የክርስቶስ መከራውና ክብሩ
‹‹ጌታችን ኢየሱስ የደረሰበት መከራ እጅግ ከፍተኛ ሲሆን፣ ይህም መሞቱ፣ መቀበሩና ወደ ሲዖልም መውረዱ ነበረ፤ እነዚህን ሁናቴዎች የታገሠውም ሰዎችን ከኀጢአታቸው ለማዳን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ እየተከበረ ሲሄድ ግን በትንሣኤና በዕርገት ሁኔታዎች ዐልፎ በአብ ቀኝ ተቀመጠ፤ እዚያም የዳግም ምጽአቱን ጊዜ ይጠብቃል›› (ትምህርተ ክርስቶስ በቄስ ማንሰል ገጽ 198) ሲሉ መከራውና ክብሩን ገልጸውታል፡፡
ሞቱ፡- ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደዚህ ምድር ከመጣበት ከውልደቱ ጊዜ ጀምሮ መከራ ተለይቶት አያውቅም፡፡ ኢየሱስ 30 ዓመት ሞልቶት አገልግሎት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ መነጋገሪያ መሆን፣ የክትትል ትኩረት መሆን፣ ስድብና ጥላቻ… የመሳሰሉት ሁሉ አልተለዩትም ነበር፡፡ ሄሮድስ በሕጻንነቱ ሊገድለው አስቦ አልተሳካለትም፤ ፈሪሳውያንም ብዙ ጊዜ ሊገድሉት ሞክረው አልተሳካላቸውም፡፡ በመጨረሻም ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ለሦስት ዓመት አብሮት የነበረው፣ ይሁዳ አስቆርቱ የተባለው በነቢያት ቃል እንደ ተጻፈው፣ የበላበትን ወጭት ሰባሪ ሆኖ፣ በ30 ብር ሸጦት ለመከራ አሳልፎ ሰጠው፡፡ ፈሪሳውያንና ካህናት ኢየሱስን ይዘው በተለያዩ ባለ ሥልጣናት ዘንድ እያቀረቡ፣ የተለያየ ጥያቄዎች በመጠየቅ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ አድርጎአል በማለትና ወንጀለኛ ነው በማለት ግርፋትና ሞት ፈረዱበት፡፡ ሰዎች የራሳቸውን ፈቃድ ሊፈጽሙበት ቢነሱም፤ በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት ግርፋቱንና መስቀል ሸክሙን አልፎ፣ በመስቀል ላይ ተንጠልጥሎ፣ ተጠማሁ እያለና ‹‹አባት ሆይ፡- ነፍሴን በእጅህ ዐደራ እሰጣለሁ›› ብሎ ነፍሱን ሰጠ (ሉቃ. 23፡46)፡፡
ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን በተነገረለት ትንቢት መሠረትና (መዝ. 22፣ ኢሳ. 53) ጌታም ራሱ ቀደም ብሎ ‹‹የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል ከሽማግሌዎችም፣ ከካህናት አለቆችም፣ ከጻፎችም ሊጣል፣ ሊገደልም፣ ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሳ እንዲገባው… ›› ብሎ ለደቀ መዛሙርት ባስተማራቸውና በተናገረው ትንቢት መሠረት መከራውን ተቀብሏል፡፡ ኢየሱስ በራሱ ላይ ሊሆን ያለውን የብሉይ ኪዳን ትንቢት በማረጋገጥ የሩቁን ትንቢት እንደገና የቅርብ አድርጎ እንደሚፈጸምበት ማስተማሩን ወንጌላት ዘግበዋል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፣ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፣ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር›› (ማር. 8፡31፣ ሉቃ. 9፡21-22)፡፡ ክርስቶስ ባስተማራቸው መሠረት፣ በራሱ ኃጢአት ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ፣ በሰዎች ተከሶና ሕማማትን ተቀብሎ ለሰው ልጆች ቤዛ ለመሆን በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞቷል፡፡ ጴጥሮስም በመልእክቱ ‹‹እርሱም ኃጢአት አላደረገም ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ›› (1ጴጥ. 2፡22-24፣ የሐዋ. 2፡23) በማለት ጠላቶቹን ማጥፋት ሲችል፣ እኛን የሰው ልጆችን ለማዳን፣ በብዙ ግርፋት፣ ሥቃይ፣ የሾህ አክሊል በመድፋት፣ በመስቀል ላይ በምስማር ተቸንክሮ፣ ጎኑን በጦር በመወጋት፣ ነፍሱን ለአባቱ ተፈጸመ ብሎ ከሰጠ በኋላ ወስደው ቀበሩት፡፡ በዚህ ሁሉ መከራ ማለፉ፣ የክርስቶስ ሞት ለእኔና ለእናንተ ስለሆነ ነው፡፡
ትንሣኤው፡- የክርስቶስ ትንሣኤ የክርስትና እምነታችን ዋና መሠረት ነው፤ መከራውንና መስቀሉን ከትንሣኤው መለያየት በፍጹም አንችልም፡፡ በትንሣኤ ድል ማድረጉ ከመከራውና ከመስቀሉ ተለይቶም ምንም ትርጉም የለውም፡፡ መከራውም፣ መስቀሉም ትንሣኤውም በየተራ በሕይወቱ የተከናወኑ የማዳን ሥራዎቹ ናቸው፡፡ ክርስቶስ ተሰቅሎ፣ ሞቶ፣ በመቃብር ሦስት ቀንና ሌሊት አድሮ መበስበስን ሳያይ፣ ሞትን ድል አድርጎና ከሙታን ተለይቶ በክብር በሕያው አካል ተነስቷል፡፡ ማቴዎስ በወንጌሉ መልአኩ ለሴቶቹ ‹‹እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና›› በማለት ትንሣኤውን እንዳበሰራቸው ይናገራል (ማቴ. 28፡5፣ 1ቆሮ. 15፡3-4)፡፡
ለክርስቶስ ክብር መሠረቱ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና በአብ ቀኝ መቀመጡ ናቸው፤ የክርስቶስን ትንሣኤ ለማስተባበል፣ የካህናት አለቆች ‹‹ከሽማግሌዎች ጋርም ተሰብስበው ተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው፡- እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ›› (ማቴ. 28፡11-15) ብለው እንዲዋሹና በኃላፊነት የሚያስጠይቅ ውሸት እንዲዋሹ አደረጓቸው፡፡ ትንሣኤውን ሰዎች እንዳይቀበሉት ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም፣ አልተሳካላቸውም፡፡ ያላመኑ ሰዎች የሃይማኖት መሪዎቻቸው ስለሆኑ ያደረጉት ድራማ እውነት መስሏችው ሊቀበሏቸው ይችላሉ፡፡ ያመኑት ግን ሊቀበሏቸው አይችሉም፤ ምክንያቱም ‹‹ክርስቶስ በጧት ከመቃብሩ ውጭ፣ በመንገድ፣ በቤት ውስጥ፣ በባሕር ዳርና በተራራ ላይ ለሴቶችም ለወንዶችም፣ ለሰዎች አንድ በአንድ፣ ለሐዋርያትና በአንድነትና ከአምስት መቶ በላይ ለሚሆኑ ወንድሞች በአንድ ጊዜ በጧት፣ እኩለ ቀን ገደማ ላይና በእራት ሰዓት ታየ›› ሲሉ ገልጸውታል (ቄስ ማንሰል ገጽ 203)፡፡ ጌታ ራሱ ከትንሣኤ በኋላ ወደ 11 ጊዜ መታየቱ የትንሣኤውን እውነትነት ያረጋግጣል፡፡ በመቀጠልም በበዓለ ኀምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስ ነብያትና ጌታ ራሱ እንደ ተናገሩት መውረዱ፣ በደቀ መዛሙርት ሕይወት የታየው ለውጥ፣ የመቃብሩ ሥፍራ ባዶ መሆን፣ በተጨማሪ የትንሣኤውን እውነተኛነት ያመለክታሉ፡፡
የክርስቶስ የትንሣኤው አካል በመጀመሪያ ወደ ምድር ሲመጣ፤ ከነበረው አካል ተመሳሳይ ሆኖ አንዳንድ የተለዩ ባህርያት የሚታዩበት የከበረ ሕያው አካል ነበረ፡፡ በተዘጋ ቤት ውስጥ በር ሳይከፈት መግባት የሚችልና ሰላም ለእናንተ ይሁን በማለት፣ መልእክተኛ እንዲሆኑ ትእዛዝ የሚሰጥ ነበረ፤ (ዮሐ. 20፡19) በእጆቹና በእግሮቹ ላይ የነበሩትን የተወጋውን ችንካሩን ለደቀ መዛሙርቱ በማሳየት፣ ‹‹በእኔ እንደምታዩት፣ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም እኔን ዳስሳችሁ እዩ›› ብሎ ያው አካሉ እንደሆነ አረጋገጠላቸው (ሉቃ. 24፡39-40)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ 11 ጊዜ የታየው ለአማኞች ብቻ ቢሆንም፤ መነሣቱ በሰዎች ሁሉ ዘንድ መወራት ተጀመረ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ትንሣኤው ያረጋገጠው፤ ሁለተኛ ሞት እንደማይገዛውና እንደማይሰለጥንበት ነበር (ሮሜ 6፡9)፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ የትንቢቱን መፈጸም፣ የትምህርቱን እውነተኛነት፣ የዘላለማዊ ዋስትናን፣ የአማኞች ከሞት መነሳትን (ትንሣኤ ማግኘት) ማረጋገጫ/ዋስትና ያስገኘ ድርጊት ነው፡፡
ሐዋርያት በትንሣኤው እርግጠኞች በመሆናቸውና ጠብቁ በተባሉት መሠረት የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ሲጠብቁ ከቆዩና ኃይሉን ከተቀበሉ በኋላ፤ ‹‹ከሰባት ሳምንት በኋላ ግን ክርስቶስ እንደተነሣ በአደባባይ መሰከሩ፤ የኢየሩሳሌም ባለ ሥልጣናት ስለ ክርስቶስ እንዳያስተምሩ ሲከለክሏቸውና ሲገርፏቸው ሥቃዩን በደስታ እየተቀበሉ አገልግሎታቸውን ቀጠሉ›› በማለት በመጽሐፋቸው ገልጸውታል (ቄስ ማንሰል ገጽ 203)፡፡ ትንሣኤው መከራ የሚያስከትል ቢሆንም፣ በመነሣቱ እርግጠኞች ስለ ነበሩ ዋጋ እየከፈሉ አወጁት፡፡ በክርስቶስ ስም በሽተኞች ሲፈውሱ፣ አጋንንት ሲያወጡ፣ ተአምራት ሲያደርጉ ሁሉ፣ ይበልጥ ለትንሣኤው ማረጋገጫ ሆነላቸው፡፡ ዛሬም በእኛ ዘመን ክርስቶስ የሚሠራበት አንዱ ምክንያት፣ በትሣኤው ሕያው ሆኖ በመኖሩ ነው፡፡
ዕርገቱ፡- ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ሲያስተምራቸው፣ ‹‹እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፡፡ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ ደግሞም ላነሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህችን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ›› (ዮሐ. 10፡18) ብሎ በሞቱና በትንሣኤው ሁሉ ሥልጣን እንደነበረው በተናገራቸው መሠረት ሁሉም ነገር አንድ በአንድ ተፈጸመበት፤ ተጠላ፣ ተገደለ፣ ተቀበረ፣ ተነሳ፣ ተነስቶም እንደተናገረው ወደ አባቱ ዕቅፍ ከፍ ከፍ በማለት ተወሰደ፡፡ ዕርገቱም የተከናወነው ደቀ መዛሙርት እያዩት ቀስ በቀስ በግዙፍ አካል፣ በደመና በመታጀብ እንደሆነ ከቃሉ መረዳት እንችላለን (ማር. 16፡19፣ ሉቃ. 24፡50-51፣ የሐዋ. 1፡9-10)፡፡ ክርስቶስ በዕርገቱ መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር አቀረበ፡፡ ደግሞም በሥጋ ሲመላለስ የነበረበትን ውስንነት አስወግዶ ወደ ቀድሞ ክብሩ መመለሱን፣ (ዮሐ. 17፡5) የአማኝ ሥጋ አስቀድሞ ወዳልነበረው ክብር መግባቱን፣ (1ቆሮ. 15፡45-49) እና ክርስቶስ በአዲስ መንገድ መንገሥ መጀመሩን፣ በዳዊት አስቀድሞ ‹‹ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ›› (መዝ. 110፡1) ብሎ በተናገረለት መሠረት በአብ ቀኝ በመቀመጡ ዕርገቱ የተረጋገጠና እውነተኛ መሆኑን ያመለክታል፡፡
አሁን በአብ ቀኝ ተቀምጦ ምን እያደረገ ነው? ወይም ምን አገልግሎት እየሰጠ ነው? የሚል ጥያቄ ቢከተል መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን መልስ ይሰጠናል፡፡ ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጦ ለቅዱሳን የመማለድ አገልግሎት እየሰጠ የሊቀ ካህንነቱን ተግባር እያከናወነ ይገኛል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ማጽደቅና መኰነን ሲናገር፣ ‹‹… የሞተው ይልቁንም ከሙታን የተነሳው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው›› (ሮሜ 8፡24) ይላል፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊም ‹‹እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሊያድናቸው ይችላል›› (ዕብ. 7፡24-25) በማለት ክርስቶስ በአብ ቀኝ ተቀምጦ እየሠራ ያለውን በግልጽ ያስቀምጣል፡፡
በአብ ቀኝ ተቀምጦ ማማለድ ብቻ ሳይሆን ለጸሎት መልስም ይሰጣል፤ የልጆቹንም መከራና ችግርም ይመለከታል፡፡ እስጢፋኖስ ሊወገር በሰዎች ተከቦ፣ ጥርሳቸውን እያፋጩበት ባሉበት ጊዜ፤ የሰው ልጅ (ክርስቶስ) በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ እንዳየው ይናገራል (የሐዋ. 7፡56)፡፡ አማኞች እንደ ቃሉና ፈቃዱ ለሚለምኑት የጸሎት ጥያቄዎች ሁሉ መልስ ይሰጣል (ዮሐ. 14፡13-14)፡፡ ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ በእርሱ የሚያምኑትን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃል (የሐዋ. 2፡33፣ 11፡15-18)፣ ከማጥመቅ ቀጥሎ እያንዳንዱ አማኝ አገልግሎቱን እንዲወጣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ይሞላል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም አገልግሎቷን እንድትወጣ ወደ ሙላት እንድትደርስና ለበጉ ሠርግ ዝግጅት እንድታደርግ ሁልጊዜ በቃሉ ያነፃታል (ኤፌ. 5፡25-27)፡፡
በመጨረሻም፣ መላእክቶች ‹‹ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፣ እንዲሁ ይመጣል›› ብለው በዕርገቱ ጊዜ ተሰብስበው ለነበሩ ሰዎች እንደ ተናገሩት፤ አንድ ቀን ተመልሶ ይመጣል (የሐዋ. 1፡11)፡፡ ለቤተ ክርስቲያን የሚገለጽበት ቀን በመድረሱ፣ ከመምጣቱ በፊት ቤተ ክርስቲያን ራስዋን እንድታዘጋጅ እያደረጋት፤ እርሱም ለቅዱሳን መኖሪያ በማዘጋጀት ላይ እንዳለ ቃሉ ይናገራል (ዮሐ. 14፤1-3)፡፡ የትንሣኤው ኃይል ከመሸነፍ በኋላ ድልን ማስገኘቱን፣ በአብ ቀኝ መቀመጡን ደግሞ ኃይሉ በውርደት ፋንታ ክብር ማምጣቱን ያረጋግጣል፡፡ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በሥጋ ሲመጣ በትሕትና ነበረ፤ ከጥቂት እረኞች በስተቀር ስለ መወለዱ ማንም ያወቀ አልነበረም፤ እናቱም ያስተኛችው በግርግም ነበር፡፡ ካህናትና ሄሮድስም ያወቁት፣ አንድ ዓመት ያህል ቆይተው በሰብዓ ሰገል አማካኝነት ነበር፡፡ አሁን ክርስቶስ ተመልሶ ሲመጣ ግን ሰዎች ሁሉ ያውቃሉ፤ በመለከት ድምጽ ታጅቦ ሲመጣ፤ የምድር ወገኖች ሁሉ ያዝናሉ፤ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክራል (ፊል. 2፡11)፡፡ በዚህ ጊዜ ክርስቶስ በዓለም ሁሉ ላይ በጽድቅ ለመፍረድ በሚዘጋጅበት ጊዜ ሰዎች ሁሉ ለፍርድ በፊቱ ይሰበሰባሉ፡፡ ከዚህ ፍርድ መዳኛው ሰዓት አሁን ነው፤ ክርስቶስን በማመንና ጽድቁን በመቀበል መዳን ይቻላል፡፡ ድነት ያገኛችሁም፣ ስለ መዳናችሁ ጌታን አመስግኑት፡፡
0 Comments