በእጮኝነት ጊዜያችሁ ከእጮኛችሁ ደብዳቤ ደርሷችሁ ያውቃል? የመጀመሪያው ደብዳቤ ደርሷችሁ ሁለተኛውን እንዴት ባለ ናፍቆት ጠበቃችሁ? የሚጠበቅ ደብዳቤ ልብ ይሰቅላል፣ ቀናት ይረዝማሉ፣ ክንፍ አውጥቶ ብረሩ ብረሩ ያሰኛል፡፡ ስለ ደረሰብኝ አውቀዋለሁ፡፡ በአሁኑ ዘመን እንኳ ምንም ችግር የለውም፣ ዕድሜ ለስልክ፣ ለሞባይል፣ ለኢሜል፣ ለስካይፒ … ችግሩን በቀላሉ ማቃለል ይቻላል፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ መልእክት ላኪው ወንጌላዊ ሉቃስም ሆነ ተቀባዩ ቴዎፍሎስ የእነዚህ ሁሉ ነገሮች ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡ ምክንያቱም የኤሌትሮኒክስ መሪሣያዎች በጊዜው ስላልነበሩ ነው፡፡ መልእክት ተቀባዩ፣ መልእክት ላኪው ወንጌሉን ከጻፈለት በኋላ ከወዳጁ ሌላ ደብዳቤ ሳይጠብቅ አልቀረም፡፡ ከወንጌሉ የሚቀጥለውን ታሪክ እጽፍልሃለሁ ብሎት ከሆነማ ጉጉቱ በጣም ይጨምራል፡፡ ስለዚህ የሐዋርያት ሥራ በናፍቆት የሚጠበቅ ደብዳቤ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እኛስ ከዚህ ደብዳቤ ለመማር በጉጉት የምንጠብቀው ነገር አለ ?
መልእክት ላኪው ወይም የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊው ማነው ብለን ብንጠይቅ ሉቃስ ነው የሚል መልስ ከውስጥ ማስረጃ ማግኘት ቢያስቸግረንም በ2ኛ ጢሞቴዎስ 4፡10 ላይ ያለውን ጳውሎስ “ሉቃስ ብቻ ከእኔ ጋር አለ” የሚለውን ሐሳብ እንደ ጠቋሚ በመውሰድ ጸሐፊው ሉቃስ ነው ማለት እንችላለን፡፡ እንዲሁም በሉቃስ ወንጌልና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የቴዎፍሎስ ስም በመጠቀሱ የሁለቱም መጽሐፎች ጸሐፊ አንድ ሰው እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት ጸሐፊው ሉቃስ ነው ካልን፣ መልእክት ተቀባዩ በሐዋርያት ሥራ 1፡1 ላይ እንደምናገኘው ቴዎፍሎስ መሆን አለበት፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም ጸሐፊው ሉቃስ እንደሆነ የሚናገርበት ሥፍራ ያለመኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ የአዲስ ኪዳንም ጸሐፊዎች ቢሆኑም ስለ ሉቃስ የሚነግሩን በሦስት ጥቅሶች ላይ ብቻ ነው፡፡ (ቆላ. 4፡ 16 ፣ ፊልሞና ቁ. 24፣ 2ጢሞ. 4፡11) ሉቃስ ሐኪም፣ የጳውሎስ ውድ፣ ታማኝ ረዳቱና የመጨረሻው እስራቱ ጓደኛው ነበረ፡፡ ሉቃስ ብቸኛው አህዛባዊ (አይሁድ ያልሆነ) የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ጸሐፊም ነበረ፡፡ ስለ መልዕክት ተቀባዩ ቴዎፍሎስ ማንነት የተለያየ አመለካከት ቢኖርም አህዛባዊ / ግሪካዊ እንደሆነና የሮማውያን ባለ ሥልጣን እንደሆነ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች ይስማማሉ፡፡ ሉቃስም በወንጌሉ “የከበርህ ቴዎፍሎስ ሆይ” በማለት ይጠራዋል፡፡ ሉቃስና ይህ የከበረ ሰው በምን እንደተገናኙና ወዳጅነት እንደጀመሩ መጽሐፉ ምንም የሚነግረን ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን መማሩና ባለሥልጣን መሆኑ ችግር ሳይፈጥርበት፣ በጣም ዕንቁ የሆነ መልእክት ለድነቱና(ደህንነት) ለሕይወቱ መመሪያ ማግኘቱ አስደናቂ ነው፡፡ ብዙዎች ያላገኙትን ድነት ማግኘቱ ጌታ ምን ያህል ይወደዋል? እርሱስ ምን ያህል ጌታን ይወዳል? ብለን እንድንጠይቅና እንድንደነቅ ያደርገናል፡፡
0 Comments