2.2 የሰው ድርሻ
ከዚህ ቀደም ብለን ባጠናነው ጥናታችን ስለ ምርጫ ቃሉ ምን እንደሚያስተምር ለማየት ሞክረናል፡፡ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ስለ ድነት ስናነሳ ሰው ምንም ድርሻ እንደ ሌለው የሚያስቡና የሚያስተምሩ ሲኖሩ፤ እንዲሁም ሰው ድርሻ አለው የሚለውን አስተሳሰብ ደግሞ የሚቀበሉና የሚያስተምሩ እንደ አሉ ተመልክተናል፡፡ አሁንም ስለ ሰው ድርሻ ስናጠና ቃሉ የሚለውን ለማየት እንሞክራለን፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን አንድ በአንድ በመውሰድና በሕይወታችን የተከናወነውንም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቃሉ የሚለውን ለማጥናትና ለማወቅ እንጀምራለን፡፡
መስማት፡- ሰው ስለ ድነት የሚተላለፈውን መልእክት የመስማት ኃላፊነት እንዳለበት ከተሰጠው ጆሮ መረዳት እንችላለን፡፡ ሰው ጆሮ የተሰጠው ማዳመጥና ምላሽ መስጠት እንዲችል ሲሆን፤ ምላሹንም ከእንስሳ በተለየ በንግግር መግለጥ ይችላል፡፡ የወንጌሉ ጥሪ በሚተላለፍበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ሰውን ስለ ኃጠአቱ በሚወቅስበት ጊዜ፤ የሰው የመጀመሪያው ኃላፊነት በቃሉና በመንፈስ ቅዱስ የሚተላለፈውን መልዕክት መስማት ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ኤፌሶን አማኞች መዳን ሲናገር፣ ‹‹እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው›› (ኤፌ. 1፡13)፤ በዚህ ሥፍራ ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ሐሳቦች፣ መስማት፣ ማመንና መታተም የሚሉት ናቸው፡፡ ጳውሎስም አንድ ሰው በድነት መንገድ እንዴት ማለፍ እንዳለበት በመልእክቱ በቅደም ተከተል አስቀምጦት እናገኛለን፡፡ ሰው ለመዳን ሊያደርጋቸው የሚገቡ መሠረታዊ ነገሮች ሀ. መስማት ለ. ማመን የሰው ድርሻ ሲሆኑ ሐ. መታተም ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ድርሻ እንደሆነ ያመለክተናል፡፡
እግዚአብሔር አስቀድሞ አዳምንና ሔዋንን ሲፈጥር ከተከለከለችው ዛፍ በስተቀር የመብላት፣ የመጠጣት፣ የመሥራት፣ የመተኛት፣ የመውለድ፣ የማየት፣ የመስማት የመንቀሳቀስና የፈለገውን ሁሉ እንዲያደርግ ለሰው ነፃ ፈቃድ ተሰጥቶት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ሰው የተሰጠውን ነፃ ፈቃድ ተጠቅሞ፤ ከእግዚአብሔር የሚለየውን ኃጠአት ሠራ፡፡ እንደዚሁም ሰው የተሰጠውን ነፃ ፈቃድ ተጠቅሞ ወንጌልን በፈቃደኝነት መስማት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ነፃ ፈቃድ ለሰው ሁሉ በመድረሱ በሐዋርያት ሥራ 2፡38 ላይ ጴጥሮስ በበዓለ ኀምሳ ቀን ለተሰበሰበው ሕዝብ በሰበከ ጊዜ፤ የተሰጣቸውን ነፃ ፈቃድ በመጠቀም ወደ ሦስት ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ቃሉን ሰምተው፤ ልባቸው በቃሉ በተነካ ጊዜ፣ ‹‹ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ?›› ብለው ሐዋርያትን ሲጠይቋቸውና ባገኙት መልስ መሠረት ክርስቶስን በማመን ሕይወታቸውን ለጌታ ሰጡ፡፡
መስማት ስንል፣ የሚሰማው ምንድን ነው ? ብለን እንጠይቅ ይሆናል፤ ብዙ የሚሰሙ ነገሮች ቢኖሩም፤ በድነት ደረጃ ሰው ሊሰማቸው የሚገቡ ሁለት ዋና ነገሮች፤ የመጀመሪያው ስለ ራሱ ኃጢአተኛነት ሲሆን፣ ሁለተኛ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ በሰማነው ቃል አማካኝነት ስለ ኃጢአታችን ሲወቅሰንና ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን እንደ ሞተልን ሲመሰክርልን ወዲያውኑ ይህን እውነት በመረዳት በነፃ ፈቃዳችን በመጠቀም ወደ ውሳኔና ማመን እንመጣለን፡፡ በማመን ውስጥ ሁለት አስፈላጊ ነገሮች አሉ፣ እነርሱም ንስሐና እምነት ሲሆኑ በአንድ ጊዜ በሰው ሕይወት ውስጥ ይከናወናሉ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ንስሐ ይቀድማል ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ እምነት ይቀድማል ብለው ያስተምራሉ፡፡ ነገር ግን ሁለቱም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ስለሆኑ ሳይቀዳደሙ፣ በአንድ ጊዜ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ኃጢአቱን የተረዳ ሰው እዚያ ላይ ሳይቆም ወዲያውኑ ስለ ኃጢአቱ ክርስቶስ እንደ ሞተለት ሲሰማና ሲያውቅ፤ ንስሐ በመግባት ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሕይወቱ በመጋበዝ ጌታውና አዳኙ አድርጎ ይቀበላል፡፡
መንፈስ ቅዱስ የሰውዬውን ውሳኔ በማየት ወደ ድነት እንዲመጣ ይህንን ርምጃ እንዲወስድ ይረዳዋል፡፡ ሰውዬው ርምጃውን በመውሰድ ዳግም ይወለዳል፤ በዚህ በኤፌሶን ትምህርት መሠረትም መንፈስ ቅዱስ ያትምበታል፡፡ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጥናታችን ላይ ባየነው መሠረት ዳግም ልደት፣ ልጅነት፣ ጥምቀት፣ ሙላትና መታተም የአንድ ጊዜ የሥራው የተለያዩ ገለጻዎች (ገጽታዎች) ናቸው፡፡ ‹‹… እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው›› (ሮሜ. 10፡17) ስለሚል ቃሉ፣ ሰው ራሱ የመስማት ድርሻ እንዳለው ሁሉ፣ ለመቀበልም ላለመቀበልም በድነት ሥራ ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡
ንስሐ፡- ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፤ ሰው ቃሉን ሲሰማ የራሱን ኃጢአተኛነትና የጌታን አዳኝነት ይረዳል፤ በዚህ መሠረት ስለ ኃጢአቱ ንስሐ ይገባል፡፡ ንስሐ ማለት ምን ማለት ነው ብለን ብንጠይቅ፤ መጸጸት፣ መመለስ፣ አቅጣጫን፣ አሳብን መቀየር ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው በድነት ሥራ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስን ጥሪ በቃሉ አማካኝነት ሰምቶ፤ ክርስቶስን ለማመን ወደ ውሳኔ የሚመጣበት ሂደት ንስሐ ይባላል፡፡ ስለ መንፈስ ቅዱስ በምናጠናበት ጊዜ እንዳየነው አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ቃል በሚሰማበት ጊዜ ቃሉ ስለ ኃጢአቱ ሲናገረውና መንፈስ ቅዱስም ስለ ኃጢአቱ ሲወቅሰው፤ ሞትና ኵነኔ እንዳለበት ይረዳል፡፡ በዚህ ጊዜ ሰውዬው በኃጢአቱ ምክንያት ሞት፣ ፍርድና ኵነኔ እንዳለበት ሲያውቅና ሲረዳ አሳቡን ለመቀየር ይነሳል፡፡ ከዚህ ሞት ሊያድነው የሚችል እንዳለ ሲያውቅ ወዲያውኑ በክርስቶስ ያምናል፡፡ ንስሐ መግባት በምንልበት ጊዜ በውስጡ በኃጢአት ማዘንን፣ መናዘዝንና መራቅን ያመለክታል፡፡
መዝሙረኛው በመዝሙሩ እንዲህ ይላል ‹‹ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል›› (ምሳ. 28፡13)፤ ሐዋርያው ዮሐንስም በመልእክቱ ‹‹በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው›› (1ዮሐ. 1፡9 ሲል፤ ጴጥሮስም ‹‹…ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም›› (የሐዋ. 3፡19-20) በማለት ሰው በድነት ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል፡፡ ለድነት ንስሐ መግባት አስፈላጊ ስለ ነበረ መጥምቁ ዮሐንስም ‹‹መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ›› እያለ እየሰበከ እንደመጣ ቃሉ ይነግረናል (ማቴ. 3፡1-2)፡፡ እንዲሁም ጌታ ኢየሱስ አገልግሎቱን በምድር ሲጀምር ‹‹ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ›› በማለት ማርቆስ በወንጌሉ አስፍሮት እናገኛለን (ማር. 1፡15)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረበት ጊዜና በትንሣኤው ቀን፤ እየተጠራጠሩ አብረውት ለተጓዙት የኤማሁስ ደቀ መዛሙርቱ የሰጠው ትእዛዝ፣ ‹‹ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሳል በስሙም ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ ይሰበካል›› (ሉቃ. 24፡47) የሚል ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ጴጥሮስና ጳውሎስም ትምህርታቸውን የጀመሩት በንስሐ ትምህርት ነበር፡፡ ጴጥሮስ በበዓለ ኀምሳ ቀን ‹‹ንስሐ ግቡ›› ብሎ (የሐዋ. 2፡38) እንደ ሰበከ፤ ጳውሎስ ደግሞ ‹‹ንስሐንና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንን…›› (20፡20) እንዳስተማረ ቃሉ ይነግረናል፡፡ ወንጌላዊው ሉቃስም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17፡30 ላይ ‹‹እንግዲህ እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል›› በማለት ንስሐ በድነት ጊዜ ከሰው የሚጠበቅ እንደሆነ ያስገነዝበናል፡፡ ንስሐ ከመስማት ቀጥሎ ከሰው የሚጠበቅ ድርሻ ነው፤ ንስሐ ስንገባ በአእምሮአችን በስሜታችንና በፈቃዳችን ለውጥ ይከናወናል (የሐዋ. 2፡37-38፣ 2ቆሮ. 7፡9)፡፡
እምነት፡- አስቀድሜ እንዳልኩት ንስሐና እምነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች (መልክ) ሲሆኑ፤ እምነት (FAITH) እና ንስሐ (REPENT) የማመን (BELIEF) ሁለት ክፍሎች ናቸው፡፡ ንስሐ በኃጢአታችን በበደላችንና በፍርዳችን እንዳንጠፋ የመመለስ እርምጃ መውሰድ ሲሆን፤ እምነት ደግሞ ኃጢአታችንን በደላችንንና ፍርዳችንን ኢየሱስ ስለ ወሰደልን፤ በእኛ ቦታ የሞተልንን ጌታ ወደ ልባችን በማስገባት፤ ጌታና አዳኝ አድርጎ፣ የተፈጸመው ድርጊት እውነት ነው ብሎ መቀበል እምነት ነው፡፡ ‹‹…የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸዋል›› (ሮሜ. 2፡7)፤ ‹‹ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣን ሰጣቸው›› (ዮሐ. 1፡12)፤ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና›› (ዮሐ. 3፡16) በሚሉት ጥቅሶች ውስጥ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ላደረገው ጥሪ፣ እምነት ምላሽ የሚሰጥበት መንገድ ነው፡፡ ለሚፈልጉ ለተቀበሉት፣ ለሚያምኑትና በእርሱ የሚያምን የሚሉት ቃላቶች ሰው ለመዳን የማመን ድርሻ እንዳለው ሲያመለክቱ፤ ሐዋርያው ጳውሎስም ቀደም ብለን ባየነው ክፍል፣ ይህን ሐሳብ በማጠናከር እንዲህ ያስቀምጠዋል ‹‹እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ›› (ኤፌ. 1፡13) በማለት በእርሱ ትምህርት (ዶክትሪን) መሠረት የድነትን ቅደም ተከተል ያስቀምጣል፡፡
ለመዳን አስቀድሞ ወንጌልን መስማት ያስፈልጋል፣ ወንጌልን ስንሰማ ሁለት ነገሮች ይፈጸማሉ፣ በኃጢአታችን ምክንያት ሞትና ኵነኔ እንደ ተፈረደብን ስናውቅ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአታችን እንደ ሞተ ስንረዳ፣ አዳኝነቱን በመቀጠል በክርስቶስ እናምናለን፡፡ ጳውሎስም በኤፌሶን መልእክቱ መስማት፣ ማመንና መታተም ብሎ በቅደም ተከተሉ ባስቀመጠው ውስጥ የሰውንና የእግዚአብሔርን ድርሻ በግልጽ ያሳየናል፡፡ ስለዚህ አስቀድሜ እንዳልኩት ንስሐና እምነት በማመን ተጠቃለው፣ የሰው ድርሻ ሲሆኑ፤ ማተም (መታተም) የእግዚአብሔር ድርሻ ነው፡፡
ቃሉን ሰምቶ፣ ንስሐ ገብቶ ያመነ ሰው ለመዳኑ ምልክቶች አሉት፤ ኃጢአትን የመጥላት ባሕርይ ከክርስቶስ ይወርሳል፣ ሰዎችን ይወዳል የእግዚአብሔር ፍቅር በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በልቡ ይፈሳል፣ ለመዳኑ በውስጡ የመንፈስ ቅዱስ ምስክርነት ሲያገኝ፣ ባገኘው ድነት የምሥጋና ሕይወት ይኖረዋል፡፡
0 Comments