ይሞላል፡- ቀደም ባሉት ሁለት ጥናቶቻችን እንዳየነው፤ በነቢያቶችና በጌታ በራሱ ስለ መንፈስ ቅዱስ የተነገሩት ትንቢቶች በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 2፡4 ላይ መፈጸሙን ተመልክተናል፡፡ ትንቢቱ በመፈጸሙ ላይ ብዙ ችግር የለንም፤ ችግራችን ያለው 2፡4 ጥምቀት ነው ወይስ ሙላት ነው የሚለው ላይ ነበር፡፡ ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ ስንሰጥ ሁለቱንም ያመለክታል ብለን መልሰናል፤ በመቀጠል በጥምቀትና በሙላት መካከል ልዩነት የለም እንዴ ብለን ለጠየቅነው ጥያቄ መልስ ስንሰጥ ልዩነት እንዳለው አሳይተናል፡፡ ጥምቀት ዳግም ልደት ማግኘት፤ የክርስቶስ አካል መሆን፣ የእግዚአብሔር ልጅነትን ማግኘትና አዲስ ፍጥረት መሆን እንደሆነ  ተመልክተናል፡፡

በዛሬው ጥናታችን የምንመለከተው ሙላት የሚለውን ይሆናል፤ ከሠላሳ ዓመት በፊት በኢቲሲ ማስተማር ካቆምኩኝ በኋላ፤ አንድ አስተማሪ ችግር ስለ ገጠመው፤ ለሁለት ሳምንት አስተምርልኝ ብሎ ጋበዘኝና ሄጄ በማስተምርበት ጊዜ የገጠመኝ አንዱ ርዕስ ይህ ነበር፡፡ ያስተማርኩት ትምህርቶች ሁለት ሲሆኑ፣ አንዱ ርዕስ ከባድ አልነበረም፤ ሁለተኛው ግን ከባድ ነበር፡፡ ክብደቱ በሁለት ምክንያት ነበር፣ የመጀመሪያው ርዕሱ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት የሚል በመሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ተማሪዎቹ የመጡት ከተለያየ ቤተ እምነት በመሆኑና የተለያየ አመለካከት ያላቸው በመሆናቸው ሁኔታውን ለእኔ ከባድ አድርጎት ነበር፡፡

እነዚህ ተማሪዎች የድግሪ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ እኔ ገና የዲፕሎም ተመራቂ ነበርኩኝ፤ ቢሆንም ጌታ ይረዳኛል ብዬ ለማስተማር ወስኜ፣ በሁለተኛው ሳምንት ይህን ርዕስ ማስተማር ጀመርኩ፡፡ አሁን እናንተን በማስተምርበት መንገድ ጥያቄዎችን እየጠየቅሁና እየመለሱ ቆይተው፤ አንዱ ከመካከላቸው እጁን አውጥቶ ‹‹ወንድም አምበርብር የብዙ ዓመት ጥያቄዬ ዛሬ ተመለሰልኝ፤ ጌታ ይባርክህ›› አለኝ፡፡ ዛሬ ያ ወንድም ትልቅ አስተማሪ፣ መጋቢና በቲኦሎጂም ዶክትሬቱን ይዞአል፡፡ እርሱ ብቻ ሳይሆን ተማሪዎች ሁሉ ረክተውና ደስ ብሏቸው የወጡበትን ጊዜ አስታውሳለሁ፡፡

የሐዋርያት ከብሉይ ኪዳን ወደ አዲስ ኪዳን የሽግግር ወቅት ላይ ነበሩ፤ ስለዚህ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትና ሙላት በሕይወታቸው የተከናውነው በአንድ ጊዜ ነው፡፡ የጥምቀቱን ባለፈው ተመልክተናል፤ አሁን ደግሞ የሙላቱን በመቀጠል እንመልከት፡፡ በሉቃስ ወንጌል 24፡49 ላይ ክርስቶስ ለኤማሁስ መንገደኞች ተገለጦላቸው በነበረ ጊዜ፣ ‹‹አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ›› ማለቱ የሚታወቅ ነው፡፡ ዮሐንስ በወንጌሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በመካከላቸው በመገኘት ከዚህ በፊት ያላቸውን ነገር ሁሉ በማስታወስ ወደፊትም ሊያደርጉት የሚገባውን ሲያሳያቸው ‹‹መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ›› ብሎአቸው ነበር፡፡ ‹‹ተቀበሉ›› የሚለው ቃል ሲጠብቅና ሲላላ ሁለት ትርጉም ይሰጣል፤ ሲጠብቅ ኃላፊ ሲሆን፣ ሲላላ ደግሞ የወደፊት ይሆናል፡፡

ሉቃስ ይህንኑ ሐሳብ በሐዋርያት ሥራ ደግሞት እናገኛለን፤ ከትንሣኤ በኋላ ደቀ መዛሙርት ስለ እስራኤል መንግሥት በጠየቁት ጊዜ የተሰጣቸው መልስ ቀጥተኛ ሳይሆን እንዲህ የሚል ነበር፤ ‹‹…መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ›› በማለት የተጠሩበትን ዋና ዓላማ የሚጠቁም መልስ ነበር፡፡ በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተጠቀሰውን ይህን ‹‹ኃይል›› በበዓለ ኀምሳ ቀን አግኝተዋል ወይስ አላገኙም? ትንቢቱ ተፈጽሞአል ወይስ አልተፈጸመም? በግላችሁ ምን ትላላችሁ? ባለፈው እንዳየነው ትንቢቱ ተፈጽሞአል፤ ኃይሉን አግኝተዋል፣ እነርሱም ለምስክርነት ተዘጋጅተዋል፡፡ ስለዚህ የሐዋርያት ሥራ 2፡4 ጥምቀትም ሙላትም ነው ያልነው ለዚህ ነው፡፡

በሉቃስ 24፡49 እና በሐዋርያት ሥራ 1፡8 በተጠቀሰው መሠረት፤ መንፈስ ቅዱስ ለምን አስፈለጋቸው? ብለን ብንጠይቅ ለ ‹‹ኃይል›› የሚል መልስ እናገኛለን፤ ኃይል ለምን አስፈለጋቸው? ብለን ብንጠይቅ ‹‹ምስክር›› ለመሆን የሚል መልስ እናገኛለን፡፡ ሐዋርያት የመጀመሪያዎቹ አማኞች በመሆናቸው ምክንያት፤ በበዓለ ኀምሳ ቀን በመንፈስ ቅዱስ ተጠመቁ፣ ተሞሉ፤ ሉቃስ ግን ሲጽፍ የመረጠው ‹‹ሙላት›› የሚለውን ቃል ነው፡፡ በጥምቀትና በሙላት መካከል ያለው ልዩነት እንደ አንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ጥምቀት የአንድ ጊዜ ድርጊት ሲሆን፣ ሙላት ግን እንደ አስፈላጊነቱ የሚደጋገም ድርጊት ሆኖ እናገኘዋለን (የሐዋ. 4፡8፣31)፡፡ በጥምቀት ከክርስቶስ አካል ጋር አንድ ሲሆኑ፣ በሙላቱ ደግሞ ኃይል ተቀብለውበታል፡፡ የመንፈስ ቅዱስን ሙላት ሲቀበሉ ድፍረት አግኝተዋል፣ ፍርሃት ከእነርሱ ተወግዶአል፣ የሚናገሩትን ቃል አግኝተዋል፣ የነፍሳት ፍቅር አድሮባቸዋል፤ ኃይሉን ሲቀበሉ ለአገልግሎት የሚረዳቸውን የጸጋ ስጦታዎቹንም ተቀብለዋል፡፡

ያትማል፡- መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ኀምሳ ቀን ከሠራው ሥራ አንዱ ማተም ነው፤ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ተዋጅተው የዳኑ ለመሆናቸው፣ የመዳን ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ ታትሞባቸዋል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን አማኞች ስለ መዳናቸው ተስፋ ሲጽፍላቸው ‹‹እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፣ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው›› (ኤፌ.1፡13-14) በማለት የድነታቸውን እውነተኛነት እንዳረጋገጠላቸው ሁሉ፤ ሐዋርያትም በድነታቸው ቀን በመንፈስ ቅዱስ ታትመዋል፡፡ ስለዚህ ዳግም ልደት፣ ልጅነት፣ መጠመቅ፣ መሞላትና መታተም በአንድ ጊዜ በሕይወታቸው እንደተፈጸመ መረዳት እንችላለን፡፡ እነዚህ ተስፋዎችና እውነቶች፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሕይወታችን እንዲገባ ንስሐ በመግባት ስንፈቅድለት፣ መንፈስ ቅዱስ ዳግም ልደትን፣ ልጅነት እና መጠመቅን ያከናውናል፡፡ ምናልባት ሙላቱ በአንድ ጊዜ ላይከናወን ይችላል፤ ምክንያቱም ኃይል የሚሰጠው ለአገልግሎት ስለሆነ የእኛን ዝግጅት ይጠይቃል፡፡ ሐዋርያት ለሦስት ዓመት ተኩል ሠልጥነው፤ በጸሎት ተዘጋጅተው እየጠበቁ ነበር፡፡ ስለዚህ እኛም በድነታችን ጊዜ፣ ወይም ቆይተን ልንሞላ እንችላለን፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሥጋውያን ለሆኑት አማኞች ሳይቀር በመንፈስ ቅዱስ ዳግም ስለ ተወለዱበት ጊዜ ስለ ነበረው ሁኔታ ሲናገር፣ ‹‹በክርስቶስም ከእናንተ ጋር… ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው›› (2ቆሮ. 1፡21-22) በማለት መዳናቸው በመታተም የተረጋገጠ እንደሆነ ያረጋግጥላቸዋል፡፡ ማተም የሚለው ሐሳብ ባለቤትነትን፣ ሥልጣንና ጥበቃን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በአብ ፍቅርና በወልድ መስዋዕትነት የተገኘውን ድነት በማረጋገጥ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን በማተም ያረጋግጥልናል፡፡

            ይቀድሳል፡- መንፈስ ቅዱስ ማተም ብቻ ሳይሆን የመቀደስም ተግባር እንደሚያከናውን ቃሉ ይናገራል፤ በአንደኛ ቆሮንቶስ 6፡11 ላይ ‹‹በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል›› በማለት ቅድስናቸውም በመዳናቸው ቀን እንደ ተከናወነ ይናገራል፡፡ ጌታም ራሱ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ሲናገር ‹‹እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ›› (ዮሐ. 17፡19) ብሎ በተናገረው መሠረት ጳውሎስም ‹‹የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ›› (1ተሰ. 5፡23) በማለት ለተሰሎንቄ አማኞች በጻፈው መሠረት  ሐዋርያት በበዓለ ኀምሳ ቀን ቅድስናን እንዳገኙ መረዳት እንችላለን፡፡ ሥላሴ በዕቅዳቸው መሠረት የተከፋፈሉ የሥራ ድርሻ እንዳላቸው የታወቀ ቢሆንም፤ ሁሉም ደግሞ አንዱን ሥራ በአንድነት ሲሠሩ እናያለን፡፡  በብሉይ ኪዳንም በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19፡2 ላይ ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› በማለት እርሱ የቅድስና ምንጭ እንደሆነ ሲናገር፤ በአዲስ ኪዳንም ጴጥሮስ ‹‹እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ›› (1ጴጥ. 1፡15-16) በማለት የቅድስናችን መሠረት የክርስቶስ ቅድስና መሆኑን ይናገራል፡፡ በዚህ መሠረት በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ የሐዋርያት ቅድስና ሲከናወን፤ የእኛም ቅድስና በዚሁ መንገድና መልክ ተከናውኖአል፤ ማለት ነው፡፡

ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን የመቀደስ ድርሻ እንዳለው ማየታችን ሥላሴ በድነት ሥራ እያንዳንዳቸው ድርሻ እንዳላቸው ማየትና መረዳት አያስቸግረንም፡፡ ለክርስቶስ ምስክር ለመሆን የምንፈልግ ሁሉ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክት ላይ ‹‹ መንፈስ ይሙላባችሁ… ›› (ኤፌ. 5፡18) ብሎ በሚያዘው መሠረት ዕለት በዕለት በመንፈስ ቅዱስ ልንሞላ ይገባናል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላት እርስ በእርሳችን በፍቅር እየተነጋገርን፣ ለጌታ መንፈሳዊ ቅኔ እየተቀኘንና እግዚአብሔርን በሁሉ ነገር እያመስገንን የምንፈጽመው መሆን እንዳለበት ቃሉ ያሳየናል፡፡

ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደባቸው/ ከተሰጣቸው/ ከተሞሉ በኋላ ምስክሮች እንዲሆኑ፣ ከፍርሃት እንዲወጡ፣ ደፋሮች እንዲሆኑ፣ ያላቸውን ለጌታ ሥራ እንዲሰጡ፣ ከአሮጌው ሕይወት ተላቀው በአዲስ ሕይወት እንዲመላለሱ አድርጓቸዋል፡፡ ጌታንም እያገለገሉ ሲሄዱ በሕይወታቸው መንፈሳዊ ፍሬ እንዲያፈሩ ረድቷቸዋል፡፡

በዘመናችን አንዳንዶች መንፈስ ቅዱስ እንደ ድሮ አይሠራም ብለው ቢያስተምሩም፤ ለቤተ ክርስቲያን የመንፈስ ቅዱስ ሙላትና ኃይል ያስፈልጋታል፡፡ እያንዳንዱ አማኝ በመንፈስ ቅዱስ ከተጠመቀ በኋላ ዕለት በዕለት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየተሞላ መኖርና ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡ ቀደም ብለን እንዳየነው ጥምቀት በእግዚአብሔር በተገባው ተስፋ መሠረት፣(የሐዋ. 1፡5) አማኞችን ማጥመቅ የእርሱ ድርሻና ኃላፊነት ሲሆን፤ ሐዋርያት ጠብቁ፤ በተባሉት መሠረት በጉጉት በመጠበቃቸው የተባለውን ተስፋ ሙላቱን እንደ ተቀበሉ፤ እኛም የተሰጠውን ተስፋ መቀበል እንችላለን፡፡

ዛሬም የመንፈስ ቅዱስ ሙላት የእኛን ጥማት፣ መሻትና መሰጠት ይጠይቃል (ኤፌ. 5፡18)፤ በመንፈስ ቅዱስ ለመሞላታችን ማረጋገጫው በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር ሆነን፤ ኃጢአትን ማሸነፋችን፣ የእግዚአብሔርን ቃል መታዘዝ መቻላችን፣ የክርስትና ሕይወትን መኖር መቻላችንና የሕይወት ለውጥ ማሳየታችን ናቸው፡፡ በገላትያ ምዕራፍ 5፡22 ላይ ‹‹የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት ነው›› ተብለው ተጠቅሰው የምናገኛቸው ፍሬዎች በሕይወታችን መታየት መጀመራቸው፤ የመለኮታዊ ባሕርይ በሕይወታችን መታየቱ፣ ሌላው ማረጋገጫ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ጴጥሮስ ምዕራፍ 1፡2-7 ላይ የመለኮቱ ተካፋዮች በመሆናችን የሚኖሩንን ባሕርይ በዝርዝር ያሳየናል፡፡

መንፈስ ቅዱስ መሞላት ለአንድ አማኝ በኃይል ተሞልቶ ለማገልገል መሠረታዊ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ አንድ አማኝ ጌታን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ ከተቀበለ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እንዲሞላ በግሉ ሊጸልይና እጅ ተጭኖ እንዲጸለይለት ቢያደርግ ምንም ችግር የለበትም፡፡ ሰጭው ተስፋ የሰጠው እግዚአብሔር ስለሆነ ያደርገዋል፤ አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ሲሞላ በልሳን ሊጸልይ ይችላል፤ ላይጸልይም ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ችግር እንዳለባችሁ እናውቃለን፤ በሚቀጥለው ጥናታችን የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ይህን በተመለከተ ዳሰሳ በምናደርግበት ጊዜ ለችግራችሁ መልስ ታገኛላችሁ ብለን እናምናለን፡፡

የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት በተስፋው መሠረት የሚፈጸም ሲሆን፤ ሙላት ግን እንደ ጥማታችንና እንደ መሰጠታችን ለአገልግሎት የምንቀበለው የኃይል ልምምድ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ለጌታና ለደቀ መዛሙርት ካስፈለጋቸው፣ ለእኛ የማያስፈልግበት ምንም ምክንያት አይኖርም፡፡ ስለዚህ ዕለት በዕለት ምዕመናን በመንፈስ ቅዱስ እንድንሞላ፣ እንዲያስተምረን፣ እንዲመራን፣ እንዲገስጸን፣ እንዲመክረንና ልምምዱን በሕይወታችን ለመተግበርና እንዲሁም በተሰጠን የጸጋ ስጦታዎቻችን መጠቀም እንድንችል፤ ቃሉን የመማር፣ ወደ መስቀሉ ሥር የመቅረብና የመጸለይ ኃላፊነት እንዳለብን ማወቅ አለብን፡፡ በየጓዳው መንፈስ ቅዱስን ተሞልቻለሁ ለማለት ብቻ ሳይሆን፤ ሁላችንም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ለጌታ ምስክሮቹ ልንሆንለት ተጠርተናል፡፡  


0 Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *