ተልዕኮው የት ደርሷል? (ተልዕኮአችንን እንፈትሽ) የሚለውን ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሱኝ የተለያዩ ምክንያቶች አሉኝ፡፡ የመጀመሪያው መጽሐፍ እንድጽፍ የሚፈልጉ የብዙ ሰዎች ጉትጎታ ሲሆን፣  ሁለተኛው ስለ ቤተ ክርስቲያን መነቃቃትና መንፈሳዊ ዕድገት በሳዳሞ ገነት (በምዕራብ ሸዋ ሆለታ ከተማ አካባቢ የሚገኝ) ቤተ ክርስቲያን እንዳስተምር በመጠየቄ የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ማጥናት መጀመሬና፣ ሦስተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ታላቅ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ታመጣለች ተብሎ እየተጠበቀች እርሷ ግን ያለ መዘጋጀቷ የልብ ሸክም ስለሆነብኝ ነው፡፡

ተልዕኮው የት ደርሷል? የሚለው ጽሑፍ በሦስት የተከፈሉ ምዕራፎች ይኖሩታል፡፡ እነርሱም ምዕራፍ አንድ ታላቁ ተልዕኮ በማንና፣ ለማን እንደ ተሰጠ፣ የተልዕኮው ስፋት ምን ያህል (ከየት እስከ የት) እንደሆነ ይዳስሳል፡፡ ምዕራፍ ሁለት ታላቁ ተልዕኮ በኢየሩሳሌም በሚለው ሥር ስለ ተሰጣቸው ተስፋ፣ በዓለ ኀምሳ፣ የሰበኩት ስብከት፣ በጌታ ስም ስላከናወኑት ፈውስ፣ ስለ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች፣ እንዲሁም ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ ብዙ ዓመት ስለ መቆየታቸው ያወሳል፡፡ ሦስተኛው ምዕራፍ ታላቁ ተልዕኮ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን የሚል ሲሆን ወንጌል እንዴት እንደ ደረሳቸው፣ የሳውል መለወጥና አገልግሎት መጀመሩ፣ የበርናባስ ጳውሎስን መከታተልና ለአገልግሎት አብረው መጠራታቸው፣ አንደኛውን፣ ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውንና አራተኛውን (እስረኛ ሆኖ) የወንጌል ጉዞ በመጓዝ ተልዕኮውን ማሳካታቸውን እንመለከታለን፡፡

ጠቅለል ባለ መልኩ የኢየሩሳሌምንና የአንጾኪያን አብያተ ክርስቲያናት ብርታትና ድካም የሚዳስስ ሲሆን፣ ከእነርሱ ተምረን በግል፣ በቡድንና በምናገለግልበት ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ተልዕኮው የት እንደ ደረሰ እንድንፈትሽ፣ እንድናስተካክልና እርምጃ መውሰድ እንድንችል ሀሳብ የሚሰጥና አቅጣጫ የሚያመላክት ይሆናል፡፡ ወ/ዊ ያሬድ ጥላሁን “እግዚአብሔርን መምሰል” በሚለው መጽሐፋቸው “ከመጻፍ መናገር ይቀላል” እንዳሉት ቢሆንብኝም ይህችን አነስተኛ ጽሑፍ በጌታ ዕርዳታ ከዳር አደርሳለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ እግዚአብሔር ሁላችንንም እንዲናገረን፣ እንዲያስተምረንና የተግባር ሰዎች እንዲያደርገን ጸሎቴና መሻቴ ነው፡፡            


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *