- አስተምህሮተ መለኮት (ክርስቶስ)
ቀደም ብለን በአስተምህሮተ ሥጋዌ ባጠናነው ጥናት፣ ኢየሱስ በቅድመ-ህልውናው (Preexistence) በብሉይ ኪዳን ጊዜ በመላእክትና በሰዎች መልክ መገለጡ የመለኮታዊነቱን እርግጠኛነት ማየት ያስችለናል፡፡ በየዘመናቱ ሰዎች የክርስቶስን መለኮታዊነት ቢክዱም መጽሐፍ ቅዱስ ግን አምላክነቱን በግልጽ ያመለክተናል፡፡ ከዚህ በፊት ባጠናናቸው ትምህርቶች ስሞቹ ሰብዓዊነቱንና መለኮታዊነቱን የሚያመለክቱ እንደሆኑ ተመልክተናል፤ ከፍጥረት በፊት አስቀድሞ መኖሩ፣ ከእግዚአብሔር መምጣቱ፣ የክርስቶስ ተከታዮች የሰጡት ምስክርነት፣ ለራሱ የሰጠው ምስክርነት ሁሉ መለኮታዊነቱን ያሳዩናል፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር በነበረ ጊዜ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው ነበር፤ ባለፈው ጥናታችን ፍጹም ሰብዓዊነቱን እንዳየን፣ ፍጹም አምላክነቱን ደግሞ አሁን በመቀጠል እናጠናለን፡፡
3.1 የአምላክነቱ አስፈላጊነት
ስለ ክርስቶስ ከመጽሐፍ ቅዱስ በምናጠናበት ጊዜ ሁለት ተፈጥሮ እንደ ነበረው ያመለክተናል፡፡ ባለፈው ስለ ሰብዓዊነቱ ስናጠና እንዳየነው ኢየሱስ በመልአኩ አማካኝነት የወጣለት የሰብዓዊ፣ የቤተ ሰብ ስሙ ሲሆን፣ መለኮታዊነቱን የሚያሳየው ስም ክርስቶስ የሚለው በግሪክኛ ‹‹ክሪስቶ›› ሲሆን በዕብራይስጥ ‹‹መሲህ›› የተቀባ የሚለው ሲሆኑ፤ እነዚህ ሁለት ስሞች ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ይህ ትምህርት በትምህርተ መለኮት ትምህርት ቤት ‹‹ሃይፖስታቲክ ዩኒየን›› (Hypostatic Union) ተብሎ ይጠራል፡፡ ስለዚህ በፍጹም አምላክነቱም ቅድመ ህልውና እንደ ነበረው እንረዳለን፡፡ የክርስቶስ ሕይወት የጀመረው ከማርያም ማህፀን፣ እንዲሁም በብሉይ ኪዳን ሳይሆን፤ ከዘላለም በፊት የነበረ እንደ ሆነ ቃሉ ያመለክተናል፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ በምዕራፍ 1፡1 ላይ ‹‹…ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ…›› ብሎ ስለ እግዚአብሔር አብ ፈጣሪነት የሚናገረው ቃል ስለ እግዚአብሔር ወልድም ከዘላለም በፊት በመኖሩ የፍጥረት ሥራ ተካፋይ መሆኑን ያመለክተናል፡፡
ጌታም ይህንን እውነት በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 8፡58-59 ላይ ‹‹እውነት እውነት እላችኋለሁ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ›› አላቸው፡፡ በዚህም ከአብርሃም በፊት እኔ ነኝ በማለቱ ዘላለማዊነቱን አረጋግጧል፡፡ ‹‹እኔ ነኝ›› የሚለው ቃል ከዕብራይስጡ ‹‹ያህዌ›› ከሚለው ቃል ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ነው፤ አይሁዶች ሊወግሩት ድንጋይ ባነሱ ጊዜ፣ ‹‹ኢየሱስ ግን ተሰወራቸው ከመቅደስም ወጥቶ በመካከላቸው አልፎ ሄደ›› የሚለው ቃል እጅግ በሚገርም ሁኔታ መለኮታዊነቱን አጉልቶ ያሳያል፡፡ ስለዚህ ፈጣሪነቱና አምላክነቱ የሚለያዩ አይደሉም፤ ስለ አንዱ ስናነሳ ስለ ሁለቱም ማንሳታችን ነው፡፡ በተጨማሪ ስለ አምላክነቱ ከሌሎች ማስረጃዎች እንመልከት፡፡
1) ጌታ ስለ ራሱ የሰጠው ማረጋገጫ፡- ከኢየሱስ ሌላ ብዙ ማስረጃዎች ቢኖሩንም፣ ራሱ ለራሱ ከሰጠው ምስክርነት አይበልጡም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ጋር እኩልነቱንና መለኮታዊነቱን ለማሳየት ‹‹እኔና አብ አንድ ነን›› (ዮሐ. 10፡30)፣ አብን አሳየን ብለው በጠየቁትም ጊዜ ‹‹እኔን ያየ አብን አይቶአል›› መልስ በመስጠት አረጋግጦአል (ዮሐ. 14፡6)፡፡ አይሁድ ባሳደዱት ጊዜ ‹‹እግዚአብሔር አባቴ ነው›› አላቸው፤ ይህ አባቴ ነው የሚለው አባባሉ ይበልጥ ስለ አበሳጫቸው ሊገድሉት አሰቡ (ዮሐ. 5፡18)፡፡ ‹‹ሊቀ ካህናቱም ፡- አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው›› (ማቴ. 26፡63-64)፡፡ ኢየሱስም ‹‹አንተ አልህ›› በማለት የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በምጸት በመናገር አረጋገጠለት፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ደግሞ እርሱ ራሱ አምላክ እንደሆነ ያመለክታል፡፡
2) ሥራዎቹ፡- እግዚአብሔር አብ ብቻ ሊያደርግ የሚችለውን ኢየሱስም እንደ አባቱ ማድረግ እንደሚችል ቃሉ ያረጋግጥልናል፡፡ ክርስቶስም እንደ እግዚአብሔር የሰዎችን ኃጢአት ማስተሰርይ (ማር. 2፡1-12)፣ በሰዎች ላይ መፍረድ (ዮሐ. 5፡27)፣ መንፈስ ቅዱስን መላክ (ዮሐ. 15፡26)፣ ሙታንን ማስነሳት (ዮሐ. 5፡25)፣ ለጸሎት መልስ መስጠት (ዮሐ. 16፡24)፣ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል መፍጠርና መደገፍና ኃጢአትን ማንጻት (ቆላ. 1፡16፣ ዕብ. 1፡3)፤ ከብዙዎቹ ሥራዎች ጥቂቶቹ ቢሆኑም፣ ኢየሱስ ሥጋ ለብሶ በመጣበት ጊዜ እንኳን፣ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ማከናወን መቻሉ አምላክነቱን ያመለክቱናል፡፡
3) ባሕርያቱ፡- ክርስቶስ ማንም ሰው ሊኖረው የማይችለው ባሕርይ፣ አምላክ ብቻ ሊኖረው የሚገባ ባሕርይ አለው፡፡ ባሕርያቱ ከመለኮታዊነቱ ጋር የተያያዙ ናቸው፤ እግዚአብሔር አብ ሁሉን እንደሚያደርግ ክርስቶስም ያደርጋል፤ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ፣ በሰማይና በምድር ሥልጣን እንደ ተሰጠው ይናገራል (ማቴ. 28፡18) በዮሐንስ ራዕይ 1፡8 ላይ ‹‹ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ፡- አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ›› በማለት ሁሉን ማድረግ የሚችል ሥልጣንና ኃይል እንዳለው ቃሉ ያመለክተናል፡፡ ሁሉን የማወቅ ችሎታ እንዳለው፣ ከምናውቅበት መንገድ አንዱ ሰዎች በልባቸው ውስጥ ያሰቡትን ሳይናገሩት ማወቁ እንደሆነ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ (ማር. 2፡8) ላይ ማንበብ አንችላለን፡፡ በዮሐንስ 1፡48 ላይ ደግሞ ፊልጶስ ናትናኤልን ከናዝሬት መልካም ነገር መውጣቱን መጥቶ እንዲያይ በነገረው ጊዜ መጣ፡፡ ኢየሱስም ተንኮል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው፣ በማለቱ ናትናኤልም መልሶ የት ታውቀኛለህ አለው? በዚህ ጊዜ ይበልጥ የሚደነቅበትንና እጁን የሚሰጥበትን ችሎታውን ነገረው፡፡ ‹‹ፊልጶስ ሳይጠራህ፣ ከበለስ በታች ሳለህ፣ አየሁህ›› ሲለው ወዲያውኑ ናትናኤል ‹‹መምህር ሆይ፡- አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፣ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ›› በማለት ሁሉን አዋቂነቱን መሰከረለት፡፡
ክርስቶስ በሁሉ ሥፍራ እንደሚገኝና እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከአማኞች ጋር እንደሚሆን በመናገሩ ምክንያት እስከ አሁን ድረስ በእርሱ በኩል ጸሎታችንን ወደ እግዚአብሔር፣ ወደ አባቱ በምናቀርብበት ጊዜ፣ ጸሎታችን መልስ ያገኛል (ማቴ. 18፡20፣ 28፡20)፡፡ ክርስቶስ ዘላለማዊ በመሆኑ (ዕብ. 13፡8) ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን አዋቂ፣ ሁሉን አድረጊና በሁሉ ሥፍራ መገኘት የመለኮታዊነቱ ባሕርይ መገለጫዎች ናቸው፡፡ መለኮታዊነቱ ባሕርዩን፣ ባሕርዩ መለኮታዊነቱን ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ ባሕርዮቹ የመለኮታዊነቱ (አምላክነቱ) ማረጋገጫዎች ናቸው፡፡
4) የማዕረግ ስሞቹ፡- እግዚአብሔር ወልድ የተጠራባቸው ስሞች ብዙ ቢሆኑም፣ ዋናዎቹ ኢየሱስና ክርስቶስ የሚሉት ሲሆኑ ትርጉማቸውን ቀደም ብለን ተመልክተናል፡፡ ሰብዓዊ ስሙ ኢየሱስ ሲሆን፣ ክርስቶስ የሚለው ደግሞ መለኮታዊ ስሙ ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል ተጨማሪ የማዕረግ ስሞቹን እንመለከታለን፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሚለውን የማዕረግ ስሙን በተለያየ ጊዜ ሰዎች ከደረሰባቸው ችግር ሲታደጋቸው፣ ይህን ስም በመጥራት ሲጠቀሙበት፣ ጌታም ይህን ስም ሲጠቀሙ ምንም ተቃውሞ አላሳየም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ እየሄዱ ሳለ፣ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እኔም እንዳንተ መሄድ እንድችል እዘዘኝ ባለው ጊዜ፣ እርሱም እንደ ጌታው በውኃ ላይ መሄድ ጀምሮ፣ ዓይኑን ከጌታ ላይ አንስቶ ውኃውን ሲመለከት መስጠም ጀመረ፡፡ ጌታም ና ብሎ እጁን ይዞ ሲያወጣው፣ ሳለ ነፋሱ ተወ፤ በዚህ ጊዜ በታንኳ የነበሩት ሁሉ ‹‹በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብለው ሰገዱለት (ማቴ. 14፡33)፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰውን ልጅ ማን ይሉታል ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ፣ ሰዎች ያሉትን የተለያዩ መልሶች ከነገሩት በኋላ፣ እናንተስ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ ብሎ መልሶ በጠየቃቸው ጊዜ፣ ጴጥሮስ ለጥያቄው ሲመልስ ‹‹አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ›› ብሎ ሲመልስለት፣ ጌታም ‹‹የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፡- በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ›› (ማቴ. 16፡16-17)፡፡ በማለት በአባቱ የታወቀና የምወደው ልጄ ብሎ ከተመሰከረለት ጋር አንድ መሆኑን መረዳት እንችላለን (ማቴ. 3፡17)፡፡
በብሉይ ኪዳን አዶናይ ተብሎ እግዚአብሔር የሚጠራበት ስም በአዲስ ኪዳን ለክርስቶስ የመለኮታዊነቱ መጠሪያ ሆኖ እናገኘዋለን፤ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ጴጥሮስ በበዓለ ኀምሳ ቀን፣ ስለ ክርስቶስ ከሞት መነሣት ሲናገር፣ ‹‹እንግዲህ ይህን እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም ክርስቶስም እንዳደረገው የእስራኤል ወገን ሁሉ በእርግጥ ይወቅ›› (ሐዋ. 2፡36) በማለት የማዕረግ (ጌታ) እና የመለኮታዊ (ክርስቶስ) ስሙን ሲጠቀም እንመለከታለን (ፊል. 2፡10፣ ሮሜ. 10፡13)፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በመልእክቱ ከዚህ በላይ የጠቀስናቸውን ስሞች ያዘለውን አጠራር ተጠቅሞ እናገኛለን፤ እንዲህ በማለት ‹‹የእግዚአብሔር ልጅ እንደ መጣ፣ እውነተኛ የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቡናን እንደ ሰጠን እናውቃለን እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፣ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ሕይወት ነው›› (1ዮሐ. 5፡20)፣ እስከ አሁን ድረስ ያየናቸውን ስሞችና ‹‹አምላክ›› የሚለውን የማዕረግ ስም ተጠቅሞ እናገኛለን፡፡ (ተጨማሪ ዕብ. 1፡8፣ ኢሳ. 9፡5 ተመልከቱ)
በመጨረሻም ካህኑ ዘካርያስ በመልአኩ ገብርኤል የተነገረውን ቃል ባለማመኑ ምክንያት፣ ባለቤቱ ኤልሳቤጥ ወንድ ልጅ ወልዳ በስምንተኛው ቀን በሚያስገርዙበት ጊዜ፣ ዘካርያስ አፉ ተከፍቶና በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ እግዚአብሔርን ስለ ልጁ ሲያመሰግን ሳለ፣ ‹‹አንተ ሕፃን ሆይ፡- የልዑል ነቢይ ትባላለህ›› በማለት የጌታን ልዑልነትና የኃያሉ ንጉሥ (እግዚአብሔር) ልጅ መሆኑን በመንፈስ በመረዳት ጸለየ (ሉቃ. 1፡76)፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በራዕዩ እንደሚገልጸው በመጨረሻው ዘመን ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ ‹‹በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት፡- የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው›› በማለት ሲመጣ የሚጠራበትን የማዕረግ ስሙን አስቀምጦአል (ራዕ. 19፡16)፡፡ ከዚህ በላይ የቀረቡት ጌታ የተጠራባቸውና ወደፊት የሚጠራባቸው ስሞቹ ሁሉ አምላክነቱንና ማዕረጉን የሚገልጹ ናቸው፡፡
5) የአጋንንት ምሥክርነት፡- ክርስቶስ በምድር በነበረው አገልግሎቱ፣ በሰው ውስጥ ገብተው ያደሩ አጋንንት፣ ‹‹የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፡- ከአንተ ጋር ምን አለን ልታጠፋን መጣህን ማን እንደሆንህ አውቄአለሁ፡- የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ›› (ማር. 1፡24)፣ በሌላ ሥፍራ ደግሞ ‹‹ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ጊዜ በፊቱ ተደፍተው፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ እያሉ ጮኹ›› ይላል ቃሉ (3፡11፣ 5፡7)፡፡ አባታቸው ዲያቢሎስ የውሸት አባት በመሆኑ፣ ሁልጊዜ የሚናገሩትን ሁሉ እውነት ነው ብሎ መቀበሉ አደገኛ ነው፡፡ ብዙ ወንድሞች ከትልቅ ስሕተት ውስጥ ገብተው በዚያው ጠፍተው ቀርተዋል፤ በዚህ ሥፍራ ግን አጋንንቶች ጌታን መዋሸት ስለማይችሉ አምላክነቱ እውነት እንደሆነ መስክረዋል፡፡ እኔም የእነርሱን ምስክርነት ያስገባሁት ሁልጊዜ የሚናገሩት እውነት ይሆናል ለማለት ሳይሆን፣ የጠላቶቹን እንኳን ምስክርነት እንዳገኘ ለማሳየት ነው፡፡ ስለዚህ አጋንንትን ስናስወጣ የሚናገሩትን ሁሉ እውነት ነው ብሎ ከመቀበል ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
3.2 ክርስቶስ ራሱን ባዶ ማድረጉ
ከዚህ በላይ እንደ ተመለከትነው ክርስቶስ መለኮታዊ መሆኑን ከራሱ ምስክርነት፣ ከሥራዎቹ፣ ከባሕርያቱ፣ ከስሞቹና ከአጋንንት ምስክርነት ማረጋገጥ ችለናል፡፡ አሁን ደግሞ በሰብዓዊነቱና መለኮታዊነቱ በምድር አገልግሎቱ ጊዜ እንዴት እንደ ተመላለሰና ራሱን እንዴት ባዶ እንዳደረገ እናጠናለን፡፡ ክርስቶስ ራሱን ባዶ ማድረጉ በሥነ መለኮት ትምህርት ኪኖሲስ (Kenosis) በመባል ይታወቃል፡፡ ወደ ፊልጵስዩስ ምዕራፍ 2 ቁ.7 ላይ ስንመለከት ‹‹ራሱን ባዶ አደረገ›› የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ በዚህ ቃል ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች የተለያየ አስተሳሰብ አላቸው፡፡ አንዳንዶች መለኮታዊነቱን የተወው ሙሉ በሙሉ ነው ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ በግማሽ እንደተወ ሲናገሩ፣ ብዙዎች ደግሞ አልተወም ብለው ያምናሉ፡፡ እናንተስ የትኛውን አስተሳሰብ የምትቀበሉ ናችሁ?
ከየትኛውም የአስተሳሰብ ወገን ብንሆንም ወይም ምንም አቋም የሌለን ብንሆንም፣ ምንም ችግር የለውም፤ የእግዚአብሔርን ቃል ረጋ ብለን አብረን በጥልቀት እናጠናለን፡፡ የፊልጵስዩስ 2፡7 ላይ ያለውን ሐሳብ ለመረዳት፣ የምዕራፉን ዐውድ በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሥፍራ ሐዋርያው ጳውሎስ በ2፡2 ላይ ‹‹ደስታዬን ፈጽሙልኝ›› በማለት አማኞችን ይጠይቃል፤ በጌታ ደስ ብሎኛል ብሎ አሥራ አንድ ጊዜ የጻፈ አገልጋይ፣ አሁን ለምን እንዲህ አለ ብለን ብንጠይቅ፣ መልሱን 4፡2-3 ባለው ክፍል መልሱን እናገኛለን፡፡ ሁለት ሴት አገልጋዮች በዚያው በምዕራፍ ሁለት ላይ ምክንያቱን እንደምናገኘው ተጣልተውና ተለያይተው እናገኛለን፤ በዚህ ምክንያት ጳውሎስ ከክርስቶስ ትሕትናን፣ ከጳወሎስ ከራሱ መሥዋዕትነትን፣ ከጢሞቴዎስ ለሌላው መኖርንና ከአፍሮዲጡ እስከ ሞት ድረስ ሌሎችን ማገልገል እንዲማሩ ይጽፍላቸዋል፡፡
ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ በሚጽፍበት ጊዜ መለኮታዊነቱን ስለ መተውና አለመተው ሳይሆን ዓላማው፣ ዓላማው ከክርስቶስ ትሕትናን እንዲማሩ ማድረግ ነበረ፡፡ ቄስ ማንሰልም ‹‹ከእናቱ ከድንግል ማርያም ተወልዶ እንደ ሰው በምድር ላይ ኖረ፤ ይህም ለእርሱ ፍጹም የሆነ ትሕትና ነበረ›› ይላሉ፡፡ ጳውሎስ፣ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ወደዚህ ምድር ሲመጣ፣ በመለኮታዊነቱ ላይ ሰብዓዊነትን ጨምሮ መምጣቱን ለማስተማር ፈልጎ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሥፍራ ‹‹ራሱን ባዶ አደረገ›› ሲል መለኮታዊነቱን ተወ ለማለት ሳይሆን መለኮታዊ ባህርዩን ሆን ብሎ ሳይጠቀም ከመለኮታዊ ውስንነቱ ጋር ሰብዓዊነትን መያዙን ያሳየናል፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 2፡19 ላይ ‹‹ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ›› በማለት ስለ ራሱ ማንነት በተናገረበት ጊዜ በሥጋ (ሰብዓዊነት) እንደሚሞት በመንፈስ (መለኮት) ሕያው ሆኖ እንደሚነሳ ሁለቱንም ማንነቱን ገልጾአል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስም በሮሜ መልእክቱ እንዲህ ይላል ‹‹ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ (ሰብዓዊነቱን) እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ (መለኮታዊነቱን) በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው›› (ሮሜ. 1፡4) በማለት ሁለቱንም ተፈጥሮ አዋህዶ፣ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ፣ ሰውነቱን ከአምላክነቱ ያለ መቀላቀልና ያለ መለዋወጥ፣ ያለ መከፋፈልና ያለ መለያየት የያዘ አዳኝ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ጌታ የምድር ተልዕኮውን ሊፈጽም በተቃረበበት ጊዜ በጸለየው ጸሎት ላይ እንዲህ ብሎአል ‹‹አሁንም አባት ሆይ፣ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ›› (ዮሐ. 17፡5) ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ክርስቶስን በመለወጥ ተራራው ላይ፣ በውኃ ሲራመድ፣ ከመቃበር በመነሣቱ ክብሩን አይተዋል፡፡ ከእነዚህ ድርጊቶችና ከጸሎቱ አባባል የምንረዳው መለኮታዊ ክብሩን በሙሉ እንዳልተጠቀመበት መረዳት እንችላለን፡፡
0 Comments