ቀደም ባለው ጥናታችን የቤተ ክርስቲያን ምንነትና ጅማሬ፤ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ምን መልክ እንደ ነበራትና ተልዕኮዋን ለመዳሰስ ጥረት አድርገናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን በሁለት መልኳ ዓለም አቀፋዊና አጥቢያዊ በሆነ ሁኔታ ይገልጣታል፤ በማትታይና በምትታይ መልኳ ሰማያዊና ምድራዊ አድርጎ አስቀምጦአታል፡፡ አንዷ የማትታየው ዓለም አቀፏ ቤተ ክርስቲያን በሚታይ መልኳ አጥቢያዊት ሆና በዓለም ዙሪያ በየክፍለ ዓለማቱ፣ በየአገሩ፣ በየአውራጃው፣ በየወረዳውና በየቀበሌው ተሠራጭታ እየሠራች እናገኛታለን፡፡ ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ስናነሳ ስለ አንዲት የተለየች በመንደራች ስለምትገኘው መናገራችን አይደለም፡፡
ስለዚች በየቦታው ስለምትገኘው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ትእዛዝ በሚሰጥበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበላችሁ በኋላ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ ከማለት በስተቀር ዝርዝር መመሪያ አልሰጣቸውም፡፡ ስለዚህ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተለይም በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ስለ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሚያስረዳው ትምህርት ግልጽ የሆነ ማብራሪያ አናገኝም፡፡ ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያን ስትጀመር በስንት ሰዎች ትቋቋም፣ ስንት አባል ስትደርስ ትከፈል፣ መሪዎቿ እንዴት ይመረጡና ለስንት ዓመት ይምሩ… የሚል ዝርዝር ነገር ባለመኖሩ በየዘመናቱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ችግር ሲገጥማትና ዛሬም እየገጠማት ትገኛለች፡፡
ትርጉም፡- አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ስንል ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሕይወታቸው አስገብተው የማትታየው ቤተ ክርስቲያን አባል በመሆን፣ የውኃ ጥምቀት በመውሰድ፣ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግና አብሮ ለማምለክ በዕውቀት፣ በቋንቋ፣ በዘርና በሀብት ሳይከፋፈሉ፤ በጌታ አዳኝነት ላይ ብቻ ተመሥርተው የተሰባሰቡና የተደራጁ ሰዎች የሚገኙባት ኅብረት ናት፤ ምንም እንኳን ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት እንደዚያ ሆነው ባይገኙም፡፡
በአዲስ ኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ የቤተ ክርስቲያንን አመሠራረት ስንመለከት ሉቃስ ‹‹በየቀኑም በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቆረሱ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር›› (የሐዋ. 2፡46) በማለት የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብና ጸሎት መጸለዩን በቤተ መቅደስ አድርገው፤ እንጀራውን (የጌታ ራት) መቁረስ በቤታቸው ያከናውኑ እንደ ነበረ ጥቅሱ ያስረዳናል፡፡ የጌታ ራት ለቤተ መቅደስ ሥርዓት አዲስ ስለ ነበረ በቤተ መቅደስ ማካሄድ አልቻሉም ነበር፡፡ በዚህም መንገድ እያመለኩ ቆይተው ሳለ፣ ‹‹የእግዚአብሔርም ቃል እየሰፋ ሄደ፣ በኢየሩሳሌምም የደቀ መዛሙርት ቁጥር እጅግ እየበዛ ሄደ፣ ከካህናትም ብዙ ሰዎች ለሃይማኖት የታዘዙ ሆኑ››፡፡ በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያን ከቤት በመጀመር በኢየሩሳሌም፣ ቀጥሎም በአንጾኪያ፣ በቆሮንቶስ፣ በገላትያ፣ በኤፌሶንና በሌሎችም ከተማዎች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት እየተመሠረቱና እየተስፋፉ እንደመጡ ከቃሉ እንረዳለን፡፡
የሐዋርያት ሥራን ስንመለከት፣ ሐዋርያው ጳወሎስ ከተለወጠ በኋላ፣ የወንጌሉን ሥርጭት በከተማዎች ላይ በማድረጉ፤ ወንጌሉ ከከተማዎች ወደ ገጠሩ በቀላሉ ሊስፋፋ ችሎአል፡፡ ኢየሱስን በሕይወታቸው ጌታ አድርገው እንዲኖር በመፍቀድ፣ አዳኝና ጌታ አድርገው በመቀበል የውኃ ጥምቀት ሲወስዱና ለአምልኮ አብረው ሲሰባሰቡ አንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ትመሠረታለች፡፡ በጌታ ኢየሱስ የሚያምኑ እየበዙ ሲመጡና በተለያየ ርቀት ባለው ሥፍራ ሰዎች ወደ ጌታ ቤት ሲጨመሩ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት እየተመሠረቱ እንደ መጡ ማየት እንችላለን፡፡ ዛሬም አንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከተወሰነ ቁጥር በላይ ሲሆኑና ሰዎች ራቅ ያለ ቦታ ሄደው ሲቀመጡ፣ ወይም በሥራ ምክንያት ቦታ ሲለውጡ፣ በዚያ ሌላ አጥቢያ ሊከፈት ይችላል፡፡
የአጥቢያ ምሥረታ፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ›› ብሎ ቢናገርም በምድር በነበረበት ጊዜ አንድ አጥቢያ እንኳን አልመሠረተም፤ በመጀመሪያ የተመሠረተችው አጥቢያ በገሊላ የምትገኘው በፍርሃት ቤት ዘግተው የተቀመጡባት (ለአሥሩ ደቀ መዛሙርት፣ ቶማስ በሌለበት እና በድጋሚ በአለበት) እና መንፈስ ቅዱስን እፍ ብሎባቸው ለቅምሻ የተቀበሉባት ቤት የመጀመሪያዋ አጥቢያ ነች (ዮሐ. 20፡19፣26)፡፡ ምክንያቱም በትንሣኤ ቀን ለመግደላዊት ማርያም፣ ለያዕቆብ እናት ማርያምና ለሰሎሜ በታየ ጊዜ ፤ መላእክቶች ለሴቶቹ ‹‹ፈጥናችሁም ሂዱና፡- ከሙታን ተነሣ እነሆም ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው›› እንዲሁም ጌታ ራሱ ‹‹አትፍሩ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ በዚያም ያዩኛል አላቸው›› (ማቴ. 28፡7፣10፤ ማር. 16፡6) ከዚህ በላይ በሚለው በቃሉ መሠረት የተሰበሰቡበት ሥፍራ ገሊላ ነበር፡፡
በሁለተኛ ደረጃ አጥቢያ ሆናለች ብለን ማሰብ የምንችለው የማርቆስ እናት ቤት ሳትሆን አትቀርም፤ ምክንያቱም ቃሉን ስናጠና የምናገኘው ማስረጃ፤ ደቀ መዛሙርት በትንሣኤ ቀን ከይሁዳ ወደ ገለላ ሄዱ፤ በዚያ ዐርባ ቀን ያህል ቆይተው፤ ዕርገቱን ከተመለከቱ በኋላ፣ ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፡፡ ‹‹በዚያን ጊዜ ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፣ …በገቡም ጊዜ ወደሚኖሩበት ሰገነት ወጡ፣ …እነዚህ ሁሉ ከሴቶችና ከኢየሱስ እናት ማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው ለጸሎት ይተጉ ነበር›› (የሐዋ. 1፡12-15)፡፡ በሐዋርያት ሥራ 8፡3 ላይ ‹‹ሳውልም ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ ነበር›› ከሚለው አባባል ስንነሳ፣ በዚህ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ከአምስት ዓመት በላይ ያስቆጠረች ብትሆንም የምታመልክበት ሕንጻ እንዳልነበራትና የምዕመኑ ቤት ሁሉ ቤተ ክርስቲያን እንደነበረ ቃሉ ይጠቁመናል፡፡
ጸሎት ቤት ከነበሩት መካከል፣ በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉባት የመጀመሪያዋ የቤት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ ‹‹ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው›› (የሐዋ. 2፡1-4)፤ በሚለው መሠረት መንፈስ ቅዱስ የወረደው በቤት ውስጥ እንደ ሆነ እናያለን፡፡ ከዚያም በኋላ ‹‹ቃሉንም የተቀበሉ ተጠመቁ … በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር … በየቀኑ በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቆረሱ፣ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር›› (የሐዋ. 2፡41-46) በማለት ከሚናገረው የምንረዳው ነገር ቢኖር የእግዚአብሔርን ቃል ማንበብና ጸሎት መጸለዩን በቤተ መቅደስ አድርገው፤ እንጀራውን (የጌታ ራት) መቁረስ በቤታቸው ያከናውኑ እንደ ነበረ ግልጽ ነው፡፡ ይህቺ ቤት በሐዋ. 12፡12 መሠረት የማርቆስ እናት የማርያም ቤት የመጀመሪያዋ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ከቃሉ መረዳት እንችላለን፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጥኩት ቤተ ክርስቲያን በዚህ መልኩ ከቤት በመጀመር በኢየሩሳሌም፣ ቀጥሎም በአንጾኪያ፣ በቆሮንቶስ፣ በገላትያና በኤፌሶን ከተማዎች አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት እየተመሠረቱና እየተስፋፉ እንደመጡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ያስረዳናል፡፡
የአጥቢያ ተግባር፡- ቤተ ክርስቲያን በተሰጣት ታላቁ ተልዕኮ መሠረት፣ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ዋና ተግባሯ ወንጌልን ለጠፉት ሰዎች እየሰበከች፣ ንስሐ እያስገባች፣ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት እንዲያምኑ እያደረገችና በውሃ ጥምቀት በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ስም እያጠመቀች፣ አባል አድርጋ በደቀ መዝሙርነት ሕይወት እንዲያድጉ የማድረግ ኃላፊነት አለባት፡፡ እያንዳንዱ አማኝ በሐዋርያት ትምህርት በጸሎትና በጌታ ራት እንዲካፈሉ እያደረገች፤ የክርስቶስን ሙላትና መልክ እስኪመስሉ ድረስ ምዕመኖቿን የማሳደግ ኃላፊነት አለባት፤ ይህንም ኃላፊነቷንና ተግባሯን በጌታ ጸጋና እርዳታ ልትወጣ ይገባታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በድፍረት ወንጌልን እየሰበከች፤ እግዚአብሕርን ማክበርና ማምለክ ዋና ሥራዋና ተግባሯን ልትወጣ እንድትችል፣ በጸሎት በጌታ ፊት ሁልጊዜ መቅረብ ይኖርባታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ አባሎች መንፈሳዊ ዲስፕሊን እንዲኖራቸው ቃሉን ማንበብ፣ በግልና በቡድን ጸሎት በመጸለይ፣ ከወንድሞችና እህቶች ጋር ሕብረት በማድረግ፣ የዳኑትንም ያልዳኑትንም በማገልገል እና በክርስትና ሕይወታቸው የክርስቶስን መከራ መለማመድ እንዲችሉ፣ የማስተማርና ምሳሌ የመሆን ትልቅ ኃላፊነት እንዳላቸው ቃሉ ያስተምረናል፡፡ መሪዎች ይህን ቢያደርጉ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊነቷን ተወጣች ማለት ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር፡- መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናጠና እንደምናገኘው የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ይዘውት የነበሩት ሐዋርያት እንደነበሩና በመካከላቸው በተፈጠረው ችግር ምክንያት በቁሳቁስ የሚረዷቸውን አገልጋዮችን መምረጣቸው ይታወቃል (የሐዋ. 6፡1-6)፡፡ በመቀጠልም የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ከምዕራፍ አንድ ጀምሮ እስከ አስራ አንድ ድረስ ያለውን ክፍል ስናይ፣ ሽማግሌ የሚለውን ቃል አናገኝም፤ ከምዕራፍ 11፡30 ጀምሮ ሽማግሌዎች የሚለውን ስም ስለምናኝ አስተዳደሩን ወደ ሽማግሌዎች እንዳዞሩት እንመለከታለን፡፡ በሐዋርያት ሥራ 15 ላይ ስንመለከት ቤተ ክርስቲያንን የሚመራው የሽማግሌዎች ሰብሳቢ የነበረው የጌታ ወንድም ያዕቆብ እንደሆነ ከቃል መረዳት እንችላለን (የሐዋ. 15፡13፣ ገላ. 1፡19)፡፡ ከዚህ በኋላ ምንም እንኳን ሽማግሌዎች ተመርጠው በሰብሳቢው (ያዕቆብ) ቢመሩም፣ ሉቃስ በሚቀጥሉት ጥቅሶች ሲጽፍ፣ ቤተ ክርስቲያን (ምዕመናን) እና ሐዋርያት ሽማግሌዎችም እያለ ያስቀምጣቸዋል (የሐዋ. 15፡2፣4፣6፣22፣23)፡፡
ከሁለተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ወደ አንድ ሰው የበላይ መሪነት የተሸጋገረ እንደ ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ መረዳት እንችላለን፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ስንመጣ ብዙ የተለያዩ ዓይነት የአስተዳደር መዋቅሮች እናገኛለን፤ ሁሉም የያዙትን ልክ ነኝ በማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በአስተዳደር በኩል ግልጽ ያለ ትምህርት አይሰጥም፡፡ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜም ቢሆን፣ ቤተ ክርስቲያኔን እመሠርታለሁ አለ እንጂ፣ በማን እንደምትመራ፣ በምን ዓይነት አስተዳደር መመራት እንዳለባት፣ ሹመት ወይም ምርጫው እንዴት መከናወን እንዳለበትና መሪዎች ለስንት ዓመት ማገልገል እንዳለባቸው ምንም ትምህርት አልሰጠም፡፡
ሉቃስም ቢሆን የሐዋርያት ሥራን በሚጽፍበት ጊዜ ስለ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ምንም አልጻፈም፤ ምክንያቱም የራሱ የሆነ ዓላማ ስለነበረው፤ ዓላማውም በአይሁድ የተጠሉት አህዛቦች ወንጌል እንዴት እንደ ደረሳቸው መተረክ ነበር፡፡ የጴጥሮስንና የጳውሎስን ታሪክ ሰፋ አድርጎ ሲጽፍ ስለ ሌሎቹ ሐዋርያት ስማቸውን ከመጻፍ በስተቀር በአገልግሎታቸው ስለ ሠሩት ሥራ ምንም አልጻፈም፡፡ የዐዲስ ኪዳን ማስረጃዎችን በሚገባ ከመረመርን በኋላ አንዱ ዓይነት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ከሌላ ዓይነት አስተዳደር የሚሻል እንደሆነ ብናምንም እያንዳንዱ ዓይነት አስተዳደር የራሱ የሆነ ደካማና ጠንካራ ጎን እንዳለው እንረዳለን፡፡ ስለዚህ ሁሉም ምዕመናን የተስማሙበት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡ እኛም ከሐዋርያት ልምምድ ተነስተን ዛሬ ያሉትን በመዳሰስ ለእኛ ይጠቅማል የምንለውን መያዝ ተገቢ ነው፡፡ በመቀጠል በሥራ ላይ ያሉትን የአስተዳደር ዓይነቶችን በጥናታችን እንመለከታለን፡፡
ሀ) ኤጲስ ቆጶሳዊ፡- ይህ አስተዳደር የተመሠረተው በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚያ ዘመን ስድስት የክርስትና ማዕከሎች የነበሩ ሲሆን፣ ኢየሩሳሌም፣ አንጾኪያ፣ ሮም፣ እስክንድርያ፣ ቆስጠንጢንያና ካርቴጅ የተባሉት ሲሆኑ፣ እያንዳንዳቸው ሜትሮፖሊያን ቢሾፕ ሲኖራቸው፤ የሮም ፖፕ (አባት) በመባል የሚታወቀው የሁሉም የበላይ ሆኖ ይመራት ነበር፡፡ በአሁኑ ዘመንም በዚህም የአስተዳደር ዓይነት የሚመሩ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ አንግሊካን፣ ሉተራውያንና ሜቶዲስቶች የሚባሉት ቤተ ክርስቲያናት በዚህ አስተዳደር በተለያየ መልኩ ሲጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ በጳጳሳቱ አስተዳደር ሥር ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ሊኖሩም ላይኖሩም ይችላሉ፡፡ በአዲስ ኪዳን የምናገኘውን አሠራር የሚመሳሰልበትም የሚለያይበትም ነገሮች አሉት፡፡
ለ) ሽማግሌያዊ፡- ከኤጲስ ቆጶስ በመቀጠል በዚህ ዘመን እየተሠራበት ያለ የአስተዳደር ዓይነት ሲሆን፣ በዚህ አስተዳደር የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች ለተወሰነ ጊዜ እንዲያገለግሉ የሚመረጡት በምዕመናን ነው፡፡ በአጥቢያ ሽማግሌ ሆነው የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች እንደየ ቤተ እምነቱ አሠራር ቢለያይም፣ በክልል ሁሉም ወይም የተወሰኑ ሽማግሌዎች የጉባኤው (ፕሬስቢቴሪ) አባል ይሆናሉ፡፡ እንደገና አሁንም ሁሉም ወይም ጥቂቶች የጠቅላላው ጉባኤ አባላት ይሆናሉ፡፡ ይህ ጉባኤ በብሔራዊ ደረጃ በፕሬስቢቴሪያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ላይ ከፍተኛውን ሥልጣን ይይዛሉ፡፡ በብሔራዊ ሽማግሌዎች የተወሰነውን በሁሉም አጥቢያዎች ተግባራዊ ያደርጉታል፡፡
ሐ) ምዕመናዊ፡- ሦስተኛው የአስተዳደር ዓይነት ምዕመናዊ ሲሆን እነርሱም ለመዋቅራቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ለማቅረብ ይሞክራሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ሊኖሩም ላይኖሩም ይችላሉ፣ ውሳኔዎች ሁሉ የሚወሰኑት በምዕመናኑ ነው፡፡ አንደንዶች በጥናታቸው እንደሚያቀርቡት፣ ይህ አስተዳደር በአምስት የሚከፈሉ የአስተዳደር ዓይነቶች እንደ አሉት ያቀርባሉ፡፡ (1. በአንድ ሽማግሌ የሚመራ/መጋቢ፣ 2. በመጋቢና ዲያቆናት፣ 3. በብዙ ሽማግሌዎች፣ 4. በቦርድ፣ 5. በእውነተኛ ዲሞክራሲ/ምዕመናን፣ በዌይን ግሩደም ስልታዊ ሥነ መለኮት ገጽ 1058-1061)
መ) መጋቢያዊ፡- በዚህ አስተዳደር የምናየው የአንድን ሰው የበላይነት ሲሆን ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ሊኖሩም ላይኖሩም ይችላሉ፤ በዚህ ባለንበት ዘመን አንደንድ አብያተ ክርስቲያናት ወደዚህ አመራር በብዛት እያዘነበሉ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ከሌሉ ከተጠያቂነትም ነጻ መሆን ስለሚቻል፣ አስተዳደሩ እየተመረጠ ይገኛል፡፡ ብዙ ጊዜ በቤተ ሰብም ስለሚያዝ ጠያቂም አይኖርም፡፡
የሽማግሌዎች ምርጫ በትክክል መቼ እንደ ተካሄደ ባናውቅም ቢያንስ እስከ አሥር ዓመት ያህል ጊዜ ድረስ ቤተ ክርስቲያንን የመሩዋት ሐዋርያት እንደሆኑ ከቃሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በመቀጠልም ሐዋርያው ጳውሎስ ተለውጦ አገልግሎት ከጀመረ በኋላ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 14፡23 ላይ እንደ ምናገኘው ጳውሎስ የወንጌል ጉዞውን በሚያደርግበት ጊዜ በየቤተ ክርስቲያኑ ሽማግሌዎችን እየሾመላቸው እንደ ዞረ ቃሉ ይናገራል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከተመረጡ ዲያቆናትም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከዚያ በኋላ የአዲስ ኪዳን አብያተ ክርስቲያናት በሽማግሌዎችና በዲያቆናት ስትመራ ደብዳቤም ሲጻፍላቸው ሁለቱም ሲጠቀሱ እናያለን፡፡ (ፊል.1፡1፣ 1ጴጥ.5፡1) ጳውሎስ ጢሞቴዎስንና ቲቶን ሽማግሌዎችን እንዲሾሙ ሲያዛቸው በነጠላ አንድ ብቻ ሳይሆን ከሁለት በላይ እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ ይህ አሠራር ይበልጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደሆነ በግሌ አምናለሁ፤ ሁላችንም ከቃሉ እውነቱን ማየት እንችላለን፡፡
0 Comments