የወዳጅ ደብዳቤ በናፍቆት የሚጠበቅ እንደሆነ ባለፈው ተመልክተናል፤ የወዳጅ ደብዳቤ ሲደጋገምና ትምህርታዊ ይዘት ሲኖረው ወደ አንድ ቁም ነገር ማድረስ ይችላል፡፡ ሉቃስ ለወዳጁ ለቴዎፍሎስ የጻፈለት ሁለተኛው ደብዳቤ ታሪካዊና ትምህርት ሰጪ ነበር፡፡ ሉቃስም አንድን ሰው ከደህንነት ጀምሮ መንፈሳዊ ዕድገት እስከሚያገኝበት ጊዜ ድረስ በትጋት፣ በጽናትና በጥንካሬ በደብዳቤ ተከታትሎ በማገልገሉ ለእኛ ትልቅ ምሳሌያችን ይሆናል፡፡ ዘመናትን አቋርጦ ወደ እኛ ስለደረሰ፣ እኛም ከትምህርቱ ተቋዳሽ ሆነናል፡፡

ድሮ እድገት በሕብረት ዘመቻ በ1967-1968 ዓ.ም በተዘመተበት ጊዜ የወር ቀለብ የሚከፈለኝ ብር 60 (ስልሳ) ቢሆንም ወደ አምስት ለሚደርሱ ተማሪዎች በባለ ሃያ ሳንቲም ኤሮግራም ፖስታ ላይ ተከታታይ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ለጥያቄአቸው መልስና የሳሙና ሳንቲም በመላክ እኔም እንደ ሉቃስ አገለግላቸው ነበር፡፡ እነርሱም የሄዱበትን የዘመቻ ግዳጃቸውን ተወጥተው፣ እምነታቸውን ጠብቀው መመለስ ችለው ነበር፡፡ ትምህርታዊ ደብዳቤ ምን ያህል እንደ ጠቀማቸው፣ ከሁሉም ከምስክርነታቸው መረዳት ችያለሁ፡፡ በዚህ መንገድ ከማገለግላቸው መካከል አንዷ ከዘመቻ መልስ ያገባኋት ባለቤቴ ነበረች፡፡

 ዛሬ አንዳንዶቻችን በአካባቢያችንና ከአካባቢያችን ራቅ ብለን ሄደን በግል ወንጌልን መስክረን ሳንከታተላቸው የምንተዋቸው ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለይም የወንጌል አገልጋዮች በየሥፍራው ለምስክርነት ሄደን፣ ቃሉን መስክረን መጽናታቸውን ሳናውቅ፣  ለሚይዙ ሰዎች ወይም ለቤተ ክርስቲያን ሳንሰጣቸው ዝም ብለን ትተናቸው እንሄዳለን፡፡ በዚህ መንገድ የሉቃስና የቴዎፍሎስ ግንኙነት ከጎረቤቶቻችን፣ በሥራ ቦታና በርቀትም ካሉ ጋር ለመገናኘት ብዙ ትምህርት ይሰጠናል፡፡ ጸሐፊው ሉቃስ ለቴዎፍሎስ ከጻፈለት ሰፊ የታሪክ ዘገባ ውስጥ ቀንጭበን፣ በመግቢያው ላይ እንደተመለከትነው የኢየሩሳሌምና የአንጾኪያ አብያተ ክርስቲያናት በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ላይ የተሰጣቸውን የተስፋ ቃል ጠብቀው ካገኙ በኋላ ታላቁን ተልዕኮ ወደ ግቡ በማድረስ ተወጥተው እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ መጠነኛ ዳሰሳ በማድረግ ጥንካሬያቸውንና ድካማቸውን እናያለን፡፡ ታሪካቸው ተጽፎ የምናገኘው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሲሆን፣ ከአዲስ ኪዳን መጽሐፍቶች ሁሉ በጣም አስፈላጊው መጽሐፍ ነው፡፡ ምክንያቱም ስለ ጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የምናውቅበት ዋና ምንጭ በመሆኑ ነው፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሐዋርያት ሁሉ ምን ምን እንደ ሠሩ ሁሉንም ነገር ባይነግረንም፤ ከሐዋርያት ውስጥ ታሪካቸው የተጠቀሰው ጴጥሮስ ያዕቆብና ዮሐንስ ሲሆኑ ሌሎች በምዕራፍ 1፡13 ላይ ስም ዝርዝራቸውን ከመጻፍ በስተቀር ምን እንደ ሠሩ ሉቃስ ምንም አይነግረንም፡፡ በምዕራፍ 12፡2 ላይ ያዕቆብ በሄሮድስ መሠዋቱን ሲገልጽ የዮሐንስን ስም ጠቅሶ ከማለፍ በስተቀር ያለው ነገር የለም፡፡ የጴጥሮስን ታሪክ ግን በሰፊው ይተነትናል፡፡ ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት ውጭ ታሪኩ በስፋት ተጽፎለት የምናገኘው ሰው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው፡፡ ሉቃስ የጳውሎስን ታሪክ በስፋት የጻፈው ለምንድነው?


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *