ለ) የወልድ ምርጫ፡- ስለ አብ ባደረግነው ጥናት፤ በድነት ሥራ ውስጥ እግዚአብሔር አብ ልጁን በሚልክበት ጊዜ ማን እንደሚያምንና እንደማያምን በመለኮታዊ ዕውቀቱ አስቀድሞ ማወቅ፤ መወሰን፤ መጥራት፤ ማጽደቅና ማክበር እንደሚከናወኑ ተመልክተናል፡፡ አብ ልጁን ሲልክ ልጁም ኢየሱስ ክርስቶስ ተልዕኮውን ተቀብሎ ተግባራዊ ሲያደርግ በቃሉ ውስጥ እናያለን፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ እንዲህ ይላል ‹‹እግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡ በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና›› (1ዮሐ. 4፡9) ‹‹እርሱ ስለ እኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል …›› (1ዮሐ. 3፡16)፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስም በገላትያ መልእክቱ ምዕራፍ 3፡13 ላይ ‹‹…ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን  ዋጀን›› በአንደኛ ጢሞቴዎስም መልእክቱ ላይ ጢሞ. 2፡6  ‹‹… ራሱን ለሁሉ ቤዛ ሰጠ›› ይላል፡፡ ጌታም ስለ ራሱ ሲናገር እንዲህ ይላል ‹‹…የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም››        (ማቴ. 20፡28)፤ ‹‹… አብ ልፈጽመው የሰጠኝን ሥራ  ይህ የማደርገው ሥራ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና›› (ዮሐ. 5፡36) በሚሉት ጥቅሶች ውስጥ፣ ጌታ ሊያድነን የመጣው የሰው ልጆችን ሁሉ እንደሆነ ያመለክተናል፡፡ የጌታ   ተልዕኮው ሰዎችን ከመፈወስ ጀምሮ በመጨረሻም ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ ለአባቱ በሚያቀርብበት ጊዜ እንዲህ ብሎ ጸለየ፡፡ ‹‹እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ›› (ዮሐ. 17፡4) አይሁድንና አሕዛብን፣ የተማረውንና ያልተማረውን፣ ድሃና ሀብታም፣ ሳይል ለሰው ሁሉ ፍቅሩን መስጠቱን፤ አባቱ የሰጠውን ተልዕኮ እንዳገባደደ በጸሎቱ ሪፖርት ያደርጋል፡፡

ምትክነት/ቤዛነት፡- የወልድ ምርጫ የተከናወነው በአራት መንገዶች እንደሆነ በጥናታችን እንመለከታለን፤ አዳምና ሔዋን በሠሩት ኃጢአት ምክንያት የሰው ልጅ ሁሉ ኃጢአተኛና ሞት የተፈረደበት እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፡፡ በዚህ መሠረት እኛ ሁላችን በኃጢአታችን ምክንያት መሞት ሲገባን፣ እርሱ በእኛ ቦታ ምትክ/ቤዛ ሆኖ እንደ ሞተልን ቃሉ ያስተምረናል፡፡ በብሉይ ኪዳን ጊዜ አንድ ሰው ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ አንድ ንፁህ የሆነ የአንድ ዓመት ጠቦት  ወደ ካህኑ ይዞ በመሄድ መሥዋዕት ያቀርባል፡፡ ካህኑም በቀረበው በግ/እንሰሳ ላይ እጁን በመጫን ጸሎት ያደርጋል፡፡ በዚህን ጊዜ የእንሰሳው ንፅህና ወደ ኃጢአተኛው ሰው፣ የሰውዬው ኃጢአት ወደ በጉ እንዲተላለፍ በመጸለይ እንሰሳው መሥዋዕት ሆኖ እንዲቀርብ ያደርጋል፡፡

በአዲስ ኪዳን የተሰዋልን የእግዚአብሔር በግ የሆነው የናዝሬቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ኢየሱስ ራሱ ሲናገር እንዲህ ይላል ‹‹…የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም         (ማቴ. 20፡28)፤ ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ የሞተበትን ዓላማና ምክንያት ሲገልጽ ‹‹ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና…›› (1ጴጥ. 3፡18)፤ ሐዋርያው ጳውሎስም በመልእክቱ እንዲህ አቅርቦታል ‹‹… ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል›› (ሮሜ. 5፡6-8)፤ ‹‹እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው›› (2ቆሮ. 5፡21)፤ ‹‹ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ›› (1ጢሞ. 2፡6)         (ዕብ. 9፡12)፡፡ ከዚህ በላይ ያሉትን ጥቅሶች ስንመለከት በድነት ውስጥ የአብና የወልድ ድርሻ ምን እንደሆነ ያሳዩናል፡፡ እግዚአብሔር አብ ፍቅሩን በልጁ በኩል ሲገልጥ እግዚአብሔር ወልድ ደግሞ ምትካችን/ቤዛችን ሆኖ፣ (እኛ በኃጢአታችን መሞት ሲገባን)፣ ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት ፍቅሩን ገለጠልን፡፡ እኛም ይህን ፍቅሩን በእምነት ብንቀበለውና ያገኘነውንም ሕይወት አጥብቀን ይዘን ብንመላለስ ሕይወት ይሆንልናል፡፡

መዋጀት፡- ክርስቶስ  ከቤዛነት ቀጥሎ በሞቱ ከሠራልን ሥራዎች አንዱ የመዋጀት ሥራ ነው፡፡ መዋጀት ማለት መግዛት ማለት ሲሆን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በድነት ሥራው ያደረገው ነገር ቢኖር፣ እግዚአብሔር ሰዎችን ሲፈጥር የራሱ ነበርን፣ በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ርቀን በጠላት እጅ ውስጥ ወድቀን የሌላ የነበርነውን በደሙ በመዋጀት እንደገና መልሶ የእግዚአብሔር የራሱ ልጆች (ገንዘቡ) እንድንሆን አደረገ፡፡

በብሉይ ኪዳን አንድ ሰው መኖር ሲያቅተው ራሱን ባሪያ አድርጎ ለሰባት ዓመት ይሸጣል፡፡ ከሰባት ዓመት በፊት ዕዳውን ከፍሎለት ነፃ የሚያወጣው/ የሚዋጀው የቅርብ ዘመድ ካገኘ ሰባት ዓመቱ ሳያልቅ ነፃ መውጣት ይችላል፡፡ እንዲሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ የሰይጣን ባሮች በነበርንበት ጊዜ፣ እኛን ለመዋጀት እንዲችል ሰው ሆኖ የቅርብ ዘመዳችን ሆነ፤ ቃሉ እንደሚል ‹‹… ባሪያዎች ነበርን ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ እንደ ልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ›› (ገላ. 4፡4፣ 3፡13)፤ ‹‹በክቡር የክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ ታውቃላችሁ›› (1ጴጥ. 1፡18)፤ ‹‹መድኃኒታችንም ከዓመፅ ሁሉ እንዲቤዠን … ስለ እኛ ነፍሱን ሰጥቶአል›› (ቲቶ. 2፡14)፤ ‹‹መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹን ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፣ ታርደሃልና፣ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው…›› (ራዕ. 5፤9)፣ (2ጴጥ. 2፡1) በማለት ጌታ የመዋጀቱን ሥራ እንደ ፈጸመ ቃሉ አስረግጦ ይነግረናል፡፡

ከዚህ በላይ ያለውን ሐሳብ ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው እግዚአብሔር ወልድ በተሰጠው የተልዕኮ ድርሻ መሠረት፣ ከአባቱ ጠፍተን የነበርነውን እንደገና ወደ ልጅነታችን እንድንመለስ በመስቀል ላይ ደሙን በማፍሰስ፤ የማስታረቁን ሥራ በመሥራት፤ በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል ሰላምን በመፍጠር፣ ዋጅቶን ድነታችንን አስገኘልን፡፡ ድነትን ማስገኘት ብቻ ሳይሆን ከዓመፅ እንድንርቅ አድርጎ ለመንግሥቱ ካህናት ሆነን እንድናገለግለው አድረጎናል፡፡

ማስታረቅ፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኃጢአታችን ቤዛ መሆንና በደሙ መዋጀት ብቻ ሳይሆን የማስታረቅም ሥራ ሠርቶአል፡፡ በአገራችን ባሕል እንደሚታወቀው ሁለት ሰዎች ሲጣሉ፤ የበደለ ሰው የበደለውን ሰው ለመታረቅ ሽማግሌ ልኮ እንዲያስታርቁት ይጠይቃል፤ ሽማግሌዎችም መካከል ገብተው ያስታርቃሉ፡፡ ሽማግሌዎችም ነገሩን ተመልክተው በባሕሉ መሠረት ያጠፋ ሰው እንዲክስ በማድረግ ያስታርቁታል፡፡

በመጽሐፍ ቅዱሳችን ስንመለከት ሰው አትብላ የተባለውን በመብላቱ ኃጢአትን ሠራ፤ ኃጢአት መሥራቱ ብቻ ሳይሆን  እግዚአብሔር በሰጠው ትእዛዝ ላይ በመጨመር ‹‹አትንኩት›› ተብለናል፤ በማለት ሔዋን በኃጢአት ላይ ኃጢአት ጨመረችበት፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰጠውን ትእዛዝ ባለ መጠበቃቸው የበደሉት እግዚአብሔርን ነው፤ እርሱ ራሱ ተበድሎ ሳለ፣ ልጁን ሽምግልና በመላክ ካሳውን ራሱ ከፍሎ፤ ከሰው ልጆች ጋር የታረቀበትን ሁኔታ ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፡፡ ‹‹… እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና…›› (2ቆሮ. 5፡18-19) ካለ በኋላ ማስታረቅ ብቻ ሳይሆን የማስታረቅም አገልግሎት እንደ ተሰጠንም ይናገራል፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስም በመጨመር እንዲህ ይላል፣ ‹‹ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን…›› (ሮሜ. 5፡10) ይልና ይህ መዳን አይሁድንና አሕዛብን አንድ አካል አድርጎ እንዳስታረቀ ሲገልጽ ‹‹… በእርሱ (በክርስቶስ) ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው›› (ኤፌ. 2፡14-16)፤ ‹‹እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፣ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአል (ቆላ. 1፡19-20)) በማለት ኢየሱስ ክርስቶስ የማስታረቅ ሥራ እንደ ሠራ ቃሉ ይናገራል፡፡ እኛም ይህን ዕርቅ በእምነት መቀበል ይኖርብናል፡፡  

ማስተስሪያ፡- ከምትክነት (ቤዛነት)፣ ከመዋጀትና ከማስታረቅ ቀጥሎ በመጨረሻ የምንመለከተው ማስተስርይ የሚለውን ሥራውን ይሆናል፤ ማስተስረይ ማለት እግዚአብሔር ተቆጥቶ በሰዎች ላይ ሊፈርድ ባለበት ጊዜ እንዳይፈርድ ቁጣውን ማብረድ ወይም ከቁጣው ረክቶ የሚመለስበትን ነገር ማድረግ ማለት ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ጊዜ፣ በቤተ መቅደስ የነበረው የታቦት ክዳን ‹‹የስርየት መክደኛ›› ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ እንዲህ ተብሎ የተጠራበት ምክንያት ሊቀ ካህኑ በዓመት አንድ ጊዜ በማስተስሪያው ቀን፣ በስርየት መክደኛው ላይ መሥዋዕት ሆኖ ከቀረበው የበግ ደም ወስዶ ሰባት ጊዜ በመርጨት የሕዝቡ ኃጢአት እንዲሸፈን ያደርግ ነበር፡፡ ‹‹ይህም አንድ ጊዜ በዓመት ለእስራኤል ልጆች ስለ ኃጢአታቸው ሁሉ ያስተሰርይ ዘንድ የዘላለም ሥርዓት ይሁንላችሁ›› (ዘሌ. 16፡34) ሕዝቡም በቀረበው ደም አማካኝነት ከእግዚአብሔር ቁጣ በመሸፈን፤ እንደገናም ለአንድ ዓመት የእግዚአብሔር ቁጣ ወደ እነርሱ እንዳይመጣና እንዳይጣላቸው ያደርግላቸው ነበር፡፡

እንዲሁም ክርስቶስ ለእኛ ማስተስረያ ሆኖ በመሞቱ ምክንያት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ሁለተኛ ጠላትነት እንዳይኖር አድርጎአል፡፡ እንደ ብሉይ ኪዳን ካህናት ለአንድ ዓመት ብቻ የሚሸፍን ሳይሆን፣ ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ጠላትነትን አስቀርቶአል፡፡ ቃሉም እንዲህ በማለት ይገልጸዋል፣ ‹‹እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው›› (ሮሜ. 3፡25፣ 1ዮሐ. 2፡2)፤ ‹‹እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም››     (1ዮሐ. 4፡10)፡፡ ይህም እግዚአብሔር በክርስቶስ መርካቱን ያመለክተናል፡፡

እግዚአብሔር ወልድ የእኛን ድነት ለመሥራት ለኃጢአታችን ምትክ በመሆን፣ በደሙ በመዋጀት፣ ከአባቱ ጋር በማስታረቅና ከእግዚአብሔር ጋር ሁለተኛ እንዳንጣላ ማስተስሪያ ሆኖ በመሞት ሕይወትን ሰጠን፡፡ የእግዚአብሔር አብ ምርጫ የሚከናወነው በልጁ በኩል በሚደረግ ጥሪ (ጥሪው ለሁሉም ነው)፤ ጥሪውን ሰምተው በመታዘዝ ምላሽ ለሚሰጡት፤ ክርስቶስ የአብን ምርጫ በማጽናት፣ ቤዛ ሆኖ፣ በደሙ ዋጅቶ፣ ከአባቱ ጋር አስታርቆና ማስተስሪያ ሆኖ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦአል፡፡ እኛም የተደረገልንን የምርጫ ሂደት በእምነት በመቀበልና ሁለተኛ ጠላትነትን በመካከላችን ላለመፍጠር በቅድስና ሕይወት እየኖርን ጌታን ልናመሰግነውና ልናገለግለው ይገባናል፡፡

            ሐ) የመንፈስ ቅዱስ ምርጫ፡- እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሁሉ መውደዱን የገለጠው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በመስቀል ላይ እንዲሞት በማድረግ እንደሆነ ቀደም ብለን አይተናል፡፡ አብ ይህን ድነት በልጁ በኩል ካዘጋጀ በኋላ በመንፈስ ቅዱስና በሰዎች በኩል፣ ለሰዎች ሁሉ እንዲሰበክ አድርጓል፡፡ ዮሐንስ በወንጌሉ እንዲህ ሲል አቅርቦታል፣ ‹‹… እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤ እናንተም ደግሞ ከመጀመሪያ ከእኔ ጋር ኖራችኋልና ትመሰክራላችሁ›› (ዮሐ. 15፡26-27)፡፡ ታላቁ ተልዕኮ የተሰጣቸውና ምስክር እንዲሆኑ የታዘዙት ሰዎች ወንጌሉን በሚናገሩበትና ለሰዎች ጥሪ በሚያደርጉበት ጊዜ ሰዎች እንዲለወጡ ልባቸውን የሚወቅሰው መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ስለዚህም አገልግሎት ጌታ ራሱ ሲናገር እንዲህ ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሮአቸዋል፡፡ ‹‹እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል፣ ስለ ኃጢአት በእኔ ስለማያምኑ ነው፤ ስለ ጽድቅም ወደ አብ ስለምሄድ ከዚህም በኋላ ስለማታዩኝ ነው፤ ስለ ፍርድም የዚህ ዓለም ገዥ ስለ ተፈረደበት ነው›› (ዮሐ. 16፡8-11)፡፡ በወንገል ሥራ መንፈስ ቅዱስ ያለውን ድርሻ ያመለክተናል፡፡

መንፈስ ቅዱስ በትራክት፣ በሰው ምስክርነት፣ በስብከት፣ በመጽሐፍ፣ በመዝሙር፣ በሬዲዮና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚቀርብለትን ጥሪ መስማትና መቀበል እንዲችል፣ ስለ ክርስቶስ ምስክርነቱን ለሰዎች ይሰጣል፡፡ ሰዎችም እግዚአብሔር ያዘጋጀላቸውን ድነት ለመቀበል፤ የወንጌል ጥሪ በሚደረግበት ጊዜ መስማትና መቀበል አለባቸው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ‹‹እግዚአብሔር በመንፈስ መቀደስ እውነትንም በማመን ለመዳን እንደ በኩራት መርጦአችኋልና ለዚህም የጌታችንን ኢየሱስ ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠራችሁ›› (2ተሰ. 2፡13-14፣ 1ተሰ. 2፡11-12)፡፡ መንፈስ ቅዱስ በወንጌል በኩል የሚያደርገውን ጥሪ ሰምተው ምላሽ በመስጠት የሚያምኑ እነርሱ በእግዚአብሔር አብ የተመረጡ ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡

ስለዚህ በድነት ሥራ ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ድርሻ የወንጌሉን እውነት እያሳየ ስለ ክርስቶስ መመስከርና ስለ ኃጢአታችን በመውቀስ አዳኙን ማሳየት ነው፡፡ ጳውሎስ የኤፌሶንን አማኞች ሲመክር እንዲህ ይላል፣ ‹‹… በተጠራችሁበት መጠራት እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ›› (ኤፌ. 4፡1)፤ ጢሞቴዎስንም ‹‹ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና…›› (2ጢሞ. 1፡9) እያለ ይመክረዋል፡፡ ጴጥሮስም ‹‹በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ…›› (1ጴጥ. 5፡10)፤ ጥሪው የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ መሆኑን ቃሉ በሚገባ ያሳየናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ መጥራት ብቻ ሳይሆን ያጥባል፣ ይቀድሳል ያጸድቃል (1ቆሮ. 6፡11)፤ መንፈስ ቅዱስ ከቃሉ ጋር የድነታችን ዋና ሥራ አስኪያጅ (Agent) ነው፡፡

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘነው ድነት ኃጢአት ብንሠራ ይጠፋል አይጠፋም የሚል ሰፊ ክርክር አለ፡፡  ዮሐንስ በወንጌሉ ምዕራፍ 3፡16 ላይ እንዲህ ይላል ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እሰኪሰጥ ድረስ ዓለሙን አንዲሁ ወዶአልና›› በ1ኛ. ዮሐንስ መልእክቱም ምዕራፍ 5፡13 ላይ ‹‹የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ›› በማለት በመጀመሪያ የተሰጠን ሕይወት ጊዜያዊ ሳይሆን የ‹‹ዘላለም ሕይወት›› እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ጌታም በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ስለ መልካም እረኝነቱ በተናገረበት ጊዜ ‹‹በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፣ እኔም አውቃቸዋለሁ፣ ይከተሉኝማል፣ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ፣ ለዘላለምም አይጠፉም ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም›› (ዮሐ. 10፡27) በማለት የሰጠን የድነቱ ዋስትና ምን ያህል እርግጠኛ እንደ ሆነ ተናግሮአል፡፡

በዚሁ ወንጌል ጌታ ስለ መለየቱ ለደቀ መዛሙርቱ ከተናገራቸው በኋላ አዝነው ስለነበር ‹‹እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል›› (ዮሐ. 14፡16) በማለት አጽናናቸው፡፡ ስለዚህ ስለ ተቀበልነው ድነት ኃጢአት ብንሠራ ይጠፋል ብለን መጨነቅ የለብንም፡፡ ኃጢአት ስንሠራ ኅብረታችን ይቋረጣል፣  ሰላማችን ይጠፋል፣ ሕሊናችን ይከሰሳል … ሌሎችም የተለያዩ ነገሮች በሕይወታችን ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ቶሎ ብለን በ1ኛ. ዮሐንስ ምዕራፍ 1፡9 ላይ የምናገኘው ቃል ‹‹በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው›› በሚለው መሠረት ሕይወታችንን ጌታ ባዘጋጀልን የኑዛዜ መንገድ ወደ ጌታ በመቅረብ ራሳችንን ማስተካከል ይኖርብናል፡፡ አለበለዚያ በኑዛዜ ራሳችንን የማናስተካክል ከሆነ እንደ ይሁዳ ከመጀመሪያውኑ የጥፋት ልጆች ነበርን፣ አሁንም ነን ማለት ነው፡፡ በመጠራት ሥር ያየነው ጥናት፣ በድነት የእግዚአብሔር ድርሻ በልጁና በመንፈስ ቅዱስ የፍቅር ጥሪውን ወደ እኛ መላክ ስሆን፣ እኛ ደግሞ ጥሪውን ስምተን ድነቱን የመቀበል ድርሻና ኃላፊነት አለብን፡፡ በድነት ስላለን ድርሻችን በሚቀጥለው ጥናታችን እንመለከታለን፡፡


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *