ውድ የተልዕኮ ኦን ላይን አገልግሎት ተከታታዮች ላለፉት አራት ዓመታት ተልዕኮ teleko.org በሚለው ድህረ ገጽ ‹‹ተልዕኮው የት ደርሷል?››፣ ‹‹የዕብራውያን ጥናት››፣ ‹‹የመጽሐፍ ቅዱስ አጠናን ዘዴ›› እና ‹‹ክርስቲያናዊ አስተምህሮ›› በሚሉ ተከታታይ የሆኑ ጽሑፎችንና ትምህርቶችን ስናጋራ መቆየታችን ይታወቃል፡፡
አሁን ደግሞ በደርግ ዘመን በሠፈረ ገነት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን (በኢትዮጵያ ገነት ቤተ ክርስቲያን) ‹‹መና›› በሚል ለግል፣ ለቡድን እና ለቤተሰብ የሚሆን ዕለታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የጸሎት መምሪያ፣ እስከ ተከለከለ ድረስ፣ በሳንሱር ክፍል ታይቶና ተፈቅዶ በመጋቢ (ቢሾፕ) ኅሩይ ጽጌና በወ/ዊ አምበርብር ገብሩ አዘጋጅነትና አርታኢነት በየወሩ የሚታተም ጽሑፍ ነበር፡፡ ከሠፈረ ገነት አጥቢያ ወንድም ብርሃኑ ከበደ (ወደ ጌታው ዕቅፍ የሄደ)፣ ወንድም ሰብስቤ ዋቅቶላ፣ ወ/ዊት መስተዋት በቀለ፣ ወ/ዊት መዓዛ በቀለ፣ ወንድም (መ/ቢ) ዓለማየሁ ደምሴ፣ ወንድም ብርሃኑ ዘርጋው፣ ከፊንላንድ ሚስዮን ሚ/ር ፓውሊ ሩኖሊና አምደኞች ሲሆኑ፤
በዚህ ጽሑፍ ላይ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችም በተጨማሪ ተሳትፎ ነበራቸው፤ ከሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ወንድም ተስፋሁን አግደው፣ አባይ ኃይሉ(በቅርቡ ወደ ጌታ እቅፍ የሄዱ)፣ ንጋቱ ገ/መድህን፣ ሚናስ ብሩክ፣ እህት (መጋቢ) ጥሩወርቅ መስፍን፣ እህት ጌጤነሽ ለገሠ፤ ከአማኑኤል ባብቲስት ቤተ ክርስቲያን መጋቢ በቀለ ላቀው (ወደ ጌታ ዕቅፍ የሄደ) እና እህት አልማዝ ዘውዴ (ባለቤቱ)፤ ከመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ (ሐዋርያው) ዳንኤል መኮንን፤ ከሕይወት ብርሃን ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ምክሩ በቀለ እና ከእምነት ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ወንድም ተወልደመድህን ሀብቱ፣ አምደኞች ነበሩ፡፡
በዚያ በችግር ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከ1969 እስከ 1971 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ከራሷ አልፋ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናትም የሚጠቀሙበት፣ ተወዳጅ የሆነ ለጸሎት መመሪያ (ዲፎሽን) የሚሆን ‹‹መና›› የተባለው ጽሑፍ በየወሩ እየወጣ ምዕመናን ተጠቅመውበታል፡፡ በስደቱ ዘመን ለብዙ ምዕመናን ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው መጽናናትና ማደግ ምክንያት ከሆናቸውና ጌታ ከተጠቀመበት ጽሑፍ በተከታታይ ልናካፍላችሁ ወደድን፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ብዙ የምንማራቸው ነገሮች እናገኛለን፤ በዚያን ጊዜ አማኞች የነበራቸውን የሕይወት አቋም፣ በመከራ ውስጥ ጌታን መውደዳቸው፣ የአብያተ ክርስቲያናት ትብብር ምን እንደሚመስል ያሳየናል፡፡
ከዚህ ጽሑፍ በተከታታይ በየቀኑ ለጸሎትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚሆኑትን ለሦስት ቀናት ተዘጋጅተው ከነበሩት በአንድነት እንለቃለን፤ እናንተ ለየቀኑ አድርጋችሁ እንደሚያመቻችሁ ለጸሎት ተጠቀሙባችው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የምንለቀው ‹‹ዘመኑን ዋጁ›› በሚለው ርዕስ ሥር ለአንድ ወር ተዘጋጅተው የነበሩትን ጽሑፎች ይሆናል፡፡
‹‹የሞቱ ቀን››
የንባብ ክፍል፡- ዘፍጥረት 47፡29 ‹‹የእስራኤል የሞቱ ቀን ቀረበ ልጁንም ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው፡- በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፣ በግብጽ ምድርም እንዳትቀብረኝ ምሕረትንና እውነትን አድርግልኝ፤ ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብጽ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፣ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ፡፡ እርሱም፡- እንደ ቃልህ አደርጋለሁ አለ››፡፡
በዚህ ዓለም ላይ ሞት ከሁሉ ነገር የበለጠ አሰፈሪ ነው፤ በሞት ኃይል ተይዞ ወደ መሬት የማይመለስ ማንም የለም፡፡ ሞትን በገንዘብ፣ በዕውቀት፣ በጥበብና በኃይል መቋቋም ስለማይቻል፣ ሁሉም በየተራው ወደ ምድረ-ከርስ ይገባል፡፡ በሞት ኃይል ተይዘን ከመሄዳችን በፊት ሕይወታችንን እንዴት መምራት አለብን? ምን ማድረግ (መሥራት) አለብን?
በዚህ በምንባብ ክፍላችን ይህን የመሰለ ታሪክ በያዕቆብ (የአብርሃም የልጅ ልጅ) ላይ ሊፈጸም ሲል የተፈጸመውን ሁኔታ እንመለከታለን፡፡ የእስራኤል ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብፅ ወርደው መኖር እንዴት እንደ ጀመሩና የተደረገላቸውንም መልካም መስተንግዶ ክፍሉ ያሳየናል፡፡ ዮሴፍ በወንድሞቹ አማካኝነት ተሽጦ ወደ ግብፅ ወረደ፤ ከዚያም በረሃብ ምክንያት ወንድሞቹም ዮሴፍ ወዳለበት ምግብ ፍለጋ መጡ፡፡ ዮሴፍም ወንድሞቹ መሆናቸውን በመናገር ራሱን ከገለጠላቸው በኋላ አባታቸውን ይዘው እንዲመጡና በዚያ እንዲቀመጡ አደረገ፡፡ ያዕቆብም ዮሴፍ የሞተ እንጂ በሕይወት ያለ አይመስለውም ነበር፤ ነገር ግን ወደ ግብፅ መጥቶ ልጁን በተገናኘው ጊዜ በጣም ደስ አለው፡፡
ያዕቆብም ከልጆቹ ጋር በግብፅ አገር አስራ ሰባት ዓመት ተቀመጠ፡፡ በዕድሜውም ገፋ ያለ ስለ ነበረ፣ የመሞቻው ቀን በተቃረበ ጊዜ ልጁን ዮሴፍን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ ‹‹በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆንኩ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፣ በግብፅ ምድርም እንዳትቀብረኝ ምሕረትንና እውነትን አድርግልኝ፤ ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብፅ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፣ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ››፡፡
እኛም አንድ ቀን በሞት ኃይል ተይዘንና ተገደን የምንሄድበት ቀን ይመጣል፤ ነገር ግን ያ ከመሆኑ በፊት የት እንደምንሄድ፣ የት እንደምናርፍ፤ እንደ ያዕቆብ ምርጫ ብናደርግ መልካም ነው፡፡ ዛሬ የምንኖርበትንም ዘመን ለወደፊት ለምንኖርበት ሥፍራ የምንዘጋጅበትና መልካም ሥራ የምንሠራበት ጊዜ መሆን አለበት፡፡ እግዚአብሔር በሰጠን ዕድሜአችን፣ ስንት ጊዜ ይሆን ሳንጠቀምበት ያለፈብን? አሁንስ በቀሪ ዘመናችን ሳንጠቀምበት የሞታችን ቀን ድንገት ይደርስብን ይሆን? በጊዜያዊ ጥቅም ተይዘን የመጨረሻውና የዘላለም መኖሪያችን የሆነውን ቤታችንን እዳናጣ፡፡
ጸሎት፡- ጌታ ሆይ ያላንተ ተስፋ ብሞት የዘላለም ሥቃይ ስለሚጠብቀኝ ተስፋህን እንድይዝ እርዳኝ፡፡
‹‹ጊዜአቸው ሳይደርስ››
የንባብ ክፍል፡- ኢዮብ 22፡16-17 ‹‹ጊዜአቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፣ መሠረታቸውም እንደ ፈሳሽ ውኃ ፈሰሰ፡፡ እግዚአብሔርንም፡- ከእኛ ዘንድ ራቅ ሁሉንም የሚችል አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል? አሉት፡፡››
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ስንመለከት፣ እግዚአብሔርን ለማመንና አምላክ ለማድረግ የማይፈልጉ ሰዎችን ታሪክ አቅርቦልናል፡፡ እግዚአብሔር ለመዳንና ከእርሱ ጋር ለመታረቅ ዕድል ሲሰጣቸው ‹‹ከእኛ ራቅ ምንም ልታደርግልን አትችልም›› በማለት ልባቸውን እያደነደኑ ጊዜአቸው ሳይደርስ በሞት እየተነጠቁ የተወሰዱ ብዙ ሰዎች ናቸው፡፡
በዚህ የምንባብ ክፍላችን የምንመለከተው፣ ቴማናዊው ኤልፋዝ፣ ኢዮብ በእግዚአብሔር ያለጊዜው እንዳይነጠቅ፣ ራሱን እንዲመረምርና ንስሐ እንዲገባ ይመክረዋል፡፡ ምንም እንኳን ኢዮብ ጻድቅ ሰው ቢሆንም፣ ራሱን መመርመር እንዳለበት ያሳስበዋል፤ ምክንያቱም ከመከራው ብዛት የተነሳ በእግዚአብሔር ላይ እንዳያማርርና ኃጢአት እንዳይሠራ ያስጠነቅቀዋል፡፡ የኢዮብን ታሪክ ስንመለከት ምክሩን ተግባራዊ እንዳደረገ እንመለከታለን፡፡
አሁን እኛ ባለንበት ዘመን፣ ከምንጊዜውም በላይ እግዚአብሔርን የሚያማርሩና የሚሳደቡ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ እነርሱ የሚመለከቱት የሚደርስባቸውን መከራና ችግር ብቻ እንጂ፣ ለምን እንዴት እንደ ደረሰባቸው ራሳቸውን በመጠየቅ አይመረምሩም፡፡ በዚህ ምክንያት በሕይወታቸው ንስሐ የተባለውን በፍጹም አያውቁትም፡፡ እንዲያውም እግዚአብሔር የመዳን ዕድል ሲሰጣቸው በቀራንዮ መስቀል ላይ ስለ ሞተው ልጁ፣ በቃሉና በመንፈስ ቅዱስ ሲናገራቸው፣ ለማሰብና ንስሐ ገብተው ለመቀበል ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ አንዳንዶችም ሳያስቡት በተለያየ ድንገተኛ አደጋ ምክንያት፣ ላይመለሱ ወደ ሞት ያዘግማሉ፡፡
ዛሬ እኔና አንተ፣ አንቺ፣ እናንተ እንዴት ነን እግዚአብሔር በሰጠን ዕድሜ (ጊዜ) ተጠቅመን ወደ ንስሐ ቀርበናል ወይስ የንስሐው ጊዜ ገና ነው እያልን ምክንያት እንሰጣለን፡፡ የመዳን ቀን ዛሬ ስለሆነ የተሰጠንን ጊዜ ሳንጠቀምበት እንዳያልፍብን፡፡
ጸሎት፡-ጌታ ሆይ ስለ ተሰጠኝ ድነት አመሰግንሃለሁ፣ የሕይወቴ ጌታ ላደርግህ እፈልጋለሁ፤
ና ወደ ልቤ ገብተህ ንገሥ፡፡
0 Comments