‹‹አስተዛዛኝ አላገኘሁም››

 የንባብ ክፍል፡- መዝ. 69፡13

            ‹‹አቤቱ በመልካሙ ጊዜ ጸሎቴ ወደ አንተ ነው፤

            አቤቱ በምሕረትህ ብዛት በማዳንህም እውነት አድምጠኝ››፡፡

            ሰው፡- ሁሉ ነገር ሲኖረው፣ በሁሉ ነገር የተሳካለት ሲሆን በዙሪያው ከበው የሚያጫውቱትና ‹‹እንብላና እንጠጣ›› የሚሉት ለማግኘት ብዙ ችግር የለበትም፡፡ በመልካም ጊዜ ጠላት የነበረው ሁሉ አብሮ ለመብላትና ለመጠጣት ስለሚፈልግ የውሸት ወዳጅ መስሎ ይቀርባል፡፡

            ሀብት ከእጅ ሲያልቅ፣ የሚበላና የሚጠጣ ሲጠፋ፣ አጫፋሪ የነበሩት ሁሉ የት እንደ ደረሱ ሳይታወቅ ይጠፋሉ፡፡ ለእርዳታና ለማስተዛዘን ወደ እኛ የሚደርስ አንድም አይገኝም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወት በነበረበት ጊዜ ሲፈውስ፣ አጋንንት ሲያስወጣ፣ ለምፃም ሲያነፃ፣ አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ አብዝቶ ሲመግብ የሚከተሉት ብዙዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ቀራንዮ መስቀል በሚጓዝበት፣ ‹‹ትንቢት ተናገር›› እያሉ በጥፊ ሲመቱት፣ ከዚያም በመስቀል ላይ አድርገው ሲቸነክሩትም የሚያግዘው የሚያስተዛዝነው አንድም ወዳጅ አላገኘም፡፡

            በዚያ ሥቃይና መከራ ጊዜ ሊረዳው ወደሚችል ‹‹አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› በማለት ድምጹንና ጩኸቱን አሰማ፡፡ ክርስቶስ ቀደም ሲል በመልካሙ ጊዜ በጌቴሴማኒ ከአባቱ ጋር በጸሎት በመገናኘት ፈቃዱን ለመፈጸም የራሱን ፈቃድ አስረከበ፡፡ በመስቀል ላይ ሆኖ ‹‹ተጠማሁ›› እያለ ሲጮህ አባቱ ፊቱን ቢያዞርበትም፤ ጸሎቱ ሊሰማለት በሚችለው በምቹ ጊዜ ወደ አባቱ በመቅረቡ፣ በመጨረሻ ተልዕኮው በመፈጸሙ የድል ጩኸት በመጮህ ተፈጸመ አለ፡፡

            ወንድሞችና እህቶች ዛሬ በችግራችንና በመከራችን ጊዜ፣ ስንት ቀን ወደ ሰዎች እርዳታ ለማግኘት ሮጠን ይሆን? እርዳታ በምንፈልግበት ጊዜ የሚያስተዛዝነን አናገኝም ይሆናል፤ ስለዚህ እንደ ዳዊት በመልካሙ ጊዜ በጸሎት ምሕረቱንና ማዳኑን ከእርሱ ለማግኘት ወደ አምላካችን መቅረብ አለብን፡፡

 ጸሎት፡- አምላኬ ሆይ፡- ‹‹አስተዛዛኝም ተመኘሁ አላገኘሁም፣ የሚያጽናናኝም አጣሁ፤ አንተ ረዳቴና አጽናኜ ሁን፡፡

‹‹ የደስታ ዘመን››

 የንባብ ክፍል፡- መዝ. 90፡14

            ‹‹በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን፤

            በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል፣ ሐሤትም እናደርጋለን››፡፡

            የሰው ልጅ በሚኖርበት ዘመን ሁሉ፣ የደስታ፣ የሐዘን፣ የጥጋብ፣ የራብና የመጠማት ጊዜ እንዲሁም ሌሎችም ብዙ ነገሮች በሕይወት ዘመኑ ያሳልፋል፡፡ ይወጣል፣ ይወርዳልም ለመኖር በብዙ መንገድ የሕይወቱን ዓላማ ይቀይሳል፡፡ ሁሉም አመቺና መልካም መስሎ ሲታየው፣ የሚኖርበት ዘመን በጣም ረጅም እንደ ሆነ ይመስለዋል፡፡

            ሙሴ በዚህ በመዝሙር ክፍል በሚጸልየው ጸሎት ትውልድንና ዘመንን ያነጻጽራል፤ መልሶም በፊቱ ከቀሩት ዘመናት ጋር ያሉትን ሁኔታዎች ይመለከታል፡፡ ብዙ ትውልዶች ያለፉበትን ሺህ ዓመት እንዴት ረጅም እንደ ሆነ ተመልክቶ፣ ዘወር ሲል ግን ለእግዚአብሔር እንደ አንድ ቀን ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ስለዚህም ያለችው አጭር ዘመን መሆንዋን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፤ ‹‹የዘመኖቻችን ዕድሜ ሰባ ዓመት፣ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፣ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤›› (90፡10) ስለዚህ በከንቱ ያለፈችዋ ጥቂት ጊዜ (ዘመን) እንኳ ብትሆን ተቀጥላ ልታበረታ አትችልም አልፋለችና፡፡ በፊታችን ያለችው ያላየናት፣ ያልያዝናት ሰከንድ፣ ደቂቃ፣ ሰዓት፣ ቀን፣ ወርና ዓመት አዲስ ናቸው፤ በዚህ በቀረን ጥቂት ዘመን በደስታ ለማሳለፍ የበለጠ ወደ ጌታ እንጠጋ፡፡

            የጊዜ ሁሉ ጌታ የሆነው ጌታ፣ በዚች በቀረችን አጭር ዘመናችን፣ ክፉ ባየንበት ዘመን ፋንታ ፣ ማለዳ ማለዳ በሚሰጠን ምሕረት ሐሤት እንድናደርግ ይወዳል፡፡ ይህ ደስታና ሐሤት የሚገኘው ከእግዚአብሔር ጋር በምናደርገው ኅብረት ነው፤ ጌታም በምድር በነበረበት ጊዜ ‹‹አብ እንደ ወደደኝ እኔ ደግሞ ወደድኋችሁ… ደስታዬም በእናንተ እንዲሆን ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን ነግሬአችኋለሁ›› (ዮሐ. 15፡9-11) በማለት ደቀ መዛሙርቱ ዘመናቸውን በደስታ እንዲያሳልፉ ነግሮአቸዋል፡፡ ሕይወታችን በእውነተኛ ደስታ እንድታልፍ ከማድረጉም በላይ፣ ሌሎችንም በማገልገል እንድንተርፍ ይረዳናል፡፡

            ዘመናችን ሲያልቅ  በምሬት ሳይሆን በደስታና በበረከት እንዲሆንልን፣ በከንቱ የምናሳልፈውን ጊዜ ከአምላካችን ጋር የምንሆንበትና ሰዎችን የምናድንበት ጊዜ እናድርገው፡፡ ጥሎን የሚያልፈው ጊዜ ተመልሶ የእኛ አይሆንም፡፡ ዛሬ የተሰጠንን ዘመን በመዋጀት ለደስታችን ይሆን ዘንድ በጥንቃቄ እንጠቀምበት፡፡

ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በምድር የሰጠኸኝን ዘመን በደስታና በእርካታ እንድጨርስ እርዳኝ፡፡

‹‹ለሁሉ ዘመን አለው››

  የንባብ ክፍል፡- መክብብ 3፡1-9

            ‹‹በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፣ ብርድና ሙቀት፣ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም›› (ዘፍ.8፡22) እግዚአብሔር አምላካችን ይህችን ምድር ሲፈጥራት ጊዜና ዘመናትን እንዳደረገላት ሁሉ በውስጧም ለተፈጠሩት ፍጥረታትና ለሰዎች ልጆችም ሁሉ ዘመንና ጊዜን ወስኖአል፡፡ በመክብብ ላይ የምንባብ ክፍላችን የሚያመለክተው በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱት ሁኔታዎች ደስታም ሆነ ችግር፣ ሳቅም ሆነ ልቅሶ፣ ብልጽግናም ሆነ ድህነት እነዚህ ሁሉ ‹‹ጊዜ›› እንዳላቸው ነው፡፡ ዛሬ የሳቀ ነገ ሊያለቅስ፣ ዛሬ የከፋው ነገ ሊደሰት፣ ዛሬ የበለጸገ ነገ ሊደኸይና ሊያጣ ሊለምንም ይችላል፤ ዛሬ የሠራ ነገ ላይሠራ ይችላል፤ ስለዚህ ሰባኪው ሊገልጽ የወደደው ለሁሉም ነገር ጊዜ እንዳለው ነው፡፡

            የእግዚአብሔር ሰው ለአምላኩ የሚሠራበት ጊዜ አለ፣ የማይሠራበትም ጊዜ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ወንጌል 17፡4 ላይ ‹‹እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርኩህ›› ብሎ ያለው፡፡ እግዚአብሔር ለሰዎች ሁሉ በየዘመናቱ የሚያዘጋጅላቸው የሥራ ድረሻ አለው፤ ምንም ዓይነት ሥራ ይሁን በታማኝነት፣ በቅንነትና በትጋት ጭምር አከናውነን መገኘት አለብን፡፡ ለሁሉ ዘመን ስላለው፣ አሁን እግዚአብሔር ለዚህ ዘመን የመደበልንን የሥራ ድርሻ፣ በሌላ ጊዜ ላናገኘው ስለምንችል፣ መሥራት ያለብንን ታማኞች ሆነን በመገኘት አሁን መሥራት ያለብንን አስቀድመን መፈጸም አለብን፡፡

            እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፣ ሩጫውን ጨርሻለሁ፣ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፣ ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል›› (2ጢሞ.4፡7) ብሎ እንዳለው እግዚአብሔር በዚች ምድር ላይ የሰጠን ዘመን እስከምታልቅበት ጊዜ ድረስ፤ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ‹‹ቃሉን ስበክ በጊዜውም ያለጊዜውም ጽና፣ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርክ፣ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም›› ብሎ እንዳሳሰበው፤ እኛም ሳይገዛን፣ ገዝተነው እግዚአብሔር በሰጠን የጊዜ ድርሻ ታማኞች ሆነን ማከናወን አለብን፡፡

 ጸሎት፡- ጌታ ሆይ በፊቴ የዕረፍት ዘመን እንዳለኝ አውቃለሁ፤ ዛሬ ግን በሰጠኸኝ ጊዜ እንዳገለግልህ እርዳኝ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *