ቀደም ብለን እንዳየነው በሦስቱም አመለካከቶች የሺውን ዓመትና የታላቁ መከራ መኖር አይክዱም፡፡ ነገር ግን በሚፈጸምበት ቦታና ጊዜ ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ ነው ያለነው ሲሉ፤ ሌሎቹ ደግሞ ሺውን ዓመት ጌታ በሰማይ ሆኖ እየገዛ ይገኛል ይላሉ፣ ሌሎቹ ደግሞ ጌታ ገና ወደፊት ሲመጣ  በምድር የሚፈጸም ግዛት ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡

     ስለ ሙታን ትንሣኤ ሲነሣም እንዲሁ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፤ አንዳንዶችም የማይቀበሉም ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ሰዎች ተቀበሉትም አልተቀበሉትም፤ መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ እና በአዲስ ኪዳን የሙታን ትንሣኤ እንዳለ የሚናገረውን ክፍል በጥናታችን እንመለከታለን፡፡ በብሉይ ኪዳን በኢዮብ 19፡25-27 ‹‹እኔን ግን የሚቤዠኝ ሕያው እንደሆነ፣  በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንዲቆም፣ ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፣ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ›› ሲል መዝሙረኛው ደግሞ በመዝ. 15፡9-10 ላይ ‹‹… ሥጋዬ ደግሞ በተስፋ ታድራለች ነፍሴን  በሲኦል አትተዋትምና፣ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትወውም›› በማለት ስለ ትንሣኤ ያላቸውን ተስፋ ይገልጻሉ፡፡ ዳንኤልም በትንቢቱ ‹‹በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፣ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጉስቁልና›› (12፡1-3)፣ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፣ ሬሳዎችም ይነሣሉ… ምድርም ሙታንን ታወጣለችና›› ሲል (26፡19)፣ በሆሴዕ ላይ ደግሞ ቃሉ ‹‹ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፣ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ማጥፋትህ ወዴት አለ? (13፡14) የሚል የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የያዘ ያስነብበናል፡፡  

      በብሉይ ኪዳን እነዚህን የመሰሉ የትንሣኤ ተስፋ አሳይቶናል፤ በአዲስ ኪዳን ደግሞ ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ  ከራሱ የተነገሩትን የትንሣኤ ተስፋዎች እንመልከት፡፡ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ (የእኔን) ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል… በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉ ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ›› በማለት ቃሉን ለሚሰሙ ሁሉ፣ በእርሱ ቢያምኑ በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚያስነሳቸው አረጋገጠላቸው (ዮሐ.5፡25-29፣ 6፡39-40፣ 44-45፣ ሉቃ. 14፡13-14፣ 20፡35-36)፡፡ ጌታ በቃሉ ትንሣኤ አለ ካለን ልንቀበለው የሚገባ እውነት ነው፡፡

     የትንሣኤያችን መሠረት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅድሚያ ራሱ በኵር ሆኖ በመነሣት ያረጋገጠው እውነት ነው፡፡ የእርሱ የትንሣኤው ቁም ነገር ምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚከተሉትን ሀሳቦች ይሰጠናል፡፡

  1. የክርስቶስ ትንሣኤ፡- የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በከፍተኛ ደረጃ  የእግዚአብሔርን ኃይል

 የገለጠድርጊት ነው፡፡ የእርሱ ትንሣኤ ከኃይል ጋር የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ በመለኮት የታወጀበትና የተረጋገጠበት ነው፡፡የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ፣ እግዚአብሔር ጌታና ክርስቶስ አድርጎ የሰው ሕይወት እንዲድንበት የገለጸበትና  እርሱ ብቻ ሰዎችን ሁሉ ከኃጢአታቸው ሊያድናቸው እንደሚችል ብቸኛ አዳኝ መሆኑን  የመሰከረበት ነው፡፡ የጌታ ትንሣኤ እርሱ ለሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ጽድቅ መሆኑን ያረጋገጠበት ሲሆን፣ በሰዎች ላይ ፈራጅ ለመሆኑ ፍጹም መለኮታዊ ማረጋገጫ ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መነሣት የሰዎች ሁሉ አካል እንደሚነሣ ተስፋ የሚሰጥ መለኮታዊ ማረጋገጫና የልጁ ትንሣኤ እግዚአብሔር አንድያ ልጁ ንጉሥ መሆኑን ያወጀበትና የጌታ ትንሣኤ ለአማኞችም፣ ለኃጢአተኞችም መሠረት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችን ስለ ሰዎች ትንሣኤ ሲያስተምረን ሳለ፣ ሰዎች ሁሉ በአንድ ጊዜ እንደማይነሡ ያስተምረናል፡፡ የጻድቃንና የኃጢአተኞች የሙታን ትንሣኤ እንደሚሆን ቃሉ ያሳየናል፡፡

  • የአማኞች ትንሣኤ፡- ጌታችን ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 11፡25 ላይ ‹‹ኢየሱስም ትንሣኤና

ሕይወት እኔ ነኝ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፣ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም›› ባለው መሠረት በክርስቶስ አምነው በሥጋቸው ቢሞቱም እንኳ ክርስቶስ አንድ ቀን ሲመጣ ይነሣሉ፡፡ የአማኞች ትንሣኤ የሚያካትታቸው የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን፣ የአዲስ ኪዳን ቅዱሳንና የመከራው ቅዱሳን ሁሉ በፊተኛው ትንሣኤ የሚነሡ ናቸው፡፡ የአማኞች ትንሣኤ የሚሆነው ከሰባት ዓመት መከራ በፊትና በኋላ ላይ የሚፈጸም ይሆናል፡፡ በሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ አማኞች በሰጠው ትምህርት መሠረት፣ ከመከራው በፊት የሚነሱት በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ያንቀላፉት ናቸው፤ (1ተሰ. 4፡13-17)፡፡

      በትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 7፡18፣22 መሠረት ከሰባቱ ዓመት መጨረሻ ላይ የሚነሱት የብሉይ ኪዳኑና የመከራው ቅዱሳን (ከእያንዳንዱ ከእሥራኤል የተመረጡና ለሐሰተኛው ክርስቶስ አንሰግድም በማለት በመስዋዕትነት ያለፉ ቅዱሳንና ሊቆጠሩ የማይችሉ ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገንና ከቋንቋ ብዙ ቅዱሳን ያሉበት ራዕ. 7) ሲሆኑ፤ ቀደም ብለን እንዳየነው የፊተኛው ትንሣኤ ተካፋዮች ናቸው (መዝ. 17፡15፣ ኢሳ. 26፡19)፡፡

      እንዲሁም በኢሳይያስ ምዕራፍ 28 ላይና በዳንኤል ምዕራፍ 9 ላይ እንደምናገኘው በ69 እና በ1 ሱባኤ መካከል የቤተ ክርስቲያን ዘመን ጣልቃ ገብቶ እናገኛለን፡፡ ይህ ዘመን ሲያበቃ የያዕቆብ መከራ (የ7 ዓመቱ መከራ) ይሆናል፡፡ (ኤር. 30፡7)  ‹‹በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፣ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፣ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ›› (ራዕ.20፡4-6) በሚለው መሠረት የብሉይና የመከራው ቅዱሳን ትንሣኤ ይሆናል፡፡

  • የኃጢአተኞች ትንሣኤ፡- የኃጢአተኞችን ትንሣኤ እግዚአብሔር በቃሉ ብዙ ትኩረት ሰጥቶት ሰፋ ያለ

ገለጻአናገኝም፤ ቢሆንም ከቃሉ ውስጥ ጥቂት ማስረጃዎችን እንመልከት፡፡ ‹‹ክፉ ሰው(wicked dead) ከትዕቢቱ የተነሣ እግዚአብሔርን አይፈልግም፣ በሐሳቡም ሁሉ አምላክ የለም›› (መዝ.10፡4 ዐ.መ.ት) ይላል፡፡ በሮሜ ምዕራፍ 1፡21-25 ላይ ‹‹እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፣ ምስጋናም አላቀረቡለትም፣ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፣ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ፡፡ ጥበበኞች ነን ቢሉም፣ ሞኞች ሆኑ፣ የዘላለም አምላክን ክብር ምዉት በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ በእንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረት መልክ መስለው ለወጡ፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር በኃጢአት በተሞላው የልባቸው ምኞት እርስ በርሳቸው የገዛ አካላቸውን እንዲያስነውሩ ቅድስና ለሌለው ሩካቤ ሥጋ አሳልፎ ሰጣቸው፡፡ የእግዚአብሔርን እውነት በሐሰት ለወጡ፣ በፈጣሪ ፈንታ ፍጡር አመለኩ፣ አገለገሉም፣ ፈጣሪም ለዘላለም የተመሰገነ ነው›› (ዐ.መ.ት) ይላል፡፡

በራዕይ ምዕራፍ 21፡8 መሠረትም ‹‹ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኩሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኞችም የአስማተኞችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፣ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው፡፡›› እግዚአብሔር ይህን ስለ አወጀ ቃሉ አይታጠፍም፡፡ በቃሉ እንዲህ ብሏል ‹‹ኃጢአታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ›› (ዘኁ. 32፡21) በተጨማሪም ‹‹አትሳቱ እግዚአብሔር አይዘበትበትም፡፡ ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና›› (ገላ. 6፡7)፤ አንድ ሰው  በእግዚአብሔር ጸጋ በልጁ በክርስቶስ ደም ታጥቦ ከኃጢአቱ ካልነፃ በስተቀር፣ ኃጢአቱ በአካል በነበረበት ጊዜ፣ ወይም በልጁ ዘመን፣ ወይም በራሱ በትንሣኤ ጊዜ የኃጢአቱ ቅጣት ያገኘዋል፡፡ በውድ ልጁ የተገለጠውን ታላቁን ድነት ችላ በማለታቸው ምክንያት የዘላለምን የሞት ቅጣት ይቀበላሉ፡፡ በክርስቶስ አምነው የከበረ አካል እንደ ለበሱት ያለ የከበረ አካል ሳይሆን፤ ያልዳኑ ሰዎች በትንሣኤ የሚለብሱት የትንሣኤ አካል ኃጢአተኛነታቸውን የሚያሳይ ይሆናል፡፡ ለፍርድ በሚነሡበት ጊዜ የእሳት ባሕር ሥቃይ ሊሰማው የሚችልና ለዘላለም የሚኖር ልዩ አካል ለብሰው ከሙታን ይነሱና ፍርዳቸውን ከተቀበሉ በኋላ ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነብይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር … ተጥለው ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ (ራዕ.20፡7-10)፡፡      

ከዚህ በላይ እንዳየነው ሦስቱም አመለካከቶች በጻድቃንና በኃጥአን ትንሣኤ መኖር ያምናሉ፡፡ ነገር ግን በሺህ ዓመቱ ግዛትና በመከራው ዘመን እንደሚለያዩ በሙታን ትንሣኤም ይለያያሉ፡፡ ሁሉም የየራሳቸው አተረጓጐምና አቀማመጥ አላቸው፡፡

      ሀ) ድህረ- ሺህ ዓመቶች ሺህ ዓመቱ ሲያልቅ (የቤተ ክርስቲያን ዘመን) ክርስቶስ ሲመጣ የሞቱ የአማኞችና የማያምኑ ሰዎች ትንሣኤ ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡

      ለ) አልቦ- ሺህ ዓመቶች ሺህ ዓመቱን ጌታ በሰማይ ሆኖ እየገዛ ያለው ጊዜ ሲያበቃ፤ የጌታ ዳግም ምፅዓት ይሆናል፡፡ በዚያን ጊዜ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ የአማኞችና ያላመኑ ሰዎች ትንሣኤ በአንድ ጊዜ ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡

      ሐ) ቅድመ- ሺህ ዓመቶች ደግሞ በታላቁ መከራ የተለያየ ሦስት አቋም እንዳላቸው ሁሉ በትንሣኤም ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው፡፡

በድኅረ- ፍዳ የሚያምኑ መነጠቅና ትንሣኤ ከታላቁ መከራ በኋላና ከሺው ዓመት አገዛዝ በፊት ይፈጸማል ብለው ያምናሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በታላቁ መከራ ግማሽ ታልፋለች የሚሉት (ማዕከላዊ የፍዳ ዘመን) ግማሹ መከራ እንዳለቀ መነጠቅና ትንሣኤ ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡ በቅድመ-ፍዳ ዘመን የሚያምኑ መነጠቅና ትንሣኤ ከመከራው በፊት ይሆናል ብለው ያምናሉ፡፡ ይህንንም የመጀመሪያው ትንሣኤ ብለው ሲጠሩት በፍዳው ዘመን አምነው የሞቱ ከሺህ ዓመቱ በፊት ይነሳሉ ብለው ሲያምኑ፤ ይህንንም ሁለተኛው ትንሣኤ ብለው ይጠሩታል፡፡ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ትንሣኤ ከቤተ ክርስቲያን ትንሣኤ ጋር ይሆናል ብለው እንደሚሆን የሚያምኑ ሲኖሩ ከሰባት ዓመቱ የታላቁ መከራ መጨረሻ (በጌታ ዳግም ምፅዓት ጊዜ) ላይ እንደሚሆንም የሚያምኑ አሉ፡፡ ስለ ኃጥአን ትንሣኤ ከሺሁ ዓመት መጨረሻ ላይ እንደሚሆን በትምህርታቸው ይገልጣሉ፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *