ስለ ቤተ ክርስቲያን አባልነት ጥናታችንን ስንጀምር፣ የቤተ ክርስቲያን አባልነት የዓለም አቀፏና የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ተብለው በሁለት መከፈላቸውን አስቀድመን ማወቅ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ቀደም ብለን ስለ ድነት ባየነው ትምህርት መሠረት አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ሰምቶ፤ በኃጢአቱ ተጸጽቶ፤ ኢየሱስ ክርስቶስን ጌታውና አዳኙ አድርጎ ሕይወቱን ለጌታ በሚሰጥበት ጊዜ ዳግም ልደትን በመንፈስ ቅዱስ በማግኘት አዲስ ፍጥረት ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜ በኢየሱስ በማመኑ የእግዚአብሔር ልጅነትን ስለሚያገኝ የዓለም አቀፏ ቤተ ክርስቲያን አባል ይሆናል፡፡
የአባልነት አስፈላጊነት፡- የዓለም አቀፏ ቤተ ክርስቲያን አባል የሆነ ሰው፣ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገልና የማትታየው ቤተ ክርስቲያን አባል መሆኑን፣ በምትታየው አጥቢያዊ ቤተ ክርስቲያን አባል በመሆን የክርስቶስ አካልነቶን በሚያደርገው ኅብረት ይገልጻል፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፡41-42 ላይ ‹‹ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ በዚያን ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስ ተጨመሩ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር›› በማለት የአጥቢያ አባልነት አስፈላጊነቱን ሲፈጽሙ እንመለከታለን፡፡ በዚህ ሥፍራ የተጠቀሱት ዋና ዋና ነገሮች ትምህርት፣ ኅብረት ማድረግ፣ እንጀራውን መቁረስና በጸሎት መትጋት ሲሆኑ፤ እነዚህ ነገሮች ዛሬም በየቤተ ክርስቲያኖቻችን የሚያስፈልጉ ዋና ነገሮች ናቸው፡፡ ችግር ሲገጥማቸውም አብረው በመሆን ችግራቸውን በጸሎት ወደ ጌታ ሲያቀርቡና መልስ ሲያገኙም ቃሉ ያሳየናል (የሐዋ. 4፡29)፡፡
በአንድነት ተባብሮ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ለመርዳት፣ በደስታ፣ በኀዘን፣ በመከራ ለመረዳዳትና የወንድማማቾች ፍቅራችንን ለመግለጥ እንዲያመቸን የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል የመሆን አስፈላጊነትን ቃሉ ያስተምረናል፡፡ በሐዋርያት ሥራ 11፡29 ላይ ‹‹ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ›› ሲል በ12፡17 ላይ ደግሞ ጴጥሮስ ‹‹… ጌታ ከወኅኒ እንዴት እንዳወጣው ተረከላቸው›› የሚለው አጥቢያ ከችግር ውስጥ ሲወጣ ጌታን ማመስገኛ ስፍራ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ በጌታ ወንድማማች ስለሆንን ማቴ. 23፡8) አብረን የጌታን ጸጋ የምንከፋፈልበትና የምንጽናናበት በመሆኑ የአጥቢያ አባልነት እጅግ አስፈላጊ ነው (ሮሜ 1፡11-12)፡፡
አጥቢያ ቃሉ በቆሮንቶስ መልእክት እንደሚለው ‹‹በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት፣ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በየስፍራው ከሚጠሩት ሁሉ ጋር ቅዱሳን ለመሆን ለተጠሩት›› (የሐዋ. 9፡13፣ 1ቆሮ. 1፡2፣ መዝ. 133፡1-3) ከሌሎች ቅዱሳን ጋር የጌታን ስም ለመጥራትና ኅብረት ለመፍጠር የሚሰበሰቡበትና የሚያደርጉበት፣ በመሆኑ አባልነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን፡፡ ጌታም ደቀ መዛሙርቱን የጠራውም በኅብረት ከእርሱ ጋር እንዲኖሩና እንዲያገለግሉት ስለ ነበረ፤ ዛሬም ጌታን በኅብረት የምናመልክበትና የምናገለግልበት ቦታ ነው (ማር. 3፡14)፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ በመልእክቶቹ ‹‹እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፣ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፣ ምስጋናም ይብዛላችሁ›› (ቆላ. 2፡7-8)፤ ‹‹ወንድሞች ሆይ፡- እንመክራችኋለን ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፣ ሰውን ሁሉ ታገሡ›› (1ተሰ. 5፡14) በማለት አንድ አማኝ የአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል ሆኖ መኖር፣ በሥርዓት ለመታጽና ለማደግ፣ ከጌታ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት፣ ለመገልገልና ለማገልገል አስፈላጊ እንደሆነ ቃሉ ያሳየናል፡፡
የአባሎች ኃላፊነት፡- ከዚህ በላይ ባደረግነው ጥናታችን እንደ ተመለከትነው፣ የአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን አስፈላጊነቱን አይተናል፡፡ የአጥቢያ አባል በምንሆንበት ጊዜ፣ የዕብራውያን ጸሐፊ ‹‹ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን… እንተያይ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ›› በማለት ቤተ ክርስቲያን በምትፈልገን ስብሰባዎች ሁሉ የመገኘት፣ ሐሰብ የመስጠትና ከሌሎች የመስማት ኃላፊነት እንዳለብን ያመላክተናል (ዕብ. 10፡24-25)፡፡
የቤተ ክርስቲያን አባሎች ስንሆን፣ በሰላምም ሆነ በመከራ ጊዜ፣ ችግር የደረሰባቸውን ምዕመናን በጸሎት የማገዝ ኃላፊነት እንደ አለብን፤ ከሚቀጥለው ታሪክ እንማራለን፡፡ ለጴጥሮስ በእስራቱ ጊዜ በማርቆስ እናት ቤት አጥብቆ የተጸለየው ጸሎት መልካም ምሳሌያችን ነው (የሐዋ. 12፡12-17)፡፡ ደግሞም ጳውሎስ ከሁሉ በላይ አንድነት መጠበቅ እንዳለብን በኤፌሶን መልእክቱ ‹‹በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ›› እያለ ያስተምረናል (ኤፌ. 4፡3)፡፡ የቆሮንቶስ አባሎች እንደታዘዙት፤ ‹‹በመቅደስ ነገር የሚያገለግሉ ከመቅደስ የሆነውን ነገርን እንዲመገቡ፣ በመሠዊያውም የሚጸኑ ከመሠዊያው እንዲካፈሉ አታውቁምን? እንዲሁ ደግሞ ወንጌልን የሚሰብኩ ከወንጌል ቀለብ እንዲቀበሉ ጌታ ደንግጎአል›› (1ቆሮ. 9፡13-14፣ ሚል. 3፡10)፣ ስለዚህ የአጥቢያ አባሎች ስንሆን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲውል አሥራት፣ በኩራትና መባ መስጠት እንደሚጠበቅብን ያስተምረናል፡፡
የአጥቢያ አባሎች ስንሆን በጌታ ራት በመሳሰሉት በቅዱስ ሥርዓቶች የመገልገል ኃላፊነት ይኖርብናል (1ኛቆሮ. 11፡23-34) እንዲሁም አጥቢያ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ እናውቅ ዘንድ የምንማርበት ሥፍራ ነው (1ጢሞ. 3፡15)፣ በዚህም ሥፍራ ስለምናከናውነው ጳውሎስ ሲናገር፣ ‹‹ወንድሞች ሆይ፡- በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም ታውቁ ዘንድ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን›› (1ተሰ. 5፡12-13) በማለት ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሥልጣን መገዛት፣ መታዘዝና ማክበር እንደሚገባን ያስተምረናል (ዕብ. 13፡7፣17)፡፡
የአጥቢያ ሽማግሌዎች በመጀመሪያ ለጌታ አገልግሎት የሚደክሙ፣ የሚያስተዳድሩ (የሚገዙ)ና የሚመክሩ (የሚገሥጹ) መሆናቸውን ልናውቅላቸው ይገባናል፡፡ ሁለተኛ እንደ ቃሉ ማክበር ያለብን በመልካም ስለሚያስተዳድሩ፣ በመስበክና በማስተማር ስለሚደክሙ ሲሆን፣ በሦስተኛ ሽማግሌዎችን መታዘዝ ያለብን ከእኛ ስለሚበልጡ ሳይሆን መንፈሳዊ ሕይወታችን ጤነኛ ሆኖ እንዲያድግ ኃላፊነት ስላለባቸውና በደስታ አገልግሎታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ነው፡፡ በትጋትና በታማኝነት ለሚያገለግሉት መሪዎቻችን የሚገባንን ልናደርግላቸው አባላት ኃላፊነት አለብን፡፡
የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት፡- አባላት ብቻ ሳይሆኑ፣ ቤተ ክርስቲያንም ለአባላቷ ሁሉ ኃላፊነት አለባት፤ ቤተ ክርስቲያንም አባሎቿን ሁሉ በእኩል ዓይን እያየች የማስተማር፣ የመምከር፣ የመጸለይ፣ የመጠበቅ፣ የመንከባከብና በሁሉ ነገር የማሳደግ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባት ከቃሉ በመቀጠል እንመለከታለን፡፡ በማቴዎስ ወንጌል 28፡18-20 ላይ ጌታ ታላቁን ተልዕኮ ለደቀ መዛሙርቱ ሲሰጥ፣ ወንጌልን ይዘው ወደ አልዳኑ ሕዝቦች ሁሉ እንዲወጡና እንዲያዳርሱ ኃላፊነት እንደ ሰጣቸው እንመለከታለን፡፡ ጳውሎስም ‹‹ሥራ የሞላበት ትልቅ በር ተከፍቶልኛል›› ይላል (1ቆሮ. 16፤9)፡፡ ጌታም ለፊልድልፍያ ቤተ ክርስቲያን መልእክት ሲልክ ‹‹እነሆ፡- በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም›› (ራዕይ 3፡8) በማለት ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ሥራ በስፋት በፊትዋ እንደ ተዘረጋ ያመለክታታል፡፡
አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያው ትልቁ ኃላፊነቷ በጨለማ ላሉት ወንጌልን መስበክ እንደሆነ ተመልክተናል፤ ሁለተኛው ሐዋርያው ጴጥሮስ ለዳኑትም አማኞች ቃሉን፣ ወተትና አጥንት የሆነውን ሁሉ እንደ አቅማቸው በማቅረብ የመመገብ ኃላፊነት እንዳለባት ያመለክተናል (1ጴጥ. 2፡2-3)፡፡ በመቀጠልም ‹‹በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ›› (1ጴጥ. 5፡2-3) በማለት ኃላፊነቷን ያመለክታል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› (የሐዋ. 20፡28) በማለት ቤተ ክርስቲያን አባሎቿን መጐብኘትና በፍቅር መያዝ እንዳለባትና አባሎችዋን ተኩላ እንዳይሰብራቸው የመጠንቀቅ ኃላፊነት እንዳለባት ያስተምረናል፡፡
ቤተ ክርስቲያን አባሎቿን መጐብኘትና በፍቅር መያዝ ብቻ ሳይሆን፤ ምክርና ተግሣጽ ለሚያስፈልጋቸው የመስጠት አስፈላጊነትን ጳውሎስ ሲገልጽ ‹‹እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለጠጎች እንዲሆኑ፣ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው›› (1ጢሞ. 6፡19)፤ ‹‹ቃሉን ስበክ፣ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፣ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርክ፣ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም›› (2ጢሞ. 4፡2፣) በማለት ቤተ ክርስቲያን ያለባትን ኃላፊነት እንድትወጣ፣ ለመንፈሳዊ ልጁ ለጢሞቴዎስ ያሳስበዋል፡፡ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀት፣ የጌታ ራት፣ የጋብቻና የቀብር የመሳሰሉትን የተለያየ ሥርዓቶች እንዲፈጸምላቸው የሚያስፈልጋቸውን የመፈጸምና ወደ ክርስቶስ ሙላት የማሳደግ ኃላፊነት አለባት (ኤፌ. 4፡11-16)፡፡ አባሎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ፤ ቤተ ክርስቲያንም የተሰጣትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለባት በሰፊው ቃሉ ያመለክተናል፤ ይህንንም ኃላፊነት ለመወጣት፣ ጌታ በጸጋው አባሎቿንም እርሷንም ይርዳ፡፡ በሚቀጥለው ጥናታችን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶችን እንመለከታለን፡፡
0 Comments