‹‹ጊዜህን ተጠቀምበት››
የንባብ ክፍል፡- መክብብ 9፡11
‹‹እኔም ተመለስሁ ከፀሐይ በታች ሩጫ ለፈጣኖች፣
ሰልፍም ለኃያላን፣ እንጀራም ለጠቢባን፣
ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፣
ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፤
ጊዜና ዕድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል››
እግዚአብሔር አምላካችን ሥራውን የሚሠራው፣ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ከሚሠሩበት የአሠራር ሁኔታ በጣም በተለየ መንገድ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስንመለከት፣ እግዚአብሔር የተጠቀመባቸው ሰዎች በጣም ዝቅተኛ የሆነ አቋምና ጐላ ብሎ የማይታይ ሕይወት የነበራቸው ሰዎች እንደሆኑ እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ ያህል ብንጠቅስ ዳዊት እረኛ፣ ጴጥሮስ ዓሣ አጥማጅ፣ ማቴዎስ ቀራጭ ነበሩ፡፡ እርግጥ እግዚአብሔር አምላክ በታላላቅ ሰዎችና በተማሩም እንደ ጳውሎስ ባሉትም የተጠቀመበት ጊዜ አለ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ እግዚአብሔር የሚመርጠው ደካማውን ሲሆን፣ ግን ፈቃዱን ለእግዚአብሔር ለማስገዛት ቆርጦ የወሰነውን ነው፡፡
እግዚአብሔር የራሱ ጥበብ፣ የራሱም ጉልበትና ብርታት ስላለው፣ ለመሥራትም የሚፈልገው በራሱ ጥበብና ኃይል ብቻ ነው (2ቆሮ. 4፡7)፡፡ ስለዚህም ኃይልንም፣ ጥበብንም፣ ሞገስንም የሚሰጥ እርሱ ስለሆነ፤ ልጆቹ በአምላካቸው ዘንድ ታላቅ ጸጋ ስላላቸው፣ ይህንን የተሰጠንን ጊዜ እያንዳንዳችን ባለንበት ዘመን በሥራ ላይ በማዋል አምላካችንን በሕይወታችን ማስከበር ይገባናል፡፡
በዘዳግም 33፡27 ላይ ‹‹መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፤ የዘላለም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው››፡፡ እግዚአብሔር ለደካማና ጥበብ ለሌላቸው፣ የእርሱ የዘላለም ክንዶች ከበታቹ እንደሆኑና በሥልጣንም ሊጠቀምባቸው እንደሚችል ይናገራል፡፡ ስለዚህ በሰጠን አገልግሎት ጊዜውን እየዋጀን፣ በአምላክ ኃይልና ብርታት ራሳችንን ጊዜአችንን እየተጠቀምንበት፣ አምላካችን በሥራው ታላቅ እንደሆነ ለዓለም ማሳየት አለብን፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ጊዜዬን ሳልጠቀምበት እንዳያልፍበኝ፣ በሰጠኸኝ ጊዜ መጠቀም እንድችል እርዳኝ፡፡
‹‹ፈጣሪህን አስብ››
የንባብ ክፍል፡- መክብብ 12፡1-14
‹‹አንተ ጐበዝ በጉብዝናህ ደስ ይበልህ፤ በጉብዝናህም ወራት ልብህን ደስ ይበለው፣ በልብህም መንገድ ዓይኖችህም በሚያዩት ሂድ፣ ዳሩ ግን ስለዚህ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ እንዲያመጣህ እወቅ፡፡ ሰው ብዙ ዘመን በሕይወት ቢኖር በሁሉም ደስ ይበለው፣ ሆኖም የጨለማውን ዘመን ያስብ፣ ብዙ ቀን ይሆናልና›› (መክ.11፡9)፡፡ የእግዚአብሔር ባሪያ ይህን በእግዚአብሔር መንፈስ ሆኖ ከጻፈ በኋላ ወዲያውኑ በመቀጠል በምዕራፍ 12፡1 ላይ ‹‹ የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፣ ደስ አያሰኙም የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ›› ብሎ ተናገረ፡፡ ሰው እንዳለ አይኖርም፤ የተለያዩ ሁኔታዎች በሕይወቱ ያልፋሉ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ፣ በሥጋችን በሠራነው ሁሉ ላይ ፍርዱን ስለሚሰጥ፣ እያንዳንዱ ሰው በእግዚአብሔር ፊት መልስ የሚሰጥበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ብዙ ሰዎች በእግዚአብሔር ትዕግሥት ባለመጠቀም በደልንና ኃጢአትን ያለአንዳች ማመንታት ሲፈጽሙ ይኖራሉ፡፡ የሁሉም ኃጢአት የሚታይበትና የሚመዘንበት ጊዜ ይመጣል፤ እያንዳንዱ ሰው ‹‹የዘራውን ሁሉ የሚያጭድበት››፡፡ ስለዚህ ሰው ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ያለበት፣ የምሕረት እጁ ተዘርግቶ ባለበት፣ አሁን በጸጋው ዘመን ‹‹እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ እኔ አሳርፋችኋለሁ›› ብሎ በሚጣራበት ጊዜ መሆን አለበት፡፡
በመጽሐፈ ምሳሌ 1፡23-31 ባለው ክፍል ላይ እግዚአብሔር ቢጠሩት የማይሰማበትና የማይመልስበት ጊዜ እንደሚመጣ ይናገራል፤ ስለዚህ የምሕረት እጁ ተዘርግቶ ባለበት ዘመን ‹‹የመዳን ሰዓት አሁን ነው›› ብሎ ቃሉ ስለሚናገር በጌታ በኢየሱስ ለማመንና ከአምላክ ጋር ለመታረቅ፣ አሁኑኑ ውሳኔ ማድረግ ይገባናል፡፡ ቃሉ ‹‹ፈጣሪህን አስብ›› ብሎ የተናገረውን፣ ዛሬ ሁሉ ነገር መልካም ሆኖ ሳለ (በተለይ ጤናችን) ወደ ፈጣሪያችን እንድንቀርብ፣ ያልቀረቡትንም እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት አለብን፡፡ የተሰጠን ጊዜ ሳንጠቀምበት እንዳያልፍብን፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ዛሬ በወጣትነት ጊዜዬ አንተን እንድከተል ስለ ረዳኸኝ አመሰግንሃለሁ፡፡
‹‹የተወደደ ጊዜ››
የንባብ ክፍል፡- ኢሳይያስ 49፡8
‹‹በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፣
በመድኃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ››፡፡
እግዚአብሔር አምላክ እርሱን አምነው ለተከተሉትና በስሙ ታምነው ላሉት የሰጠው ዕድልና ሥልጣን ተወዳዳሪ የለውም፡፡ እግዚአብሔር በቃሉ እንዲህ ይላል፡- ‹‹በተወደደ ጊዜ ሰምቼሃለሁ፣ በመድኃኒትም ቀን ረድቼሃለሁ፣ እጠብቅህማለሁ፣ ምድርንም ታቀና ዘንድ፣ ውድማ የሆኑትንም ርስቶች ታወርስ ዘንድ፣ የተጋዙትንም ውጡ፣ በጨለማ የተቀመጡትን ተገለጡ፣ ትል ዘንድ ቃል ኪዳን አድርጌ ለሕዝቡ ሰጥቼሃለሁ›› ይላል፡፡
ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ‹‹የዓለም ብርሃን የምድር ጨው›› ነው፤ በዚህም ሕይወቱ የሰይጣን ምርኮኞች ሆነው፣ በኃጢአት ጨለማ ውስጥ ያሉትን ወደ ብርሃን ለማውጣት፣ የእግዚአብሔር ልጆች ለማድረግ፣ ያዘኑትንና ያለ ተስፋ ያሉትን፣ በዚህ ዓለም ኑሮ ተጠላልፈው፣ ግራ ተጋብተው ያሉትን፣ ወደ እግዚአብሔር ሰላምና ደስታ፣ ዳርና ድንበር ወደማይገኝለት ወደ አምላካቸው እረፍት፣ የሰዎችን ልጆች ለመጥራትና ለማስገባት ሥልጣን ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጆች በዚህ በተሰጠንና በተወደደ ጊዜ ሰዎችን ከአምላካቸው ጋር እንዲታረቁ ማድረግ አለብን፡፡
ጌታም በምድር በነበረበት ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ‹‹እናንተ፡- ገና አራት ወር ቀርቶአል መከርም ይመጣል ትሉ የለምን? እነሆ እላችኋለሁ ዓይናችሁን አንሡ አዝመራው አሁን እንደ ነጣ እርሻውን ተመልከቱ›› ብሎ የጊዜውን ሁኔታ (የወንጌሉ አዝመራ) እንዲመለከቱ አድርጐአቸው ነበር፡፡ የጸጋው ዘመን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እስከሚገለጥበት ጊዜ ድረስ ምክንያትን ሳንሰጥ፣ ጊዜው ገና ነው ሳንል፣ እግዚአብሔር በልጁ ደም ዋጅቶ፣ እኛን ምስክሮች አድርጎናልና አምላካችንን መታዘዝ ይገባናል፡፡
የተወደደው ጊዜ ሳያልፍ፣ የመዳንም ቀን ሳያበቃ፣ ዛሬ ወደ አምላካችን የበለጠ ብንጠጋና ብንቀርብ መልካም ነው፡፡ ሌሎችም ወደ ክርስቶስ እንዲመጡና ሕይወታቸውንም ‹‹በተወደደ ጊዜ›› ለእርሱ እንዲሰጡ ልንመሰክርም ይገባናል፡፡ ለጌታ ሕይወታችንን ያልሰጠን ብንኖር፣ ዛሬ ምሕረት እያለ ወደ ምሕረቱ እንምጣ፡፡
ጸሎት፡- ኦ! ጌታ ሆይ በተወደደ ሰዓት ስማኝ፣
በመድኃኒትም ቀን እርዳኝ፡፡
0 Comments