2.3 የድነት ውጤት

ሰው የእግዚአብሔርን ቃል ሲሰማ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስለ ኃጢአቱ ይወቀሳል፤ በኃጢአቱም ምክንያት ሞትና ኩነኔ እንዳለበት ሲረዳ፣ በመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት አማካኝነት ንስሐ በመግባት ክርስቶስን ሲያምን በመንፈስ ቅዱስ እንደሚታተም ተመልክተናል፡፡ ቃሉም መንፈስ ቅዱስም የኃጢአቱ ዋጋ በክርስቶስ እንደ ተከፈለለት ሲያውጁለት ንስሐ በመግባት ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ልቡ በማስገባት ያምናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአል››   (ዮሐ. 3፡16) በሚለው መሠረት የዘላለም ሕይወት ያገኛል፡፡ ይህን ሕይወት ማግኘቱ ልጅነትን፣ ጽድቅንና ቅድስናን ያስገኝለታል፡፡

ልጅነት፡- ሰው በወንጌል ጥሪ አማካኝነት የእግዚአብሔርን የጸጋ ስጦታ በንስሐና በእምነት ሲቀበል የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ የቤተሰብን አባልነት ያገኛል፡፡ ዮሐንስ በወንጌሉ ይህን እውነት ሲገልጸው እንዲህ ይላል ‹‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን፣ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው››     (ዮሐ. 1፡12)፤ በዚህ ሥፍራ ስንመለከት የወንጌልን ጥሪ መቀበልና ማመን የሰው ድርሻ ሲሆን፣ የልጅነትን (የዘላለም ሕይወትን) መብት መስጠት የእግዚአብሔር ድርሻ እንደሆነ ያሳያል፡፡

ጳውሎስም እንዲህ ይላል ‹‹በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና፡፡ አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል፡፡ ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፣ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን›› (ሮሜ. 8፡14-17)፤ ‹‹በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና›› (ገላ. 3፡26)፣ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደ ሰጠን እዩ›› (1ዮሐ. 3፡1-2) እግዚአብሔር ፍቅር በመሆኑ አባት ሲሆነን፤ እኛን ደግሞ ልጆቹ በማድረግ መብት ሰጠን፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችን ማረጋገጫው መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠን ምስክርነት ነው፡፡

ዛሬ ያላመኑ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ብለው ባይጠሩንም፣ በእግዚአብሔር ዓይን ጌታን ባመንበት ጊዜ ልጅነትን  አግኝተናል፡፡  ልጅነትን ማግኘት በዕድገት የሚመጣ ሳይሆን፣ ጌታን ባመንበት ጊዜ ወዲያው (በቅጽበት) በማመናችን የሚሰጠን መብት ነው፡፡ ልጅነታችን ወደፊት በክብር እንደሚገለጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እርሱም ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን›› (ሮሜ. 8፡23) ይህ የልጅነት መብት የተሰጠን የአንድ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ ልጆች ሆነን በኅብረት አብረን እንድንኖር ነው፡፡ እግዚአብሔር አባታችን በመሆኑ ‹‹መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ›› (ማቴ. 5፡16) ብሎ በሚናገረው መሠረት እግዚአብሔርን እያገለገልን፣ እርሱን የሚያስከብር ኑሮ መኖርና ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ልጆች በመሆናችን በንጹሕ ልብና ባሕርይ አባታችንን እየመሰልን ልንኖር ተጠርተናል፡፡

ጽድቅ፡- ጽድቅ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች የፍርድ ቤት ቋንቋ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በእምነት መጽደቅ  የክርስቲያን ሥነ-መለኮት ትምህርት ከሁሉ በላይ የላቀና የመጀመሪያውን ሥፍራ የያዘ የክርስትና ትምህርት ነው፡፡ እግዚአብሔር ጽድቅን በጸጋ ሲሰጥ፣ ሰው ደግሞ ይህን ጸጋ የተቀበለው በእምነት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምረናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ 3፡21-26 ባለው ክፍል ውስጥ ስንመለከት እግዚአብሔር የሰውን ልጆች ሁሉ ከኃጢአት በታች ከዘጋ በኋላ በሕግና በነቢያት የተመሰከረለትን የራሱን ጽድቅ እንዳቆመ ይናገራል፡፡ በተለይ ቁ.22፣ 25፣ 28፣ እና 30 ላይ ትኩረት ስናደርግ የእግዚአብሔር ጽድቅ በእምነት ብቻ እንደሚገኝ እንረዳለን፡፡ ቁ.24 እንዲህ በማለትም ያስቀምጠዋል ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ››፡፡ ሰው የእግዚአብሔርን ነጻ ስጦታ ሲቀበል ያለ ሥራ እንዲሁ በነጻ የእግዚአብሔርን ጽድቅ ያገኛል፡፡

ጽድቅ ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ ከቃሉ የምናገኘው መልስ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል፣ ከፍርድ ነፃ መሆንና ትክክለኛውን ማድረግ የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ቃሉ ‹‹እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ›› (ሮሜ 5፡1፣ ቲቶ 3፡7) በሚለው መሠረት ለሕይወታችን ሰላምን እናገኛለን፡፡ ስለዚህ የጽድቅ ውጤት ሰላም፣ ከፍርድ ነፃ መሆን፣ ወራሽነትና ክብር ናቸው፡፡ ጳውሎስም በሕግ ትምህርት ሥር ወድቀው ለነበሩት ለገላትያ ሰዎች ሲጽፍላቸው እንዲህ ይላል ‹‹ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል›› (ገላ. 2፤16)፤ ‹‹እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው›› (2ቆሮ. 5፡21) በሮሜም 8፡1 ላይም ‹‹እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም›› ይላል፡፡ ክርስቶስ የእኛን ሞት ሲወስድ፣ እኛ ደግሞ የእርሱን ጽድቅ ወሰድን፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በልጁ ሞት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጽድቆናል፡፡

እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ኃጢአት በሠሩበት ጊዜ ሞትን እንዲሞቱ ፈርዶባቸው ነበር፡፡ አሁን ያንን ፍርድ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በማድረግ እኛን ከፍርድ ነጻ አወጣን፡፡ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለ እኛ ኃጢአት በተደረገበትና በሞተበት ጊዜ አባቱ ፊቱን አዞረበት፡፡ እኛ ግን የእርሱን ጽድቅ እንድንወስድ በማድረግ ከፍርድ ነጻ መሆናችንን አወጀ፡፡ ኃጢአት ሠርተን እንዳልሠራን ቆጠረን፡፡ ጌታን ከመቀበላችን በፊትም ሆነ ዛሬም እስክንሞትም ድረስ የምንሠራው ኃጢአት ሁሉ ዋጋው ስለ ተከፈለ እኛ በኃጢአታችን አንጠየቅም፤ ይህ ማለት ኃጢአት ስንሠራ ንስሐ መግባት የለብንም ማለት አይደለም፡፡ ዮሐንስ በአንደኛ በመልእክቱ  እንዲህ  ይላል፡- ‹‹ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፣ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም፡፡ በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጠአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነፃን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡ ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን፣ ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም›› (1ዮሐ. 1፡8-1)፤ በመቀጠልም ‹‹ልጆቼ ሆይ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ፡፡ ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው›› (1ዮሐ. 2፡1) ሁልጊዜ ሕይወታችንን በንፅህና ለመጠበቅና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ኅብረት ለመጠበቅ የኃጢአት ኑዛዜ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳየናል፡፡

በክርስቶስ በኩል ባገኘነው ጽድቅ ምን ያህል ደስተኛ ነህ ? ደስተኛ ከሆንክ ጌታን አመስግን፡፡

ቅድስና፡- ከድነት ውጤቶች ከልጅነትና ከጽድቅ ቀጥሎ ከምናገኘው በረከት አንዱ ቅድስና ነው፤ እግዚአብሔር በወንጌሉ አማካኝነት ወደ መንግሥቱና ክብሩ የጠራን፤ ልባችንን ከፍተን የምሥራቹን ቃል እንድንሰማ፤ ንስሐ እንድንገባና ክርስቶስን በማመን የሕይወታችን ጌታ በማድረግ፤ አዲስ ፍጥረት እንድንሆን ነው፡፡ ቃሉ እንደሚናገረው ‹‹ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው አሮጌው ነገር አልፎአል እነሆ፡- ሁሉም አዲስ ሆኖአል›› (2ቆሮ. 5፡17) ስለሚል ጌታን ካመንበት ቀን ጀምሮ በቅድስና ሕይወት መኖር እንጀምራለን፡፡ ይህ የቅድስና ሕይወት የልጁን መልክ እስክንመስል ድረስ የምናድግበት ሕይወት ነው፡፡

ቅድስና ማለት ምን ማለት ነው? ብለን ብንጠይቅ ቅድስና ማለት መለየት ማለት ነው፣ የሚል መልስ እናገኛለን፡፡ በትርጉም  ደረጃ መለየት ማለት ነው ብንልም፣ ለቅድስናችን ምንጭ የሆኑትን በጥናታችን ትኩረት እንሰጣቸዋለን፡፡ የመጀመሪያው  ‹‹በእውነትህ ቀድሳቸው፣ ቃልህ እውነት ነው›› ባለው መሠረት የእግዚአብሔር ቃል ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ የሚመጣው ጌታ ራሱ ነው፣ ‹‹እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ›› (ዮሐ. 17፡17-19) በዚህ ጥቅስ ላይ እንደሚናገረው የቅድስናችን ምንጭ ቃሉና ኢየሱስ ራሱ እንደሆኑ እናገኛለን፡፡ ሦስተኛው የቅድስና ምንጫችን መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ፤ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ አማኞች ሲጽፍላቸው እንዲህ ይላል፣ ‹‹በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል›› (1ቆሮ. 6፡11፣ 1ጴጥ. 1፡1-2፣ 2ተሰ. 2፡13) በማለት በግልጽ የቅድስናችን ምንጭ መንፈስ ቅዱስ እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ቅዱሳን መባላችን የጠራን ታማኝ ስለሆነ እንጂ፣ መልካም ነገር ተገኝቶብን አይደለም፤ ስለዚህ ስሙ የተመሰገነና የተባረከ ይሁን፡፡

ይህ በእግዚአብሔር በኩል ያለ ክንዋኔ ሲሆን በእኛም በኩል የሚጠበቅብንን ድርሻ መወጣት አለብን፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ‹‹እኔ ቅዱስ እንደ ሆንኩ ቅዱሳን ሁኑ›› ብሎ እንደ ተናገረው በአዲስ ኪዳንም ጴጥሮስ ይህንኑ እውነት ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተም ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ›› (1ጴጥ. 1፡15-16) ብሎ አስቀምጦታል፡፡ ስለዚህ ዕለት በዕለት ጌታን እየመሰልን በቅድስና ሕይወት መመላለስና ማደግ ይጠበቅብናል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም በሮሜ መልእክቱ ራሳችንን በቅድስና እንዴት መጠበቅ እንዳለብን ሲያስረዳ ‹‹ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ›› (ሮሜ 6፡13) በማለት ስለ ቅድስና በሰፊው ያስተምረናል፡፡ በመቀጠልም ‹‹እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ››   (ሮሜ 12፡1) ‹‹እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ›› (ሮሜ 8፡13)፡፡ በመጨረሻም ጳውሎስ የተሰሎንቄን ክርስቲያኖች ሲመክር እንዲህ ይላል ‹‹የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ›› (1ተሰ. 5፡23)፤ አዲስ ሰው በመሆን፣ በቅድስና፣ ክርስቶስን በመምሰል፣ እግዚአብሔርን በመምሰል፣ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እያፈራን፣ በመንፈሳዊነት  ሁሉ የመኖር ግዴታ አለብን፡፡ እነዚህ ሁሉ የተለያዩ ሀሳቦች ሳይሆኑ መለወጣችን እውነት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱሳችን በተለያየ አገላለጽ  የሚጠቀምባቸው ሀሳቦች ናቸው፡፡

እግዚአብሔር ድነትን ስንቀበል ቀድሶናል፤ ከኃጢአት ቅጣት ድነናል፤ ዛሬ ደግሞ በመታዘዝ ሕይወት ከኃጢአት ኃይል ጋር እየታገልን መቀደስ ይጠበቅብናል፤ አንድ ቀን ደግሞ ስንሞት ወይም ጌታ መጥቶ ሲወስደን ከኃጢአት ህልውና ፍጹም እንሆናለን፡፡ ስለዚህ በቅድስና ሕይወት የመኖርና የመመላለስ ድርሻና ኃላፊነት ስለ አለብን የጌታን እርዳታ በጸሎት እየጠየቅን መኖር ይፈለግብናል፡፡ በዚህ ጥናታችን መሠረት በድነት የእግዚአብሔርም የሰውም ድርሻ እንዳለ ተመለክተናል፡፡ በዚህ ትምህርት ተራርቆ ከመኖር ተቀባብሎና ተከባብሮ መኖር ለአገልግሎታችን እጅግ ጠቃሚና አስፈላጊ ነው፡፡ በክርስቶስ ያገኘነውን አንድ አካልነት ከሁሉ በላይ አጉልተን እናሳይ፡፡ በእኔ የድነት አስተምህሮ  የእግዚአብሔር ድርሻ አስቀድሞ ማወቅ፣ መወሰንና መጥራት ሲሆን፤ የሰውም ድርሻ ደግሞ ጥሪውን መስማት፣ ንስሐ መግባትና በክርስቶስ ማመን ሲሆን፤ በመጨረሻም የተቀበሉትን ማጽደቅና ማክበር የእርሱ ድርሻ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ 

ከዚህ በመቀጠል አስተምህሮተ መንፈስ ቅዱስ በሚለው ርዕስ ሥር ትምህርተ ቤተ ክርስቲያንን አናጠናለን፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *