በአገራችን ስመ ጥር የሆኑ ወንድና ሴት ሯጮች ነበሩ፣ አሉም፡፡ ለምሳሌ ያህል ከወንዶች አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና (የክብር ዶክተር) ቀነኒሳ በቀለ፤ እንዲሁም ከሴቶች ደግሞ ደራርቱ ቱሉ፣ ጌጤ ዋሚ፣ መሠረት ደፋርና ጥሩነሽ ዲባባ (የክብር ዶክተር) የመሳሰሉትን ሩዋጮች ሁሉ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ አትሌቶች በዓለም አደባባይ ዝም ብለው ታዋቂ አልሆኑም፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን በዓለም ታዋቂና ምርጥ አትሌት ለመባልና የአገራቸውንም ስም ለማስጠራት ዓላማ ነበራቸው፡፡ ይህንን ዓላማ እውን ለማድረግ ዕቅድ ስለነበራቸው በሚሰለፉበት የሩጫ ውድድር ሁሉ ዓላማቸው ማሸነፍ ነበር፡፡ በስፖርት እየተወዳደረ ለማሸነፍ ዓላማ ያለው ስፖርተኛ ሁሉ የሚፈለግበትን ዲሲፒሊን፣ ብቃት፣ ሥልጠናና የአመጋገብ ሥርዓት ሊጠብቅ ይገባል፡፡ አትሌቶች በተሰለፉበት ሁሉ ድል አድርገው የሚመለሱት የአትሌቲክስ ሕጎችንና ደንቦችን ማወቅና ማክበር ሲችሉና ብቁ ሆነው ሲገኙ ነው፡፡ የሚያሰክር ነገር የሚጠጣ፣ ዕፅ የሚጠቀም ከሚጎዱ ምግቦች ራሱን የማያገል ሯጭ ባለ ድል ሊሆን አይችልም፡፡ እንደ እነዚህ ስፖርተኞች ዓላማ ሲኖረንና ለአንድ ነገር የተሰጠን ስንሆን በሕይወታችንና በአገልግሎታችን ውጤታማና ፍሬአማ እንሆናለን፡፡
ሉቃስም መልእክቱን በሚጽፍበት ጊዜ ዓላማውን በሚገባ ያውቅ ነበር፣
- የመልእክቱ ዓላማ ሕያው የሆነው ክርስቶስ ከሞት ከተነሳ በኋላ በመቀጠል ያደረገውንና የሠራውን ለወዳጁ መግለጽ፣
- ሕያው የሆነው የክርስቶስ ወንጌል በሐዋ. 1፡8 መሠረት (ክርስትና) እንዴት እንደተስፋፋና አሕዛብ ወንጌልን እንዴት እንደተቀበሉ መግለጽ፣
- ወዳጁ ቴዎፍሎስ የክርስቶስን ሕያውነት በሕይወቱ ማየት እንዲችል ማድረግ ናቸው፡፡ (የዚህ ጽሑፍ አንዱ ዓላማም የክርስቶስን ሕያውነት በሕይወታችን ማየት እንድንችል ማድረግ ነው፡፡)
ሉቃስም ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ይልቅ፣ ለአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ትኩረት የሰጠበት ምክንያት የእኔንም ትኩረት በመሳቡ፣ ጠለቅ ያለ ጥናት እንዳደርግ አስገድዶኛል፡፡ በመጀመሪያ፣ ክርስቶስ በዚህ ምድር ለ33 ዓመት ተኩል ሲመላለስ ቆይቶ ተልዕኮውን ከፈጸመ በኋላ፣ የሰው ልጆችን ኃጢአት በመስቀል ተሸክሞ ሞተ፤ በሦስተኛውም ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ ለጥቂቶች አማኞች ብቻ፣ በተለያየ ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ 11 ጊዜ በአካል ከመገለጡ በስተቀር፣ በመንፈስ ሕያው ሆኖ በመመላለስ በአባቱ ቀኝ ተቀምጧል፡፡ ሉቃስ በጽሑፉ ክርስቶስ ከሞት በመነሳቱ ምክንያት ወንጌሉ በተለያዩ ከተማዎችና ገጠሮችም እየተሰበከ እንዳለ በግልጽ ያሳየናል፡፡ ወንጌሉ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማሪያ መስፋፋቱን ለማሳየት የሰጠው ምዕራፍ 9 ሲሆን ወንጌሉ ወደ አሕዛብ(ዓለም ሁሉ) ስለ መድረሱ የሰጠው ምዕራፍ 19 ነው፡፡ ይህም ሉቃስ ለአሕዛብ የሰጠው የጽሑፉ መጠን ፣ የጸሐፊውን ዋና ዓላማና ትኩረቱን ያሳየናል፡፡ እኛስ በሕይወታችን በዚህች ምድር ለ60 እና 80 ዓመት ስንኖር፣ ሠፊ ሥፍራ የሰጠነው ምንድን ነው? በዚህ ምድር ስንኖር የሕይወታችን ዋና ዓላማ አድርገን የያዝነውና የተሰጠንለት ነገር ምንድን ነው?
0 Comments