የኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት
የሰው አካል ነበረው፡- ኢየሱስ ሰማያዊ አካል እንደ ነበረው፣ እንዲሁ ምድራዊ የሰው አካል ነበረው፡፡ ከማርያም ሥጋ ነስቶ በመወለዱ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ የሚያንቀላፋ፣ የሚደክም፣ የሚተኛ፣ የሚያለቅስ፣ የሚደሰትና የሚያዝን አካል እንደ ነበረው፤ የሚከተሉት ጥቅሶች ያመለክቱናል፡፡ መራቡን ማቴ.4፡2፣ መጠማቱን ዮሐ. 19፡28፣ መድከሙን 4፡6፣ መታወኩን ዮሐ. 12፡27፣ 13፡21፣ ማዘኑን ማቴ. 26፡38፣ ማልቀሱን ዮሐ. 11፡35፣ መፈተኑን ዕብ. 4፡15፣ ርኅራኄውን ማቴ. 9፡36 እነዚህ ከላይ ያየናቸው ነጥቦች ኢየሱስ አካልና የሰው ባሕርይ እንደ ነበረው ያመላክቱናል፡፡ አሁን ደግሞ በሚቀጥለው ጥናታችን ስለ ነበረው ቤተ ሰብ፣ ባሕርይና ሰብዓዊ መገለጫዎቹ፤ ከማርያም መወለዱን፣ ጠቢባኖቹ በእናቱ አጠገብ እንዳገኙት፣ ቤተሰቦች እንዳሉትና እንደፈለጉት፣ እንዲሁም የአናጺው ልጅ በመባል እንደ ተጠራ እናጠናለን፡፡ ( 12፡47፣ 13፡55፣ የሐዋ. 13፡23-24፣ ሮሜ. 1፡3)
ቤተሰብ ነበረው፡- ማቴዎስ ስለ ኢየሱስ ልደት ሲጽፍ ‹‹እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች›› (ማቴ.1፡18)፣ በዚህ ጊዜ እጮኛዋ በስውር ሊተዋት ባሰበ ጊዜ፣ የጌታ መልአክ በሕልሙ ተገልጦለት፣ የፀነሰችው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ለመውሰድ አትፍራ ብሎ ተናገረው፡፡ (1፡20) እርሱም ጌታ እንደ ተናገረው፣ ወደ ቤቱ ወሰዳት፣ እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም (1፡24-25)፡፡
በመቀጠልም ሉቃስ እንደሚተረክልን፣ ማርያም ነፍሰ ጡር ሆና የመውለጃዋ ጊዜ ደርሶ ሳል፣ በዚህ ዘመን እንዳለው የሕዝብ ቆጠራ ጊዜው ደርሶ ስለ ነበረ፣ ዮሴፍ እጮኛውን ይዞ ከናዝሬት ወደ ቤተ ልሔም ለቆጠራ ወጡ፡፡ ‹‹በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፣ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፣ በመጠቅለያም ጠቀለለችው በእንግዶችም ማደሪያ (ሆቴል) ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው›› (ሉቃ. 2፡7)፡፡ በዚህ ጊዜ መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ ላደሩት እረኞች፣ የጌታ መልአክ ተገልጦ፤ ሕዝብን ሁሉ ሊያድን የሚችል መድኃኒት ተወልዶአል ብሎ አበሰራቸው፡፡ እረኞቹም በተነገራቸው መሠረት ወደ ተባለው ሥፍራ ሕፃኑን ለማየት፣ ‹‹ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ›› (2፡16)፡፡ በዚህ ጊዜ ቃሉ እንደሚነግረን ሰብአ ሰገል ኢየሱስ መወለዱን አውቀው፣ ከጥቂት ወራት በኋላ በኮከብ እየተመሩ መጥተው ስጦታ በመስጠት ሰገዱለት፡፡ ሰብአ ሰገል የመራቸው ኮከብ ስለ ጠፋባቸው፤ ወደ ሄሮድስ ቤተ መንግሥት በመሄድ፣ ስለ ኢየሱስ መወለድ ጠየቁት፡፡ በዚህም ምክንያት ሄሮድስ መወለዱን ሰምቶ ሊገድለው አሰበ፡፡ የጌታም መልአክ እንደ ተለመደው፣ ለዮሴፍ ተገልጦ ‹‹ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ›› አለው (ማቴ. 2፡13)፡፡ ዮሴፍ ቤተ ሰቡን ይዞ፣ በተባለው መሠረት በማድረግ ሄሮድስ እስከሚሞትበት ጊዜ ድረስ በዚያ ተቀመጠ፡፡
ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም ለመምጣት የሚወለድበት ቤተ ሰብ፣ የሚያሳድጉት፣ በመከራው አብረው የሚሳተፉ፣ ከሞት የሚታደጉትና ሙሉ ሰው እስከሚሆን ድረስ የሚያሳድጉትና የሚከባከቡት ቤተ ሰቦች እንደ ነበሩት ቃሉ ያሳያል፡፡ ጌታም በምድር በነበረ ጊዜ ‹‹…እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ›› (ዮሐ. 8፡40)፣ እንደገናም በጸሎቱ ጊዜ ‹‹ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች…›› በማለት ሰብዓዊነቱን ገልጾአል (ማቴ. 26፡38)፡፡ ዓልዓዛር በሞተ ጊዜም ‹‹… በመንፈሱ አዘነ… ታወከ›› በማለት ዮሐንስም በሰው አካል የሚታዩት ስሜቶች እንደ ታዩበት ጽፎለታል (ዮሐ. 11፡33፣ 13፡21)፡፡ ሉቃስም በወንጌሉ ‹‹ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር›› (ሉቃ. 2፡52) በማለት ሰብዓዊነቱ ሰው ሊያየውና ሊዳስሰው የሚችል አካል እንደነበረው ይገልጻል፡፡
ማንኛውም ሰው በዚህ ምድር ሲኖር ስም እንዳለው ሁሉ ወልድም ሰብዓዊ ስሞች ነበሩት፡፡ ዮሴፍ ማርያምን በስውር ሊተዋት አስቦ ሳለ የጌታ መልአክ ተገልጦ እንዳይተዋት በነገረው ጊዜ፣ ‹‹እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ›› (ማቴ. 1፡21)፤ በማለት ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት በመልአኩ ስም እንደ ወጣለት ቃሉ ይገልጻል፡፡ ኢየሱስ ማለት በዕብራይስጥ ‹‹ዬሱ›› ማለት ሲሆን ትርጉሙም ‹‹አዳኝ›› ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በመልአኩ የወጣለት ስም ቢሆንም፣ በቤተሰብ ደረጃም ወጥቶለት የተጠራበትና የተጠቀመበት ስም ነው፡፡
በመጨረሻም ሐዋርያው ጳውሎስ በአንደኛ ጢሞቴዎስ መልእክቱ ‹‹አንድ እግዚአብሔር አለና በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፣ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው›› በማለት ኢየሱስ ፍጹም ሰው፣ እንዲሁም ፍጹም አምላክ (ክርስቶስ) መሆኑን በማረጋገጥ ጽፎ እናገኛለን (1ጢሞ. 2፡5)፡፡
ከዚህ በላይ ኢየሱስ ፍጹም ሰው መሆኑን ተመልክተናል፤ በሚቀጥሉት ጥናቶች ደግሞ ፍጹም አምላክ ሆኖ መምጣቱን የተለያዩ ማረጋገጫዎችን በማየት እናጠናለን፡፡
ሰብዓዊ መገለጫዎች፡- ቀደም ብለን እንዳየነው ኢየሱስ ሰው ሆኖ በመምጣቱ፣ በሰዎች የሚታዩት ሰብዓዊነትን የሚያመለክቱ ነገሮች ሁሉ በእርሱም መታየታቸውን ተመልክተናል፡፡ አሁን ደግሞ በኢየሱስ ሰብዓዊነት ላይ ተጨማሪ ሆነው የተጠራበትን መገለጫዎችን በመቀጠል እንመለከታለን፡፡ እነርሱም የሰው ልጅ (ሉቃ. 19፡10) እና የዳዊት ልጅ (ማር. 10፡47) የሚሉት ናቸው፡፡ የሰው ልጅ የሚለውን ቃል ነቢዩ ዳንኤል በትንቢቱ ተጠቅሞበት እናገኘዋለን (ዳን. 6፡13)፤ ጌታም ወደ ዘኪዎስ ቤት በገባ ጊዜ ያወጀው ይህን የተነገረለት፣ ትንቢት ለመፈጸም መጀመሩን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው መገለጫው የተከናወነው በርጤሜዎስ በተባለው ዓይነ ስውር ነበር፤ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ኢያሪኮ ሲመጣ ሳለ፣ በርጤሜዎስ የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፣ ‹‹የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ሆይ ማረኝ›› እያለ ይጮኽ ጀመር፡፡ ይህ ጩኸት የሚያመለክተንና የሚጠቁመን፣ አይሁድ በዘመናቸው ሁሉ የዳዊት ልጅ ይመጣል እያሉ ይጠብቁ እንደ ነበር ነው፡፡ ኢሱስም አንድ ጊዜ ፈሪሳውያንን ስለ ራሱ ሰዎች ምን እንደሚሉ በጠየቃቸው ጊዜ ‹‹የዳዊት ልጅ ነው›› ብለው እንደ መለሱለት ማቴዎስ በወንጌሉ ላይ አስፍሮት እናገኛለን (22፡42)፡፡
ኃጢአት አለመሥራቱ፡- ኢየሱስ የሰው ልጆችን ለማዳን ሰብዓዊነትን ይዞ (ሰው ሆኖ) እንደ መጣ በሰፊው ተመልክተናል፡፡ ፍጹም አምላክነቱ ወደ ፊት የምናጠናው ቢሆንም፣ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆኖ በምድር ለ33 ዓመት ተኩል ተመላልሷል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ በተለያዩ ፈተናዎችም ቢያልፍም፤ እንኳን ኃጢአት አልሠራም፡፡ ሰው በዚህ ምድር ሲኖር በተለያዩ ኃጢአቶች ውስጥ እንደሚመላለስና እንደሚኖር የታወቀ ነው፡፡ ኢየሱስ በዚህ ምድር ሲመላለስ፣ ሰው ሁልጊዜ በቀላሉ የሚለማመደውን የስድብ ኃጢአት እንኳን አላደረገም፤ በማለት ቃሉ ይመሰክርለታል፡፡ ጴጥሮስ በመልእክቱ ሲመሰክርለት እንዲህ ይላል ‹‹እርሱም ኃጢአት አላደረገም፣ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፣ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፣ መከራንም ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ›› (1ኛ.ጴጥ. 2፡22-24) በማለት በሰብዓዊነቱ ድካም ታይቶበት ኃጢአት እንዳላደረገ ይናገርለታል፡፡
የዕብራውያን ጸሐፊም ደግሞ እንዲህ ይላል ‹‹ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው›› ይህ ማለት በሰብዓዊነት ኃጢአት ሊሠራ የሚችል ማንነት ቢኖረውም እንኳን ኃጢአትን አልሠራም ማለት ነው፡፡ ‹‹እንደ እኛ›› የሚለው ቃል የሚፈተን ሥጋ ስለ ያዘ መፈተን መቻሉን ያስረዳል፡፡ ‹‹ከኃጢአት በቀር›› የሚለው ቃል የኃጢአት ባሕርይ ስለሌለው ማለት ሲሆን በእኛ የሚታዩ ሰብዓዊነቶችም (ቢደክምም፣ ቢተኛም፣ ቢራብም፣ ቢጠማምና ቢያንቀላፋም) ኃጢአት በሚያሠራውና ከአባቱ ጋር በሚያጣላው ነገሮች ላይ ተፈትኖ ራሱን በመግዛቱ በድል አድራጊነት ተወጥቶአል ማለት ነው (ዕብ. 4፡15)፡፡ ጸሐፊው ይህን ድል በቀላሉ እንዳላገኘው ሲገልጥ እንዲህ ይላል ‹‹እርሱም በሥጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፣ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት ምንም ልጅ ቢሆን ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ›› በማለት ኃጢአት የሚያሠራውን ማንነት እንደ ጳውሎስ እየጎሰመ ራሱን እንደገዛ ማየት እንችላለን (ዕብ. 5፡7-8)፡፡
ምድራዊ አገልግሎቱ፡- አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ባወጡት ዕቅድ መሠረት ወደ ምድር በመምጣት ከድንግል ማርያም ሥጋ ነስቶ ማለት በመንፈስ ቅዱስ በመፀነስና (ወደ ፊት ስለ መንፈስ ቅዱስ ስናጠና በስፋት እናየዋለን) በመወለድ እንደ ማንኛውም ሰው በእናቱ ማህፀን አድሮ፣ ተወልዶና አድጎ ሙሉ ሰው እስከሚሆን ድረስ ቤተሰቡን አገለገለ፡፡ ሠላሳ ዓመት ከሞላው በኋላ በመጥምቁ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ የአባቱን ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው›› (ማቴ.3፡16-17) የሚለውን ምሥክርነት ካገኘ በኋላ በሰይጣን በምድረ በዳ ተፈትኖ አገልግሎቱን ቀጠለ፡፡ በተለያዩ ቦታዎች በገሊላ፣ በይሁዳ በሰማርያ በመላለስ ትምህርቶችን እያስተማረ፣ ሰዎችን እየፈወሰ፣ አጋንንትን እያወጣ፣ ደቀ መዛሙርቱን ለሦስት ዓመት ተኩል አሰልጥኖ፣ አባቱ በላከው ዕቅድ መሠረት ወደ መስቀል በመሄድ፣ የሰው ልጆችን ኃጢአት ተሸክሞ፣ የኃጠአታችንን ዋጋ በመክፈል ከአባቱ ጋር አስታረቀን፡፡
በአገልግሎቱ ውስጥ የምናያቸው ዋና ነገሮች የመጀመሪያው ለኃጢአታችን በመስቀል ላይ መሞቱ ሲሆን፣ ምንም እንኳን በሰብዓዊነቱ ቢሞትም ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ምዕራፍ 1፡4 ላይ እንደሚነግረን በሥጋ የዳዊት ዘር በመሆኑ ሞተ፣ በመንፈስ ግን መለኮታዊ በመሆኑ ሕያው ሆነ ይለናል፡፡ ጴጥሮስም በ1ኛ. ጴጥ. 3፡18 ላይ ‹‹ክርስቶስ ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርበን እርሱ ጻድቅ ሆኖ ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ›› በማለት ይህንኑ ሐሳብ ያረጋግጣል፡፡ ይህ ማለት ሰብዓዊነትንና መለኮታዊነት ይለያያሉ ማለት አይደለም፡፡
በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ፡፡ ለዚህ አይሁዶች ተሠርቆ ነው ብለው ለማስተባበል ቢሞክሩም አልቻሉም፡፡ አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ መነሳቱን ቢጠራጠሩም፣ በትንሣኤ የከበረ አካል በመልበሱ ምክንያት በተዘጉ ቤቶች በሮች ሳይከፈቱ በመካከላቸው እየተገኘ ሰላም ለእናንተ ይሁን ይላቸው ስለ ነበር (ዮሐ. 20፡19)፣ መነሣቱን ከሴቶችም፣ ከኤማሁስ መንገደኞችና ከሌሎችም ከታያቸው ግለ ሰቦች በማረጋገጣቸው፣ ትንሣኤውን በስፋት አወጁት፡፡ ጌታ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኋላ በምድር ላይ አርባ ቀን ያህል ከአምስት መቶ ለሚበዙ አማኞች እየታየ ከተመላለሰ በኋላ በመጨረሻ ደቀ መዛሙርትና ብዙ ሰዎች እያዩት ወደ ሰማይ ዐርጎ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ (ሐዋ. 1፡9-11)፡፡ ትንሣኤው በወንጌል ትምህርቱ የተናገራቸው እውነቶች የተፈጸሙበት፣ ለኃጢአት ይቅርታ ዘላለማዊ ዋስትና የተገኘበት፣ በአንደኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ላይ ጳውሎስ በትምህርቱ እንደሚገልጠው፣ ትንሣኤው የአማኞችን ከሞት የመነሳት ተስፋ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ትንሣኤው የክርስትና ሕይወትና ትምህርት ዋና መሠረት ነው፤ ትንሣኤ ከሌለ ክርስትና የለም ማለት ነው፡፡ ዕርገቱም የሰብዓዊ ውርደቱና ውስንነቱ ማብቃቱንና ወደ ክብሩ መመለሱን፣ በጸሎቱ ጊዜ፣ ‹‹አባት ሆይ፡- ሰዓቱ ደርሷል… ልጅህን አክብረው… ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ›› ብሎ እንደ ጸለየው መክበሩን ያሳያል (ዮሐ. 17፡1-5)፡፡
0 Comments