳል፤ በአምላኩ የተፈጠረው የሰው ልጅ ፈጣሪውን አውቆ፣ ከእርሱም የሚገኘውን በረከት እንዲቀበል፣ የአምላካችን ፈቃድ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በበለጠ እንድናውቀውና እንድንረዳው ችግር ሲገጥመን ለችግራችን መፍትሔ በመስጠት በተለያየ መንገድ የምሕረት እጁን ይዘረጋልናል፡፡

የሰው ልጅ ሐሳብ ግን ሁልጊዜ ወደ ጥፋት ያዘነበለ ስለሆነ፣ የእግዚአብሔርን መንገድ ይዞ ለመራመድ በጣም ያዳግተናል፡፡ ኑ ሲለን እንሸሸዋለን፣ እወቁኝ ሲለን እንርቀዋለን፣ እንታረቅ ሲለን እንጣላዋለን፤ ግን ይህ ሁሉ ሁኔታ የሚቀጥል አይደለም፡፡ ስንፈልገው የሚገኘው ስንጠራው የሚሰማን ጌታ፣ በፍርድና በቁጣው ቀን የማይገኝበት፣ ስንጠራው የማይመልስበት ጊዜ ይመጣል፡፡ በዮሐንስ ራዕይ 6፡12-17 ባለው ላይ ሰዎች ለተራራዎችና ለዓለቶች የሚጸልዩበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል፤ አሁን ግን ያለንበት ዘመን የምሕረት ጊዜ ስለሆነ፣ ዛሬውኑ አምላካችንን በመፈለግ በንስሓ ቀርበን መታረቅ አለብን፡፡ ለዚህ ነው ቃሉ ‹‹እግዚአብሔርን ፈልጉት›› ብሎ የሚናገረው፡፡       

ዛሬ አምላካችን ከእኛ የራቀ መስሎ የታየን ካለን፣ የምሕረት እጁ እንደ ተዘረጋች ስለሆነ ወደ እርሱ በክርስቶስ በኩል መቅረብ እንችላለን፡፡ የልብ መሻት ካለን፣ ፈልገን ልናገኘው የምንችልበትን መንገድ አዘጋጅቷል፡፡

 ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ በጸሎቴ የማላገኝህ፣

    የማትሰማኝ ሲመስለኝ፣ በጸጋህ ቅረበኝ፣

     ፊትህንም ግለጥልኝ፡፡

‹‹የጥፋት መጐብኘት››

 የንባብ ክፍል፡- ኤርሚያስ 46፡21

   ‹‹በእርስዋም ያሉ የተቀጠሩ ሠራተኞች

    እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፣

   የጥፋታቸው ቀንና የመጐብኘታቸው ጊዜ

  መጥቶባቸዋልና ተመለሱ፣ በአንድነትም ሸሹ፣

   አልቆሙም››

አንድ መሪ ወይም ኃላፊ ከእርሱ በታች ላሉት የሥራ ድርሻ ይሰጥና ሥራውን ሠርተው በሚጨርሱበት ጊዜ መጐብኘትና ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ መሪው የሰጠውን ሥራ የማይጐበኝ ከሆነ ሥራው መልካም ይሁን መጥፎ፣ ዋጋ ያለው ይሁን አይሁን ማወቅ አይችልም፡፡ በሥራው የሚተጋውን፣ የሚለግመውንና ሥራውን አውቆ የሚያበላሸውን ሊያውቅና በሥራቸው ሽልማትና የደረጃ እድገት ሊሰጥ አይችልም፡፡ የተሠራውን ካላወቀ በዚያ ነገር ላይ ተማምኖ፣ ለሰዎች ማስረዳትም አይችልም፡፡

እግዚአብሔርም የፈጠራቸውን ሰዎች ምን እንደ ተናገሩ፣ ምን እንደ ሠሩና ምን ፍሬ እንዳፈሩ የሚጐበኝበት ጊዜ አለው፡፡ እግዚአብሔር ደህንነትንና ፍርድን ለሰዎች ለመስጠት ይጐበኛል፤ የሥራቸውንም ዋጋ ይከፍላል፡፡ ሕዝብ መሪ ከሌለው መረን ስለሚሆን፣ መሪው የሥራ ድርሻ ሊሰጥ፣ የተሠራውን ሊጐበኝና ሊመለከት ኃላፊነት አለበት፡፡ እግዚአብሔርም ለሰው ልጆች ሁሉን መልካም አድርጐ ፈጥሮ ሰጥቶአል፤ ምን ያህል እንደ ተጠቀመበት ማየትና መጐብኘት ይፈልጋል፡፡ ጉብኝቱ በሕይወት እያለንም፣ ወደ እርሱም ዘንድ ሄደንም ይሆናል፡፡ ሁለቱም የጥፋት ጉብኝት እንዳይሆንብን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባናል፡፡

በምንባብ ክፍላችን የምንመለከተው ግብጽ ሥራዋ ክፉና መጥፎ ስለነበረ፣ እግዚአብሔር በጥፋት ማለት በፍርድ ሊጐበኛት  እንዳሰበ ቃሉ ይናገራል፡፡ ‹‹ግብጽ የተዋበች ጊደር ናት፣ ጥፋት ግን ይመጣል›› (46፡20) በማለት ወደ ቅጣት እንደምትሄድ ይናገራል፡፡ ወንድሜ ሆይ ዛሬ የምትሠራው ሥራህና ተግባርህ ለደህንነት የሚያስጎበኝህ ነው ወይስ ለጥፋት? ለጥፋት ከመጐብኘትህ በፊት እግዚአብሔር ለደህንነት እንዲጎበኝህ በጸሎት ጠይቀው፡፡

 ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፣

        በመጠን እቀጣሃለሁ፣ ያለ ቅጣት

        አልተውህም ብለሃልና እርዳኝ፡፡

‹‹ጽድቅን መዝራት››

 የንባብ ክፍል፡- ሆሴዕ 10፡12

   ‹‹እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ፣

  እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፣

  እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፣ ጥጋታችሁንም እረሱ›› ቁ 12

ገበሬ ትንሽ የደመና ፊት በሰማይ ላይ ካየ፣ መሬቱን ለማረስ ይዘጋጃል፤ ዝናብ ሲዘንብ ወዲያውኑ መሬቱን ማረስ ይጀምራል፡፡ ዝናቡ የሚቀጥል ከሆነ ዘሩን ይዘራል፤ ዝናቡ በአንድ ጊዜ ብቻ ያበቃ ከሆነ ጠቀም አድርጐ እስኪዘንብ ድረስ መሬቱን በማረስ ብቻ ይቆያል፤ እንጂ ዘሩን አይዘራም፡፡ምክንያቱም በቂ ዝናብ ካላገኘ የተዘራው መብቀል ስለማይችል ነው፡፡

እግዚአብሔር ለእሥራኤላውያን የመዳን መንገድ በተለያየ ሁኔታ አዘጋጅቶላቸው ነበር፤ እነርሱ ግን አልተጠቀሙበትም፡፡ እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ ለመጨረሻ ጊዜ ጽድቁን የሚያዘንብላቸው፣ የሚልክላቸው ጊዜ እንዳለው ነቢዩ በትንቢቱ ያሳስባቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ጽድቁን እስከሚልክበት ጊዜ ድረስ እነርሱ ራሳቸውን ማዘጋጀትና ማቅረብ እንዳለባቸው ያሳስባቸዋል፡፡

ከኃጢአታቸው፣ ከክፋታቸው፣ ከተንኮላቸው… ሁሉ መመለስና ንስሓ መግባት እንዳለባቸውና ጽድቅን መዝራት ማጨድ እንዳለባቸው ይናገራቸዋል፡፡ ያልታረሰውን መሬታቸውን የሚያርሱበት፣ ያለማውን የሚያለሙበት ዘመን እንደሆነ ያመለክታቸዋል፡፡ ወንድሞችና እህቶች በኃጢአት የደነደነ ያልታረሰ፣ ቃል ያልተዘራበት መሬት በሕይወታችን ውስጥ ይኖር ይሆን? ለምን አልታረሰም? አሁንስ ለማረስ ምን የሚከለክለን ነገር ይኖር ይሆን? በሕይወታችን ጽድቅን ለመዝራት ዛሬውኑ እንነሣ፤ ጌታም ይረዳናል፡፡

 ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ በሕይወቴ ውስጥ የተደበቀ

   ያልታረሰ መሬት ካለ እይ፤ ጽድቅህንም ዝራብኝ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *